ንድፈ ሃሳባዊ አቅጣጫዎች።
በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የህግ ሚና ውስብስብ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በመንግስት አስተዳደር ስራ ወይም በአስተዳደራዊ ሂደት ውስጥ ሊኖረው የሚችለው አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ እና ውጤት ተግባራዊ የሆነ ጥናትና ትንተና የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከተግባራዊ መመዘኛው በተጨማሪ ዓይነተኛ ሚና እና ተግባሩን በተመለከተ የሚቀረጽበት ማዕዘን ወይም እይታ በተለያዩ ወገኖች የተለያየ አቋም ተይዞበት ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበት ግን የአስተዳደር ህግ ለብቻው ተነጥሎ የሚጠና የህግ ክፍል ሳይሆን መሰረት ከሆኑት ተጨባጭ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ግንኙነት፤ ግጭትና ስምምነት እንዲሁም መስተጋብራዊ ውጤት አንጻር መታየት ይኖርበታል፡፡
ምንም እንኳን የአስተዳደር ህግን በተመለከተ ጐራ ለይቶ የተቀመጠ ፍንትው ያለ ንድፈ ሀሳብ ባይኖርም ጠቅለል ባለ መልኩ በሁለት አቅጣጫዎች እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ሃርሎው እና ሮውሊንግ የተባሉ የአስተዳደር ህግ አጥኝዎች እነዚህን ሁለት ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫዎች በመለየት ‘የቀይ መብራት’ (የቁም!) ንድፈ ሀሳብ እና ‘የአረንጓዴ መብራት’ (የእለፍ!) ንድፈ ሀሳብ የሚል ስያሜ በመስጠት የሚያንፀባርቁትንና የሚወክሉትን አቋም በተመለከተ ትንተና አቅርበዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው የቁም ንድፈ ሀሳብ በአቀራረቡ ወግ አጥባቂ ሲሆን ቁጥጥርን ዓይነተኛ የአስተዳደር ህግ ሚና አድርጐ ይወስዳል፡፡ ንድፈ ሀሳቡ ከአስተዳደር ህግ መጸነስና መወለድ ጋር አብሮ የዳበረ የኋለኛው ዘመን (traditional) እይታን ያንጸባርቃል፡፡ ይህ ሲባል ግን ታሪካዊ ውልደቱንና አመጣጡን ለማሳየት እንጂ በአሁኑ ወቅት በተግባር የሚገለፅ አቀራረብ እንዳልሆነ ለመጠቆም አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ የተነሳበት ዋነኛ አጀንዳ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ስልጣን በቅጡ መቆጣጠርና በዚህም የዜጐች መብትና ጥቅም እንዳይጣስ መከላከል ነው፡፡ የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናት ከስልጣናቸው ገደብ አልፈው በሚፈፅሙት ድርጊት የተነሳ በዜጐች ላይ በደል እንዳይደርስ ስልጣናቸው እንደፈረስ ልጓም መቆጣጠሪያ መሳሪያ ያስፈልገዋል፡፡
በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት ይህ መሳሪያ የአስተዳደር ህግ ነው፡፡ የቁጥጥር መሳሪያ ከሆኑት መንገዶች አንዱ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ህጋዊት በፍ/ቤቶች የሚታረምበት የአጣሪ ዳኝነት ስርዓት አንዱና ዋነኛው ሲሆን የቁም ንድፈ ሀሳብ ፍ/ቤቶች አስተዳደራዊ ተቋማትን የመቆጣጠር ጠንካራ ሚና እንዲኖራቸው በአጽንኦት ይከራከራል፡፡
የንድፈ ሀሳቡን ዳራ በቅጡ ለመረዳት ምንጩ ከሆነው የነፃ ገበያ የፖለቲካ ፍልስፍና አንፃር መመርመሩ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ እይታ ምርጥ መንግስት ማለት የታቀበ መንግስት ነው፡፡ ፒተር ለይላንድ እና ቴሪ ውድስ ይህንኑ በማጉላት እንዲህ ይላሉ፤
‘የቁም ንድፈ ሀሳብ’ አመጣጡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰፍኖ ከነበረው የነፃ ገበያ ንድፈ ሀሳብ ነው፡፡ ነፃ ገበያ ለግለሰለቦች ነፃነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአንፃሩ ግን የመንግስትን ስልጣን በጥርጣሬ በማየት ውስን አገዛዝን በዋነኛነት ይደግፋል፡፡
የነፃ ገበያ ስርዓት ነፀብራቅ የሆነው የቁም ንድፈ ሀሳብ የመንግስትን ረጃጅም እጆች ለማሳጠር የአስተዳደር ህግን እንደ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ይጠቀምበታል፡፡ ጠንካራ መንግስት በግለሰቦች እንቅስቃሴ ውስጥ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ ስለሚያስቸግር የግለሰቦች ነፃነት ጠር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በተግባር እንደታየው ግን ከ19
ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የመንግስት ስልጣንና ሚና ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እያደገ መጥቷል፡፡ የተለያየ ተግባራትን የሚያከናውኑ የአስተዳደር ተቋማት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት በህግ አውጭው በሚሰጣቸው ስልጣን መሰረት መጠነ ሰፊ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት በታሪክ ሂደት እያደገ የመጣውን የመንግስት ስልጣንና በየጊዜው የሚፈጠሩትን የአስተዳደር ተቋማት ከግለሰቦች ነፃነት ጐን ለጐን አጣጥሞ

መሄድ የሚቻለው በህግ ማዕቀፍ ጠንካራ ቁጥጥር ሲደረግባቸው ነው፡፡
ሁለተኛውን የእለፍ ንድፈ ሀሳብ ያየን እንደሆነ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ለመንግስት ስልጣንና ለአስተዳደር ተቋማት የአረንጓዴ መብራት ማለትም የእለፍ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ በዚህ ንድፈ ሀሳብ መሰረት የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ሚና የመንግስትን ስራ ማቀላጠፍ ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ሲቀር የመንግስት ቢሮክራሲ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይሰራል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ህግ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማነትን ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ አስተዳደር በቁጥጥር ሰበብ እጆቹ የሚታሰሩ ከሆነ ተጨማሪ አስተዳደራዊ በደልን ከማስከተል በቀር ፋይዳ የለውም፡፡
ፖለቲካዊ ዳራውን ያየን እንደሆነ የማህበራዊ ዲሞክራሲ (social democracy) ንድፈ ሀሳብ ነፀብራቅ ነው፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ መሰረት መንግስት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመሳተፍ አቅም ለሌለው ህብረተሰብ ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት የአስተዳደር ህግ የ‘መንገድ ጠራጊነት’ ሚና ሊኖረው ይገባል፡፡
የእለፍ እና የቁም ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫዎች በየፊናቸው የአስተዳደር ህግን ዓይነተኛ ሚና ያንፀባርቃሉ፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያው የማቀብ፤ ሁለተኛው ደግሞ የማሳለጥ ሚናዎችን ይወክላሉ፡፡ ፒተር ኬን ይህንን ሀሳብ እንደሚከተለው በተብራራ መልኩ ይገልጸዋል፡፡
We can think about government as having a complex set of (‘policy’) objectives and about administrative law as both facilitating and constraining the realization of those objectives. Law can facilitate by defining objectives and by creating institutions, conferring powers, and establishing processes for realizing those objectives. Law can constrain by specifying how such institutions must behave in operating such processes and exercising such powers lawfully, fairly, reasonably, and so on. Law as facilitator is concerned primarily with ends; law as constraint is concerned primarily with means to ends.
ከላይ የቀረበው ሀሳብ እንደሚያስረዳን ‘
እለፍ’
እና ‘
ቁም’
ተብለው የተፈረጁት አመለካከቶች ተነጣጥለው የቆሙ አይደሉም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ገፅታው ግምት ውስጥ ሳይገባ ማንኛውም የመንግስት አስተዳደር ስራ የሚሰራው የስልጣን አሰጣጥንና እና መገልገልን በሚመሩ ህጎች እየታገዘ ነው፡፡
የአስተዳደር ህግ የሚመራባቸው መርሆዎች እና ደንቦች ከተለያዩ ምንጮች ይገኛሉ፡፡ የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ የዛችን አገር ፖለቲካዊና ህገ–መንግስታዊ ስርዓትና አወቃቀር የሚያንጸባርቅና ከዚሁ አንጻር የተቀረጸ እንደመሆኑ እነዚህን ምንጮች ወጥ በሆነ መልኩ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ከአጠቀላይ ምልከታ በመነሳት ምንጮቹን እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል፡፡
የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ መልክና ቅርጽ ምን እንደሚመስል ለመረዳት መነሻችን የዛች አገር ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነው፡፡ ብዙዎቹ የአስተዳደር ህግ መርሆዎች መሰረታቸው የተተከለው በህገ መንግስት ላይ ከመሆኑም በላይ ወሰንና አፈጻጸማቸው እንዲሁ ለብቻው ተነጥሎ የቆመ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ ተፈጻሚነት የሚያገኘው በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡
ህግ የመንግስት ስልጣን ዋነኛ ምንጩ በህግ አውጭው የሚወጣው ህግ ሲሆን በአስተዳደር ህግ ውስጥ በተለምዶ ‘ማቋቋሚያ አዋጅ’ ወይም ‘እናት ህግ’ እየተባለ ይጠራል፡፡ በአገራችን በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በተዋቀረው ህግ አውጪ አካል የሚወጣው አዋጅ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶችን ስልጣን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም ይህ አዋጅ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ በጥልቀት ሊመረምርና ሊተነተን ይገባዋል፡፡
ህግ አውጪው ስልጣን ከመስጠት በተጨማሪ ስልጣኑ ተግባር ላይ የሚውልበትን መንገድና ስርዓት ይደነግጋል፡፡ በስልጣን መገልገል ሂደት ተፈጻሚ የሚሆነው ስነ–ስርዓት አብዛኛውን ጊዜ ስልጣን በሚሰጠው አዋጅ ላይ ይካተታል፡፡ በሌላ መልኩ ህግ አውጪው በሁሉም ስልጣን በተሰጣቸው አካላት ላይ በጠቅላላው ተፈጻሚ የሚሆን ወጥ ደንብ በማስቀመጥ ሁሉን አቀፍ ስርዓት ሊዘረጋ ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም የወጣው የአስተዳደር ስነ–ስርዓት ደንብ (Administrative Procedure Act) ተጠቃሽ ነው፡፡ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ተፈጻሚ የሚሆኑ ደንቦችና ስርዓቶች አስገዳጅነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ስነ–ስርዓቱን የሚጥስ ውሳኔ ጸንቶ የሚቆምበት የህግ መሰረት አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ የስልጣን ምንጭ የሚወሰንበት መንገድ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡
በአገራችን በተለይም በፌደራል መንግስቱ ደረጃ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የተለያዩ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በውክልና በሚተላለፍላቸው ስልጣን መሰረት ደንብና መመሪያ ያወጣሉ፡፡ የእነዚህ አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አወጣጥ ስርዓት እንዲሁም ህጋዊነታቸውና ህገ መንግስታዊነታቸው የሚረጋገጥበት መንገድ በህጉ አብይ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በእርግጥ የእያንዳንዱ ደንብና መመሪያ ይዘት ከአስተዳደር ህግ ጥናት ወሰን ውጭ ነው፡፡ ህጉ እንደ ስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያነቱ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ መውጣቱን ማረጋገጥ አይነተኛ ዓላማው ነው፡፡ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያለው ቦታ መቃኘት ያለበትም ከዚሁ ነጥብ አንፃር ነው፡፡ ለህጋዊነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ደንብና መመሪያው ላይ አስገዳጅ ውጤት ኖሯቸው የተደነገጉት ጉዳዮች ስልጣን በሰጠው አዋጅ ስር የተሸፈኑ መሆናቸውን መመርመርን ይጠይቃል፡፡
መደበኛ ፍ/ቤቶች የስልጣን መገልገልን ህጋዊነትና ፍትሐዊነት በመቆጣጠር ለግለሰቦች መብትና ነፃነት መጠበቅ የሚያበረክቱ አስተዋጽኦ በአስተዳደር ህግ ጥናት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ፍ/ቤቶች አስተዳደሩ በህግ እንዲመራ እና ለህጋዊነት መርህ ተገዢ እንዲሆን በተጨማሪም በህግ የተሰጠውን ስልጣን በፍትሀዊ መንገድ እንዲገለገል የተለያዩ መለኪያዎችንና መስፈርቶችን በማስቀመጥ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ህገ–መንግስታዊ ሚናቸው የመልካም አስተዳደር እሴቶች ገንቢ ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የፌደራል እና የክልል መደበኛ ፍርድ ቤቶች በአስተዳደራዊ ክርክር የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ለአስተዳደር ህግ ጥናት ግብዓት ናቸው፡፡ በተለይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው እንደመሆኑ የአስተዳደር ህግን ተግባራዊ አፈጻጸም ለመመዘን ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ከመደበኛ ፍ/ቤቶች በተጨማሪ በአስተዳደር ተቋማት ውስጥ ወይም ለብቻቸው ገለልተኛ ሆነው የሚቋቋሙት በተለምዶ ‘የአስተዳደር ፍ/ቤት’ በሚል የሚታወቁት የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative Tribunals) የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የአንዲት አገር የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ፍትህ ምን እንደሚመስልና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት አጋዥ ምንጮች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ የመደበኛ ፍ/ቤት ሆነ የአስተዳደር ጉባዔዎች ውሳኔዎች በአስተዳደር ህግ ውስጥ ያላቸው ቦታ ውስን ነው፡፡ በየአስተዳደር መስሪያ ቤቱ በየጊዜው በሚሰጡት ውሳኔዎችና በሚወጡት ደንብና መመሪያዎች አማካይነት በዜጋው ላይ የሚፈጸሙት በደሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቢሆንም የፍ/ቤትን ደጃፍ የሚረግጡት ግን በጣት የሚቆጠሩት ናቸው፡፡ ከሚቀርቡት አቤቱታዎች መካከልም በተለያዩ የስነ–ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ ዳኝነት ሳይታይ አብዛኛዎቹ ወዲያውኑ ውድቅ ይደረጋሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ውሳኔዎቹ አጠቃላዩን የአስተዳደር ሂደት ባህርይ እና አካሄድ ገላጭ ወይም ወካይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡


Like this:
Like Loading...
Related
You must be logged in to post a comment.