ጋብቻ በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ውጤት
አንቀጽ ፵፱ መከባበር መተጋገዝና መደጋገፍ
፩. ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ አለባቸው፡፡
፪. በጋብቻው ውል ውስጥ ይህንን የሚቃረን ስምምነት ማድረግ አይችሉም፡፡
አንቀጽ ፶ የቤተሰብ የጋራ አመራር (፩) ጠቅላላ
፩. በቤተሰብ አመራር ረገድ ባልና ሚስት እኩል መብት አላቸው፡፡
፪. ባልና ሚስቱ በማናቸውም ረገድ የቤተሰቡን ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ለልጆቻቸው በመልካም ሥነምግባር እንዲታነፁ፣ ተገቢ ትምህርት እንዲቀስሙና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ መተባበር አለባቸው፡፡
አንቀጽ ፶፩ (፪) ከተጋቢዎቹ አንዱ ቤተሰቡን ለመምራት ስላለመቻሉ
፩. ከባልና ሚስት አንደኛው ችሎታ ያጣ፣ የጠፋ ወይም ቤተሰቡን ጥሎ የሔደ ወይም ከመኖሪያ ሥፍራው በመራቁም ሆነ በማናቸውም ሌላ ምክንያት ፈቃዱን ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ በሚገኝበት ጊዜ፣ በአንቀጽ ፶ የተመለከተውን የቤተሰብ አመራር አንደኛው ተጋቢ ብቻውን ይፈጽማል፡፡
፪. ባልና ሚስት በጋብቻ ውላቸው ውስጥ ይህንን የሚቃረን ስምምነት ማድረግ አይችሉም፡፡
አንቀጽ ፶፪ ከጋብቻ በፊት ከሌላ ስለተወለዱ ልጆች
፩. ከባልና ከሚስቱ አንዱ ከጋብቻው በፊት ከሌላ የወለዳቸውን ልጆች መልካም አስተዳደግ በሚመለከት በራሱ አሳብና መሪነት የፈቀደውን ውሳኔ ለማድረግ ሙሉ መብት ይኖረዋል፡፡
፪. ይህንን የሚቃረን ማናቸውም ስምምነት ውጤት አይኖረውም፡፡
አንቀጽ ፶፫ አብሮ መኖር
፩. ባልና ሚስት አብረው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡
፪. ለጤናቸው አደገኛ ካልሆነ በስተቀር ባልና ሚስት ከጋብቻ የሚጠበቀውን መደበኛውን የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም አለባቸው፡፡
፫. ይህንን የሚቃረን ማናቸውም ስምምነት ውጤት አይኖረውም፡፡
አንቀጽ ፶፬ የመኖሪያ ሥፍራን ስለመወሰን
ባልና ሚስት የሚኖሩበትን ሥፍራ በጋራ ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ ፶፭ በስምምነት ተለያይቶ ስለመኖር
፩. በዚህ ሕግ በአንቀጽ ፶፫ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው ቢኖርም ባልና ሚስቱ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው ለመኖር መስማማት ይችላሉ፡፡
፪. ስለዚህ ጉዳይ የተደነገገውን ስምምነት መለወጡ የማይገባ ካልሆነ በስተቀር ከሁለቱ ተጋቢዎች አንደኛው አስቦ ሊሰርዘው ይችላል፡፡
አንቀጽ ፶፮ የመተማመን ግዴታ
ባል ለሚስቱ፣ ሚስት ለባልዋ ታማኝ የመሆን ግዴታ አለባቸው፡፡

Thanks so much
LikeLiked by 1 person
you welcome
LikeLike