የኢ-አድሎአዊነት መርህ

የኢ-አድሎአዊነት መርህ
ከአድልኦ የፀዳ ፍርድ (The rule against bias) የሚለው መርህ በኮመን ሎው አገራት በስፋት የዳበረ መሰረተ ሀሳብ ሲሆን በአጭሩ ሲገለጽ አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ መሆን የለበትም እንደማለት ነው፡፡ ኢ-አድሎአዊነት አብዛኛውን ጊዜ ራሱን የቻለ የተፈጥሮ ፍትህ መርህ ተደርጐ ቢጠቀስም በተግባር ሲታይ ግን በመሰማት መብት ውስጥ የሚጠቃለል የፍትሐዊ ስነ-ስርዓት አንድ አካል ነው፡፡ አንድ ሰው በአስተዳደር ጉባዔ (Administrative Tribunal) ፊት ቀርቦ የመሰማት እድል ሊሰጠው ይገባል ሲባል በውስጠ ታዋቂነት ፍ/ቤቱ ከአድልኦ የፀዳ እንደሆነ ግምት በመውሰድ ነው፡፡
ፍርደ ገምድል ያልሆነ፤ ያልተዛባ ውሳኔ መኖር ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ የሚያንፀባርቅ እንደመሆኑ ተፈፃሚነቱም /በተለይ በኮመን ሎው አገራት/ እጅግ ጥብቅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የታወቁት የእንግሊዝ ዳኛ ሎርድ ሄዋርት እንዲህ ብለው ነበር፡፡
ፍትህ መሰራቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ፍትህ ሲሰራ ጭምር በማያጠራጥርና ግልጽ በሆነ አኳኋን መታየት መቻል አለበት፡፡
የዳኛው ልጅ ‘ቀማኛ’ ተብሎ በአባቱ ፊት ችሎት ሲቀርብ በእርግጥም በህጉ መሰረት ጥፋተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ጥፋተኛ ካልሆነ መለቀቁ ፍትህ ነው፡፡ ግን ለማንም አይመስልም፡፡ ፍትህ ሲሰራ አይታይምና፡፡ ዋናው ቁም ነገር ዝምድና፤ የገንዘብ ጥቅም ወይም ሌላ ምክንያት በዳኛው ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተጽእኖ አለማድረጉ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች እስካሉ ድረስ ዳኛው ምንም ያህል ንፁህና ጻድቅ ሰው ቢሆን እንኳን በችሎት ላይ ተቀምጦ ሲያስችል አመኔታ ያጣል፡፡ የኢ-አድሎአዊነት መርህ ዋና አላማ ውሳኔ ሰጭው አካል የተዛባ ፍርድ እንዳይሰጥ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ራሱም ሳያውቀው እንኳን በንፁህ ህሊናው ላይ ተፅእኖ ሊያደርሱ ከሚችሉ ሁኔታዎች ነጻ ሆኖ ዳኝነት እንዲሰጥ ለማስቻል ነው፡፡
ይህ የኢ-አድሎአዊነት መርህ በተለይ በመደበኛ ፍ/ቤት፣ በአስተዳደር ጉባኤ እና ዳኝነታዊ ውሳኔ በሚሰጡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ጥብቅ ተፈጻሚነት አለው፡፡ ውሳኔ ሰጪው አካል በያዘው ጉዳይ በህሊናው ላይ ተፅእኖ ሊያመጣ የሚችል ሁኔታ መኖሩን በተረዳ ጊዜ ራሱን ከውሳኔ ሰጪነት ማግለል አለበት፡፡ ይህ ባልሆነበት ጊዜ በቂ ጥርጣሬ ያደረበት ወገን አቤቱታ አቅርቦ ዳኛው እንዲቀየርለት ማመልከት ይችላል፡፡ ሁኔታው መኖሩ የታወቀው ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ከሆነ የዛ ውሳኔ እጣ ፈንታ ዋጋ አልባ መሆን ነው፡፡
አድሎአዊ ውሳኔ ተሰጥቷል የሚባለው የውሳኔ ሰጭው ህሊና የተዛባ እንደሆነ ነው፡ ለመሆኑ የሕሊና መዛባት ምን ማለት ነው?
በጥሬ ትርጉሙ ሲታይ ማንኛውም ነገር በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ውሳኔ ሰጭው በነጻ ህሊናው ተመርቶ ሊሰጥ ይችል ከነበረው ውሳኔ በተቃራኒ የተለየ ውሳኔ ላይ ያደረሰ ከሆነ ህሊናው ተዛብቷል ብለን መናገር እንችላለን፡፡ ህሊና ከተዛባ የክርክሩ ውጤት (ማለትም ውሳኔው) ጉዳዩ ከመመርመሩ በፊት ድምዳሜ ተደርሶበታል፡፡ ዳኛው ከከሳሽ ወይም ተከሳሽ ጉቦ ከተቀበለ ፍርዱ ለማን እንደሚሰጥ አስቀድሞ ታውቋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚሰጥ ፍርድ በተዛባ ህሊና የተሰጠ አድሎአዊ ፍርድ ነው፡፡
የተዛባ ህሊና ከምንጩ አንፃር በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ልዩ ሁኔታዎችና የተፈጻሚነት ወሰን

ልዩ ሁኔታዎችና የተፈጻሚነት ወሰን
በፍርድ ቤቶች የዳበሩ መሰረታዊ መርሆዎች እንዲሁም አስገዳጅነት ያላቸው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ህጎች በሁሉም አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ወጥ ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡ የእያንዳንዱ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከግለሰቦች መብትና አንጻር ሲመዘን ከቀላል እስከ ከባድ የሚያስከትለው ውጤት እና ተፅዕኖ ይለያያል፡፡ የውሳኔውም ዓይነት እንዲሁ ወጥ መልክ የለውም፡፡ የመንግስት ሠራተኛን ከስራ ማባረር፣ አስተዳደራዊ ቅጣት መጣል፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታ ማፈናቀል፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት (ካርታ) መሰረዝ፣ የብቃት ማረጋገጫ፣ የሙያ ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ፣ የስራ ፈቃድ መሰረዝና ማገድ፣ የሊዝ ውል ማቋረጥ፣ በአንድ የስራ ዘርፍ የተሰጠ ዕውቅና (ለምሳሌ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) መሰረዝ እና ሌሎች መሰል ውሳኔዎች ህገ መንግስታዊ ጥበቃ ያገኙ መብቶችን የመጣስ ከፍተኛ አዝማሚያ ስላላቸው ፍትሐዊ ስርዓት ተከትለው መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ አስተዳራዊ ቅሬታ እና ይግባኝ የሚስተናገድበት መንገድ እንዲሁ ፍትሐዊ ስነ ስርዓት እና አንጻራዊ ገለልተኘነት ካላንፀባረቀ የይስሙላ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡
ስለሆነም በእነዚህ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ስር የሚወድቁና ሌሎች ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ለመሰማት መብት እና ኢ-አድሎአዊነት መርሆዎች ተገዢ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግትር ተፈጻሚነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ አስተዳደራዊ አመቺነትን ያላማከለ የሰነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ውጤታማነትን ያኮላሻል፡፡ ለምሳሌ በከፊል አስተዳደራዊ ክርክሮች በጠበቃ የመወከል መብት በአስተዳደሩ ላይ ከሚያመጣው ጫና አንጻር እንዲቀር ቢደረግ የመሰማት መብትን አያጣብብም፡፡
ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች አንድ የአስተዳደር መ/ቤት በየዕለቱ ይቅርና በየወሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት አይደሉም፡፡ በቁጥር በእጅጉ በልጠው የሚገኙት ውሳኔዎች ግዙፋዊ የመብት መጓደል አያስከትሉም፡፡ ሆኖም በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የግለሰቦችን መብትና ጥቅም የሚነኩ ከሆነ በዘፈቀደ መወሰድ የለባቸውም፡፡ ይብዛም ይነስም በተነካው መብት ልክ ፍትሐዊነት በገሀድ እንዲታይ ይጠበቃል፡፡
እስካሁን የቀረበው ዳሰሳ አንድ መሰረታዊ ጥልቅ መልዕክት ያስጨብጠናል፡፡ ይኸውም፤ ማንኛውንም አስተዳደራዊ ውሳኔ ለአንድ ወጥ ስነ ስርዓት ተገዢ ማድረግ ሊሞከር ቀርቶ አይታሰብም፡፡ ፍርድ ቤት ብቻ ነው አንድ ወጥ ስነ-ስርዓት የሚከተለው፡፡ ያላደገ ሆነ የዳበረ የአስተዳደር ህግ ያላቸው አገራት በማንኛውም አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አንድ ወጥ ስነ ስርዓት የላቸውም፡፡ አንድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከቀላል እስከ ጥብቅ የትኛውን ስነ ስርዓት መከተል እንዳለበት ለመወሰን ለህግ አውጪው አስቸጋሪ ስራ ነው፡፡ ውስብስብ የሆነው የአስተዳደር ስራ ባህርይ በዚህ ረገድ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ፈተናው በወጉ ካልተመለሰ ፍትሐዊነትና ውጤታማ አስተዳደር ሚዛናቸውን ይስታሉ፡፡
እንደ ፒተር ዎል አገላለጽ በአስተደደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተፈጻሚ የሚሆኑት አነስተኛ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች እንደ ጉዳዩ ዓይነትና ውስብስብነት፣ የማስረጃዎችና የሚረጋገጡት ፍሬ ነገሮች ዓይነት፣ የውሳኔ ሰጭው ማንነትና የሚያከናውነው የአስተዳደር ተግባር ባህርይ እንዲሁም ውሳኔው በግለሰቦች ላይ ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት አንጻር ደረጃቸው ይለያያል፡፡
[W]hat constitutes a minimum compliance with due process in the way of administrative hearing…will vary to a considerable extent with the nature of the substantive right, the character and complexity of the issues, the kinds of evidence and factual material, the particular body or official, and the administrative functions involved in the hearing.a
የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ፍትሐዊነት እንዲሰፍን ከዚያም አልፎ በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር እንዲያብብና እንዲጎለብት የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ በሀሳብ ሆነ በተግባር ደረጃ ተፈትኖ የተረጋገጠ ቢሆንም አፈጻጸሙ በጥንቃቄ ወሰን ካልተበጀለት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ፍርድ ቤቶች እንደሚከተሉት የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ጥብቅ እና መደበኛ በሆነ ቁጥር አስተዳደራዊው ሂደት እጅና እግሩ ይታሰራል፡፡ በዚህ የተነሳ ዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ያጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደግሞ የዜጎችን ብሶት ‘ከፍትሕ ጥማት’ ወደ ‘አገልግሎት ረሀብ’ ቢቀይረው እንጂ ፍሬ አያስገኝም፡፡
እ.ኤ.አ በ1946 በወጣው የአሜሪካው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ (Administrative Procedure Act) የአስተዳደር ዳኝነት መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሚል ለሁለት ተከፍሏል፡፡ መደበኛው የአስተዳደር ዳኝነት ከክስ መስማት እስከ ውሳኔው ይዘት ድረስ በዝርዝር አስገዳጅ ደንቦች የሚገዛ ሲሆን ኢ-መደበኛው ግን በቀላልና ልል ስርዓት ይመራል፡፡ አስተዳደራዊ አመቺነትን ያማከለው ይህ አካሄድ በአንድ በኩል በዘፈቀደ በሚወሰድ እርምጃ ፍትሕ እንዳይጓደል በሌላ በኩል ደግሞ በጥብቅ ስነ ስርዓት ሳቢያ ውጤታማ አስተዳደር እንዳይሰናከል ህጉ የተከተለው አስታራቂ መስመር ነው፡፡
በመደበኛው የአስተዳደር ዳኝነት ከክስ መሰማት (hearing) ጀምሮ አጠቃላይ ክርክሩ በመዝገብ (on the record) እንዲካሄድ የሚያስገድድ ሲሆን በይዘቱም ጠበቅ ያለ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ተፈጻሚ የሚሆነው በልዩ ህግ በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህጉ የመደበኛውን የአስተዳደር ዳኝነት የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች በመደንገግ ተፈጻሚነቱን ግን ህግ አውጪው በዝርዝር ህግ በግልጽ በወሰናቸው ሁኔታዎች ላይ ብቻ ገድቦታል፡፡b በዚህ መልኩ በመደበኛው የዳኝነት ሂደት የሚያልፉ የአስተዳደር ክርክሮች በቁጥር ከአምስት ፐርሰንት አይበልጥም፡፡c የተቀሩት ኢ-መደበኛውን ስርዓት የሚከተሉ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር መደበኛው አስተዳደራዊ ክርክር ተፈጻሚነቱ በልዩ ሁኔታዎች ብቻ ነው፡፡
አሜሪካኖች ከሞላ ጎደል ሁሉም አስተዳደራዊ ክርክሮች ኢመደበኛ አካሄድ እንዲከተሉ የመረጡበት ምክንያት ንድፈ ሀሳባዊ ሳይሆን ተጨባጭና ተግባራዊ ነው፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እየሰሙ በማከራከር ውሳኔ የሚሰጡ ከሆነ የተቋቋሙለትን ዓላማ መቼም ቢሆን አያሳኩም፡፡ መደበኛ የአስተዳደር ክርክር ከሚፈጀው ጊዜ እንዲሁም ከሚያስፈልገው የሰው ሀይልና የገንዘብ ወጪ አንጻር በሁሉም አስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ ተፈጻሚ ቢደረግ ውጤታማ አስተዳደር ይቅርና ‘አስተዳደር’ የሚባል ነገር ራሱ አይኖርም፡፡
በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም. እና 2001 ዓ.ም. የተዘጋጁት ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጆች ይህን መሰረታዊ ተጨባጭ እውነታ በቅጡ አልተረዱትም፡፡ ሁለቱም ረቂቆች አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት መደበኛው የክስ መሰማት ስርዓት እንዲከናወን በአስተዳደር መ/ቤቶች ላይ ግዴታ ያስቀምጣሉ፡፡ ከሁለቱ ረቂቆች አንዳቸው ጸድቀው አስገዳጅ ህግ ከሆኑ የአስተዳደር መ/ቤቶች ወደ መደበኛ ፍ/ቤቶች መቀየራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሜሪካ በዚህ ዓይነት የክርክር ሂደት የሚያልፉ ጉዳዮ
ች ከአምስት ፐርሰንት አይበልጡም፡፡ የተቀረው 95 ፐርሰንት ኢመደበኛ ነው፡፡ በረቂቅ ህጎቹ የተመረጠው አቅጣጫ ደግሞ ሁሉም (ማለትም 100 ፐርሰንት) አስተዳደራዊ ክርክሮች መደበኛ ስርዓት እንዲከተሉ ያስገድዳል፡፡ በዚህ ሁኔታ አስገዳጅ ህግ ሆነው በተወካዮች ም/ቤት ቢታወጁ ሊከተል የሚችለውን አስተዳደራዊ መንዛዛት ለመገመት ከወደሁ ያስቸግራል፡፡
የመሰማት መብት
የመሰማት መብት
በተከሰሰበት ጉዳይ መልስ ሳይሰጥ እንዲሁም ማስረጃውን ሳያሰማ የንግድ ፍቃዱ የተሰረዘበት ነጋዴ፣ የቤት ካርታው የመነከበት ግለሰብ፣ ከዩኒቨርሲቲ የተባረረ ተማሪ… ሁሉም የአስተዳደር በደል ሰለባዎች ናቸው፡፡ የአንድን ግለሰብ መብትና ጥቅም ሊጐዳ የሚችል ማንኛውም አስተዳደራዊ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ግለሰቡ የመሰማት ዕድል ሊያገኝ ይገባል፡፡ የመሰማት መብት በዘፈቀደ በሚወሰድ አስተዳደራዊ እርምጃ የተነሳ ዜጎች ህይወታቸውና ንብረታቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ ይከላከላል፡፡
መሰማት ሲባል ከክስ እስከ ውሳኔ ድረስ ያሉ ዝርዝር የክርክር ሂደቶችን ያቅፋል፡፡ እያንዳንዱ ሂደት በራሱ ካልተሟላ በቂ የመሰማት ዕድል እንዳልተሰጠ ይቆጠራል፡፡ በአስተዳደር ዳኝነት ውስጥ የዚህ መብት ዝርዝር ሂደቶችና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በዋነኛነት የሚከተሉትን ያካትታል፡፡
ቅድመ-ክስ ማስታወቂያ
የክስ መሰማት ውሳኔ ሰጭው ባለስልጣን ለባለጉዳዩ /ለተከሳሹ/ በሚሰጠው የክስ ማስታወቂያ ይጀመራል፡፡ ማስታወቂያ ተከራካሪው እንዲቀርብ የሚሰጥ መጥሪያ ነው፡፡ በይዘቱ ባለጉዳዩ የቀረበበትን ክስ በሚገባ ተረድቶ መልሱን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ የሚያስችለው በቂ ማስታወቂያ መሆን አለበት፡፡ ተከራካሪው ራሱን ለመከላከል የሚችለው የተከሰሰበትን ጉዳይ በማያሻማ ሁኔታ የተገለጸለት እንደሆነ ነው፡፡a ከዚህ አንጻር የክሱ ዓይነትና ምክንያት ቀጥተኛና ግልጽ በሆነ መንገድ በማስታወቂያው ላይ መስፈር ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ እንዲቀርብ የተጠራው ባለጉዳይ የመንግስት ሰራተኛ ወይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆነ በደፈናው ‘የዲሲፕሊን ክስ ስለቀረበብህ እንድትቀርብ!’ የሚል መጥሪያ ግልጽነት ይጐድለዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ በላይ ክስ በቀረበ ጊዜ እያንዳንዱ ክስ በዝርዝር ሊገለጽ ይገባል፡፡ በሌላ መልኩ በክስ ማስታወቂያው ላይ የቀረበው የክስ አይነት ክሱ በሚሰማበት ቀን የተቀየረ እንደሆነ ክሱ እንዳልተገለጸ ወይም በቂ ማስታወቂያ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል፡፡ በስርቆት ተከሶ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ፊት እንዲቀርብ የተጠራ ተማሪ ክሱ በሚሰማበት ቀን የመጀመሪያው ክስ ተቀይሮ ‘በፈተና ማጭበርበር’ ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ተማሪው የተቀጣው በቂ ማስታወቂያ ሳይሰጠው እንደመሆኑ ቅጣቱ መሰረታዊ የሆነውን የመሰማት መብት ይጻረራል፡፡
ክሱ የሚሰማበት ጊዜና ቦታ
‘በቂ’ ሊባል የሚችል የክስ ማስታወቂያ መለኪያ ባለጉዳዩ ራሱን በሚገባ እንዲከላከል በሚያስችል መልኩ በቂ መረጃና ጊዜ የሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ ክርክሩን ለማካሄድ ስልጣን የተሰጠው አካል ተከራካሪዎች የሚመቻቸውን ጊዜ በመወሰን ክሱ ስለሚሰማበት ቦታ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ መጥሪያውን መላክ ይጠበቅበታል፡፡ ጊዜው ሲገለጽ ትክክለኛው ሰዓት ጭምር መገለጽ አለበት፡፡ ቦታውም እንዲሁ ትክክለኛ መለያ አድራሻውን በመጥቀስ ለባለጉዳዩ/ለተከሳሹ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡
ከጊዜ ጋር በተያያዘ መልስ ለማቅረብ የሚሰጠው የዝግጅት ጊዜ እንደክሱ ክብደትና ውስብስብነት ሚዛናዊ የጊዜ መጠን መሆን ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ክሱ ተሰጥቶት ለነገ መልስ መጠበቅ በተዘዋዋሪ የመሰማት መብትን እንደመንፈግ ይቆጠራል፡፡ በመጨረሻም ክሱን የሚሰማው አካል ትክክለኛ ማንነት በማስታወቂያው ላይ መመልከት ይኖርበታል፡፡
የክስ ማስታወቂያ በአካል ስለመስጠት
የጥሪ ማስታወቂያው በይዘቱ በቂ ሊባል የሚችል ቢሆንም ለባለጉዳዩ በአግባቡ እስካልዳረሰው ድረስ የመሰማት መብቱ ተጓድሏል፡፡ ባለጉዳዩ በቅርብ የሚገኝ ከሆነ በተቻለ መጠን መጥሪያው ለራሱ በአካል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከተገቢ ጥረት በኋላ ለማግኘት የማይቻል ከሆነ ማስታወቂያውን ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ መለጠፍና ለተወሰነ ጊዜ በተለጠፈበት ቦታ እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በሚሰማበት ቀን አለመቅረብ ክርክሩ በሌለበት እንዲቀጥል የሚያደረግ በመሆኑ የመጥሪያ በአግባቡ መድረስ የመስማት መብት አካል ተደርጐ መቆጠር ይኖርበታል፡፡
ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ መብት
ክስ የቀረበበት (ባለጉዳይ) ጉዳዩ በተቀጠረበት ቀን በአካል ወይም በወኪሉ ተገኝቶ ክርክሩን የመከታተል፤ መልስ፣ ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ ዕድል ሊያገኝ ይገባል፡፡ ይህ መፈጸሙን ማረጋገጥ ክርክሩን የሚሰማው አካል ግዴታ ነው፡፡ መልሱ የሚቀርብበት መንገድ እንደየሁኔታው በቃል ወይም በጽሑፍ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚቀርበው የማስረጃ ዓይነት የቃል (የሰው ምስክር) ወይም የጽሑፍ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ማስረጃው በ3ኛ ወገን እጅ የሚገኝ ከሆነ ባለጉዳዩ እንዲቀርቡለት በጠየቀ ጊዜ ክርክሩን የሚሰማው አካል እንዲቀርቡ ማድረግ አለበት፡፡
መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ መብት
ባለጉዳዩ የተቃራኒ ወገን ክስና ማስረጃ በአግባብ ሊደርሰውና ሊመለከተው እንደሚችል ከዚህ በፊት ተገልጿል፡፡ የዚህ ዓላማ በአንድ በኩል ባለጉዳዩ የራሱን መከራከሪያና ማስረጃ በማቅረብ ክሱን በቀጥታ እንዲከላከል ሲሆን በሌላ በኩል የተቆጠረበትን ማስረጃ ማስተባበል እንዲያስችለው ጭምር ነው፡፡
በፍርድ ቤት በሚካሄድ መደበኛ ክርክር መስቀለኛ ጥያቄ የምስክሮችን ተዓማኒነት ለማሳጣትና በአጠቃላይ እውነትን ለማውጣት ውጤታማ መሳሪያ ነው፡፡ ተከሳሹ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድሉ ተነፍጐት የተሰጠ የምስክርነት ቃል ህጋዊ ብቃቱም አጠያያቂ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የአስተዳደር ክርክር በዓይነቱና በይዘቱ የፍርድ ቤት ክርክር መልክ ከያዘ ውጤታማ አስተዳደርን ወደ ኋላ መጎተቱ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የመስቀለኛ ጥያቄ መቅረት ባለጉዳዩ ውጤታማ መከላከያ እንዳያቀርብ የሚያግደው ካልሆነ በስተቀር ውሳኔ ሰጭው አካል በመብቱ ላይ ገደብ ሊያደርግ ይችላል፡፡b ይሁን እንጂ ምስክርነቱ በቃለ መሀላ ስር የተሰጠ ከሆነ መስቀለኛ ጥያቄ መከልከል አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ የ1967ቱ ረቂቅ አዋጅ መስቀለኛ ጥያቄ የማቅርብ መብት ለባለጉዳዩ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ የለውም፡፡ በተቃራኒው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ (1993) በአንቀጽ 6 (3)(ሐ) ላይ ይህን መብት በግልፅ አካቷል፡፡
በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ መብት ከሞላ ጎደል በሁሉም ህጎችቻን ላይ አልተካተተም፡፡ ልዩ ሁኔታ የሚገኘው በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ 847/2006 ላይ ነው፡፡ በአንቀጽ 39/2/ እንደተመለከተው የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበት ሰው የከሳሽን ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን ክስ በሚሰማበት ወቅት እንዲሁ ግራ ቀኙ መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በፌደራል መንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓት ደንብ ቁ. 77/1994 አንቀጽ 17/5/ እንደሰፈረው የከሳሽ ምስክሮችን ተከሳሹ፤ የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮችን የመንግስት መስሪያ ቤቱ ተወካይ፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የጠራቸውን ተጨማሪ ምስክሮች ደግሞ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ፡፡
በጠበቃ ተወክሎ የመከራከር መብት
የባለጋራን ክስና ማስረጃ ለማስተባበል የህግ ባለሙያ እገዛ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ በተለይ ውስብስብ በሆኑ የአስተዳደር ክርክሮች ተካፋይ የሆነ ወገን ካለባለሙያ እገዛ ራሱን በውጤታማ መንገድ ለመከላከል ያለው ዕድል አነስተኛ ነው፡፡ ሆኖም በጠበቃ መወከል መሰረታዊ የመሰማት መብት አካል ተደርጐ አይቆጠርም፡፡ በመብቱ ላይ የሚጣለው ገደብ የራሱ አሳማኝ ምክንያቶች አሉት፡፡
የአስተዳደራዊ ዳኝነት ክርክር ጥብቅ የሆነ የመደበኛ ፍ/ቤቶች ዓይነት የስነ-ስርዓት አካሄድ ሳይከተል በፍጥነት ጉዳዩን ለመቋጨት ያለመ ነው፡፡ የጠበቃ መኖር ክርክሩ የባሰ እንዲወሳሰብና ከተገቢው ጊዜ በላይ እንዲንዛዛ በማድረግ የክርክሩን ኢ-መደበኛ ባህርይ ያጠፋዋል፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር በጠበቃ ውክልና ከሚታገዝ ይልቅ ባለጉዳዩ ራሱ የሚከራከርበት አስተዳደራዊ ክርክር በአጭር ጊዜ እልባት ያገኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን ክርክር የሚካሄድበት ጉዳይ በባሉጉዳዩ መብትና ጥቅም ላይ ሊኖረው ከሚችለው አሉታዊ ውጤት አንጻር ማለትም የክርክሩን ክብደትና ውስብስነት መሰረት አድርጐ እንደየሁኔታው በጠበቃ የመወከል ጥያቄን ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡
ምክንያታዊ ውሳኔ
ዜጐች በሰውነታቸውና በንብረታቸው ላይ እርምጃ ሲወሰድ ከመንግስት ምክንያት ይሻሉ፡፡ አንዳችም ምክንያት የሌለው ውሳኔ የአስተዳደር በደል መገለጫ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት በሁለት መልኩ ይገለጻል፤ የመጀመሪያው ምክንያት ሳይጠቀስ በደፈናው ውሳኔ ሲሰጥ፣ ሁለተኛው ደግሞ ውሳኔው በራሱ ፍርደገምድል፣ ሚዛናዊነት የጐደለውና በአሳማኝ ምክንያት ያልተደገፈ ሲሆን፡፡
ለውሳኔ ምክንያት መስጠት በአስተዳደር ህግ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እያያዘና እያደገ የመጣ መሰረተ ሀሳብ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከአሜሪካው የአስተዳደር ስነስርዓት በስተቀር በእንግሊዝ ሆነ በህንድ ምክንያት እንዲሰጥ የሚያስገድድ በሁሉም የአስተዳደር አካላት ተፈጻሚ የሆነ ጠቅላላ ደንብ የለም፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ ማቋቋሚያው አዋጅ ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ምክንያት እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡
አስተዳደራዊ ውሳኔ ሊኖረው የሚገባውን ይዘትና ቅርጽ በተመለከተ በ1967 ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 13 እንዲሁም በፌደራሉ ረቂቅ አዋጅ (1993 ዓ.ም.) አንቀጽ 32 ላይ ቅድመ ሁኔታዎቹ ተዘርዝረዋል፡፡ በዚሁ መሰረት አስተዳደራዊ ውሳኔ በጽሑፍ መሰጠት ያለበት ሲሆን ውሳኔውም የክርክሩን ፍሬ ነገር፣ የማስረጃዎች ፍሬ ጉዳይና ምንጭ፣ የነገሩን ጭብጥ አወሳሰን እንዲሁም በውሳኔው መሰረት ተመስርቶ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡ ምንም እንኳን በረቂቆቹ ላይ ‘ምክንያት’ የሚለው ቃል በግልጽ ባይጠቀስም የውሳኔ ምክንያትን የሚያያቋቁሙ ሁኔታዎች የተካተቱ እንደመሆኑ ምክንያት መስጠት እንደአስገዳጅ ሁኔታ ተቀምጧል ማለት እንችላለን፡፡
በአንዳንድ አዋጆች ላይ ውሳኔን በምክንያት ማስደገፍ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ለአብነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁ. 980/2008 አንቀጽ 6/2/ የንግድ ምዝገባ ማመልከቻ ውድቅ ከተደረገ መዝጋቢው አካል ምክንያቱን ገልጾ ለአመልካቹ ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት፡፡
ከቀረጥ ዋጋ አወሳሰን ጋር በተያያዘ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ተጨማሪ መግለጫ ወይም ሰነድ ከዲክላራሲዮን አቅራቢው ከተቀበለ በኋላ ስለግብይት ዋጋው ትክክለኛነት ያለውን ጥርጣሬ ማስወገድ ካልቻለ ወይም ዲክላራሲዮን አቅራቢው ምላሽ ካልሰጠ በጉምሩክ አዋጅ ቁ. 859/2006 አንቀጽ 90 መሰረት ዋጋውን መወሰን እንዳልተቻለ ይቆጠራል፡፡ በዚሁ መሰረት የቀረበው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ ተቀባይነት ያላገኘበት ምክንያት በጽሑፍ ለአስመጭው ወይም ለወኪሉ ይገለጽለታል፡፡c
በነዳጅ አቅርቦት ስራ ለመሰማራት የተጠየቀ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተቀባይነት ካላገኘ ምክንያቱ ለአመልካቹ ይገለጽለታል፡፡d
የስደተኝነት ዕውቅና እንዲሰጥ የሚቀርብ አቤቱታ ተቀባይነት ቢያገኝም ባያገኝም ውሳኔው ለአቅራቢው በጽሑፍ መገለጽ አለበት፡፡e
ኢ አድሎኣዊነት
LikeLiked by 1 person