ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር


ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር

  1. ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር እና ስደቶኞችን በሕገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደ እና እየተባባሰ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እየዳረገ በመሆኑ፣ ችግሩን ለመፍታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የሕግ ማዕቀፉ በመከላከል ላይ የተመሠረተ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤

የወንጀሉ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና መልሶ ማቋቋም ሊደረግላቸው እንደሚገባ በመገንዘብ እና ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን፣ ጾታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በማመን፤

በወንጀል ሕጉም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ ምላሽ የማይሰጡ በመሆናቸው እና በወንጀለኞች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 18 (2) በተደነገገው መሠረት በሰዎች መነገድ የተከለከለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ አገር በመሆኗ፣ ስምምነቱን ተከትለው በወጡት ሕገ-ወጥ የሰዎች በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት በወጣው ፕሮቶኮል እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የወጣ ፕሮቶኮልን ያጸደቀች በመሆኗ፣ እንዲሁም ከሕገ መንግስቱ እና ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ጋር የተጣጣመና የተሟላ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ይህ አዋጅ “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 909/2007” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፡-

“ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪ” ወይም “ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር አሻጋሪ” ማለት፦

በማንኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ ሕግን በመጣስ ወይም በራሱ ፈቃድ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል የፈፀመ ወይም ለመፈፀም የሞከረ፤

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር የወንጀል ድርጊት ላይ በአባሪነት የተሳተፈ፤

ሌሎች ሰዎች በወንጀል ድርጊቱ እንዲሳተፉ ያደራጀ ወይም በተደራጀ የወንጀል ቡድን ውስጥ አመራር የሰጠ፤

ሰዎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጀምሮ የተስፋ ቃል በመስጠት ለወንጀል ድርጊቱ ወይም ለስደተኝነት የዳረገ፤

በማንኛውም መልኩ የወንጀል ድርጊቱን ያበረታታ፣ የወንጀል ድርጊቱ እንዲስፋፋ ያደረገ ወይም የተደራጀው የወንጀል ቡድን በዚህ አዋጅ የተደነገጉ ወንጀሎችን ለመፈፀም ማሰቡን እያወቀ ለጋራ ዓላማ በቡድን ለተሰባሰቡ ሰዎች አስተዋፅዖ ያደረገ፤

በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌላ አገር የሚገኝ ማንኛውም ሰው ነው።

“የተደራጀ የወንጀል ቡድን” ማለት በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌላ አገር የሚገኝወይም የሚንቀሳቀስ ሆኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ሌላ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ዓላማ አንድ ወይም ከዚያ በላይ በዚህ አዋጅ የተደነገጉ ወንጀሎችን ለመፈፀም የተሰባሰቡና የሚንቀሳቀሱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የያዘና ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የተደራጀ ቡድን ሲሆን በማናቸውም መልኩ በሰዎች ለመነገድ የተቋቋመ ቡድንን ወይም ማህበርን ይጨምራል፤

“ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጊት” ማለት በዚህ አዋጅ የተደነገገው ወንጀል፦

ከአንድ በላይ በሆኑ አገራት የተፈጸመ፤

በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈጸመ ሆኖ የድርጊቱ ዝግጅት፣ እቅድ፣ አመራር ወይም የገንዘብ ምንጭ በሌላ አገር የሆነ፤

የተፈጸመው በሌላ አገር ሆኖ የድርጊቱ ዝግጅት፣ እቅድ፣ አመራር ወይም የገንዘብ ምንጭ በኢትዮጵያ ከሆነ ወይም በሌላኛው አገር የግዛት ክልል አማካይነት የሆነ፤

የተፈፀመው ከአንድ በላይ በሆኑ አገራት በሚንቀሳቀስ የተደራጀ የወንጀል ቡድን የሆነ፤ ወይም

በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ ወይም በሌላ አገር የተፈፀመ ቢሆንም የወንጀሉ ውጤት በሌላ አገር ወይም በኢትዮጵያ ላይ የሆነ፤

ድርጊት ነው።

“ብዝበዛ” ማለት የሚከተሉትን ያካትታል፦

በሌሎች ሰዎች ዝሙት አዳሪነት መጠቀም ወይም ሌላ ማንኛውም አይነት ወሲባዊ ብዝበዛን፤

የጉልበት ብዝበዛ፣ የግዳጅ ሥራ ወይም አገልጋይነት፤

ባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር፤

የወሲብ አገልጋይነትን ጨምሮ ሰውን የማይገባ አገልጋይ ማድረግ፤

በመያዣነት መያዝ ወይም አሳልፎ ለሌላ መስጠት፤

የሰው ልጅን አካል ማውጣት ወይም መውሰድ፤

አስገድዶ በልመና ተግባር ማሰማራት፤ ወይም

ህፃናትን ለወታደራዊ አገልግሎት ማሰማራት።

“ባርነት” ማለት የሌላ ሰው የባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እየተፈጸመበት ያለ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ ወይም አቋም ነው፤

“ሰውን በማይገባ አገልጋይ ማድረግ” ማለት አንድ ሰው ሊያስቀረው፣ ሊከላከለው ወይም ሊቀይረው በማይችልበት ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ወይም ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ወይም ማስገደድ ነው፤

“የዕዳ መያዣ ማድረግ” ማለት በሌላ ሦስተኛ ወገን አስቀድሞ በማናቸውም ሁኔታ ግዴታ ለተገባ ወይም ለተጠየቀ ዕዳ የራስን ወይም ኃላፊ የሆነውን ሰው አገልግሎት በመያዣ ከማቅረብ የሚመነጭ ሆኖ የሚሰጠው አገልግሎት ዓይነትና የጊዜ መጠን ባልተወሰነበት ሁኔታ የሚከሰት ማንኛውንም ዓይነት በሰው ልጅ የመነገድ ተግባርን ታሳቢ የሚያደርግ የመያዣነት ተግባር ነው፤

“በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር” ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ወይም ሌላ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሰዎችን ዜግነት ወደሌላቸው ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ወዳላገኙበት አገር በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህር ወይም በአየር ማስገባት ወይም እንዲወጡ ማድረግ ነው፤

“ዲፕሎማቲክ ሚሲዮን” ማለት እንደ አግባብነቱ የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ሃገራት ያቋቋማቸው ኤምባሲዎች፣ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤቶች እና የክብር ቆንሲላዎች ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ኤምባሲዎች እና ቆንሲላ ጽሕፈት ቤቶች ማለት ነው፤

“ስደተኛ” ማለት በስደተኞች ጉዳይ አዋጅ የተመለከቱ መስፈርቶችን የሚያሟላ ሰው ነው፤

“ተጎጂ” ማለት በዚህ አዋጅ የተደነገጉ የወንጀል ድርጊቶች የተፈፀበት ሰው ወይም የወንጀል ድርጊቱ በመፈፀሙ ጉዳት የደረሰበት ሰው ሲሆን ማንኛውንም የሥነ-ልቦና፣ ሞራላዊ፣ አካላዊ ወይም የኢኮኖሚ ጉዳት ወይም ሌላ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የደረሰበት ሰው ነው፤

“ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 47 (1) የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል የአዲስ አበባንና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርን ይጨምራል፤

“ሕጻን” ማለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው፤

“ሚኒስቴር ወይም ሚኒስትር” ማለት እንደቅደም ተከተሉ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትህ ሚኒስቴር ወይም የፍትህ ሚኒስትር ነው፤

“ፖሊስ” ማለት የፌዴራል ፖሊስ ወይም በዚህ አዋጅ ለተመለከቱ ጉዳዮች የፌዴራል ፖሊስ ሥልጣን በውክልና የተሰጠው የክልል ፖሊስ ነው፤

“ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤

ማንኛውም በወንድ ፆታ የተገለጸው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡

ክፍል ሁለት

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች

ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውጪ ለብዝበዛ ዓላማ ሲባል፦

በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ወይም ለሥራ ወይም ለሥራ ልምምድ ወደ ውጭ አገር መላክ በሚል ሽፋን፤

የጉዲፈቻ ስምምነት በማድረግ ወይም በጉዲፈቻ ሽፋን፤ ወይም

ለሌላ ማንኛውም አይነት ዓላማ፤

ዛቻን፣ ሀይልን ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በማገት፣

በመጥለፍ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት፣

ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ሰዎችን የመለመለ፣

ያጓጓዘ፣ ያዘዋወረ፣ ያስጠለለ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከብር 150,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው የወንጀል ድርጊት የተፈፀመው፦

በሕጻናት፣ በሴቶች ወይም በአዕምሮ ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፤

ተጎጂው ለአካላዊ ወይም አዕምሯዊ ጉዳት ከተዳረገ፤

አደንዛዥ ዕፅ፣ መድሃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንደሆነ፤

በመንግስት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ ከሆነና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ፤ ወይም

በተጎጂው ወላጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ አሳዳጊ ወይም በተጎጂው ላይ ሥልጣን ባለው ሰው የሆነ እንደሆነ፤

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.