መገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?


ህገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?

ገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?

የተፈጥሮ ፍትሕ በእንግሊዝና ሌሎች ኮመን ሎው አገራት በዳኞች የዳበረ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርህ ነው፡፡ ይህ መርህ በህግ በግልጽ እንደ ቅድመ ሁኔታ ባይቀመጥም ዳኞች ተፈጻሚ እንዳያደርጉት አያግዳቸውም፡፡ በአሜሪካ እንዲሁ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኘው ዱ ፕሮሰስ ኦፍ ሎው (Due Process of Law) በመባል የሚታወቀው ህገ መንግስታዊ መርህ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን የሚገዛ ልዩ ህግ ባይኖርም እንኳን ፍርድ ቤቶች እንደ አግባብነቱ ተፈጻሚ ያደርጉታል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ሁለት አገራት ሆነ በሌሎችም ዘንድ አስተዳደር የሚመራበት ስነ ስርዓት ምንጩ በህግ አውጪው የሚወጣ ህግ ነው፡፡

ግልጽ የህግ ድንጋጌ ካለ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት ውሳኔ በፍርድ ቤት ሊሻር ወይም ሊሰረዝ እንደሚገባው አያጠራጥርም፡፡ አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ከሌለስ? ፍርድ ቤቶቻችን እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ፍርድ ቤቶች ፍትሐዊ የውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ማዳበርና ተፈጻሚ ማድረግ አለባቸው? ካለባቸውስ አቋማቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት አለው? በአስተዳደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የመሰማት መብት እንዲሁም ኢ-አድሎአላዊነት መርህ በህግ በግልጽ ባልተደነገገበት ሁኔታ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት አስተዳደራዊ ውሳኔ ዕጣ ፋንታ መወሰን በብዙ መልኩ ከባድ ነው፡፡

በአንድ በኩል ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የማረጋገጥ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ህጉን ከማንበብና ከመተርጎም ባለፈ ህግ መጻፍ ህገ መንግስታዊ ሚናቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጠረው ‘ህገ መንግስታዊ አጣብቂኝ’ ብርታትና ጥንቃቄ ካልታከለበት በቀላሉ አይፈታም፡፡ በተጨማሪም ‘መርህ’ በተጨባጭ ‘መሬት ሲወርድ’ ከልዩ ሁኔዎች ጋር ሊጣጣምና የተፈጻሚነት ወሰኑ በአግባቡ ሊሰመር ይገባል፡፡ የመሰማት መብት የግድ የሚልበት ሁኔታ ቢኖርም ከተግባራዊ ፋይዳውና ውጤታማ አስተዳደር አንጻር የሚገደብባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በተጨማሪም የተፈፃሚነቱ ወሰን የግለሰብ መብት ወይም ጥቅም በሚነካ የዳኝነታዊ ባህርይ ባለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አስቸጋሪው ስራ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን በጠቅላላው መቀበሉ ሳይሆን እንደ ጉዳዩ አይነት ልዩ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የተፈጻሚነቱን አድማስ መለየቱ ላይ ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 43511a በ2005 ዓ.ም. በሰጠው ፈር ቀዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ባይኖርም ከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው አካል የመሰማት መብትን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ የችሎቱን አቋም በጥልቀት ለመረዳት በሐተታው ክፍል የሰፈረውን የሚከተለውን አስተያየት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡…የመሰማት መብት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሊከበር የሚገባው መብት ነው፡፡ የመሰማት መብት ከመጀመሪያው ክርክር ጀምሮ እስከመጨረሻው የዳኝነት ሰጪ አካል መከበር ያለበት ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱና ስለ ክርክር አመራር በተደነገጉት እንደፍትሐብሔር ስነ ስርአት አይነት ሕጎች ከተደነገጉት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

የችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ዜጎች ሀሳባቸው ሳይደመጥ መብትና ጥቅማቸውን የሚጎዳ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዳይሰጥባቸው ከለላ በማጎናጸፍ ረገድ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ‘ታሪካዊ’ ሊሰኝ የሚችል ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ለአገራችን የአስተዳደር ህግ ዕድገት ችሎቱ ካደረጋቸው አስተዋጽኦዎች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ በእርግጥ የውሳኔው ፋይዳ ብቻውን በቁሙ መለካት በተግባር ያስከተላቸውን ለውጦች በማጋነን ያስተቻል፡፡ የሰ/መ/ቁ. 43511 አስተዳደሩ አካሄዱን ከችሎቱ አቋም ጋር እንዲያስተካክል በዚህም የመሰማት መብትን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ አካል አድርጎ እንዲያቅፍ የፈጠረው ጫና ሆነ በተግባር ያስከተለው ተጨባጭ ለውጥ የለም፡፡ አስገዳጁን የህግ ትርጉም መቀበልና መተግበር ያለባቸው የስር ፍርድ ቤቶችም ቢሆኑ በአስተዳደራዊ ክርክሮች የመሰማት መብትን በትጋት እንዲያስከብሩ የለውጥ ምንጭ አልሆነላቸውም፡፡ ምናልባትም ውሳኔው ስለመኖሩ ራሱ ገና አልሰሙ ይሆናል፡፡ የሰበር ውሳኔዎች የተደራሽነት ችግር እንዲሁም በውሳኔዎቹ ላይ ጠንካራ ምሁራዊ የሀሳብ ልውውጥ ባህል አለመዳበር በርካታ አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች በቅጾች መጽሐፍ ውስጥ ተቀብረው እንዲረሱ ያደርጋቸዋል፡፡

የሰ/መ/ቁ. 43511 ከህገ መንግስታዊ ፋይዳው ባሻገር ክርክሩ የተጓዘበት መስመር ትኩረት ይስባል፡፡ የክርክሩ መነሻ አመልካቾች ከአዋጅ ውጪ የተወረሰ ቤት እንዲመለስላቸው ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን ኤጀንሲውም ተጠሪ ምላሽ እንዲሰጡበት ካደረገ በኋላ ማስረጃና ክርክሩን ሰምቶ ቤቱ እንዲመለስላቸው ወስኗል፡፡ በውሳኔው ባለመስማማት ተጠሪ ለኤጀንሲው ቦርድ ይግባኝ በማቅረባቸው ቦርዱ የኤጀንሲውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ከመሻሩ በፊት ግን አመልካቾችን ጠርቶ ክርክራቸውን አልሰማም፡፡

በመቀጠል አመልካቾች የመሰማት መብታቸው አለመጠበቁን በመግለጽ በቀጥታ የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም አጣሪ ችሎቱ የቦርዱን ውሳኔ የማረም ስልጣን እንዳልተሰጠው በመግለጽ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እንደሚያስነሳ በመጠቆም ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አመለከቱ፡፡ እዛም ተቀባይነት አጡ፡፡ አሁንም ሰሚ ፍለጋ ‘አቤት!’ ማለታቸውን ባለማቆም ጉዳያቸውን እንዲያይላቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አቀረቡ፡፡ በመጨረሻ ጥያቄያቸው ፍሬ አግኝቶ የአጣሪ ችሎቱ ውሳኔ ተሻረ፡፡

አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ እስከ ፌዴሬሽን ም/ቤት ድረስ ዘልቀው ድል መጎናጸፋቸው በራሱ የተለየ ስሜት ቢያጭርም በተለየ መልኩ ትኩረት የሚስበው ግን የክርክሩ ሂደት ሳይሆን የም/ቤቱ ውሳኔ ይዘት ነው፡፡ የሰበር ችሎት የዳኝነት ስልጣንን በማስፋት አዲስ ህገ መንግስታዊ መልክ ያላበሰው ይኸው ውሳኔ የሰበር ችሎት የቦርዱን መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል፡፡ የም/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ መነሻ ያደረገው የኤጀንሲው ቦርድ ዳኝነታዊ ስልጣን ነው፡፡ ስለሆነም ቦርዱ የዳኝነት መሰል አካል (quasi judicial body) በመሆኑና ይህ አካል የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ስልጣኑ ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው፡፡

የስልጣን ጥያቄው እልባት ካገኘ በኋላ መዝገቡ ከፌዴሬሽን ም/ቤት ወደ ሰበር ችሎት ሲመለስ የቦርዱ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መሰረታዊ ጭብጥ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ጭብጡን ለመፍታት ችሎቱ የቦርዱን የማቋቋያ አዋጅb የተመለከተ ቢሆንም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ቦርዱ የተከራካሪዎችን የመሰማት መብት እንዲጠብቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ አላገኘም፡፡

በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የመሰማት መብት የሚጠብቅ ህግ በሌለበት ሁኔታ ውሳኔው ሰጭው አካል በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት መብቱን እንዲያከብር ግዴታ መጫን ለችሎቱ ፈታኝ ስራ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከህግ የመነጨ ግዴታ በሌለበት ቦርዱ የመሰማት መብት መርሆዎችን እንዲከተል ማስገደድ በውጤቱ የችሎቱን ተግባር ከህግ መተርጎም ወደ ‘ህግ መጻፍ’ ያሸጋግረዋል፡፡ ስለሆነም ችሎቱ በስልጣን ክፍፍል መርህ የተሰመረውን ድንበር ሳይሻገር በራሱ የዳኝነት ስልጣን ዛቢያ ውስጥ ሆኖ ውሳኔውን በአሳማኝ ምክንያት ማስደገፍ አለበት

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.