ጣልቃ ገብ፦


ጣልቃ ገብ፦ በፍትሃ ብሔር ክርክር ተካፋይ ያልነበረ ሰው የክርክሩ ተካፋይ የሚሆንበትና መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር ተገቢውን ክርክር እንዲያቀርብ በህጉ የተዘረጋ ስርዓት ጣልቃ ገብ ወደ ክርከሩ የሚገባው በተከሳሽ ጠያቂነት ወይም በራሱ አነሳሽነት ሊሆን እንደሚችል የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41 ድንጋጌ ይዘት ያሳያል፡፡ በዚህ ድንጋጌ እንደተመለከተው ሌሎች ወገኖች በሚከራከሩበት ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሶስተኛ ወገን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር እንዲፈቀድለት ሊከራከር ይችላል፡፡ ሆኖም የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብ ለመሆን ሌሎች ሰዎች በሚከራከሩበት ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ በቀጥታ መብቱንና ጥቅሙን የሚነካ መሆኑን የማስረዳት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ በሌላ አገላለፅ ጣልቃ ልግባ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲኖረው ውሳኔው የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነውን ሰው መብትና ጥቅም በሚጎዳ መልኩ በቀጥታ የሚፈጸም መሆኑንና ሌላ አዲስ ክስ በማቅረብ ለማስቀረት የማይቻል መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ጣልቃ ገብ ልሁን በሚል ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው ውሳኔው በቀጥታ መብቱንና ጥቅሙን የማይጎዳ ከሆነ እና አዲስ ክስ በማቅረብ ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ ያለው ከሆነ ጥያቄው በህግ ፊት ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ጣልቃ ልግባ የሚለው ወገን በተከራካሪ ወገኖች መካከል ባለው ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ መብቱን በምን አግባብና መልኩ ሊነካ እንደሚችል ማሳየት እንደአለበት የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41(2) ድንጋጌ ያሳያል፡፡ በመሆኑም አመልካቹ ዝርዝር ምክንያቱን በማስፈር ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ የጣልቃ ገብነቱ አቤቱታ ሊቀርብ የሚገባውም ጊዜ ለማራዘም፣ ክርክሩን ለማጓተት ሊሆን እንደማይገባው ከተጠቃሹ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ እንዲሁም ከፍትሃ ብሔር ስነ ስርዓት ህጉ መሰረታዊ አላማ የምንገነዘበው ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 41 በአንድ ክስ ሌሎች ተከራካሪ ወገኖች በክርክር ላይ ባሉበት ጊዜ ማናቸውም ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ያገባኛል የሚል ሲሆን ከፍርድ ውሳኔ በፊት ጣልቃ ገብ ሆኖ ለመከራከር እንደሚችል እና የጣልቃ ገብነት ማመልከቻው በክሱ ውስጥ ያገባኛል የሚልበትን ምክንያት የሚዘረዝርና በተለይም የመብቱን ሁኔታ የሚገልጽ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም የጣልቃ ገብነት ጥያቄ አቅራቢው በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር የሚያስችል መብት ያለው መሆን አለመሆኑ በቅድሚያ ሊወሰን እንደሚገባው፣ ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል መብት የለውም በተባለ ጊዜ መሰናበት እንደሚገባው እና መብት አለው በተባለ ጊዜ ግን የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን ከተደረገ በኃላ ከጣልቃ ገቡ መብት አንፃር ጭምር አጠቃላይ ክርክሩ ተመርምሮ ተገቢ ነው የሚባል ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ከፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 41 (1)፣ (2) እና (3) ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ቤትና ይዞታን በሚመለከት በሚደረግ ክርክር አንድ ጣልቃ ገብ አመልካች ክርክር በሚደረግበት ቤትና ይዞታ ላይ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር መብት አለኝ በማለት መብቱን የሚያሳዩ ሰነዶችን አቅርቦ እያለ የባለይዞታነት ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አላቀረብክም ተብሎ ከወዲሁ ጣልቃ ገብተህ ልትከራከር አትችልም ተብሎ አቤቱታውን ውድቅ ማድረግ አግባብነት የለውም፡፡

ጠባቂ


 በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089/2/ ድንጋጌ መሰረት ጥቅም የሌለው ግንኙነት መኖሩ ቢረጋገጥም የመኪና ባለሃብት ወይም ጠባቂ ጥፋት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ በመኪናው በነጻ ተሳፍሮ ሲጓዝ ጉዳት ለደረሰበት ተሳፋሪ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ በድንጋጌው ስር “ጠባቂ” የሚለው ቃል የአማርኛው አቻ የእግሊዘኛ ቃሉ ‘’holder’’ በሚል የተቀመጠ ሲሆን ይህ ቃል በሕግ መዝገበ ቃላት ከተሰጠው ትርጉም አንዱ a person who possesses or uses property በሚል የተቀመጠ መሆኑን ታዋቂው የብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት ያሳያል፡፡ ስለሆነም ጠባቂ የሚለው ቃል የሚመለከተው ለራሱ ጥቅም መኪናውን ይዞ የሚገኘውን ሰው ነው፡፡

የአስተዳደር መንግስት እና የአስተዳደር ህግ ውልደት


የአስተዳደር መንግስት እና የአስተዳደር ህግ ውልደት
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ገኖ የነበረው የነፃ ገበያ (laisse faire) ንድፈ ሀሳብ በዋነኛነት ውስን የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ሰፊ የግለሶቦች ነፃነትን ያቀነቅናል፡፡
a በዚሁ ንድፈ ሀሳብ መሰረት የመንግስት ሚና ህግና ስርዓት ከማስጠበቅና አገርን ከጠላት ወረራ ከመከላከል የዘለለ መሆን የለበትም፡፡ ምርጥ መንግስት ማለት በስሱ (በትንሹ) የሚገዛ መንግስት ማለት ነው፡፡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን መምራት፣ መቆጣጠርና መግራት እንደ መንግስት ኃላፊነት አይቆጠርም፡፡ሆኖም ነፃ የሆነው የገበያና የመንግስት ስርዓት እግረ መንገዱን ይዞ የመጣቸው አሉታዊ ውጤቶች በዋነኛነት ያረፉት በደካማውና ደሀው የህብረተሰብ ክፍል ጫንቃ ላይ ነበር፡፡ በሀብታምና ደሀ መካከል የተፈጠረው የሀብት ድልድል ልዩነት በእጅጉ እየሰፋ በመምጣቱ ሀብታም የበለጠ ሲበለፅግ ደሃው ግን ይባስ እየቆረቆዘ መሄድ ጀመረ፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የነበረው የመደራደር አቅም ልዩነት ታይቶ ለማይታወቅ የጉልበት ብዝበዛ ምክንያት ሆነ፡፡ እነዚህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቆች ለነፃ ገበያ ስርዓትና አስተሳሰብ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ስለሆነም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቆች መፍትሔ መስጠት የመንግስት ግዴታና ኃላፊነት የመሆኑ እውነታ ቀስ በቀስ እየተገለጠ መጣ፡፡b በተለይም የሁለተኛው የአለም ጦርነትን ተከትሎ የተከሰቱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ በገሃድ አስረግጠዋል፡፡ መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው ደግሞ አወቃቀሩና አደረጃጀቱ ሲገፉት የሚፍረከረክ ዓይነት ‘ልል’ ወይም ውስን መንግስት መሆኑ ቀርቶ ጡንቻው የዳበረና ስልጣኑ የሰፋ ጠንካራ መንግስት ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቆች መፍትሔ መስጠት የመንግስት ግዴታ ነው ሲባል ሚናው ከተለመደው ስርዓትና ፀጥታ ማስከበር ባሻገር ሰፊና ውስብስብ አዎንታዊ ተግባራትን ወደ ማከናወን መሸጋገር እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡በዚሁ መሰረት የመንግስት ሚና ቀስ በቀስ ከፖሊስነት (Police State) ወደ ማህበራዊ አገልግሎት አቅራቢነት ሊሸጋገር ችሏል፡፡ መንግስት በአገልግሎት አቅራቢነት ሚናው ውሀ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ ወዘተ የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጐቶችን የማሟላት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅጣጫውን ፈር ለማስያዝና ፍትሐዊ የሀብት ድልድል እንዲኖር እንዲሁም ለደካማው የህብረተሰብ ክፍል ጥበቃና ከለላ ለማድረግ በአጠቃላይ የነፃ ገበያን አሉታዊ ውጤቶችን ለመቀነስ ሰፊና ተከታታይ ቁጥጥርና ክትትል (Regulation) ያደርጋል፡፡ አዲሱ የማህበራዊ መንግስት አዲሱን አዎንታዊ ሚናውን በብቃትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ይወጣ ዘንድ በዓይነትና በይዘት የጠንካራ ስልጣን ባለቤት ሊሆን የግድ የሚል ሀቅ ነው፡፡cየስልጣን አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስልጣን በየጊዜው ወሰኑ፣ መጠኑና ቅርጹ እያደገና እየሰፋ በመጣ ቁጥር ግን የግለሰቦችን መብትና ነፃነት መንካቱ አይቀርም፡፡ የመንግስት ስልጣን እየተለጠጠ መሄድ አቅመቢስ ለሆነው ዜጋ የስጋት ምንጭ ነው፡፡ ፍፁም የሆነና ወደ ፍፁምነት የተጠጋ ስልጣን ወደ ህገ ወጥነትና የበዘፈቀደ ድርጊት የማምራት አደገኛ አዝማሚያ አለው፡:የአስተዳደር ህግ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የመንግስት ‘ጡንቻ መፈርጠም’ በቅጡ ለመቆጣጠር በታሪክ ሂደት በተጓዳኝ የተፈጠረ የህግ መሳሪያ ነው፡፡ መንግስት ተግባራቱን ለማከናወን ፖሊሲ ቀርጾ፣ ህግ አውጥቶ በሚያስፈጽምበት ወቅት በስልጣን እና በፍትህ (የግለሰቦች ነፃነት) መካከል ቅራኔ መከሰቱ የማይቀር እውነታ ነው፡፡ ጥያቄው ቅራኔው እንዴት ይፈታል? ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ የዚህ ቅራኔ የራሱ ውጤት ሲሆን ቅራኔውን በአንፃራዊ መልኩ ለማስማማትና ለማጣጣም በታሪክ ሂደት ብቅ ያለ ተግባራዊ መሳሪያ ነው፡፡d የአስተዳደር ህግ በዕቅድ ታስቦ የተወለደ ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ ህጉ በሁለት በጉልበት የማይመጣጠኑ ጐራዎች ማለትም በመንግስትና በግለሰብ መካከል ሚዛናዊነትንና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ይጥራል፡፡የአስተዳደር ህግ መንግስት በተለይ ስራ አስፈፃሚውና የአስተዳደር አካላት በህግ ከተፈቀደላቸው የስልጣን ክልል አልፈው ህገ ወጥ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ቁጥጥር የሚያደርግና ይህንንም የሚያረጋግጥ ህግ ነው፡፡e በዚህም የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የግለሰቦች ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዳይሸራረፉና እንዳይጣሱ ከለላ በመስጠትf ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው ስልጣን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል መሪ ደንቦችን በማስቀመጥና ስነ ስርዓታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን በመዘርጋት የተለያዩ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችን በመጠቀም የግለሰቦችና የዜጐች መብቶችና ነፃነቶች እንዳይገሰሱና እንዳይደፈሩ ከለላ በመስጠት የህገ መንግስት ማስፈፀሚያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የአስተዳደር ህግ ምንነትለአስተዳደር ህግ ብያኔ በማበጀት ረገድ የመስኩ ባለሙያዎች በከፊልም ቢሆን የተለያየ እይታ አላቸው፡፡ በእርግጥ የአስተዳደር ህግ የጥናት ወሰኑን አስመልክቶ የሚከሰት ልዩነት ካልሆነ በቀር በመሰረታዊ እሳቤው ላይ የተራራቀ አቋም የለም፡፡ እንደ ህንዳዊው የአስተዳደር ህግ ምሁር አይ.ፒ. ማሴይ አገላለጽ በአስተዳደር ህግ ትርጓሜ ላይ ያለው ልዩነት ምንጩ በየጊዜው እያደገና እየተወሳሰበ የመጣው አስተዳደራዊ ሂደት ሲሆን ይህም ሂደቱን በሙሉ አጠቃሎ የያዘ ወጥ ትርጉም ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡gያም ሆኖ የአስተዳደር ህግ ትርጓሜ ቢያንስ ሁለት መሰረታዊ አላባውያንን ማካተት ይጠበቅበታል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ህግ ከይዘት ይልቅ ስነ ስርዓት ላይ የሚያተኩር ህግ ስለመሆኑ ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ውሳኔው እንዴት ተሰጠ? እንጂ ይዘቱ ትክክል ይሁን አይሁን ፍርድ ቤቶች ሆነ የአስተዳደር ህግ ጣልቃ የሚገባበት ጉዳይ አይደለም፡፡በሁለተኛ ደረጃ ማንኛውም የአስተዳደር ህግ ትርጓሜ የህጉን ዓላማ ግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ አቀራረብ እንዲያቅፍ ይጠበቅበታል፡፡ የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማ ወይም ተግባር ስልጣንን መቆጣጠር ነው፡፡h ያ ሲባል ግን የአስተዳደር አካላት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩና እንዳይላወሱ ማነቆ ሆኖ ያግዳቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የስልጣን ቁጥጥር ሲባል ማንኛውም ባለስልጣን ሆነ መስሪያ ቤት በህግ ተለይቶ ከተቀመጠለት የስልጣን ገደብ እንዳያልፍና ስልጣን ቢኖረውም እንኳን ስልጣኑን ፍትሐዊና አግባብ በሆነ መንገድ እንዲወጣ ያደርጋል ለማለት ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማና ተግባር ስልጣንን በተግባር መቆጣጠር እንደመሆኑ ይህን ባህርዩን ግምት ውስጥ ያላስገባ ብያኔ የተሟላ ተብሎ ሊወሰድ ሆነ ሊወደስ አይችልም፡፡ለንጽጽር እንዲረዳን በመስኩ ባለሙያዎች ለአስተዳደር ህግ የተሰጡ ትርጓሜዎችን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡ቤርናርድ ሺዋሬዝ (Bernard Schwartz) የአስተዳደር ህግን ‘በውክልና ህግ የማውጣትና አስተዳደራዊ ዳኝነት የመስጠት ስልጣን ባላቸው የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ህግ’ በማለት ይገልፀዋል፡፡i ይህ ብያኔ ጠባብ ከመሆኑ በቀር ስለ ህጉ ይዘት ገላጭ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በውክልና ስልጣን ህግ ከማውጣትና ከአስተዳራዊ የዳኝነት ስልጣን በተጨማሪ ይህ ስልጣን በፍርድ የሚታረምበትን የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስነ-ስርዓት እንዲሁም በፖርላማና በተለያዩ ተቋማት የሚደረግ ቁጥጥርንም ያካትታል፡፡ጄኒንግስ በበኩሉ የአስተዳደር ህግ ማለት ‘አስተዳደርን የሚመለከት ህግ ነው፡፡ ይህ ህግ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ግዴታ ይወስናል፡፡’ በማለት ይገልጸዋል፡፡j እንደ አይ.ፒ ማሴይ አስተያየት ይህ ትርጓሜ የአስተዳደር ህግን ከህገ መንግስት በግልጽ አይለይም፡፡ አስተዳደር ወይም ማስተዳደር ማለት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስልጣንን በመጠቀም የህብረተሰቡን ጉዳይ መምራት ማለት ነው፡፡k ለዚህም በዋነኛነት አደራ የተጣለባቸው አካላት የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የእነዚህ ተቋማት ስልጣንና ግዴታ በዝርዝር ህግ ተለይቶ ቢወሰንም የስራ አስፈፃሚው አካል ስልጣን በጠቅላላው የሚቀመጠው በህገ መንግስት ላይ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ሆነ ህገ መንግስት ሁለቱም የመንግስት አስተዳደርን ወይም የግለሰብና የመንግስትን ግንኙነት የሚመሩ ህጐች እንደመሆናቸው በመካከላቸው ያለው መለያ ክር በጄኒንግ ትርጓሜ ላይ በግልጽ ነጥሮ አልወጣም፡፡ታዋቂው የህገ መንግስት ሊቅ ኤ. ቪ. ዲሴይ የአስተዳደር ህግን በሶስት ደረጃዎች ከፋፍሎ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡lየአስተዳደር ህግ የመንግስት ባለስልጣናትን የህግ ስልጣንና ተጠያቂነት የሚወስኑትን የአንድ አገር የህግ ስርዓት የሚመለከት የህግ ክፍል ነው፡፡ግለሰቦች ከመንግስት አካላት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ያላቸውን መብትና ግዴታ ለይቶ ይወስናል፡፡እነዚህ መብቶችና ግዴታዎች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን ስርዓት ይዘረጋል፡፡እንደ ማሴይ ትችት ይህ ትርጓሜ የአስተዳደር ህግ አንድ አካል የሆነውን አጣሪ ዳኝነት (judicial review) ብቻ የሚመለከት እንደመሆኑ በይዘቱ ጠባብ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ከአጣሪ ዳኝነት በተጨማሪ በህግ አውጭውና በተቋማት (ለምሳሌ በእንባ ጠባቂ ተቋምና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን) አማካይነት የሚደረግ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችንም ያካትታል፡፡ ህጉ ከመንግስት ባለስልጣናትና ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ ከፊል የአስተዳደር አካላት ተብለው የሚፈረጁትን መንግስታዊ ኮርፖሬሽኖች፤ ዩኒቨርሲቲዎች እና በከፊል መንግስታዊ ነክ ስልጣን ያላቸውን ማህበራትm በተመለከተም ተፈጻሚነት አለው፡፡በመጨረሻም ታዋቂው የህንድ ምሁር አይ.ፒ. ማሴይ ከላይ ከተሰጡት ሰፋ ያለና የህጉን ባህሪያትና ተግባራት ጠቅልሎ የያዘ ብያኔ እንደሚከተው ያስቀምጣል፡፡የአስተዳደር ህግ የህዝብ አስተዳደር ህግ አካል ሲሆን የአስተዳደርና ከፊል አስተዳደር መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀትና ስልጣን የሚደነግግ፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥበትን ደንብና መርህ የሚያስቀምጥ፣ እንዲሁም ከግለሰቦች መብትና ነፃነት ውሳኔው የሚታረምበትን ስርዓት የሚወስን የህግ ክፍል ነው፡፡nይህ ትርጓሜ ከሞላ ጐደል ሁሉንም የአስተዳደር ህግ ባህርያት አጠቃሎ የያዘ በመሆኑ ተመራጭነት አለው፡፡ ከላይ ከቀረቡት የተለያዩ ትርጓሜዎች የሚከተሉት የጋራ ነጥቦች ይመዘዛሉ::አንደኛ፤ የአስተዳደር ህግ የአስተዳደር እና ከፊል የአስተዳደር አካላት ያላቸውን ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት ያጠናል፡፡o የማንኛውም የአስተዳደር አካል የስልጣን ምንጭ የሚገኘው ከማቋቋሚያ አዋጁ (Enabling Act) ሲሆን አልፎ አልፎ በሌላ ዝርዝር ህግ ይወሰናል፡፡ በአስተዳደር ህግ የመጀመሪያው ጥያቄ ውሳኔ ወይም እርምጃ የወሰደው አካል በህግ የተሰጠው ስልጣን አለው? የሚል ነው፡፡ ከሌለ ድርጊቱ ከስልጣን በላይ ስለሆነ ዋጋ አልባ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከድርጊቱ በስተጀርባ የህግ ስልጣን ካለ ውሳኔ ሰጪው ስልጣኑን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደተገለገለ ይጣራል፡፡ ካልሆነ ስልጣኑን ያለ አግባብ በሚገለገለው አካል ላይ ህጉ ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡ሁለተኛ፤ ህጉ ስልጣንን በመገልገል ሂደት ተፈጻሚ የሚሆኑ መሪ ደንቦችን፤ ስነ ስርዓቶችንና መርሆዎችን ያስቀምጣል፡፡ ህግ አውጭው ለአስተዳደር አካላት ስልጣን ሲሰጥ ስልጣኑ ተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ ህጋዊነቱንና ፍትሐዊነቱን የሚያረጋግጥ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታ አብሮ እንዲደነግግ ይጠበቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል ደንብና መመሪያ በማውጣት ረገድ ከሚመለከተው አካል ጋር የመመካከርና የህትመት ቅድመ ሁኔታዎች፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጥ የመሰማት መብትና የኢ- አድሎአዊነት መርሆዎችን በአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ወይም በዝርዝር ህግ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም በአስተዳደር ሂደቱ ውስጥ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ስፍራ አላቸው፡፡ ስልጣን በዘፈቀደ ሳይሆን በአግባቡ ስራ ላይ ዋለ ለማለት የሚቻለውም ያኔ ነው፡፡ሶስተኛ፤ የአስተዳደር ህግ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችን በተመለከተ የሚያጠና ህግ ነው፡፡p ልጓም የሌለው ስልጣን ለዜጎች መብትና ነፃነት ፀር ነው፡፡ የተጠያቂነት መርሕ እውን እንዲሆን የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶችም በግልጽ ተለይተው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ህግ በፍርድ ቤት፤ በአስተዳደር ፍርድ ቤት፤ በህግ አውጭው እና በተቋማት የሚደረጉ የስልጣን መቆጣጠሪያ መንገዶችን በተግባር እየፈተነ ያጠናል፡፡አራተኛ፤ ህጉ በአስተዳደር አካላት ወይም በመንግስት ባለስልጣናት በተወሰዱ እርምጃዎች መብታቸው ለተጣሰና ነፃነታቸው ለተገፋ ዜጎች መፍትሔ ይሰጣል፡፡q መብት ያለ መፍትሔ ‘ላም አለኝ በሰማይ’ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ መብቱ የተጓደለበት ሰው አቤቱታ አቅርቦ መፍትሔ የሚጠይቅበትና የሚያገኝበት የህግ ክፍል ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ግብና ተግባራትየአስተዳደር ህግ ዋነኛ ዓላማና ተግባር ስልጣንን መቆጣጠር ስለመሆኑ በመስኩ ምሁራን ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሆኖም በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡ እንደ ብዙዎች የአስተዳደር ህግ ሊቃውንት የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ግብ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን ሲሆን የሚከተሉት ተግባራት ይኖሩታል፡፡ስልጣን መቆጣጠር (Control Function)የአስተዳደር ህግ ስራ አስፈፃሚው የመንግስት አካልና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች፣ ሚኒስትሮች፣ ባለስልጣናትና ሌሎች ሹመኞች በህግ ተለይቶ የተሰጣቸውን ስልጣን አልፈው እንዳይሄዱና ህጋዊ ስልጣናቸውንም አለአግባብ እንዳይገለገሉበት ለመቆጣጠር የሚያስችለን የህግ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም ስልጣን በህገ ወጥ መንገድ አለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመከላከል እንደ መገደቢያ መሳሪያነት ያገለግላል፡፡rግዴታ ማስፈፀም (Command Function)በአስተዳደሩ በሚፈፀም ድርጊት የዜጋው መብት ከሚጣስበት ሁኔታ ባልተናነስ ህጋዊ ግዴታን አለመወጣት በግል መብትና ጥቅም ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል፡፡ የአስተዳደር ህግ ስልጣን በልኩና በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውል ከመቆጣጠር ባሻገር የአስተዳደር አካላት በህግ ተለይቶ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ አስገዳጅ የስነ ስርዓትና ተቋሟዊ ስልቶችን ይቀይሳል፡፡s አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ከሌለ ግዴታ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ውዴታ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡የአስተዳደር ፍትህ ማስፈንበየትኛውም ህግን ለማስፈፀም ስልጣን በተሰጠው የመንግስት አካል የሚወሰዱ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የህዝብ አመኔታና ተቀባይነት እንዲያገኙ ፍትሐዊነታቸው በተጨባጭ ሊታይ ይገባል፡፡ የአስተዳደር ህግ አይነተኛ ተልዕኮ የአስተዳደር ፍትህን ማስፈን ነው፡፡tግልጽነት ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎየአስተዳደር ህግ በመንግስት አስተዳደር ስራ ውስጥ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ተግባራዊ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ የስልጣን ልኩ ሳይታወቅና ከልክ በላይ የሆነ ስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቱ ሳይቀየስ ስለተጠያቂነት ማውራት የማይመስል ነገር ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን በህግ የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በህዝብ አስተዳደር ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የስነ- ስርዓት ደንቦችን ይዘረጋል፡፡ለተበደለ ወገን መፍትሔ መስጠትየአስተዳደር ህግ ዜጎች ለደረሰባቸው በደል በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ባሉ መንገዶች አቤቱታ አቅርበው በአነስተኛ ወጪ እና በቀላሉ መፍትሔ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ስለ አስተዳደር ህግ በተደጋጋሚ ቢወራ ‘አንጀት ጠብ’ የሚል፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፣ መፍትሔ እስከሌለ ድረስ ረብ የለሽነቱን ያጎላው እንደሆነ እንጂ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የአስተዳደር ህጋቸው በዳበረ አገራት የመንግስት ባለስልጣናት በህዝብ ላይ ለሚፈፅሟቸው አስተዳደራዊ በደሎች በዝርዝር የተቀመጡ የመፍትሔ መንገዶች አሏቸው፡፡በአንድ አገር ውስጥ የአስተዳደር ህግ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተወጥቷል ለማለት ከአገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ስርዓት፤ ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ዕድገትና የአስተዳደር ህግ ተቋማት መዳበር ከግምት ውስጥ በማስገባት አንፃራዊ በሆነ መልኩ የሚለካ ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በአንድ አገር ውስጥ ሁሉን አቀፍ ውጤታማና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የአስተዳደር ህግ ስርዓት አለ ለማለት ከሚከተሉት ሶስት ዋነኛ መርሆዎች አንጻር እየተመነዘረ መገምገም አለበት፡፡የአስተዳደር ፍትህየአስተዳደር በደል በፍርድ የሚታረምበትና አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚገኝበት የፍርድ ሂደትና መንገድ እንዲሁም ተሞክሮ በአገራችን ውስጥ በግልጽ የሚታወቅ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ፍትሕ የአስተዳደር ህግ ‘ልቡ’ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አስተዳደራዊ በደል አለቅጥ በተንሰራፋበት አገር ውስጥ የአስተዳደር ህግ ትንፋሽ ያጠረው ህላዌነቱ የሚያጠራጥር ህግ ነው፡፡ የከለላው መጠን የአስተዳደር ፍትህ ደረጃ አንጻራዊ መለኪያ ነው፡፡የስራ አስፈፃሚው ተጠያቂነትየዚህ መርህ ዋና አላማ ህግ የማስፈፀም ስልጣን ያለው አካል ለሚፈፅመው ድርጊት እና ለሚወስደው እርምጃ በህዝብ ፊት ተጠርቶ እንዲጠየቅና ማብራሪያ እንዲሰጥ ለማስገደድ ነው፡፡ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣንን የተቀበለ አካል ወይም ባለስልጣን የሚፈፅመው ድርጊት የህዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ውሳኔ ሰጭው ለድርጊቱ ትክክለኛነትና ፖለቲካዊ ተገቢነት ህግ አውጭው ፊት ተጠርቶ በመቅረብ ለማብራሪያ የሚገደድበት ስርዓት ከሌለ በቀር ተጠያቂነት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ በዜጎች መብት ለሚያደርሰው ጉዳት በፍርድ ሂደት ለድርጊቱ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፡፡መልካም አስተዳደርበዚህ መርህ መሰረት አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ላገኙ መሪ ደንቦች መገዛት አለበት፡፡ እነዚህም የፍትሀዊነት፣ ምክንያታዊነት፣ ሚዛናዊነትና የግልፅነት መርሆዎችን ያጠቃልላሉ፡፡ አስተዳደራዊ ውሳኔ በህጉ መሰረት መወሰዱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የውሳኔው መሰረት ከቅን ልቦና የመነጨ፣ ለባለጉዳዩ ግልፅ በሆነ አሰራርና መንገድ ያልተወሰደ ካልሆነ በስተቀር የመንግስት አስተዳደር ወደ መልካምነት ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ የአስተዳደር ህግ እነዚህን መርሆዎች እንዲዳብሩ ከማድረግ አንፃር አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለሆነም የህጉ የእድገት ደረጃ የአንድ አገር የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ጠቋሚ መለኪያ ነው ማለት እንችላለን፡፡

የተፈጻሚነቱ ወሰን የአስተዳደር ህግ የመንግስትንና የግለሰብ ግንኙት በሚገዛው የህዝብ አስተዳደር ህግ (Public law) ውስጥ ይመደባል፡፡ ይህም ማለት በሁለት ግለሰቦች ወይም በንግድ ድርጅቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም ሁሉም በመንግስት እና ግለሰብ መካከል የሚፈጠር ግንኙነት በአስተዳደር ህግ ውስጥ አይወድቅም፡፡ ተፈጻሚነቱ የአስተዳደር አካላት በህግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ግዴታ ተጠቅመው ህዝባዊ ተግባራት በሚያከናውኑበት ጊዜ ነው፡፡ ከህግ አውጭው የተሰጣቸውን ውክልና ተጠቅመው ደንብና መመሪያ ሲያወጡ እንዲሁም የግለሰቦችን መብትና ጥቅም የሚነካ አስተዳደራዊ ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ ለአስተዳደር ህግ መርሆዎች ተገዢ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አንድ መስሪያ ቤት ባወጣው መመሪያ ወይም በወሰደው የአስተዳደር ውሳኔ ምክንያት የሚነሳ ክርክር በአስተዳደር ህግ የሚመራ የአስተዳደር ክርክር ነው፡፡ከዚህ በተለየ መልኩ ከግለሰቦች ወይም ከድርጅቶች ጋር በሚመሰርቱት የውል ግንኙነት ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው መደበኛው የውል ህግ እንጂ የአስተዳደር ህግ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የውሉ አይነት በአስተዳደር ውል ውስጥ የሚመደብ ከሆነ የተለዩ የውል ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የኃላፊነታቸው ምንጭ በውል ላይ ካልተመሰረተ ተጠያቂነታቸው የሚወሰነው ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነትን በሚገዙት የፍትሐብሔር ድንጋጌዎች ነው፡፡ሌላው ከተፈፃሚነት ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ህጉ የሚያካትታቸወ ውሳኔ ሰጪ አካላት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ ማለት አስተዳደር የሚመራበት ህግ እንደመሆኑ ፓርላማው በህግ አውጪነት ስልጣኑ በሚያወጣቸው ህጎች ወይም በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ስልጣናቸው በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ መከላከያ ሰራዊትን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ከዚህ ህግ ማእቀፍ ውጭ ናቸው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተዳደር ህግ ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ባሻገር ብቸኛ አገልግሎት አቅራቢ የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች (Public Corporations) ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይም ተፈፃሚነት እያገኘ ነው፡፡ አንድ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ጋር ያለው ግንኙነት ምንም እንኳን በውል ላይ የተመሰረተ ቢሆንም አገልግሎቱን ከማግኘት መብት ጀምሮ እስከ አገልግሎቱ መቋረጥ ድረስ በድርጅቱ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከምንም በላይ ፍትሐዊነታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ድርጅቱ በዋጋ አተማመን እና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎችና ይህንን ተከትሎ የሚያወጣቸው የአሰራር ደንቦችና መመሪያዎች ለራሱ ለብቻው የሚተዉ ሳይሆን በህግ በተለይም በአስተዳደር ህግ ደንቦች መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው የመንግስት ልማት ድርጅቶች እንደ ነጋዴ ድርጅት መታየት የሌለባቸው፡፡በተመሳሳይ መልኩ የመንግስት ቤቶችን የሚያስተዳድሩት የቀበሌ መስተዳድር እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሁለቱም ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በተራ ውል ብቻ የተመሰረተ ቢመስልም ከዚህ ባለፈ በመንግስትና ግለሰብ ግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ መታየት አለበት፡፡ የመንግስት ቤቶችን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንa ‘እንደማንኛውም ባለሃብት ቤቶቹን ለፈለገው ሰው የማከራየት ሕጋዊ መብት’b የለውም፡፡ ይልቅስ በህግ የተቋቋመበትን የቤት እጥረት የማቃለል ዓላማ፤..ለማሳካት የሚችሉ ግልፅ የአሠራር ሥርዓቶችን በመቀየስ የቤት ኪራይ ግልጋሎት የሚሰጥባቸውን መመዘኛዎች በማውጣት መመዘኛውን ለሚያሟሉ ሰዎች በቅደም ተከተል ክፍት ቤት ሲኖረው የማስተናገድ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡’cስለሆነም መንግስት ለዜጎቹ በሚያቀርባቸው አገልግሎቶች የሂደቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ በእርግጥ የአስተዳደር ህግ ተፈፃሚነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሆነ የቀበሌ መስተዳድር አገልግሎታቸውን ለማቋረጥ በቂ የህግ ምክንያት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ከመሆኑም በላይ ውሳኔያቸው ከህገ መንግስቱ የዜጐች መጠለያ የማግኘት መብት አንጻር መቃኘት ይኖርበታል፡፡በመጨረሻ የተፈጻሚነት ወሰኑ ከአስተዳደራዊ ውሳኔ ይዘትና ሂደት አንጻር የራሱ ገደብ እንዳለበት መገንዘብ ያሻል፡፡ አስተዳደር ህግ አካሄድን እንጂ ይዘትን የሚመለከት ህግ አይደለም፡፡ ትኩረቱ ደንብና መመሪያው እንዴት ወጣ? አስተዳደራዊ ውሳኔው እንዴት ተሰጠ? እንጂ የመመሪያው ወይም የውሳኔው ይዘት ትክክለኛ መሆን አለመሆን አይደለም፡፡ ድርጊቱ ትክክለኛ ነበረ ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ላለው የአስተዳደር አካል የሚተው እንጂ በፍርድ ቤት ምላሽ የሚያገኝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል በግብር አወሳሰን ወቅት በህግ ተለይተው የተቀመጡ የተለያዩ ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ የግብር ሰብሳቢው አካል የተወሰነ የገንዘብ መጠን ሊወስን ይችላል፡፡ የአስተዳደር ህግ የግብር አወሳሰኑን ህጋዊነት ወይም ፍትሐዊነት በተመለከተ ካልሆነ በስተቀር በእርግጥ የገንዘቡ መጠን ምን ያህል መሆን አለበት? የሚለውን ጥያቄ ለመዳሰስ ሆነ ለመመለስ ወሰኑ አይፈቅድለትም፡፡

 ንድፈ ሃሳባዊ አቅጣጫዎች።


ንድፈ ሃሳባዊ አቅጣጫዎች።

በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የህግ ሚና ውስብስብ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በመንግስት አስተዳደር ስራ ወይም በአስተዳደራዊ ሂደት ውስጥ ሊኖረው የሚችለው አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ እና ውጤት ተግባራዊ የሆነ ጥናትና ትንተና የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከተግባራዊ መመዘኛው በተጨማሪ ዓይነተኛ ሚና እና ተግባሩን በተመለከተ የሚቀረጽበት ማዕዘን ወይም እይታ በተለያዩ ወገኖች የተለያየ አቋም ተይዞበት ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበት ግን የአስተዳደር ህግ ለብቻው ተነጥሎ የሚጠና የህግ ክፍል ሳይሆን መሰረት ከሆኑት ተጨባጭ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ግንኙነት፤ ግጭትና ስምምነት እንዲሁም መስተጋብራዊ ውጤት አንጻር መታየት ይኖርበታል፡፡
ምንም እንኳን የአስተዳደር ህግን በተመለከተ ጐራ ለይቶ የተቀመጠ ፍንትው ያለ ንድፈ ሀሳብ ባይኖርም ጠቅለል ባለ መልኩሁለት አቅጣጫዎች እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ሃርሎው እና ሮውሊንግ የተባሉ የአስተዳደር ህግ አጥኝዎች እነዚህን ሁለት ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫዎች በመለየትየቀይ መብራት’ (የቁም!) ንድፈ ሀሳብ እናየአረንጓዴ መብራት’ (የእለፍ!) ንድፈ ሀሳብ የሚል ስያሜ በመስጠት የሚያንፀባርቁትንና የሚወክሉትን አቋም በተመለከተ ትንተና አቅርበዋል፡፡a
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው የቁም ንድፈ ሀሳብ በአቀራረቡ ወግ አጥባቂ ሲሆን ቁጥጥርን ዓይነተኛ የአስተዳደር ህግ ሚና አድርጐ ይወስዳል፡፡ ንድፈ ሀሳቡ ከአስተዳደር ህግ መጸነስና መወለድ ጋር አብሮ የዳበረ የኋለኛው ዘመን (traditional) እይታን ያንጸባርቃል፡፡ ይህ ሲባል ግን ታሪካዊ ውልደቱንና አመጣጡን ለማሳየት እንጂ በአሁኑ ወቅት በተግባር የሚገለፅ አቀራረብ እንዳልሆነ ለመጠቆም አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ የተነሳበት ዋነኛ አጀንዳ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ስልጣን በቅጡ መቆጣጠርና በዚህም የዜጐች መብትና ጥቅም እንዳይጣስ መከላከል ነው፡፡ የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናት ከስልጣናቸው ገደብ አልፈው በሚፈፅሙት ድርጊት የተነሳ በዜጐች ላይ በደል እንዳይደርስ ስልጣናቸው እንደፈረስ ልጓም መቆጣጠሪያ መሳሪያ ያስፈልገዋል፡፡
በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት ይህ መሳሪያ የአስተዳደር ህግ ነው፡፡ የቁጥጥር መሳሪያ ከሆኑት መንገዶች አንዱ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ህጋዊት በፍ/ቤቶች የሚታረምበት የአጣሪ ዳኝነት ስርዓት አንዱና ዋነኛው ሲሆን የቁም ንድፈ ሀሳብ /ቤቶች አስተዳደራዊ ተቋማትን የመቆጣጠር ጠንካራ ሚና እንዲኖራቸው በአጽንኦት ይከራከራል፡፡b
የንድፈ ሀሳቡን ዳራ በቅጡ ለመረዳት ምንጩ ከሆነው የነፃ ገበያ የፖለቲካ ፍልስፍና አንፃር መመርመሩ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ እይታ ምርጥ መንግስት ማለት የታቀበ መንግስት ነው፡፡ ፒተር ለይላንድ እና ቴሪ ውድስ ይህንኑ በማጉላት እንዲህ ይላሉ፤
‘የቁም ንድፈ ሀሳብ’ አመጣጡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰፍኖ ከነበረው የነፃ ገበያ ንድፈ ሀሳብ ነው፡፡ ነፃ ገበያ ለግለሰለቦች ነፃነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአንፃሩ ግን የመንግስትን ስልጣን በጥርጣሬ በማየት ውስን አገዛዝን በዋነኛነት ይደግፋል፡፡c
የነፃ ገበያ ስርዓት ነፀብራቅ የሆነው የቁም ንድፈ ሀሳብ የመንግስትን ረጃጅም እጆች ለማሳጠር የአስተዳደር ህግን እንደ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ይጠቀምበታል፡፡ ጠንካራ መንግስት በግለሰቦች እንቅስቃሴ ውስጥ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ ስለሚያስቸግር የግለሰቦች ነፃነት ጠር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በተግባር እንደታየው ግን 19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የመንግስት ስልጣንና ሚና ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እያደገ መጥቷል፡፡ የተለያየ ተግባራትን የሚያከናውኑ የአስተዳደር ተቋማት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት በህግ አውጭው በሚሰጣቸው ስልጣን መሰረት መጠነ ሰፊ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት በታሪክ ሂደት እያደገ የመጣውን የመንግስት ስልጣንና በየጊዜው የሚፈጠሩትን የአስተዳደር ተቋማት ከግለሰቦች ነፃነት ጐን ለጐን አጣጥሞ

መሄድ የሚቻለው በህግ ማዕቀፍ ጠንካራ ቁጥጥር ሲደረግባቸው ነው፡፡

ሁለተኛውን የእለፍ ንድፈ ሀሳብ ያየን እንደሆነ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ለመንግስት ስልጣንና ለአስተዳደር ተቋማት የአረንጓዴ መብራት ማለትም የእለፍ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ በዚህ ንድፈ ሀሳብ መሰረት የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ሚና የመንግስትን ስራ ማቀላጠፍ ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ሲቀር የመንግስት ቢሮክራሲ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይሰራል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ህግ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማነትን ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ አስተዳደር በቁጥጥር ሰበብ እጆቹ የሚታሰሩ ከሆነ ተጨማሪ አስተዳደራዊ በደልን ከማስከተል በቀር ፋይዳ የለውም፡፡
ፖለቲካዊ ዳራውን ያየን እንደሆነ የማህበራዊ ዲሞክራሲ (social democracy) ንድፈ ሀሳብ ነፀብራቅ ነው፡፡d በዚህ ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ መሰረት መንግስት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመሳተፍ አቅም ለሌለው ህብረተሰብ ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት የአስተዳደር ህግ መንገድ ጠራጊነትሚና ሊኖረው ይገባል፡፡
የእለፍ እና የቁም ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫዎች በየፊናቸው የአስተዳደር ህግን ዓይነተኛ ሚና ያንፀባርቃሉ፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያው የማቀብ፤ ሁለተኛው ደግሞ የማሳለጥ ሚናዎችን ይወክላሉ፡፡ ፒተር ኬን ይህንን ሀሳብ እንደሚከተለው በተብራራ መልኩ ይገልጸዋል፡፡
We can think about government as having a complex set of (‘policy’) objectives and about administrative law as both facilitating and constraining the realization of those objectives. Law can facilitate by defining objectives and by creating institutions, conferring powers, and establishing processes for realizing those objectives. Law can constrain by specifying how such institutions must behave in operating such processes and exercising such powers lawfully, fairly, reasonably, and so on. Law as facilitator is concerned primarily with ends; law as constraint is concerned primarily with means to ends.
ከላይ የቀረበው ሀሳብ እንደሚያስረዳንእለፍእናቁምተብለው የተፈረጁት አመለካከቶች ተነጣጥለው የቆሙ አይደሉም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ገፅታው ግምት ውስጥ ሳይገባ ማንኛውም የመንግስት አስተዳደር ስራ የሚሰራው የስልጣን አሰጣጥንና እና መገልገልን በሚመሩ ህጎች እየታገዘ ነው፡፡
የህጉ ምንጮች
የአስተዳደር ህግ የሚመራባቸው መርሆዎች እና ደንቦች ከተለያዩ ምንጮች ይገኛሉ፡፡ የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ የዛችን አገር ፖለቲካዊና ህገመንግስታዊ ስርዓትና አወቃቀር የሚያንጸባርቅና ከዚሁ አንጻር የተቀረጸ እንደመሆኑ እነዚህን ምንጮች ወጥ በሆነ መልኩ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ አጠቀላይ ምልከታ በመነሳት ምንጮቹን እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል፡፡
ህገ መንግሰት
የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ መልክና ቅርጽ ምን እንደሚመስል ለመረዳት መነሻችን የዛች አገር ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነው፡፡ ብዙዎቹ የአስተዳደር ህግ መርሆዎች መሰረታቸው የተተከለው በህገ መንግስት ላይ ከመሆኑም በላይ ወሰንና አፈጻጸማቸው እንዲሁ ለብቻው ተነጥሎ የቆመ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ ተፈጻሚነት የሚያገኘው በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡a
ህግ የመንግስት ስልጣን ዋነኛ ምንጩ በህግ አውጭው የሚወጣው ህግ ሲሆን በአስተዳደር ህግ ውስጥ በተለምዶ ማቋቋሚያ አዋጅ ወይም እናት ህግ እየተባለ ይጠራል፡፡ በአገራችን በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በተዋቀረው ህግ አውጪ አካል የሚወጣው አዋጅb የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን ስልጣን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም ይህ አዋጅ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ በጥልቀት ሊመረምርና ሊተነተን ይገባዋል፡፡
ህግ አውጪው ስልጣን ከመስጠት በተጨማሪ ስልጣኑ ተግባር ላይ የሚውልበትን መንገድና ስርዓት ይደነግጋል፡፡ በስልጣን መገልገል ሂደት ተፈጻሚ የሚሆነው ስነስርዓት አብዛኛውን ጊዜ ስልጣን በሚሰጠው አዋጅ ላይ ይካተታል፡፡ በሌላ መልኩ ህግ አውጪው በሁሉም ስልጣን በተሰጣቸው አካላት ላይ በጠቅላላው ተፈጻሚ የሚሆን ወጥ ደንብ በማስቀመጥ ሁሉን አቀፍ ስርዓት ሊዘረጋ ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ በአሜሪካ ... 1946 . የወጣው የአስተዳደር ስነስርዓት ደንብ (Administrative Procedure Act) ተጠቃሽ ነው፡፡ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ተፈጻሚ የሚሆኑ ደንቦችና ስርዓቶች አስገዳጅነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ስነስርዓቱን የሚጥስ ውሳኔ ጸንቶ የሚቆምበት የህግ መሰረት አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ የስልጣን ምንጭ የሚወሰንበት መንገድ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡
ደንብና መመሪያ
በአገራችን በተለይም በፌደራል መንግስቱ ደረጃ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የተለያዩ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በውክልና በሚተላለፍላቸው ስልጣን መሰረት ደንብና መመሪያ ያወጣሉ፡፡ የእነዚህ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አወጣጥ ስርዓት እንዲሁም ህጋዊነታቸውና ህገ መንግስታዊነታቸው የሚረጋገጥበት መንገድ በህጉ አብይ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በእርግጥ የእያንዳንዱ ደንብና መመሪያ ይዘት ከአስተዳደር ህግ ጥናት ወሰን ውጭ ነው፡፡ ህጉ እንደ ስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያነቱ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ መውጣቱን ማረጋገጥ አይነተኛ ዓላማው ነው፡፡ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያለው ቦታ መቃኘት ያለበትም ከዚሁ ነጥብ አንፃር ነው፡፡ ለህጋዊነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ደንብና መመሪያው ላይ አስገዳጅ ውጤት ኖሯቸው የተደነገጉት ጉዳዮች ስልጣን በሰጠው አዋጅ ስር የተሸፈኑ መሆናቸውን መመርመርን ይጠይቃል፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔዎች
መደበኛ /ቤቶች የስልጣን መገልገልን ህጋዊነትና ፍትሐዊነት በመቆጣጠር ለግለሰቦች መብትና ነፃነት መጠበቅ የሚያበረክቱ አስተዋጽኦ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ /ቤቶች አስተዳደሩ በህግ እንዲመራ እና ለህጋዊነት መርህ ተገዢ እንዲሆን በተጨማሪም በህግ የተሰጠውን ስልጣን በፍትሀዊ መንገድ እንዲገለገል የተለያዩ መለኪያዎችንና መስፈርቶችን በማስቀመጥ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ህገመንግስታዊ ሚናቸው የመልካም አስተዳደር እሴቶች ገንቢ ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የፌደራል እና የክልል መደበኛ ፍርድ ቤቶች በአስተዳደራዊ ክርክር የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ለአስተዳደር ህግ ጥናት ግብዓት ናቸው፡፡ በተለይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው እንደመሆኑ የአስተዳደር ህግን ተግባራዊ አፈጻጸም ለመመዘን ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ከመደበኛ /ቤቶች በተጨማሪ በአስተዳደር ተቋማት ውስጥ ወይም ለብቻቸው ገለልተኛ ሆነው የሚቋቋሙት በተለምዶ የአስተዳደር /ቤት በሚል የሚታወቁት የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative Tribunals) የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ፍትህ ምን እንደሚመስልና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት አጋዥ ምንጮች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ የመደበኛ /ቤት ሆነ የአስተዳደር ጉባዔዎች ውሳኔዎች በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያላቸው ቦታ ውስን ነው፡፡ በየአስተዳደር መስሪያ ቤቱ በየጊዜው በሚሰጡት ውሳኔዎችና በሚወጡት ደንብና መመሪያዎች አማካይነት በዜጋው ላይ የሚፈጸሙት በደሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቢሆንም የፍ/ቤትን ደጃፍ የሚረግጡት ግን በጣት የሚቆጠሩት ናቸው፡፡ ከሚቀርቡት አቤቱታዎች መካከልም በተለያዩ የስነስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ ዳኝነት ሳይታይ አብዛኛዎቹ ወዲያውኑ ውድቅ ይደረጋሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ውሳኔዎቹ አጠቃላዩን የአስተዳደር ሂደት ባህርይ እና አካሄድ ገላጭ ወይም ወካይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡