
በክብር መዝገብ ሹም ፊት ስለሚፈፀም ጋብቻ
አንቀጽ ፳፪ ሥልጣን ያለው የክብር መዝገብ ሹም
ጋብቻ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ከተጋቢዎቹ ወላጆች ወይም የቅርብ ዘመዶች አንዱ ጋብቻው ከሚፈጸምበት ጊዜ በፊት ቢያንስ ለስድስት ወራት ያህል ሳያቋርጥ በሚኖርበት ቦታ በሚገኘው የክብር መዝገብ ሹም ፊት ይፈጸማል፡፡
አንቀጽ ፳፫ ጋብቻ ለመፈፀም ጥያቄ ስለማቅረብ እና ስለሚቀርብበት ጊዜ
ተጋቢዎች ጋብቻ ለመፈፀም ማሰባቸውን እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸውን ለመፈፀም ከወሰኑበት ቀን ከአንድ ወር በፊት ለክብር መዝገቡ ሹሙ ማስታወቅ አለባቸው፡፡
አንቀጽ ፳፬ ጋብቻ የሚፈፀምበትን ቀን ስለመወሰንና ስለማስታወቅ
የክብር መዝገብ ሹሙ ጥያቄው እንደቀረበለት ከተጋቢዎቹ ጋር በመነጋገር ከወሰነ በኋላ ጋብቻው የሚፈፀምበትን ቀን በመግለጽ አመቺ በሆነው መንገድ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡
አንቀጽ ፳፭ የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት እና ጋብቻው መፈፀሙን ስለማስታወቅ
፩. ጋብቻው ሁለቱ ተጋቢዎች እና ከእያንዳንዱ ተጋቢ በኩል ሁለት ሁለት ምስክሮች በተገኙበት በግልጽ ይፈፀማል፡፡
፪. ተጋቢዎችና ምስክሮቹ ጋብቻ ለመፈፀም አስፈላጊ የሆኑት ሁኔታዎች አለመጣሳቸውን በቃለ መሐላ ያረጋግጣሉ፡፡
፫. ተጋቢዎችና ምስክሮቹ የመሐላ ቃል ከመስጠታቸው በፊት የሚሰጡት ቃል ስለሚያስከትለው ኃላፊነት የክብር መዝገብ ሹሙ በግልጽ ማስረዳት አለበት፡፡
፬. ሁለቱም ተጋቢዎች ጋብቻ ለመፈፀም መፍቀዳቸውን ለክብር መዝገብ ሹሙ በግልጽ ያረጋግጣሉ፡፡
፭. ሁለቱም ተጋቢዎችና ምስክሮቻቸው በክብር መዝገብ ላይ መፈረም አለባቸው፡፡
፮. ከዚህ በላይ የተገለጹት ሥርዓቶች የተፈፀሙ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ የክብር መዝገብ ሹሙ ተጋቢዎቹ በሕጋዊ ጋብቻ የተሳሰሩ መሆናቸውን አስታውቆ ለተጋቢዎቹ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል፡፡