የወ/ህ/ቁ. 2/5/፣ 24/1/፣ ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41፣ 111፣ 112፣ 130፣ 131 ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 23፣ 13/2/፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥምምነት አንቀጽ 14 ንዐስ አንቀጽ 7በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የተከለከለው የመጨረሻ ውሳኔ በሆነ ጥፋተኝነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል ሲሆን ነው፡፡ በዚህም መሰረት በወንጀል ሥነ ሥርዓቱ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጉዳዩ ክስ ለመመስረት የሚያስችል አይደለም በማለት ተጠርጣሪውን በነፃ የመልቀቅ የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የመከልከልን ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም፡፡ በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የመከልከል ጥያቄ በፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ተገቢ ነው የተባለ ውሳኔ መሰጠቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 42// ሀ፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 23


ድጋሚ ያለመከሰስና ያለመቀጣት መብት
• አንድ ሰው በአንድ የወንጀል ድርጊት ክስ ቀርቦበት የመጨረሻ በሆነ ውሣኔ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ በተቀጣበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና ያለመከሰስና ያለመቀጣት መብት
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርህ አድርጎ ከደነገጋቸው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች አንደኛው አንድ ሰው በአንድ የወንጀል ድርጊት ክስ ቀርቦበት የመጨረሻ በሆነ ውሣኔ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ በተቀጣበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና መከሰስና መቀጣት የለበትም የሚለው ነው፡፡ ይህ የወንጀል ሕግ መርህ በሕገ መንግስቱ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 5 ተደንግጓል፡፡ ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 23 ‘’ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነሥርዓት መሰረት ተከስሶ የመጨረሻ በሆነ ውሣኔ ጥፋተኝነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም‘’ በማለት ደንግጓል፡፡ የወንጀል ህግ መርሁ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መርህ ሲሆን አገራችን ባጸደቀችው በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥምምነት አንቀጽ 14 ንዐስ አንቀጽ 7 “No one shall be liable to be tried or punished again for an offence for which he has already been finally convicted or acquitted in accordance with the law and penal procedure of the country” በሚል መንገድ ተደንግጓል፡፡
ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 23 አቀራረፅና ይዘት ለመረዳት የሚቻለው አንድ በወንጀል የተከሰሰ ሰው በድጋሚ የቀረበበትን የወንጀል ክስ በአንድ ጉዳይ በድጋሚ ያለመከሰስና ያለመቀጣት መብቴን የሚጥስ ነው ብሎ ለመከራከርና የህገ መንግስቱም ድንጋጌ ተፈፃሚ እንዲሆንለት ለመጠየቅ ሁለት መሠረታዊ መስፈርቶች ሊሟሉ ይገባል፡፡ የመጀመሪያው ተከሣሹ በተመሣሣይ የወንጀል ድርጊት በወንጀል ህግና ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት የተከሰሰ የነበረ መሆኑ ማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ተከሣሹ ከዚህ በፊት በተከሰሰበት ወንጀል ድርጊት የመጨረሻ በሆነ ፍርድ ጥፋተኛ ሆኖ የተቀጣ ወይም በነፃ የተለቀቀ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በአንድ ተከሣሽ ላይ የወንጀል ክስ ለማቅረብ ወይም ላለማቅረብ የሚሰጠው ውሣኔና የወንጀል ክስ ለማቅረብ ከወሰነ በኋላ ተከሣሹ በኃላፊነት ሊጠየቅ የሚችልበትን የወንጀል ድርጊትና የወንጀል ሕግ ድንጋጌ በወንጀል የፍትህ ሥርዓቱና በወንጀል የፍርድ ሂደት ውስጥ እጅግ ወሣኝና የመጀመሪያውና መሠረታዊ ውሣኔና ክንውን ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በአንድ ተከሣሽ ላይ የወንጀል ክስ ከማቅረቡ በፊት ተከሣሹ አንድ ወንጀል በመፈጸም ሃሣብ የሰራው አንድ የወንጀል ድርጊት ያስከተላቸውን ወይም ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ውጤቶች ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ በማገናዘብና አግባብነት ያላቸውን ህግ ድንጋጌዎች በመለየትና በመጥቀስ የወንጀል ክሱን በጥንቃቄ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 24 ንዐስ አንቀጽ 1፣ ከወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 41፣ አንቀጽ 111 እና አንቀጽ 112 እና ሌሎች አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ክስ ሲያቀርብ በህግ የተጣለበትን ግዴታ ሣይወጣ ተከሣሹን በቀላል ወንጀል ኃላፊና ተጠያቂ የሚያደርግ የወንጀል ድንጋጌ ጠቅሶ ክስ አቅርቦ ተከሣሹም የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የእምነት ክህደት ቃሉን ከሰጠና ተከራክሮ በቀረበበት የወንጀል ክስ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ከተቀጣ ወይም በነፃ ከተለቀቀ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት በተከሰሽ ላይ የወንጀል ክስ ሳቀርብ የተከሳሽ ድርጊት በግል ተበዳይ ላይ ያስከተለውን ወይም ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በማገናዘብም ሆነ አግባብነት ያለውን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ በመምረጥና በመጥቀስ ተሳሳቻለሁ በሚል በተከሣሹ ላይ በድጋሚ የወንጀል ክስ ቢያቀርብ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 23 እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 5 በምን መንገድ መተርጎምና ተፈጻሚ መሆን አለባቸው የሚለውን ነጥብ እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡
የዚህ አይነት ክርክር ሲያጋጥም ከሁሉም በፊት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌው ሊያሳካው የሚፈልገውን ግብና ዓላማ መሠረት በማድረግ ክርክሩን በመመርመር መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 23 ትርጉምና የተፈፃሚነት ወሰን አስመልክቶ የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮች በህገ መንግስቱ አንቀፅ 13 ንዐስ አንቀፅ 2 መሠረት ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነቶች በተለይም ከዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥምምነት አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 7 ይዘት፣ ትርጉምና የተፈፃሚነት ወሰን ጋር ማገናዘብና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ዓለም ዓቀፍ የወንጀል ህግ መርህ መሠረታዊ ዓላማ የአንዲት አገር መንግስት ህግ አስከባሪ አንድ ጊዜ የወንጀል ክስ አቅርቦበትና ተከራክሮ የመጨረሻ ፍርድ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት በሌላ ጊዜ ተከሳሹን በድጋሚ ለመክሰስና ለማስቀጣት የማይችል መሆኑን በመደንገግ ሰዎችን በአንድ ወንጀል ድርጊት በተደጋጋሚ በሚቀርብ የወንጀል ክስ ስጋት ውስጥ እንዳይወድቁ በመከልከል ለሰዎች የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ ዋስትና እና ጥበቃ መስጠት ነው፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀጽ 23 በአቀራረጹና በይዘቱ በአንድ በኩል ዓቃቤ ህግ ለአንድ የወንጀል ድርጊት በተለያየ ጊዜ የተለያየ የወንጀል ርዕስና የህግ ድንጋጌ በመጥቀስ ወይም ተመሳሳይ የወንጀል ህግ ድንጋጌ በመጥቀስ ተከሳሽ ተከስሶ በፍ/ቤት በተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ ነፃ ከወጣ ወይም ከተቀጣ በኋላ በድጋሚ በወንጀል እንዳይከሰስና እንዳይጠየቅ የሚከለክል በሌላ አነጋገር የመንግስት የወንጀል ክስ የማቅረብ ሥልጣንን የሚገድብ መሰረታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ በሌላ በኩል ድንጋጌው አንድ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊት ፈፅሟል ተብሎ ከወንጀል ክሱ በነፃ በተለቀቀበት ወይም በተቀጣበት ጉዳይ ላይ የወንጀል ክስና ተጠያቂነት ይመጣብኛል በሚል ጭንቀትና ሥጋት እንዳይሸማቀቅ ህገ መንግስታዊ ዋስትናና ጥበቃ በመስጠት ተከሳሹ በወንጀል ተከስሶ በመጨረሻ ፍርድ በነፃ በተለቀቀበት ወይም በተቀጣበት የወንጀል ድርጊት በድጋሚ የማይከሰስና የማይፈረድበት ስለመሆኑ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያለው መሆኑን በማረጋገጥ የተረጋጋ ህይወት እንዲኖር የማድረግ ዓላማና ግብ ያለው ነው፡፡
አንድ ሰው በወንጀል ህግና በወንጀል ስነ ስርዓት ተከስሶ የመጨረሻ ፍርድ በተሰጠበት ጉዳይ ጥፋተኛ ሆኖ ተቀጥቷል ወይም በነፃ ተለቋል የሚለው መከራከሪያ በመጀመሪያ የወንጀል ክስ የክስ መቃወሚያ ሆኖ መቅረብ ያለበት መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 የተደነገገ ሲሆን ፍ/ቤቱ የቀረበውን የክስ መቃወሚያና ማስረጃ በመመርመር ውሳኔ መስጠት ያለበት መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 131 ተደንግጓል፡፡ ሆኖም አንድ ተከሳሽ በወንጀል ተከስሶ በመጨረሻ ፍርድ በነፃ በተለቀቀበት ወይም በተቀጣበት የወንጀል ድርጊት በድጋሚ ያለመከሰስና ያለመጠየቅ መብት መሰረታዊና ህገ መንግስታዊ መብት በመሆኑ ክርክሩ በሚካሄድበት በማናቸውም ደረጃ ሊነሳ የሚችልና በማስረጃ ተረጋግጦ በተገኘ ጊዜ ፍ/ቤቶች ተቀብለው ብይን የሚሰጡበት የመከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡
የወ/ህ/ቁ. 2/5/፣ 24/1/፣ ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41፣ 111፣ 112፣ 130፣ 131 ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 23፣ 13/2/፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥምምነት አንቀጽ 14 ንዐስ አንቀጽ 7
በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የተከለከለው የመጨረሻ ውሳኔ በሆነ ጥፋተኝነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል ሲሆን ነው፡፡ በዚህም መሰረት በወንጀል ሥነ ሥርዓቱ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጉዳዩ ክስ ለመመስረት የሚያስችል አይደለም በማለት ተጠርጣሪውን በነፃ የመልቀቅ የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የመከልከልን ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም፡፡ በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት የመከልከል ጥያቄ በፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ተገቢ ነው የተባለ ውሳኔ መሰጠቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡
ወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 42// ሀ፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 23

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.