⚖️በአገራችን ስላለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ አጠቃላይ ዳሰሳ ⚖️መመሪያ የሌለው መመሪያ ⚖️


በአገራችን ስላለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ አጠቃላይ ዳሰሳ በህግ አውጭው የወጣ አንድ አዋጅ ስጋና ደም ለብሶ በተጨባጭ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ብዙውን ጊዜ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች ያስፈልጉታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተወካዮች ም/ቤት ከሚወጣው አዋጅ ይልቅ በየጊዜው ስለሚደነገጉት መመሪያዎች የተለየ ቅርበትና እውቀት አለው፡፡ በእያንዳንዱ አስተዳደር መ/ቤት ውስጥ የመንግስት ስራ የሚሰራው ‘በህጉ መሰረት’ ሳይሆን ‘በመመሪያው መሰረት’ ስለመሆኑ እውነትነት ያለው ሀቅ ነው፡፡ስልጣን በሰጠው አዋጅ መሰረት እስከወጣ ድረስ በመመሪያ መስራቱ ባልከፋ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ‘መመሪያ’ ሲባል ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት፣ ለህገ ወጥነትና ለኢ-ፍትሐዊነት የሚሰጥ የሽፋን ልብስ ነው፡፡ ዋና ችግሩ ከውክልና ሰጪው ከተወካዮች ም/ቤት ይጀምራል፡፡ በተለያዩ አዋጆች ላይ ለሚኒስትሮች ም/ቤትና ለአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና የሚተላለፈው ስልጣን እንደሰማይ የሰፋ ቢሆንም ጥያቄው የህግ የበላይነትና የህገ-መንግስታዊነት ሆኖ ተመክሮበት አያውቅም፡፡ከዚህ ባሻገር አነስተኛ ስነ-ስርዓት ፈጽሞ አለመኖሩ መመሪያዎች ‘የስርቻው ስር ህጎች’ ሆነው እንዲቀሩ አድርጐታል፡፡ በተጨማሪም ህጋዊነታቸውንና በህግ አውጭው ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ አለማለፋቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ውጤታማ የቁጥጥር ስልት አልተዘረጋም፡፡

መመሪያ የሌለው መመሪያ

አስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት (Rule–Making Procedure) ግልፅነትና የህዝብ ተሳትፎን በማሳካት ረገድ ካለው ወሳኝ ሚና በተጨማሪ በዘፈቀደ በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች አማካይነት የዜጐች መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ከለላና ውጤታማ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ በአገራችን በሚኒስትሮች ም/ቤትና በአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ለየትኛውም አይነት አስገዳጅ ስነ-ስርዓት አይገዙም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ህግ አውጭው አንድ ደንብ በሚኒስትሮች ም/ቤት የሚወጣበትን ስነ-ስርዓት በአዋጅ ደንግጐ አላስቀመጠም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአስተዳደር መ/ቤቶች መመሪያ ሲያወጡ ሊከተሉት ስለሚገባ ስነ-ስርዓት የሚደነግግ አስገዳጅ ህግ የለም፡፡ከመሰረታዊ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች  አንዱና ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ ቀላል በሆነ መንገድ ታትሞ መሰራጨት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተግባር ያለው እውነታ እንደሚያሳየን መመሪያዎች በአስተዳደር መ/ቤቱ ውስጥ ተደብቀው የሚቀሩ የጓዳ ህጐች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መመሪያዎች በ3ኛ ወገን ላይ አስገዳጅነት ቢኖራቸውም ሊታወቁና ሊከበሩ የሚችሉበት አንዳችም አማራጭ መንገድ የለም፡፡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በመመሪያው መሰረት እርምጃና ቅጣት ሲወሰድባቸው መመሪያዎቹ ባልታወቁበትና ባልታተሙበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም የግልፅነትን መርህ የሚጥስ፣ ለሙስናና ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል በአጠቃላይ ለአስተዳደራዊ ብልሹነት የሚያጋልጥ አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ማንም ዜጋ ላልታተመ፣ ለማያውቀው እና ሊያውቀው ለማይችል ህግ የመገዛት ግዴታ የለበትም፡፡የመመሪያዎች አለመታተም ተፈጻሚነት (ውጤት) የሚያገኙበትን ጊዜ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ አንድ መመሪያ ውጤት የሚኖረው ከመቼ ጀምሮ ነው? በተለምዶ በመ/ቤቱ ኃላፊ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ውጤት ያገኛል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ያልተፈረመ መመሪያ በተግባር ተፈጻሚ የሚደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በአንዳንድ መመሪያዎች ላይ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን በግልጽ ቢመለከትም የመ/ቤቱ ኃላፊ ፊርማ የለውም፡፡በስነ-ስርዓት አለመኖር ምክንያት በየአስተዳደር መ/ቤቱ የሚወጡት መመሪያዎች ቅርጽና ይዘት ወጥነት አጥቷል፡፡ መመሪያ ለአውጭውም አካል ሳይቀር አስገዳጅ ህግ እንደመሆኑ አነስተኛ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመመሪያው መለያ ቁጥር፣ የተሻረ መመሪያ ካለ ቁጥሩና የወጣበት ጊዜ አንዲሁም ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ቁጥርና አንቀጽ መጥቀስ ይገባል፡፡ እንዲሁም መመሪያው በምእራፍ፣ በክፍልና በአንቀጽ (ቁጥር) ተከፋፍሎ አስገዳጅነት ያለው ድንጋጌ ሊያስቀምጥ ይገባል፡፡ ይዘቱ ጥናት፣ ጥቆማ ወይም ምክር ወዘተ… መምሰል የለበትም፡፡

አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስርዓት

ስነስርዓት ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ ሲሆን የበዘፈቀደ አሰራርን በማስወገድ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ዝርዝር የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስነ-ስርዓት በውክልና የተሰጠ ስልጣን በአግባቡ ተግባር ላይ ስለመዋሉ አንዱ መለኪያ መስፈርት ነው፡፡በአንዳንድ አገራት አስተዳደራዊ ድንጋጌ የሚወጣበት ወጥ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ደንብ (Administrative procedure code) ራሱን ችሎ በተለይ ይደነገጋል፡፡ ወጥ ስነ-ስርዓት በሌለበት ሁኔታ ግን የውክልና ስልጣኑን የሚሰጠው ህግ የአስተዳደር መ/ቤቱ መከተል ያለበትን አነስተኛ የስነ-ስርዓት አካሄድ ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ በአገራችን በሚኒስትሮች ም/ቤት ደረጃ ሆነ በአስተዳደር መ/ቤቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አስገዳጅና ወጥ የስነ-ስርዓት ደንብ ካለመኖሩም በላይ የውክልናው ምንጭ የሆነው አዋጅ ዝርዝር የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎችን አያስቀምጥም፡፡ በዚህ የተነሳ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ውጤታማ አስተዳደር በማስፈን ረገድ ያላቸውን ሚና ከማሳነሱም በላይ ለህገ-ወጥ አሠራር፣ ሙስና እና አስተዳደራዊ ብልሹነት መንሰራፋት አይነተኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ከሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደምንረዳው ልዩ ሁኔታዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው በውክልና ህግ የሚያወጣ አካል የሚከተሉትን የስነ-ስርዓት ደንቦች መከተል ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህም ስነ-ስርዓቶች ማስታወቂያና መረጃ መስጠት፣ ምክክር (የህዝብ ተሳትፎ)፣ ክለሳ እንዲሁም ህትመት በሚል በአራት ዋና ዋና ንዑስ ስርዓቶች ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡እነዚህ ንዑስ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ጥሩ ሊባል የሚችል አስተዳደራዊ ደንብ ወይም መመሪያ ከማርቀቅ ሂደት እንደሚጀምር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ሲረቀቅ ያላማረ ሲጸድቅም አያምርም፡፡ ስለሆነም ደንቡ ወይም መመሪያው ግልጽ፣ በቀላሉ የሚገባ፣ የማያደናግር ይሆን ዘንድ በማርቀቅ ሂደቱ ላይ የህግ ባለሙያ ተሳትፎ ተመራጭነት አለው፡፡aማስታወቂያ እና መረጃ መስጠትየህዝብ ተሳትፎ ለአስተዳደራዊ ድንጋጌው ተዓማኒነትና ተቀባይነት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ መሰረት ሀሳብ በተግባር የሚተረጎመው ግልፅ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ ማስፈፀሚያ ስርዓት ሲኖር ነው፡፡ በዚህ ረገድ አስተዳደራዊ ደንቡ ወይም መመሪያው ከመታተሙ በፊት የሚመለከተው የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ፣ ጥቆማ፣ አስተያየት፣ ትችትና ሂስ ለመስጠት እንዲያስችለው ረቂቁን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ለምሳሌ በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት በውክልና ህግ የማውጣት ስነ-ስርዓት ብንወስድ የሚመከለተው የአስተዳደር መ/ቤት መመሪያ ለማውጣት ሲያቅድ አስቀድሞ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ጋዜጣ (state register) ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ረቂቁ መመሪያ በሙሉ ወይም በከፊል ከማስታወቂያው ጋር የሚወጣ ሲሆን በከፊል ከታተመ የረቂቁ ሙሉ ቅጂ ስለሚገኝበት አድራሻና ሁኔታ በጋዜጣው ላይ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ስለሆነም አስተያየት ማቅረብ የሚፈልግ ወገን መመሪያ በሚያወጣው የአስተዳደር መ/ቤት በቀጥታ በአድራሻው በመሄድ የረቂቁን ቅጂ በነጻ ወይም በአነስተኛ ክፍያ ማግኘት ይችላል፡፡ በተጨማሪም ከኢንተርኔት ድረ-ገጽ ላይ በቀላሉ ይገኛል፡፡bማስታወቂያው በጋዜጣ ላይ ከታተመበት ዕለት ጀምሮ ለ45 ቀናት መቆየት ያለበት ሲሆን ዓላማውም በጉዳዩ ጥቅም ያላቸው ወገኖች አስተያየት፣ ጥቆማና ሂስ ለማቅረብ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ነው፡፡ ሀሳብ መስጠት የፈለገ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት አስተያየቱን በጽሁፍ፣ በፋክስ፣ በኢ-ሜይል ወይም በሌላ በሚያመቸው መገናኛ ዘዴ መላክ ይችላል፡፡በካሊፎርኒያ ሆነ በሌሎች ግዛቶች ያለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት ከሞላ ጎደል እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. በፌደራል መንግስት ደረጃ ከወጣው የአስዳደር ስነ ስርዓት ደንብ (Administrative Procedure Act, 1946) ከሚደነግጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ በዚህ ህግ መሰረት የአስተዳራዊ ድንጋጌ (በህጉ አነጋገር ‘Rule’) አወጣጥ ስርዓቱ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሚል ለሁለት (እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም. የህግ ዕውቅና ያገኘውን Negotiated Rulemaking ሳይጨምር) ተከፍሏል፡፡cመደበኛው ስርዓት እንደ ፍርድ ቤት ክርክር ዓይነት የጉዳዩ መሰማት የሚካሄድበት ሲሆን የሚመለከታቸው ወገኖች አስተያየት ከመስጠት ባለፈ የኤጀንሲውን አቋም ለማስተባበል ተቃራኒ ክርክር እና ማስረጃ ማቅረብ ይፈቀድላቸዋል፡፡d በአሜሪካ የፌደራል መ/ቤቶች በስፋት የሚከተሉትና እንዲከተሉትም የሚገደዱት ኢ-መደበኛውን ስርዓት ሲሆን መሟላት ያላባቸው አነስተኛ ቅድመ ሁኔታዎች ማስታወቂያ፣ አስተያትና ህትመት ናቸው፡፡ የአስተዳደራዊ ድንጋጌ (Rule) አወጣጥ ስርዓቱ ፌደራል ሬጅስተር በሚባለው ዕለታዊ የመንግስት ጋዜጣ ይፋ ማስታወቂያ በማውጣት ይጀመራል፡፡e ማስታወቂያው የሚከተሉትን መግለጫዎች መያዝ ይኖርበታል፡፡ሊወጣ የታቀደው አስተዳደራዊ ድንጋጌ የሚገኝበትን ቦታ፣ ጊዜ እና አጠቀላይ ባህርያቱንስልጣን የሰጠው አዋጅና ለድንጋጌው መውጣት መነሻ የሆነውን የህግ ምክንያትሊወጣ ስለታሰበው ድንጋጌ ይዘት እና በውስጡ የተካተቱ ጭብጦች አስመልክቶ አጠቃላይ መግለጫበአገራችን 1993 ዓ.ም. በተዘጋጀው ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግf መሰረት ደንብ ማውጣት የሚፈልግ የአስተዳደር መ/ቤት ከ30 ቀናት በፊት የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች የያዘ ማስታወቂያ በጋዜጣg ማውጣት አለበት፡፡ስለ ረቂቅ ደንቡ ዓላማ አጭር ማብራሪያየደንቡ ረቂቅ የተፈቀደበት ሕጋዊ ስልጣንየደንቡ ረቂቅ ሰነድየደንቡ ረቂቅ ላይ ሰዎች የት፣ መቼና እንዴት አስተያየታቸውን እንደሚያቀርቡናየደንቡ ረቂቅ ላይ ስለሚሰጥ የቃል አስተያየት የማቅረብ ስርዓት በሚመለከት የት፣ መቼና እንዴት እንደሚካሄድ መጠየቅ እንደሚችሉ የሚገልጽ መረጃበ2001 ዓ.ም. ድጋሚ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይም እነዚህን አምስት መግለጫዎች የያዘ ማስታወቂያ በጋዜጣ ወይም በሌላ መገናኛ ብዙኃን ሊነገር እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡ የቃል አስተያየት (hearing) በአሜሪካ የመደበኛው ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ተፈጻሚነቱ ተቋሙ ይህን ስርዓት እንዲከተል ህግ አውጭው በልዩ ህግ በግልጽ ባመለከታቸው ውስን ሁኔታዎች የተገደበ ነው፡፡ የአገራችን አርቃቂዎች ባይገለጥላቸውም አሜሪካኖች ይህን አካሄድ የመረጡበት ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ የየትኛውም አገር አስተዳደር ውጤታማነት እና ቅልጥፍና ተቀዳሚ እሴቶቹ ናቸው፡፡ አንድ መመሪያ ለማውጣት እንደ ፍርድ ቤት ዓይነት ሙግት እየተደረገ፣ ደጋፊና የሚያስተባብል ማስረጃ እየቀረበ፣ የቃል ክርክር እየተሰማ በአጠቃላይ ከፍተኛ ወጪና ጊዜ በሚጠይቅ ሂደት ማለፍ አስገዳጅ ከሆነ አስተዳደር ይንዛዛል እንጂ አይቀላጠፍም፡፡ከላይ ከተዘረዘሩት የማስታወቂያ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በመጨረሻ ላይ የሚገኘው የቃል አስተያይት አቀራረብ ስርዓት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንደምታቸው ግዙፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መወሰን ይኖርበታል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ለመለየት ቋሚ መለኪያ ማበጀት ብዙም አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱም በጊዜና በሁኔታ ይለዋወጣሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሲመዘን ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ በጊዜ ሂደት ፋይዳው ሊያንስ ይችላል፡፡ ስለሆነም አሜሪካኖቹ እንደተከተሉት አማራጭ ህግ አውጭው በየጊዜው በሚያወጣቸው አዋጆች ቢወሰኑ ይሻላል፡፡ በሌላ አነጋገር የቃል አስተያየት የማቅረብ ስርዓት አስገዳጅነት የተወካዮች ም/ቤት በየጊዜው በሚያወጣቸው አዋጆች በግልፅ ሲደነገግ ብቻ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡ማማከር እና ማሳተፍ‘ምክክር’ የሚለው ቃል ከህዝብ አስተያየት መሰብሰብንና በአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ሂደት እንደ ግብዓት መጠቀምን ያመለክታል፡፡ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ሀሳብ ከመቀበል በተጨማሪ ምክክር አልፎ አልፎ በተወሰኑ ሁኔታዎች በቀጥታ የሚደረግ ውይይት ወይም ስብስባ ሊያካትት ይችላል፡፡ በጉዳዩ ጥቅም ያላቸው ወገኖች ተሳትፎ ሕዝባዊ ተቀባይነትና አመኔታን ያረጋግጣል፡፡ ተግባራዊ አፈጻጸሙንም ምቹ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም ዜጐች በቅድሚያ አውቀውት እንቅስቃሴያቸውን በደንቡና መመሪያው መሰረት እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል፡፡ምክክር ትርጉም የሚኖረው እውነተኛና በተግባር ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በካሊፎርኒያ ግዛት መመሪያውን የሚያወጣው የአስተዳደር መ/ቤት በህዝብ ከቀረቡ አስተያየቶችና ጥቆማዎች መካከል ያመነባቸውና የተቀበላቸው ካሉ በረቂቁ ላይ ማካተትና የማይቀበል ከሆነም ያልተቀበለበትን ምክንያት በመግለጽ ለሁለቱም መግለጫ (statement of reasons) ማቅረብ አለበት፡፡ተጠያቂነት እና የክለሳ ስርዓትበውክልና የሚወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በህግ አውጭው ከተሰመረለት ስልጣን በላይ አለማለፉን ማረጋገጥ ዋነኛው የአስተዳደር ህግ ዓላማ ነው፡፡ ዓላማውን ለመተግበር የስልጣን ወሰን ወይም ገደብ የሚቆጣጠር አካል ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ በእንግሊዝ ይህ የማጣራት ወይም የክለሳ ሂደት የሚከናወነው በዋነኛነት በራሱ በፓርላማ ሲሆን በአሜሪካ በተለይ በካሊፎርኒያ ግዛት በህግ የተቋቋመና ራሱን የቻለ የአስተዳደር ህግ ጽህፈት ቤት (Administraive Law office) ተብሎ በሚጠራ ተቋም አማካይነት ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በእንግሊዝ የመመሪያውን ህጋዊነት የማጣራት ሂደትና ስነ-ስርዓት ብዙውን ጊዜ ውክልና በሰጠው አዋጅ ላይ ይደነገጋል፡፡ ይህ ስነ-ስርዓት የማንጠፍ ስነ-ስርዓት (Laying procedure) ተብሎ ሲጠራ ውክልና ተቀባዩ አካል አስተዳደራዊ ድንጋጌውን ለፓርላማው የማቅረብ (በፓርላማ ፊት የማንጠፍ ወይም የመዘርጋት (laying before parlament) ወይም (laying before the table) ቅድመ ሁኔታን ያሰቀምጣል፡በዚህ ስነ-ስርዓት ፓርላማው በሚያደረገው ፍተሻና ምርመራ መሰረት ድንጋጌው ከስልጣን በላይ አለመሆኑና በአግባቡ ስለመውጣቱ ይጣራል፡፡ የማንጠፍ ስነ-ስርዓቱ የተለያዩ ቅርጽና መልክ ይኖረዋል፡፡ ነፃ የማንጠፍ ስነ-ስርዓት (Bare laying procedure) ድንጋጌው ተፈፃሚነት ከማግኘቱ በፊት ትክክለኛ ቅጂው ለፓርላማው እንዲቀርብ ያስገድዳል፡፡h ዋና ዓላማው ፓርላማው የድንጋጌውን ይዘት እንዲያየው ከማድረግ አይዘልም፡፡ ስለሆነም ለፓርላማ ከቀረበበት ቀን አንስቶ ወዲያውኑ ውጤት ይኖረዋል፡፡አሉታዊ የማንጠፍ ስርዓት (Negative resolution procedure) ከሆነ ደግሞ ድንጋጌው ለፓርላማ ከቀረበ ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ጥያቄ ከቀረበበትና ግድፈት ከተገኘበት ይሰረዛል ፡፡ ሆኖም ከመሰረዙ በፊት በድንጋጌው መሰረት የተወሰዱ እርምጃዎች እንደጸኑ ይቆያሉ፡፡ ካልተሰረዘ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ይሁንታ አግኝቷል ማለት ነው፡፡i ከዚህ በተቃራኒ ስርዓቱ አዎንታዊ የማንጠፍ ስርዓት (positive resolution procedure) በሚሆንበት ጊዜ ለፓርላማ ቀርቦ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡j የማንጠፍ ስርዓት መከተል ያለበት አስተዳደራዊ ድንጋጌ ስርዓቱን ባልተከተለ መንገድ የወጣ እንደሆነ ዋጋ አልባ (void) እንደሆነ ይቆጠራል፡፡በአገራችን ይህን መሰሉ ሆነ ሌላ ዓይነት የክለሳ ስርዓት አልተለመደም፡፡ ከስልጣን በላይ የሆኑ ደንብና መመሪያዎች ሲወጡ ህግ አውጭው የሚቆጣጠርበት መንገድ ባለመኖሩ የሚኒስተሮች ም/ቤትና የአስተዳደር መ/ቤቶች ልጓም አልባ ለመሆን ብሎም በዘፈቀደ ህግ ለመደንገግ አጋጣሚ ያገኛሉ፡፡ ይህ ያልተገራ ስልጣን የዜጐች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ፀር ሲሆን ህገ መንግስታዊ ዋስትናን ያሳጣል፡፡በካሊፎርኒያ በውክልና የሚወጣ ህግ ውጤት ኖሮት ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት የተወሰኑ መመዘኛዎች ማሟላት አለበት፡፡ መመዘኛዎቹ መሟላታቸውን የአስተዳደር ህግ ጽህፈት ቤት (Administraive Law Office) የተባለ በህግ የተቋቋመ አካል ያረጋግጣል፡፡ እያንዳንዱ መ/ቤት የሚያወጣውን አስተዳደራዊ ድንጋጌ ረቂቅ ለክለሳ ለዚህ ጽህፈት ቤት በቅድሚያ መላክ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር ከእንግሊዝ የማንጠፍ ስነ-ስርዓት ጋር በከፊል ይመሳሰላል፡፡ ጽህፈት ቤቱ ድንጋጌውን ሲከልስ የሚከተሉትን መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ ነው፡፡ስልጣን (Authority)፤ የአስተዳደር መ/ቤቱ ድንጋጌውን እንዲያወጣ ከህግ አውጭው በእርግጥ ውክልና የተሰጠው መሆኑማጣቀስ (Reference)፤ የአስተዳደር መ/ቤቱ በሚያወጣው ድንጋጌ ላይ የሚያስፈጽመው ህግ እና ስልጣን የሰጠውን ህግ አንቀጽ መጥቀሱ (ማመልከቱ)ወጥነት (Consistencey)፤ ድንጋጌው ስልጣን ከሰጠው ወይም ከሌላ ህግ ጋር የተስማማ ወይም የማይቃረንና የማይጋጭ መሆኑግልፅነት (Clarity)፤ የድንጋጌው ትርጉም ግልጽና በቀላሉ ለመረዳት የሚቻል መሆኑአለመደጋገም (Non- duplication)፤ ድንጋጌው ስልጣን የሰጠውን ህግ ድንጋጌዎች መድገም የለበትም፡፡ የህጉ ይዘት በከፊል ወይም በሙሉ በድጋሚ በድንጋጌው ላይ ከሰፈረ መመዘኛው አልተሟላም፡፡ህትመት‘ህትመት’ የሚለው ቃል በአፍ የሚደነገግ መመሪያ እንደሌለ ያመለክታል፡፡ ‘የህግ መታተም’ ሲባል አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ለህዝብ በቀላሉ ሊደርስ በሚችል ወጥ የህትመት ውጤት ላይ ታትሞ ለህዝብ ማሰራጨት ማለት ነው፡፡ ህግ በጽሑፍ ላይ ሰፍሮ መውጣቱ ብቻ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ታትሞ መውጣቱ ሳይሆን ህትመቱ ይፋ መደረጉና በቀላሉ ለህዝቡ የሚደርስ መሆኑ ነው፡፡ ዜጎች ላልታተመና ይፋ ላልሆነ ብሎም በቀላሉ ለማይገኝ ህግ ሊገዙ አይችሉም፡፡ ድብቅ ህግ ህጉን ካወጣው አካል በስተቀር አውቆት የሚያከብረው አይኖርም፡፡በእንግሊዝ ውስጥ በብላክፑል ኮርፖሬሽን እና ሎከር (Blackpool Corporation Vs. Locker) መካከል በነበረው ክርክር ላይ በተሰጠ ውሳኔ የህትመት አስፈላጊነት እንዲህ ተገልጾ ነበር፡፡kህግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም የሚለው መርህ በእንግሊዝ ዲሞክራሲ የህግ የበላይነት የቆመበትን መሪ ሀሳብ ይወክላል፡፡ ነገር ግን የዚህ መርህ የትክክለኛነቱ መሰረት ሁሉም ህጐች በቀላሉ ለህዝቡ እንደሚደርሱ ግምት በመውሰድ ነው፡፡በአሜሪካ በእያንዳንዱ የፌደራል መንግስት የአስተዳደር መ/ቤት የሚወጣ አስተዳደራዊ ድንጋጌ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ ፌደራል ሬጅስተር (Federal Regiser) ተብሎ በሚጠራ ወጥና መደበኛ ጋዜጣ ላይ መታተም አለበት፡፡ እያንዳንዱ መመሪያ በጋዜጣው ላይ ሲታተም የራሱ መለያ ቁጥር ስለሚሰጠው ፈልጐ ለማግኘት በጣም ቀላል ያደርገዋል፡፡ መመሪያውን ማግኘት የሚፈልግ ሰው ከመ/ቤቱ ወይም ከጋዜጣው ድረ-ገጽ ላይ በቀላሉ በነጻ ማንበብና መቅዳት ይችላል፡፡ በተጨማሪ በአካል ሄዶ ጋዜጣውን በአነስተኛ ክፍያ መግዛት ሌላው አማራጭ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1946 ዓ.ም. በወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ (Administrative Procedure Act) መሰረት ማንኛውም መመሪያ ተፈፃሚነት የሚኖረው በፌደራል ሬጅስተር ከታተመ ከ30 ቀናት በኃላ ነው፡፡ በእነዚህ 30 ቀናት ውስጥ ማንኛውም ሰው መመሪያውን ለማግኘትና ይዘቱን ለመረዳት በቂ ጊዜ ያገኛል፡፡በተመሳሳይ ወቅት (እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም.) በእንግሊዝ የወጣው ህግ (statutory instrumnets act) ከተወሰኑ አስተዳራዊ ድንጋጌዎች በስተቀር ከሞላ ጎደል ሁሉም ተፈጻሚ ከመሆናቸው በፊት በይፋ እንዲታተሙና ለህዝብ እንዲሰራጩ ያስገድዳል፡፡m ህጉ በማያካትታቸው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ ዓይነቶች ህትመት ቅድመ ሁኔታ ባይሆንም አብዛኛዎቹ የአስተዳደር መ/ቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲታተሙ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም በልዩ ህግ ላይ ህትመት እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጠ አስገዳጅ ነው፡፡ ድንጋጌው በይፋ ካልታተመ ውጤት ወይም ዋጋ አይኖረውም፡፡በህንድ ኦፊሴሊያዊ በሆነ ጋዜጣ እንዲታተሙና ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ የሚያስገድድ አንድ ወጥ ህግ የለም፡፡ ሆኖም ስልጣን በሚሰጠው ህግ ላይ የህትመት ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ እንደሆነ በአስተዳደር መ/ቤቱ ላይ አስገዳኝነት አለው፡፡nበኢትዮጵያ ውስጥ ከአዋጅና ደንብ በስተቀር በአስተዳደር መ ቤቶች  በየጊዜው የሚወጡት  ስፍር ቁጥር የሌላቸው መመሪያዎች በነጋሪት ጋዜጣ አይታተሙም፡፡ ስልጣን የሚሰጠው አዋጅም በስተቀር ህትመትን እንደቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም፡፡

2 thoughts on “⚖️በአገራችን ስላለው የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ አጠቃላይ ዳሰሳ ⚖️መመሪያ የሌለው መመሪያ ⚖️”

  1. Thank you for your instructive and helpful legal knowledge.I am always your follower on the website. I always receive a daily email address for legal information that you write on your website. Thank you for your knowledge. Turn us on

    Liked by 1 person

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.