አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት ስልጣን ባህርያትና የስልጣን 4-አስተዳደራዊ ድንጋጌ…


የአስተዳደር መንግስት እና የአስተዳደር ህግ ውልደት

ህገ መንግስታዊ ገደብበውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን የአስፈላጊነቱ አጥጋቢ ምክንያት ተግባራዊ ችግሮች ቢሆኑም የመንግስት አስተዳደርን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ራሱን የቻለ የጐላ ጥቅም አለው፡፡ በእርግጥ የስልጣን አምባገነንነትን ሊያስከትል ከመቻሉ የተነሳ የራሱ አደጋዎችም አሉት፡፡ አደጋውና አላስፈላጊ ጐኑ ሊወገድ የሚችለው ልኩ ተለይቶ በታወቀ ገደብ ውሰጥ ተግባር ላይ የዋለ እንደሆነ ነው፡፡ ውክልናው ግልጽ፣ የማያሻማ፣ ጠባብና ገደብ የተሰመረለት ሊሆን ይገባዋል፡፡የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ህግ የማውጣት ስልጣን ለተወካዮች ም/ቤት እንደተሰጠ በግልፅ ይደነግጋል፡፡a ይህ ስልጣን በውክልና እንዲተላለፍ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ ግን አልሰፈረም፡፡ ስልጣኑን በውክልና እንዲያስተላልፍ የሚፈቅድለት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ባይኖርም የተለያዩ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ውክልና ቢያንስ በተዘዋዋሪ የተከለከለ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ በተለይ አግባብነት ያለው የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የተጠቀሰው ድንጋጌ ህግ የማውጣት ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ ኢ- ህገ መንግስታዊ ስላለመሆኑ በቂ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ለአስተዳደር ህግ አስጨናቂው ጥያቄ ህገ መንግስቱ የተወካዮች ም/ቤት በውክልና ስልጣኑን እንዲያስተላልፍ የመፍቀዱ ነገር ሳይሆን በውክልና ሊተላለፍ የሚችለው ስልጣን ወሰንና ገደቡ የትላይ ነው? የሚለው ነው፡፡ ህግ አውጭው በህዝብ የተመረጠው ህግ ለማውጣት ነው፡፡ ስለሆነም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ያለገደብ ወይም ሙሉ በሙሉ ለአስፈፃሚው አካል ማስተላለፍ የለበትም፡፡

የአስተዳደር መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህግ አውጭነት ስልጣን በህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት ገደቦች አልተገታም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም የህግ አውጭነት ስልጣኑን ለማስጠበቅ አቅም ያጣ ይመስላል፡፡ በውክልና ሰበብ የሚወጡትን ደንቦች ሊቆጣጠር ቀርቶ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣኑን ጭምር እያጋራው ይገኛል፡፡ በ2001 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁ. 603/2001a የተወካዮች ምክር ቤት የውክልና ዲሞክራሲን መርህ ከስሩ የሚንድ መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ለሚኒስትሮች ም/ቤት አስተላልፏል፡፡ ይኸው አዋጅ በአዋጅ ቁ. 691/2001 ቀጥሎም በአዋጅ ቁ. 916/2008 ተተክቷል፡፡ በእነዚህ ህጎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት መነሻና መድረሻ የሌለው የህግ አውጭነት ስልጣን ተጎናጽፏል፡፡ በሶስቱም ህጎች የሚገኘው ድንጋጌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት፣ ማንኛውም አስፈፃሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈፃሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም እንዲከፋፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈፃሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን እንዲኖረው ፈቅደዋል፡፡እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ስልጣን በ1923 ዓ.ም. ህገ መንግስት አንቀጽ 11 እና 34 እንዲሁም በ1948 ዓ.ም. ህገ መንግስት (አንቀጽ 27) ንጉሱ አላስነካም ብለው በብቸኝነት ይዘውት ነበር፡፡ በ1980 ዓ.ም. በቆመው የደርግ ህገ መንግሰት እንዲሁ መ/ቤቶችን የማቋቋም ስልጣን በተዘዋዋሪ ከስራ አስፈፃሚው እጅ አልወጣም፡፡ በአንቀጽ 82/3/፣ 83/1/ እና 86/4/ በተሰጣቸው ስልጣን ዋናዎቹ ህግ አውጭዎች ምክር ቤቱ (Council of State) እና ፕሬዚዳንቱ ነበሩ፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ግን የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን የአስተዳደር ተቋማትን አደረጃጀት ከመወሰን እንዳያልፍ ገድቦታል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 77/2/ እንደሰፈረው የሚኒስትሮች ም/ቤት የሚኒስቴሮችንና በቀጥታ ለራሱ ተጠሪ የሆኑ የመንግስት አካላት አደረጃጀት (በእንግሊዝኛው ቅጂ organizational structure) ይወስናል፡፡ አደረጃጀት ሲባል የአንድን ተቋም ውስጣዊ መዋቅር ይመለከታል፡፡ ማቋቋም፣ ማጠፍ፣ ማዋሃድ፣ መከፋፈል እንዲሁም ስልጣንና ተግባር መለወጥ በህዝብ ከተመረጡ ተወካዮች እጅ መውጣት የሌለበት መሰረታዊ የህግ አውጭነት ስልጣን ነው፡፡በውክልና ዲሞክራሲ መርህ መሰረት የሁሉም ስልጣን መነሻ እና ባለቤት የሆነው ህዝብ የሚያስተዳድሩትን ተወካዮች ሲመርጥ በምርጫው (ወዶና ፈቅዶ) በውክልና ስልጣኑን ያስረክባቸዋል፡፡ በህዝብ ያልተመረጡ የመንግስት ባለስልጣናት እና ሹመኞች ከእነዚህ የህዝብ ተወካዮች በከፊል ተቆርሶ ከሚሰጣቸው ስልጣን በስተቀር ከሌላ ምንጭ የሚያገኙት ስልጣን የለም፡፡ ሆኖም የተሻሩትን ጨምሮ አዋጅ ቁ. 916/2008 ስራ አስፈጻው ራሱ ስልጣን ሰጪ ራሱ ተቀባይ እንዲሆን በማድረግ ህግ አውጭውን ‘ከተወካዮች ም/ቤት ወደ ወካዮች ም/ቤት’ አሳንሰውታል፡፡

የአስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነትማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የመሻት ቀዳሚ ኃላፊነት የተጣለባቸው በየዘርፉ የተቋቋሙት የአስተዳደር መ/ቤቶች ናቸው፡፡ ከትምህርት አሰጣጥ ወይም ጥራት ጋር የተያያዘ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ሲከሰት የትምህርት ሚኒስቴር እንቅስቃሴ ይጀምራል፡፡ በጉምሩክ ህግ አፈጻጸም አቤቱታዎች ሲጎርፉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መፍትሔ ያፈላልጋል፡፡ በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ላይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ትኩረት ሰጥቶ ስራ ይጀምራል፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ መላ መዘየድ ችግር የለውም፤ እንዲያውም ይበረታታል፡፡ይሁን እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች ሊቀረፉ የሚገባው በህግና በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ከፊል ጉዳዮች የተወካዮች ም/ቤትን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ችግር ፈቺነት በህግ ከተፈቀደላቸው ስልጣን በላይ ሊለጠጥ አይችልም፡፡ አዋጅ ሊመልሰው የሚገባውን መመሪያ ከቀደመው መ/ቤቶች ችግር ፈቺ መሆናቸው ቀርቶ ችግር ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡ የአስተዳደር ድንጋጌዎች መመዘኛ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ህጋዊነት ነው፡፡ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ተወካዮች ሊመክሩበትና ሊፈቱት የሚገባውን ችግር ተሿሚዎች በመመሪያ ለመቅረፍ መሽቀዳደም የለባቸውም፡፡ ከላይ የቀረበውን ሀሳብ በተጨባጭ የሚያሳዩ ጥቂት አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይጠቀሳሉ፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች አስተዳዳርፍትህ የማግኘት መብትን የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀፅ 37/1/ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 በልዩ ሁኔታ ሰራተኞችን ማሰናበትን በተመለከተ በአንቀጽ 37 እንደሚከተለው ደንግጓል፡፡1) በዚህ ደንብ በሌላ ሁኔታ የተደነገገው ቢኖርም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ሰራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈፃፀም ስርዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናበት ይችላል፡፡2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ስራ መመለስ አይችልም፡፡የህገ መንግስቱና የደንብ ቁ. 155/2000 ድንጋጌዎች በስም (አንቀጽ ቁጥር) ይመሳሰላሉ፡፡ በተግባር ግን ተጻራሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መብት ያናጽፋል፤ ሁለተኛው ይነፍጋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ ከተጣለባቸው አካላት መካከል አንደኛው ነው፡፡ በዚህ ግዴታው የህግ አውጭነት ስልጣኑ ምንጭ የሆነው ህግ ያሰመረለትን ወሰን ሊያከብር ይገባል፡፡ ምክር ቤቱ ደንብ ቁ. 155/2000 ለማውጣት ህግ እንደፈቀደለት የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ አዋጅ ቁ. 587/2000 አንቀጽ 19/1/ ለ ድንጋጌ ነው፡፡ ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡[የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን] ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይመራል፡፡በስልጣን ምንጭነት የተጠቀሰው ህግ ም/ቤቱ የሠራተኞች አስተዳደርን በተመለከተ ደንብ እንዲያወጣ ይፈቅድለታል፡፡ ይሁን እንጂ ሠራተኞች በጥርጣሬ እንዲሰናበቱና በየትኛውም የፍርድ አካል መብቸውን እንዳይጠይቁ የሚከለክል ኢ-ህገ መንግስታዊ ደንብ እንዲያወጣ ስልጣን አልሰጠውም፡፡