በህግ የተቀመጠ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት
በህግ የተቀመጠ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት

በህግ የተቀመጠ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት
በአገራችን ወጥ የአስተዳደር ህግ ባይኖርም የአስተዳደር መ/ቤቶች በግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ እርምጃ የሚወስዱት ሁለወጊዜ በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ይብዛም ይነስም በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ተደንግገዋል፡፡ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ከክስ መሰማት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ድረስ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚከተሉት ስነ ስርዓት በዚህም ፍትሐዊነት የሚገለጽበት መንገድ ደረጃው ይለያያል፡፡ በአንዳንዶቹ ጠበቅ ያለና መደበኛነት የሚታይበት ሲሆን በሌሎቹ ደግሞ ቀላል እና ‘ልል’ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡
ከሞላ ጎደል ሁሉንም የመሰማት መብት እና የኢአድሎአዊነት መርሆዎች ያሟላ በዓይነቱ በአሜሪካው የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ላይ ‘መደበኛ’ ተብሎ የተገለጸውን የአስተዳደር ዳኝነት የሚመስል የክርክር ስርዓት የሚገኘው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006 ላይ ነው፡፡ ስርዓቱ የተዘረጋው ህግን በመተላለፍ ጥፋት በሚፈጽም ኦዲተር ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ነው፡፡ ከክስ አመሰራረት እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ የክርክሩ አመራር ስርዓት በአዋጁ ከአንቀጽ 38-43 ባሉት ድንጋጌዎች የሚመራ ሲሆን ሂደቱ አጠር ተደርጎ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል፡፡
አዋጁ የኢ-አድሎአዊነት መርህን ለማረጋገጥ የሚና መደበላለቅን አስቀርቷል፡፡ የመርማሪነት፣ ከሳሽነት እና ውሳኔ ሰጭነት ሚናዎች በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሰራተኛ/ተሿሚ ተለይተው ተከፋፍለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ‘መርማሪ ሹም’ የሚባል የቦርዱ ተቀጣሪ ሠራተኛ ወይም ከቦርዱ ጋር የቅጥር ግንኙነት ያልመሰረተ ብቃት ያለው ባለሞያ የምርመራ ተግባር ያከናውናል፡፡ መርማሪ ሹሙ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያምንበት ክስ እንዲመሰረት ለቦርዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ የውሳኔ ሀሳብ ከማቅረብ ውጪ በራሱ ክስ አያቀርብም፡፡ በአዋጁ የከሳሽነት ሚና የተሰጠው ለስራ አስፈፃሚው ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚው ክስ ለመመስረት ከወሰነ በምርመራ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩ ከመካከላቸው አንዱ የህግ ባለሞያ የሆነ ሶስት የቦርዱን ሰራተኞች በክስ ሰሚነት ይሰይማል፡፡ እነዚህ ክስ ሰሚዎች (hearing examiners) ክርክሩን ሰምተው የመጨረሻ ውሳኔ የማስተላፍ ስልጣን አላቸው፡፡
የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበት ሰው ስለቀረበበት ክስ ይዘት የማወቅ እና በራሱ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ቀርቦ ማስረጃውን የማቅረብ፣ ምስክሮቹን በመጥራት ቀጥተኛ ጥያቄ መጠየቅና እና ለከሳሽ ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብቱ በአዋጁ አንቀጽ 39/2/ ተጠብቆለታል፡፡ በግራ ቀኙ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች በተጨማሪ ክስ ሰሚዎች ለጉዳዩ አወሳሰን ጠቃሚ ማስረጃ ይዞ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በመጥሪያ በመጥራት በቃለ መሀላ የማረጋገጫ ቃሉን መቀበልና አግባብነት ያላቸውን ሰነዶችና ማስረጃዎች እንዲያቀርብ የማስገደድ ሰፊ ዳኝነታዊ ስልጣን ተጎናጽፈዋል፡፡ ክስ ሰሚዎች በክርክሩ ሂደት የቀረቡትን ማስረጃዎችና ክርክሩን ከመረመሩ በኋላ ክስ የቀረበበት ተከሳሽ አዋጁንና በአዋጁ መሰረት የወጣን ደንብና መመሪያ መተላለፍ አለመተላፉን ይወስናሉ፡፡ የህግ መተላለፍ ከተፈጸመ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ እስከ ፈቃድ መሰረዝ ብሎም እስከ 25,000 (ሃያ አምስት ሺ ብር) የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ሌሎች በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡
ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በሚወስዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች ላይ ተፈጻሚ ይደረጋል፡፡ በሲቪል አቪዬሽን አዋጅ ቁ. 616/2001 አንቀጽ 80/1/ ላይ እንደተደነገገው ባለስልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሊወስደው ስላሰበው እርምጃ ለሚመለከተው ሰው ማሳወቅና እርምጃው ሊወሰድ አይገባም የሚልበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ዕድል መስጠት አለበት፡፡ ማስታወቂያው ጥፋት መፈጸሙን የሚገልጽ ክስ ሳይሆን በምርመራ ግኝት ባለስልጣኑ ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ ድምዳሜውን ለማስተባበል የሚደረግ ጥሪ ነው፡፡ ስለሆነም በምርመራ ሂደት ባለስልጣኑ የሚሰማቸውን ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ ዕድል አይኖርም፡፡ ሆኖም ቀጣይ የአዋጁ አንቀጽ 80/4/ ድንጋጌ በጠበቃ ወይም በባለጉዳዩ በራሱ ክርክር የማሰማት መብትን የሚፈቅድ እንደመሆኑ ማስረጃ የማቅረብና ምስክር ማሰማት የስነ ስርዓቱ አካል አድርጎ መቁጠር ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የባለስልጣኑ ሠራተኛ የግል ጥቅሙን በሚነካ ጉዳይ በምርመራ ሂደት እንዳይሳተፍ ገደብ የሚጥለው የአዋጁ አንቀጽ 80/3/ በከፊልም ቢሆን ከአድልኦ የፀዳ ውሳኔ እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የአስተዳደር መስሪያ ቤት ህግን በማስከበር ስልጣኑ በቀጥታ ከሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና ከሚወስዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ ዳኝነታዊ ተግባራት ሲያከናውን ጠበቅ ያለ ስርዓት ይከተላል፡፡ በኢትዮጵያ የውሀ ሀብት አስተዳደር አዋጅ ቁ. 197/1992 የማዕከል ውሀ ሀብት አስተዳደርን አስመልክቶ የቁጥጥር ተግባራት እንዲያከናውን ስልጣን የተሰጠው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የውሀ ግልጋሎት ፈቃድ የተሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ከፈቃዱ ጋር የተያያዙ መብትና ግዴታዎችን አስመልክቶ በመካከላቸው የሚነሱ ክርክሮችን እንዲሁም በባለ ፈቃድ እና በሌላ ሶስተኛ ወገኖች መካከል የሚፈጠሩ ማናቸውንም ክርክሮች ሰምቶ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በውክልና በሰጠው የህግ አውጭነት ስልጣን መሰረት ክርክሮቹ የሚመሩበት ስርዓት በደንብ ቁ. 115/1997a ተደንግጓል፡፡
በተቆጣጣሪው ባለስልጣን ዘንድ በሚካሄደው የክርክር አመራር ስርዓት ላይ መደበኛው የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ተፈጻሚነት አለው፡፡ በደንቡ ላይ ተለይተው የተቀመጡት ጥቂት የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎችም ቢሆኑ ጠበቅ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በተቆጣጣሪው አካል የሚካሄደው ክርክር በይዘቱ ፍርድ ቤቶች ከሚከተሉት የሙግት ስርዓት ጋር ይቀራረባል፡፡
ክርክሩ የሚጀመረው አቤት ባዩ በሚያቀርበው ማመልከቻ ነው፡፡ ማመልከቻው የክርክሩን ፍሬ ሀሳብ (በእንግሊዝኛው ቅጂ memorandum summarizing the dispute) እና ማስረጃ እንዲሁም የአቤት ባዩን ቅሬታ እና እንዲሰጥለት የሚፈልገውን ውሳኔ አካቶ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በይዘቱ ከመደበኛው የክስ አቤቱታ ብዙም አይለይም፡፡ ተቆጣጣሪው አካል ማመልከቻውን እንደተቀበለ ክርክሩ የሚሰማበትን ቦታና ጊዜ የሚገልጽ መጥሪያና የማመልከቻ ቅጂ ለተከሳሹ እንዲደርሰው ያደርጋል፡፡ በቀጠሮ ቀን ባለጉዳዮች በቀጠሮ ሰዓትና ቦታ ተገኝተው ጉዳያቸውን ያስረዳሉ፡፡ ማስረጃም ያቀርባሉ፡፡ በሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡ ማስረጃዎች በተቆጣጣሪው አካል ይመዘገባሉ፡፡ ተከሰሹ መጥሪያ ደርሶት ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት ይሰማል፡፡ ተቆጣጣሪው ጉዳዩን ሰምቶ የሚሰጠውን ውሳኔ ባለጉዳዮች እንዲያውቁት ማድርግ ያለበት ሲሆን በተጨማሪም የውሳኔውን መዝገብ ግልባጭ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
በደንቡ ላይ ለውሳኔ ምክንያት መስጠት እንደ ቅድመ ሁኔታ አልተቀመጠም፡፡ ይሁን እንጂ ተቆጣጣሪው እንደ አግባብነቱ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህጉን ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ ያለበት እንደመሆኑ ምክንያት የጎደለው ውሳኔ በፍርድ ቤት መሻሩ አይቀርለትም፡፡
የመሰማት መብት በህጉ ቢፈቀድም በጥቅል አነጋገር በሚገለጽበት ጊዜ የመብቱን ወሰን አፈጻጸም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የክፍያ መ
ፈጸሚያ ተቋምን ወይም የግብይት ፈጻሚዎችን ወይም የማህበራቸውን ዕውቅና ከማገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት መጀመሪያ የተቋሙ ኃላፊዎች በማስታወቂያ እንዲያውቁት ማድረግና ለባለጉዳዩ የመሰማት ዕድል መስጠት ይኖርበታል፡b የድንጋጌው አነጋገር የጠቅላላነት ባህርይ ቢታይበትም የመሰማት መብት መሰረታዊ የአስተዳደር ፍትሕ ጥያቄ እንደመሆኑ ዕውቅና ከመታገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት ቅድመ ክስ ማስታወቂያ፣ ማስረጃ የማቅረብ መብትና ተቃራኒ ማስረጃ የማስተባበል መብት ተሟልተው ሊገኙ ይገባል፡፡
ከላይ ያየነው ዓይነት ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጋር የሚቀራረብ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት አፈጻጸሙ በውስን አስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ በጣም በርካታ መ/ቤቶች ለስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የሚገዙት በጣም በስሱ ነው፡፡ አብዛኛው ቀዳሚ ውሳኔ /initial decision/ በአስተዳደራዊ የሙግት ሂደት ስር አያልፍም፡፡ ውሳኔ አሰጣጡ በባህርዩ መርማሪ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል አያሳትፍም፡፡ ህግ መጣሱ የሚረጋገጠው መ/ቤቱ በሚቀርብለት ጥቆማ ወይም በራሱ አነሳሽነት በሚያካሂደው ምርመራና ማጣራት አማካይነት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ጥፋት መፈጸሙ አስቀድሞ አቋም ይያዝበታል፡፡ ሆኖም መ/ቤቱ የደረሰበት ድምዳሜ አስገዳጅነት ወዳለው የመጨረሻ ውሳኔ ከመሸጋገሩ በፊት የሚመለከተው አካል አስተያየት ወይም ምላሽ እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡ መልስ ሰጭው የቀረበበትን ማስረጃ የማስተባበል አሊያም ተቃራኒ ማስረጃ የማቅረብ በህግ የተጠበቀ መብት የለውም፡፡
ልል የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ከሚደነግጉ ህጎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመድን ሰጪ ድርጅት ያካሄደው ምርመራ የመጨረሻ ሪፖርት ከመዘጋጀቱ በፊት ለተመርማሪው መድን ሰጪ ድርጅት እንዲደርሰው ተደርጎ በሪፖርቱ ላይ አስተያየቱን እንዲያቀርብ ዕድል ይሰጠዋል፡፡c
/ንግድና ኢንዱስትሪ/ ሚኒስቴሩ ወይም የእርሱ ተወካይ የአንድ ባለዕቃ ማከማቻ ቤት የግብርና ምርት ውጤቶች ተቆጣጣሪ፣ መዳቢ፣ ደረጃ ሰጪ፣ መዛኝ ወይም ናሙና አውጭ የሥራ ፈቃድ ለዘለቄታው እንዲሰረዝ ከመወሰኑ በፊት አጥፍቷል የተባለው ጥፋት በጽሑፍ እንዲገለጽለትና በቂ ጊዜ ተሰጥቶት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥበት ወይም መቃወሚያ እንዲያቀርብበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡d
በአንዳንድ ህጎች ላይ ደግሞ የመሰማት መብት ውሳኔውን በማሳወቅ ላይ ብቻ ይገደባል፡፡ በእርግጥ ውሳኔው አግባብ እንዳልሆነ በቃል ሆነ በጽሑፍ ማስተባበል ካልተቻለ የመሰማት መብት መነፈጉን እንጂ በከፊል መገደቡን አይደለም የሚያሳየው፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴሩ የዕፅዋት አዳቃዮችን መብት ለመሰረዝ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ለመሰረዝ የበቃበትን ምክንያት በመግለጽ ለባለመብቱ የጽሑፍ ማስታወቂያ መስጠትና መብቱ የተሰረዘ መሆኑን ለሕዝብ ማስታወቅ አለበት፡፡e ማስታወቂያው የመሰረዝ ውሳኔውን ከማሳወቅ የዘለለ ውጤት የለውም፡፡ ባለመብቱ የእርምጃውን ህጋዊነት ለመቃወም የሚችልበት ቀዳዳ የለም፡፡
አንዳንድ ጊዜ የመሰማት መብት የሚፈቀደው ከውሳኔ በኋላ ይሆናል፡፡ የዘር አስመጪ፣ ላኪ፣ የዘር አምራች፣ አዘጋጅ፣ ጅምላ ሻጭ፣ አከፋፋይ ወይም ቸርቻሪ በዘር አዋጅ ቁ. 782/2005 አንቀጽ 21/1/ እና /2/ መሰረት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ወይም በክልል ባለስልጣን ከመታገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት በድንጋጌው ላይ የተጠቀሱት በቂ ምክንያቶች እውነት ስላለመሆናቸው ለማስረዳትና ተቃራኒ ማስረጃ ለማቅረብ ዕድል አልተሰጠውም፡፡ ሆኖም ከውሳኔው በኋላ ውሳኔውን ለሰጠው አካል አስተዳደራዊ ቅሬታ የማቅረብ መብቱ በአንቀጽ 25/1/ ተጠብቆለታል፡፡ አመልካቹ በተሰጠው ምላሽ ካልረካ ቅሬታውን ለሚመለከታው የፍትሕ አካል ሊያቀርብ እንደሚችል በድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ 2 ተመልክቷል፡፡

ህገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?

ህገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?
የተፈጥሮ ፍትሕ በእንግሊዝና ሌሎች ኮመን ሎው አገራት በዳኞች የዳበረ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርህ ነው፡፡ ይህ መርህ በህግ በግልጽ እንደ ቅድመ ሁኔታ ባይቀመጥም ዳኞች ተፈጻሚ እንዳያደርጉት አያግዳቸውም፡፡ በአሜሪካ እንዲሁ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኘው ዱ ፕሮሰስ ኦፍ ሎው (Due Process of Law) በመባል የሚታወቀው ህገ መንግስታዊ መርህ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን የሚገዛ ልዩ ህግ ባይኖርም እንኳን ፍርድ ቤቶች እንደ አግባብነቱ ተፈጻሚ ያደርጉታል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ሁለት አገራት ሆነ በሌሎችም ዘንድ አስተዳደር የሚመራበት ስነ ስርዓት ምንጩ በህግ አውጪው የሚወጣ ህግ ነው፡፡
ግልጽ የህግ ድንጋጌ ካለ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት ውሳኔ በፍርድ ቤት ሊሻር ወይም ሊሰረዝ እንደሚገባው አያጠራጥርም፡፡ አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ከሌለስ? ፍርድ ቤቶቻችን እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ፍርድ ቤቶች ፍትሐዊ የውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ማዳበርና ተፈጻሚ ማድረግ አለባቸው? ካለባቸውስ አቋማቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት አለው? በአስተዳደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የመሰማት መብት እንዲሁም ኢ-አድሎአላዊነት መርህ በህግ በግልጽ ባልተደነገገበት ሁኔታ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት አስተዳደራዊ ውሳኔ ዕጣ ፋንታ መወሰን በብዙ መልኩ ከባድ ነው፡፡
በአንድ በኩል ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የማረጋገጥ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ህጉን ከማንበብና ከመተርጎም ባለፈ ህግ መጻፍ ህገ መንግስታዊ ሚናቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጠረው ‘ህገ መንግስታዊ አጣብቂኝ’ ብርታትና ጥንቃቄ ካልታከለበት በቀላሉ አይፈታም፡፡ በተጨማሪም ‘መርህ’ በተጨባጭ ‘መሬት ሲወርድ’ ከልዩ ሁኔዎች ጋር ሊጣጣምና የተፈጻሚነት ወሰኑ በአግባቡ ሊሰመር ይገባል፡፡ የመሰማት መብት የግድ የሚልበት ሁኔታ ቢኖርም ከተግባራዊ ፋይዳውና ውጤታማ አስተዳደር አንጻር የሚገደብባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በተጨማሪም የተፈፃሚነቱ ወሰን የግለሰብ መብት ወይም ጥቅም በሚነካ የዳኝነታዊ ባህርይ ባለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አስቸጋሪው ስራ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን በጠቅላላው መቀበሉ ሳይሆን እንደ ጉዳዩ አይነት ልዩ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የተፈጻሚነቱን አድማስ መለየቱ ላይ ነው፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 43511a በ2005 ዓ.ም. በሰጠው ፈር ቀዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ባይኖርም ከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው አካል የመሰማት መብትን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ የችሎቱን አቋም በጥልቀት ለመረዳት በሐተታው ክፍል የሰፈረውን የሚከተለውን አስተያየት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡
…የመሰማት መብት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሊከበር የሚገባው መብት ነው፡፡ የመሰማት መብት ከመጀመሪያው ክርክር ጀምሮ እስከመጨረሻው የዳኝነት ሰጪ አካል መከበር ያለበት ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱና ስለ ክርክር አመራር በተደነገጉት እንደፍትሐብሔር ስነ ስርአት አይነት ሕጎች ከተደነገጉት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡
የችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ዜጎች ሀሳባቸው ሳይደመጥ መብትና ጥቅማቸውን የሚጎዳ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዳይሰጥባቸው ከለላ በማጎናጸፍ ረገድ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ‘ታሪካዊ’ ሊሰኝ የሚችል ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ለአገራችን የአስተዳደር ህግ ዕድገት ችሎቱ ካደረጋቸው አስተዋጽኦዎች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ በእርግጥ የውሳኔው ፋይዳ ብቻውን በቁሙ መለካት በተግባር ያስከተላቸውን ለውጦች በማጋነን ያስተቻል፡፡ የሰ/መ/ቁ. 43511 አስተዳደሩ አካሄዱን ከችሎቱ አቋም ጋር እንዲያስተካክል በዚህም የመሰማት መብትን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ አካል አድርጎ እንዲያቅፍ የፈጠረው ጫና ሆነ በተግባር ያስከተለው ተጨባጭ ለውጥ የለም፡፡ አስገዳጁን የህግ ትርጉም መቀበልና መተግበር ያለባቸው የስር ፍርድ ቤቶችም ቢሆኑ በአስተዳደራዊ ክርክሮች የመሰማት መብትን በትጋት እንዲያስከብሩ የለውጥ ምንጭ አልሆነላቸውም፡፡ ምናልባትም ውሳኔው ስለመኖሩ ራሱ ገና አልሰሙ ይሆናል፡፡ የሰበር ውሳኔዎች የተደራሽነት ችግር እንዲሁም በውሳኔዎቹ ላይ ጠንካራ ምሁራዊ የሀሳብ ልውውጥ ባህል አለመዳበር በርካታ አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች በቅጾች መጽሐፍ ውስጥ ተቀብረው እንዲረሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የሰ/መ/ቁ. 43511 ከህገ መንግስታዊ ፋይዳው ባሻገር ክርክሩ የተጓዘበት መስመር ትኩረት ይስባል፡፡ የክርክሩ መነሻ አመልካቾች ከአዋጅ ውጪ የተወረሰ ቤት እንዲመለስላቸው ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን ኤጀንሲውም ተጠሪ ምላሽ እንዲሰጡበት ካደረገ በኋላ ማስረጃና ክርክሩን ሰምቶ ቤቱ እንዲመለስላቸው ወስኗል፡፡ በውሳኔው ባለመስማማት ተጠሪ ለኤጀንሲው ቦርድ ይግባኝ በማቅረባቸው ቦርዱ የኤጀንሲውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ከመሻሩ በፊት ግን አመልካቾችን ጠርቶ ክርክራቸውን አልሰማም፡፡
በመቀጠል አመልካቾች የመሰማት መብታቸው አለመጠበቁን በመግለጽ በቀጥታ የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም አጣሪ ችሎቱ የቦርዱን ውሳኔ የማረም ስልጣን እንዳልተሰጠው በመግለጽ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እንደሚያስነሳ በመጠቆም ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አመለከቱ፡፡ እዛም ተቀባይነት አጡ፡፡ አሁንም ሰሚ ፍለጋ ‘አቤት!’ ማለታቸውን ባለማቆም ጉዳያቸውን እንዲያይላቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አቀረቡ፡፡ በመጨረሻ ጥያቄያቸው ፍሬ አግኝቶ የአጣሪ ችሎቱ ውሳኔ ተሻረ፡፡
አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ እስከ ፌዴሬሽን ም/ቤት ድረስ ዘልቀው ድል መጎናጸፋቸው በራሱ የተለየ ስሜት ቢያጭርም በተለየ መልኩ ትኩረት የሚስበው ግን የክርክሩ ሂደት ሳይሆን የም/ቤቱ ውሳኔ ይዘት ነው፡፡ የሰበር ችሎት የዳኝነት ስልጣንን በማስፋት አዲስ ህገ መንግስታዊ መልክ ያላበሰው ይኸው ውሳኔ የሰበር ችሎት የቦርዱን መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል፡፡ የም/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ መነሻ ያደረገው የኤጀንሲው ቦርድ ዳኝነታዊ ስልጣን ነው፡፡ ስለሆነም ቦርዱ የዳኝነት መሰል አካል (quasi judicial body) በመሆኑና ይህ አካል የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ስልጣኑ ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው፡፡
የስልጣን ጥያቄው እልባት ካገኘ በኋላ መዝገቡ ከፌዴሬሽን ም/ቤት ወደ ሰበር ችሎት ሲመለስ የቦርዱ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መሰረታዊ ጭብጥ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ጭብጡን ለመፍታት ችሎቱ የቦርዱን የማቋቋያ አዋጅb የተመለከተ ቢሆንም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ቦርዱ የተከራካሪዎችን የመሰማት መብት እንዲጠብቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ አላገኘም፡፡
በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የመሰማት መብት የሚጠብቅ ህግ በሌለበት ሁኔታ ውሳኔው ሰጭው አካል በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት መብቱን እንዲያከብር ግዴታ መጫን ለችሎቱ ፈታኝ ስራ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከህግ የመነጨ ግዴታ በሌለበት ቦርዱ የመሰማት መብት መርሆዎችን እንዲከተል ማስገደድ በውጤቱ የችሎቱን ተግባር ከህግ መተርጎም ወደ ‘ህግ መጻፍ’ ያሸጋግረዋል፡፡ ስለሆነም ችሎቱ በስልጣን ክፍፍል መርህ የተሰመረውን ድንበር ሳይሻገር በራሱ የዳኝነት ስልጣን ዛቢያ ውስጥ ሆኖ ውሳኔውን በአሳማኝ ምክንያት ማስደገፍ አለበት
You must be logged in to post a comment.