ግዴታን አለመወጣት


ግዴታን አለመወጣት

ህጋዊ ግዴታ የተጣለበት አካል በቸልተኝነትና በንዝልልነት አሊያም ሆነ ብሎ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ግዴታውን ለመፈፀም ፍቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ዜጋው በእርግጥም የአስተዳደር በደል ደርሶበታል፡፡ ግዴታውን ያልተወጣው አካል ተገዶ ግዴታውን እንዲፈጽም በማድረግ በደል ለደረሰበት ወገን ፍትህ ማጎናፀፍ የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት ነው፡፡ የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት ሕገ መንግስቱን የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት በህግ አውጭና ህግ አስፈፃሚው እንዲሁም በዳኝነት አካላት ላይ ይጥላል፡፡ በህገ-መንግስቱ ላይ የተመለከቱት መብቶችና ነፃነቶች በአስተዳደራዊ ድርጊት ብቻ ሳይሆን ግዴታን ባለመወጣት በሚፈፀም በደል ምክንያት እንዳይጣሱና እንዳይገረሰሱ በመጠበቅ ፍርድ ቤቶች ህገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን ሊወጡ የሚችሉት ህገወጡን ድርጊት ሲሰርዙ (ሲሽሩ) እንዲሁም ግዴታውን ያልተወጣውን አካል ማስገደድ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ አንድ የአስተዳደር መስሪያ ቤት ግዴታውን አልተወጣም ተብሎ ከመወቀሱና ፍርድ ቤቱም የማስገደጃ ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት መስሪያ ቤቱ ከህግ የመነጨ ግዴታ እንዳለበትና ግዴታው ለአመልካቹ በቀጥታ የሚፈጸም መሆኑ መረጋገጥ የሚኖርባቸው ፍሬ ነገሮች ናቸው፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል እንበልና የአንድ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት (ስም) የማዛወር እና ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ስም የማዛወር ግዴታ በህግ የተቀመጠ ግዴታ ከመሆኑም በላይ ለአመልካቹ በቀጥታ የሚፈፀም ስለሆነ ስም ለማዛወር የሚያበቁ ህጋዊ ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ ማዘጋጃ ቤቱ ዝውውሩን ሊያከናውን ይገደዳል፡፡ ፈቃደኛ ሳይሆን ከቀረ ግን በፍርድ ቤት አስገዳጅነት ስም ማዛወር ይኖርበታል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 91622a አንደኛውን ተከራካሪ ባለመብት የሚያደርግ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ በስሙ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት አካል ውሳኔ ያረፈበትን ቤት በሌላ ሰው ስም እንደተመዘገበ በመግለጽ ከግዴታው ሊያመልጥ እንደማይችል ችሎቱ የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ከተማዋን የማጽዳት ግዴታ እንደ መጀመሪያው ለአንድ ግለሰብ የተሰጠ ሳይሆን ህዝባዊ ግዴታ (public duty) ነው፡፡ ስለሆነም በግዴታው አለመወጣት መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ወገን ግዴታው እንዲፈጸምለት በፍርድ መጠየቅ አይችልም፡፡ አጣሪ ዳኝነት ሆነ የህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ክስ (Public interest litigation) ብዙም ባልተለመደበት በአገራችን ህዝባዊ ግዴታን ማስፈጸም በባህርዩ አስቸጋሪ የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከተማ ለማጽዳት ማዘጋጃ ቤቱ በቂ የሰው ኃይል መቅጠር፣ የደረቅ ፍሳሽ ማስወገጃ መኪኖችን መግዛት ወዘተ…ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ በቂ በጀት ካልተመደበለት የፍርድ ማስገደጃ ትዕዛዝ ተግባራዊ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የግዴታ ባህሪያት በተጨማሪ የሚፈጸመው ግዴታ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ወይም ሊሟሉ የሚገባቸውን ፍሬ ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ላይ የመድረስ ፈቃደ ስልጣን (discretion) የሚሰጥ ሊሆን ይችላል፡፡ በህጉ መሰረት የንግድ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ ያለበት አካል ግዴታው የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥና ውሳኔ ላይ መድረስ ብቻ ነው፡፡ ማመልከቻ ቀርቦለት መርምሮ ተገቢ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ማመልከቻውን አይቶ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ በፍርድ ሊገደድ ይችላል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ከዚህ አልፎ ራሱን በፈቃድ ሰጪው አካል ቦታ በመተካት የማመልከቻውን ትክክለኛነት መርምሮ ለአመልካቹ ፈቃድ እንዲሰጠው የማስገደጃ ትዕዛዝ ከመስጠት መቆጠብ አለበት፡፡