ሚዛናዊ የግብረ ስጋ ግኑኝነት


ሚዛናዊ የግብረ ስጋ ግንኙነት

ለመሆኑ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ከህግ አንፃር የተፈቀደው የግብረ ስጋ ግንኙነት አቅጣጫ (position) የትኛው ነው? በ ዶ እና ሞ (Doe Vs. Moe) መካከል በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ግዛት የተካሄደ የይግባኝ ክርክር እና ውሳኔ ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ በመዝገቡ ላይ ይግባኝ ባይ የሆነው ግለሰብ “ፍቅረኛዬ የግብረስጋ ግንኙነት ስናደርግ ተገቢና ተስማሚ ያልሆነ አቅጣጫ እንድንጠቀም በማድረግ (በግልፅ አስገደደችኝ ባይልም ወትውታና ገፋፍታ የሚሉትን ቃላት ግን ተጠቅሟል) በዚህም የተነሳ በብልቴ ላይ የማይመለስ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ስለሆነ በቸልተኝነት ለፈጸመችው ድርጊት ተጠያቂ ስለሆች ካሳ ትክፈለኝ” በማለት በስር ፍርድ ቤት ክስ ያቀርባል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ አድርጎ ተከሳሽን በነፃ ያሰናብታል፡፡ ከሳሽ በውሳኔው ቅር ተሰኘና ይግባኝ አቀረበ፡፡ ይግባኙን የመረመሩት ዳኛ በስምምነት በሚደረግ የግብረስጋ ግንኙነት ሁለቱም ወገኖች ስለሚጠበቅባቸው ጥንቃቄ በተመለከተ ወጥ መለኪያ ወይም መስፈርት ለማስቀመጥ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ ሲያደርጉ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “በስምምነት የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ስርዓትን የሚገዙ ሁሉን ዓቀፍ የህግ ድንጋጌዎች የሉም፡፡ በተጨማሪም ይህንን ከስሜት አንፃር እሳታዊ በዓይነቱም ዥንጉርጉር በሆነው ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ የጋራ ተቀባይነት ያላቸው ልማዶች እና እሴቶች የሉም፡፡” በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ቸልተኝነት በተለመደው ሚዛናዊ ጥንቃቄ የማድረግ መለኪያ ማየት ወይም መወሰን እንደማይቻል በውሳኔው ላይ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ለሚደርስ ጉዳት መቼም ቢሆን ካሳ ሊከፈል እንደማይቻል ፍጹም አቋም ላይ አልደረሰም፡፡ በፍርድ ቤቱ የውሳኔ ሐተታ ላይ እንደተመለከተው በስምምነት በሚፈጸም የግብረ ስጋ ግንኙነት በአንደኛው ወገን ላይ ጉዳት በደረሰ ጊዜ ካሳ ሊከፈል የሚችለው ሌላኛው ቸልተኛ በሚሆንበት ወቅት ሳይሆን ከዚህ ከፍ ብሎ ግድየለሽነት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በይግባኝ መዝገቡ ላይ የመልስ ሰጭ ቸልተኝነት የተረጋገጠ ቢሆንም ይግባኝ ባዩ ግድ የለሽ መሆኗን በሚገባ ስላላስረዳ ያቀረበው የካሳ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡