መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች


መሰረታዊ የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች

መልካም አስተዳደር ምንም እንኳን በጥቅሉ ሲታይ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ እንዲሁም የአመራር እና የአሰራር ሂደቶችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ እንደምታዎች ያሉት ቢሆንም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሲታይ ግን ከአስተዳደር ፍትህ ጋር አቻ ሆኖ ሊገለጽ ይችላል፡፡ መልካም አስተዳደር ዋና ግቡ ዜጐች ብቁና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል መቅረፍ እና አስተዳደራዊ ፍትህን እውን ማድረግ እንደመሆኑ ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት ያስቸግራል፡፡ መልካም አስተዳደር ሆነ የአስተዳደር ህግ በራሳቸው አቅጣጫና ሂደት ተጉዘው የግባቸው መድረሻ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ ስለሆነም በይዘቱ ሰፊ በሆነ የመልካም አስተዳደር እሳቤ ውስጥ የአስተዳደር ህግ አንድ ቁስ ሆኖ በማገልገል የተቆራኘና የተዛመደ ተግባራዊ እገዛ ያደርጋል፡፡በመልካም አስተዳደርና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለውን ተዛምዶ በቅጡ ለመቃኘት ህግ በአስተዳደሩ አካሄድ (Administrative behavior) ወይም በስራ አስፈፃሚው እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በተግባር የታገዘ ጥልቅ ጥናት ምላሽ መስጠት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ሚናዎችና ተግባራት ቢያንስ እንደጠቅላላ ሀሳብ በመውሰድ የአስተዳደር ህግ እንደ አንድ የህግ ዘርፍ የራሱ አዎንታዊ ፋይዳ እንዳለው መደምደም እንችላለን፡፡ ያም ሆኖ ግን አስተዳደሩ መልካም እንዲሆን የአስተዳደር ህግ ስልጣን ከመቆጣጠር ባሻገር እንዴት ተቃኝቶ መቀረጽ አለበት? የሚለው ጥያቄ ለአስተዳደር ህግ አጥኚዎች ሆነ ምሁራን የውይይት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የጥናት መሰረት መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡የመልካም አስተዳደር እና የአስተዳደር ህግን ተዛምዶ ለማየት የሁለቱም መድረሻ ከሆነው የአስተዳደር ፍትህ ትርጓሜ እንነሳለን፡፡ የአስተዳደር ፍትህ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው የመንግስት አካላት ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት ከዜጐች መብትና ነፃነት አንጻር ፍትሃዊ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ መርህ ነው፡፡ የመንግስት አስተዳደር ፍትሃዊ ሲሆን መልካም ይሆናል፡፡የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ቁልፍ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ ይኸውም፡-አንደኛ፦ የመንግስት ባለ ስልጣናት ወይም የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ወቅት አነስተኛ ለሆኑ የስነ-ስርዓት ደንቦች እና ተቀባይነት ላላቸው መርሆዎች መገዛት አለባቸው፡፡ ከአነስተኛ የስነ-ስርዓት ደንቦች በተጨማሪ የመንግስት አስተዳደር ተቀባይነት ባላቸው የህግ፣ የአስተዳደርና የፍትህ መርሆዎች መመራት አለበት፡፡ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡የህጋዊነት መርህ (ህጋዊ ስልጣን ሳይኖር አንዳችም እርምጃ አለመውሰድ፤ በህጉ መሰረት መወሰን)የሚዛናዊት መርህ (የአስተዳደር አካላት ውሳኔ ወይም እርምጃ እንደየሁኔታው ብዙ ነገሮች ግምት ያስገባ እንጂ ፍርደገምድል መሆን የለበትም፡፡)የተመጣጣኝነት መርህ (የሚወሰደው እርምጃ ተፈጸመ ከተባለው ጥፋት አንፃር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡)የእኩልነት መርህ (ተመሳሳይ በሆኑ ሁኔታዎች ወይም ጉዳዮች አስተዳደሩ የተለያየ ውሳኔ ላይ መድረስ የለበትም፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተመሳሳይ መንገድ መወሰን አለባቸው፡፡)ለውሳኔ በቂ ምክንያት መስጠት (አስተዳደራዊ ውሳኔ የተወሰደበት ምክንያት በግልጽ መጠቀስ አለበት፡፡ ውሳኔውም ፈጽሞ የማያሳምንና ኢ- ምክንያታዊ መሆን የለበትም፡፡)ሁለተኛ፦ ከላይ የተመለከቱትን ደንቦችና መርሆዎች በመጻረር በህግ ከተወሰነው ስልጣን በላይ እርምጃ ከተወሰደ መብታቸው የተጐዳ ዜጐች አቤቱታ አቅርበው ፍትህ (መፍትሄ) የሚያገኙበት መንገድ መኖር አለበት፡፡ በአስተዳደር አካላት መብታቸው የተጣሰ ሰዎች ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት አቤቱታ አቅርበው ቀልጣፋ መፍትሔ የሚያገኙበት አሰራር ወይም መንገድ ከሌለ የአስተዳደር ፍትህ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አካልን ነፃ የማውጣት መብት በህገ-ወጥ መንገድ ከ48 ሰዓት በላይ የታሰረ ሰው ራሱ በቀጥታ ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን በቀላሉ አቤቱታ አቅርቦ ነፃ የሚለቀቅበት ፈጣን ስነ-ስርዓት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በህገ ወጥ መንገድ ንብረቱን በአስተዳደደሩ የተቀማ ወይም ፈቃዱ አለአግባብ የተሰረዘበት ሰው ቀላል በሆነ ስነ-ስርዓት መፍትሔ የሚያገኝበት የህግ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ነው የአስተዳደር ህግ መኖር ለአስተዳደራዊ ፍትህ ሆነ ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሳሪያ ነው የሚባለው፡፡ የአቤቱታው ስርዓት እንዳለ ሆኖ የአስተዳደራዊ ፍትህ የሚገኝበት ተቋም ገለልተኛ፣ ተደራሽ እና ነፃ ሆኖ ቀልጣፋና ውጤታማ ግልጋሎት መስጠት መቻሉ የአስተዳደር ፍትህን በማሳካት ረገድ ዋናውና መሰረታዊው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡