የአስተዳደር ጥፋት ምንድነው?


የአስተዳደር ጥፋት ምንድነው?

የአስተዳደር ጥፋት ምንድነው?

የእንባ ጠባቂን የስልጣን ገደብ በመወሰን ረገድ ዓብይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ‘የአስተዳደር ጥፋት’ ለሚለው አገላለጽ የሚሰጠው ፍቺ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ እንባ ጠባቂው የሚቀርብለት አቤቱታ የአስተዳደር ጥፋት ተብሎ የሚፈረጅ አይነት ካልሆነ ጉዳዩን ተቀብሎ የመመርመር ስልጣን የለውም፡፡ የአስተዳደር ጥፋትን የማይመለከት አቤቱታ ከእንባ ጠባቂው የስልጣን ክልል ስለሚያልፍ አቤቱታውን ተቀብሎ ከማስተናገድ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
ለዚህ ደግሞ በአስተዳደር ጥፋት ስር የሚጠቃለሉትን ድርጊቶች፣ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ምንነት፣ አይነትና ይዘት ግልጽ በሆነ መለኪያ መለየት ይጠይቃል፡፡ የእንባ ጠባቂ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ‘የአስተዳደር ጥፋት’ በእንግሊዘኛው maladministration የሚል አቻ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በአዋጁ መግቢያ ደግሞ ይኸው የእንግሊዝኛ ቃል ‘አስተዳደራዊ በደል’ ለሚለው የአማርኛ ቃል ወካይ ትርጉም ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
ምንም እንኳን አዋጁ የአስተዳደር በደል የሚለውን አገላለፅ በመግቢው ላይ አንድ ጊዜ ብቻ የተጠቀመበት ቢሆንም በተወሰነ መልኩ የአስተዳደር ጥፋት እና የአስተዳደር በደል ተመሳሳይ ትርጓሜ እንዳላቸው አመላካች ይመስላል፡፡ አዋጁ ሲረቅቅ በጊዜው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የህግና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ‘የአስተዳደር በደል’ የሚለውን ቃል የተጠቀመ ሲሆን ለቃሉ የሚሰጠው ፍቺም የእንባ ጠባቂውን ስልጣን በመወሰን ረገድ ዋናውና ቁልፍ ስለመሆኑ አስምሮበታል፡፡ ቁልፍና ወሳኝ ጉዳይ ቢሆንም የአስተዳደር ጥፋቶች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ማቋቋሚያ አዋጁ ግልጽና የማያወላዳ መለኪያ ሳያስቀምጥ አልፎታል፡፡ በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ላይ ‘የአስተዳደር ጥፋት’ ምንነት እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
የአስተዳደር ጥፋት ማለት ማናቸውንም የአስተዳደር ህግን፣ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ህግን ወይም አስተዳደር ነክ ህጐችን በመጻረር በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚፈፀሙ ድርጊቶችን ወይም የሚሰጡ ውሳኔዎችን ይጨምራል፡፡a
የድንጋጌውን ግልጽነት በሚገባ ለመፈተን የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፡፡ በመንግስት ዩኒቨርሲቲ በሚማሩ ተማሪዎች በሚከተሉት ሁኔታዎች የአስተዳደር በደል ተፈፅሞብኛል የሚል አቤቱታ ለእንባ ጠባቂው ሊቀርብ ይችላል፡፡
በአንድ የትምህርት አይነት የወሰድኩት ፈተና ትክክለኛ መልሱን የመለስኩ ቢሆንም አለአግባብ ዝቅተኛ ውጤት ተሰጠኝ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሬጅሰትራር አማካይ ውጤቴን ከሴኔት ደንብ ውጭ በማስላት ዝቅ አድርጐብኛል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የመግቢያ ሰዓት እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ብቻ እንዲሆን መደረጉ የመንቀሳቀስ መብታችንን የሚጋፋ ነው፡፡
ጥፋት ሳልፈጽምና ስለመፈጸሜም በቂ ማስረጃ ሳይኖር አለአግባብ ከዩኒቨርሲቲው በዲሲፒሊን ተባረርኩኝ፡፡
የወጪ መጋራት ክፍያ ካልከፈልክ የትምህርት ማስረጃ አይሰጥህም ተባልኩኝ፡፡
ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ በግቢው ውስጥ ከወንድ ጋር ተገኝተሻል በሚል ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲሲፒሊን መተዳደሪያ ደንብ ጠቅሶ እንድቀጣ ተደርጌያለሁ፡፡ ስለሆነም ህገ- መንግስቱን በተጻረረ መልኩ በወጣ ደንብ የተወሰደብኝ ቅጣት እንዲነሳልኝ፡፡
በተወሰደብኝ የዲሲፕሊን እርምጃ ላይ ለዩኒቨርሲቲው የበላይ አካል ያቀረብኩት ይግባኝ አለአግባብ ምላሽ ሳይሰጠው ዘግይቷል፡፡
የመኝታ ክፍላችን (ዶርም) ከህግና ከህገ መንግስት ውጭ በጥናት ደክመን በምንተኛበት ወቅት እኩለ ለሊት ላይ በግቢው የጥበቃ አባላት ይፈተሻል፡፡
የተመደበልን መምህር እንዲቀየርልን በተደጋጋሚ ለዩኒቨርሲቲው ያቀረብነው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ አልተሰጠውም፡፡
የሚቀርብልን ምግብ ጥራቱን የጠበቀ አይደለም፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲው መግቢያ የሚወስደው መንገድ መብራት ስለሌለው በሴት እህቶቻችን ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው፡፡ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ላቀረብነው ተደጋጋሚ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አልተሰጠንም፡፡
ከላይ ከቀረቡት መላምታዊ ምሳሌዎች መገንዘብ እንደሚቻለው በአንድ የመንግስት ተቋም ውስጥ ብቻ የተራራቀ ይዘት ያላቸው የተለያዩ የቅሬታ ምክንያቶችን መሰረት ያደረጉ አቤቱታዎች ለእንባ ጠባቂው ይቀርባሉ፡፡ ተቋሙ አንድን አቤቱታ ተቀብሎ ከማስተናገዱ በፊት አቤቱታው እውነት ነው ተብሎ ቢገመት የአስተዳደር ጥፋት ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ስለመሆኑ በቅድሚያ ማረጋገጥና መወሰን ይኖርበታል፡፡
ማናቸውም አቤቱታ ተመርምሮ ለአቤቱታ አቅራቢው መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ይህ ጥያቄ መጀመሪያ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ የቀረበው አቤቱታ የአስተዳደር ጥፋትን የማይመለከት ከሆነ ምርምራ ሳይጀመር ውድቅ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በህጉ ላይ ለአስተዳደር ጥፋት የተሰጠው ትርጓሜ የእንባ ጠባቂውን ፈተና አያቃልልም፡፡ በደፈናው ሲታይ በአዋጁ ላይ ለአስተዳደር ጥፋት የተሰጠው ትርጓሜ ከህግ ውጪ የተፈጸመ ድርጊትን ብቻ የሚሸፍን ይመስላል፡፡ በዚህ መልኩ ከተረዳነው የአስተዳደር ጥፋት ይዘት የእንባ ጠባቂውን ስልጣን በጣም ያጠበዋል፡፡
የአስተዳደር ጥፋት በግልፅ የተቀመጠን ህግ መጻረር ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‘የመንገድ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ለጾታዊ ጥቃት ተጋለጥን፣ ለጥያቄያችንም በቂ ምላሽ አልተሰጠንም፡፡’ የሚል አቤቱታ ‘ህግ መጻረር’ ውስጥ አይካተትም፡፡ ሆኖም ለዜጐች ተገቢ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ በአፋጣኝ አለመስጠት የአስተዳደር ጥፋት ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ጉዳዮች የአስተዳደሩ የውስጥ ጉዳዮች በመሆናቸው ለአስተዳደሩ ለራሱ መተው ያላባቸው ናቸው፡፡ ህገ መንግስታዊው የስልጣን ክፍፍል መርህ እንባ ጠባቂው ራሱን በአስተዳደሩ ምትክ ቦታ እንዳያስገባ ገደብ ያደርግበታል፡፡
የምርመራ አካሄድ ስርዓትና መፍትሔዎች
እንባ ጠባቂ ተቋም እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረበላቸው አቤቱታ ይዘት በስልጣናቸው ክልል ውስጥ የሚወድቅ ከሆነ ቀጣዩ ተግባር የአስተዳደር ጥፋት ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙንና ጥፋቱ የተፈፀመበትን ሁኔታ ብሎም የጥፋቱን ደረጃ ለመወሰን ምርመራ ማከናወን ነው፡፡ ምርመራው አቤቱታ ባይቀርብም በራስ ተነሳሽነት ሊካሄድ ይችላል፡፡ ቅሬታ በደረሰበት ወገን የሚቀርበው አቤቱታ የግድ በማስረጃ የተደገፈ መሆን አይኖርበትም፡፡ ከአቤቱታ አቅራቢው የሚጠበቀው ‘በተቻለ መጠን’ ደጋራ ማስረጃ ማቅረብ ነው፡፡
በዚህ የምርመራ ሂደት ውስጥ ተመርማሪው አካል መልሱን የማቅረብ መብት ያለው ስለመሆኑ በማያሻማ መልኩ አልተገለጸም፡፡ በሁለቱም አዋጆች አንቀጽ 25 መሰረት ተመርማሪዎች መልስ እንዲሰጡ ማድረግ የመርማሪው ስልጣን እንጂ የተመርማሪው መብት አይደለም፡፡
የምርመራው አካሄድና ስርዓት በተመለከተ ሁለቱም ተቋማት በማቋቋሚያ አዋጃቸው አንቀጽ 24 የተሰጣቸው ስልጣን ተግባራቸውን በሚገባ ለማከናወን በሚገባ፡፡ በአንቀጽ 24 መሰረት የምርመራ ስልጣን፤
ተመርማሪዎች ለጥያቄ እንዲቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ
ምስክሮች ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ
በሶስተኛ ወገን እጅ ያለ ማስረጃ እንዲቀርብ ማድረግን ይጨምራል፡፡
በምርመራ ሂደት ውስጥ ሆነ በሌሎች የተቋሙና የኮሚሽኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ማንኛውም ሰው በተለይም አስፈፃሚ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠትና የመተባበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በተወሰኑ ሁኔታዎች ለመተባበር ፍቃደኛ አለመሆን የወንጀል ተጠያቂነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ተቋሙ እና ኮሚሽኑ ምርመራቸውን ሲያከናውኑ መጥሪያ ተቀብሎ ካለበቂ ምክንያት መቅረት፣ ሰነዶች ለመስጠት ወይም ለማስመርመር ፍቃደኛ አለመሆን እንዲሁም ቀርቦ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን ከአንድ ወር እስከ 6 ወር በሚደርስ እስራት ወይም ከብር ሁለት መቶ እስከ አንድ ሺህ በሚደርስ ገንዘብ መቀጫ ወይም በሁለቱም ያስቀጣል፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.