የፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት


የፍርድ ቤቶች የአጣሪ ዳኝነት

ስልጣንየዳኝነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 79/1/ አጣሪ ዳኝነትን እንደሚጨምር አይጠቁምም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ የፌደራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ከክልሎች ውክልና ጋር በተያያዘ በስም ቢጠቀሱም የስልጣናቸው ምንጭ ህገ መንግስቱ ሳይሆን የተወካዮች ም/ቤት የሚያወጣው ህግ እንደሆነ በአንቀጽ 78/2/ ተመልክቷል፡፡ በአንጻሩ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ የሚመነጨው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን ያላቸው አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ህጋዊነት ለማጣራት ያስችለዋል፡፡ ይህ ስልጣን ከሁሉም የፌደራልና የክልል ፌደራል ፍርድ ቤቶች (የክልል የሰበር ችሎቶችን ሳይጨምር)በዓይነቱ የተለየና ብቸኛ ነው፡፡የፌደራል ፍ/ቤቶችመደበኛ ፍርድ ቤቶች የስልጣንን ህጋዊነት በሁለት ዓይነት መንገድ ይቆጣጠራሉ፤ በመደበኛ የፍትሐብሔር ክስ እና በአስተዳደራዊ ይግባኝ፡፡ መንግስት ተከራካሪ በሚሆንባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በርካታ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በተለይም ከውል ውጪ ኃላፊነት፣ ከንብረት ህግ እና በከፊል ከውል ህግ የሚመዘዙ በርካታ የህጋዊነት ጥያቄዎች በተዘዋዋሪም ቢሆን አስተዳደሩ ለህግ እንዲገዛ ያስገዱዱታል፡፡ ፍ/ቤቶች ጠቅላላ ከሆነው መደበኛ ስልጣናቸው በተጨማሪ የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት በይግባኝ እንዲያጣሩ በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፍሬ ነገርና በህግ ጉዳይ ላይ የሚፈቀድ ይግባኝ ከዜጋው መብት አንጻር ከአጣሪ ዳኝነት የበለጠ ጠቀሜታ አለው፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ ነገሩን እንደ አዲስ የማየትና ክርክሩ ከተቋጨ በኋላ በራሱ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የተለጠጠ ስልጣን ያጎናጽፈዋል፡፡ አጣሪ ዳኝነት ግን ህጋዊነትን ከማጣራት አይዘልም፡፡ የአስተዳደራዊ ውሳኔን በመቃወም ለፌደራል ፍ/ቤቶች ይግባኝ የማቅረብ መብት ከሚፈቅዱ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትመረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ መረጃ ተጠይቆ መረጃውን የያዘው አካል በመከልከሉ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ ከቀረበ በኋላ እንባ ጠባቂው በሚሰጠው ውሳኔ ላይaየአካባቢ ተቆጣጣሪዎች በሚሰጡት ውሳኔ እንዲሁም እንዲሁም በአካባቢ ላይ የደረሰ ጉዳትን አስመልክቶ ለአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አቤቱታ ቀርቦ ሚኒስቴሩ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ bየፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትከጥራት ጋር በተያያዘ ቡና የተያዘበት ወይም መጋዘኑ የታሸገበት ሰው ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ወይ አግባብ ላለው የክልል መንግስት አካል ቅሬታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣcየጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚነሳ ክርክርdለሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ አቅራቢነት፣ ላኪነት ወይም አገልግሎት ሰጪነት የብቃት ማረጋገጫ ማመልከቻ ውድቅ ከተደረገ የህግ አተረጓጎምን በተመለከተ ወይም ተፈቅዶለት በዚህ ንግድ የተሰማራ ሰው ከጥራት ጋር በተያያዘ ሰሊጥ ወይም ነጭ ቦሎቄ ተይዞበት ለሚኒስትሩ ወይም አግባብ ላለው የክልል መንግስት አቤቱታ አቅርቦ ተቀባይነት ካጣeየጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት የቀረበ ማመልከቻ ተቀባይነት እንዲያጣ ወይም ፈቃድ የተሰጠው ጠበቃ በዲሲፕሊን ጥፋት ምክንያት ቅጣት በመጣል በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የተወሰደ እርምጃ (በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ)fየሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበር ምዝገባ ባለመፍቀድ እንዲሁም ለስራ ውል መታገድ በቂ ምክንያት አለመኖሩን በመግለጽ በሚሰጠው ውሳኔ እና የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወምgየዕፅዋት አዳቃዮች መብት መስጠትን፣ መከልከልን፣ መሰረዝን ወይም መገደብን በተመለከተ በሚሰጥ ውሳኔ ላይhየምርት ገበያ ባለስልጣን በሚሰጣቸው በአዋጁ በተመለከቱ ውሳኔዎችiየፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ውድቅ በማድረግ ወይም በመሰረዝ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚሰጥ ውሳኔjየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔ እንዲሁም ባንኩ የሾመው ሞግዚት በሚያስተላልፈው ውሳኔkየኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ፈቃድ በመሰረዝ በሚሰጠው ውሳኔlየፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትየፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን በቀጥታ ከህገ መንግስቱ ይመነጫል፡፡ ሆኖም የስልጣኑን ወሰን የሚያሰምረው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ የአማርኛውና እንግሊዝኛው ቅጂ ግልጽ መፋለስ ይታይበታል፡፡ በአማርኛው ንባብ የሰበር ችሎት መሰረታዊ ‘የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ’ የማረም ስልጣን ይኖረዋል፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ) የእንግሊዝኛው ቅጂ ደግሞ Over any final court decision የሚል አገላላጽ በመጠቀም ስልጣኑን ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይገድበዋል፡፡የድንጋጌውን ይዘት ዝርዝር የሚወስነው ህግ ከእንግሊዝኛው ቅጂ ጋር ይስማማል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1988 አንቀጽ 10 የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስልጣን የሚያገኝባቸው ሶስት ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም፤የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮችየፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮችየክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት መደበኛ ችሎት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮችበሶስቱም ጉዳዮች በውሳኔ ሰጭነት የተጠቀሱት ተቋማት መደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ረ ህገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ ሀ የእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ court የሚለው ቃል እንዲሁ ይህንኑ ሀሳብ ያንጸባርቃል፡፡ ሆኖም የአማርኛው ንባብ ውሳኔ ሰጭውን በዝምታ አልፎታል፡፡ ላይ ላዩን ሲታይ ዝምታው ለህገ መንግስታዊ ትርጉም በር የከፈተ አይመስልም፡፡ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ የሚለው አገላለጽ ፍርድ ቤትን ታሳቢ አድርጓል ቢባል ብዙዎችን ያስማማል፡፡ሆኖም ችግሩ ከቋንቋ አጠቃቀም ያልዘለለ የሚመስለው የአንቀጽ 80/3/ ሀ ድንጋጌ በተግባር ህገ መንግስታዊ ጥያቄ አስነስቶ የሰበር ችሎትን የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አስፍቶታል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 43511m ከአዋጅ ውጪ የተወረሱ ንብረቶችን በተመለከተ ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጠው የፕራይቬይታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ በቀጥታ በሰበር እንዲታይ አቤቱታ ቢቀርብም አጣሪ ችሎቱ ጉዳዩ አስተዳደራዊ መሆኑን በመጠቆም ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሆኖም በመዝገቡ ላይ አመልካች ሆነው የቀረቡት አቤቱታ አቅራቢዎች የውሳኔውን ህገ መንግስታዊነት በመሞገት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ አቤቱታ አስገቡ፡፡ አጣሪውም ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ የመጨረሻ አማራጫቸውን በመጠቀም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አመለከቱ፡፡ ም/ቤቱ የችሎቱን ስልጣን በማረጋገጥ መዝገቡን ወደ ሰበር ችሎት መለሰው፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቦርዱን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው በማረጋገጥ የተሰጠው ይህ የም/ቤቱ ውሳኔ ‘የመጨረሻ ውሳኔ’ በሚል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ ላይ የተቀመጠውን አገላለጽ ከእንግሊዝኛ ቅጂ ፍጹም የተለየ ይዘትና መልዕክት ሰጥቶታል፡፡ በውጤቱም ከፍርድ ቤት ውጭ ያሉ ከፊል የዳኝነት አካላት ላይ የሰበር ችሎት የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል፡፡የም/ቤቱ ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ስር ነቀልና መሰረታዊ ነው፡፡ የስር ፍ/ቤቶችን የህግ ስህተት በማረም ብቻ ተወስኖ የነበረው የሰበር ችሎት በም/ቤቱ ‘በተጨመረለት’ ስልጣን ከፊል ዳኝነታዊ ስልጣን የተሰጣቸው የአስተዳደር አካላት የሚያስተላልፉትን ውሳኔ ጭምር የማረም የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ችሎቱም ዳኝነታዊ የአስተዳደር ውሳኔዎችን ማረም ህገ መንግስታዊ ሚናው እንደሆነ በሌሎች ሁለት መዝገቦች በሰጣቸው ውሳኔዎች በተግባር አረጋግጧል፡፡በሰ/መ/ቁ. 92546n የድሮው ፍትሕ ሚኒስቴር የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የዲሲፕሊን ውሳኔ በቀጥታ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ተሸሯል፡፡ አቤቱታ አቅራቢው በሚኒስትሩ የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደው በዓቃቤ ህግ ላይ ሲሆን ጉዳዩ በሰበር ችሎት ከመስተናገዱ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት አልታየም፡፡ በመዝገቡ ላይ የችሎቱ የዳኝነት ስልጣን አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ባይወጣም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ ሀ እና አዋጅ ቁ. 25/88 አንቀጽ 10 ተጠቅሶ የቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ መቀበሉ ሲታይ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣኑ ጠንካራ መሰረት እየያዘ እንደመጣ አስረጂ ነው፡፡ በሰ/መ/ቁ. 61221 ቅጽ 14o የተያዘው አቋም ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ በዚህ መዝገብ በሰፈረው የህግ ትርጉም በፍርድ ቤት እንዳይታዩ በመጨረሻ ማሰሪያ ድንጋጌ (finality clause) ገደብ የተደረገባቸው ውሳኔዎች ሳይቀር በችሎቱ የአጣሪ ዳኝነት ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ ጉዳዩ የታየው አዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 ከመውጣታቸው በፊት ሲሆን ቀድሞ በነበሩት የጡረታ ህጎች የማህበራዊ ዋስትና ጉባኤ ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ በይግባኝ ሆነ በቀጥታ ክስ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሊታይ አይችልም፡፡በሰ/መ/ቁ. 61221 የሰበር አቤቱታ የቀረበው የጉባዔውን የመጨረሻ ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ ሆኖም በችሎቱ የዳኝነት ስልጣን ላይ በተጠሪ በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ የስልጣን ምንጭ አከራካሪ ጭብጥ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ይህንን በማስመልከት ህገ መንግስቱን እና አዋጅ ቁ. 25/88 በማጣቀስ የሚከተለው የህግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ስራ ላይ በነበረው ሕግ አግባብ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ከተባለ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተመለከተው አግባብ ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ ከማቅረብ የሚከለክል ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡የከተማ ፍ/ቤቶችበአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ የተቋቋሙት የከተማ ፍርድ ቤቶች በውስን ጉዳዮች ላይ ቢሆንም የማይናቅ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አላቸው፡፡ ስልጣናቸውን በሚወስኑት ህጎች ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትp በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአጣሪ ዳኝነት የሚታዩ ናቸው፡፡የከተማውን መሪ ፕላን አፈጻጸም የሚመለከት የይዞታ ባለመብትነት፣ የፈቃድ አሰጣጥ ወይም የቦታ አጠቃቀምን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችከከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችበየከተሞቹ ቻርተር ላይ በተመለከቱት የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ክሶችየከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በከተማው አስተዳደር ባለቤትነት ስር ያሉ ተቋማት የሚገቧቸውን አስተዳደራዊ ውሎች በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮችበከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ወይም በስሩ ባሉ ተቋማት መካከል የሚነሱ ክርክሮችየከተማው አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ቤቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችበህግ ከተሰጣቸው የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን በተጨማሪ በከፊል ጉዳዮች አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በይግባኝ ያያሉ፡፡ ለምሳሌ የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ በሚሰጠው ውሳኔq የመጀመሪያና የይግባኝ ስልጣን አላቸው፡፡የከተማ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ክልል በህጉ ላይ በወጉ አልተሰመረም፡፡ ህግ አውጭው ‘በተመለከተ…በተያያዘ…’ በሚል የተጠቀመው አገላለጽ መብት ጠያቂውን ሆነ ፍርድ ቤቶችን ያደናግራል፡፡ የዳኝነት ስልጣን ሊወሰን የሚገባው በክስ ምክንያት፣ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው መፍትሄ ወይም በተከራካሪዎች ማንነት ነው፡፡ ለምሳሌ የይዞታ ባለመብትነትን በተመለከተ እንዲሁም ከአስፈፃሚ አካላት የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች እንደ ሁኔታው በፌደራል ወይም በከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር ይወድቃሉ፡፡ ይዞታን የሚመለከት ክስ በሁከት ይወገድልኝ ወይም በመፋለም ክስ አሊያም ደግሞ በይዞታ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ በመጠየቅ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከግንባታ ፈቃድ ወይም ስም ከማዛወር አስተዳደራዊ ግዴታ ጋር በተያያዘም ይዞታን የሚመለከት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ከዚህ አንጻር በደፈናው ‘በተመለከተ…’ በሚል የተደለደለው የዳኝነት ስልጣን የመደበኛ እና የከተማ ፍ/ቤቶችን ድርሻ በአግባቡ አይለይም፡፡ህጉ ግልጽነት ቢጎድለውም ከሰበር ችሎት አካሄድ እና የህግ አውጭው ሀሳብ በመነሳት የከተማ ፍ/ቤቶች መደበኛ የፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣን እንዳልተሰጣቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ህግ አውጭው እነዚህን ፍ/ቤቶች ሲያቋቁም ከተወሰኑት በግልፅ ከተነገሩት በስተቀር መደበኛውን የፍትሐብሔር ዳኝነት አላስተላለፈላቸውም፡፡ የሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች ያንጸባረቀው አቋም ከዚህ ሀሳብ ጋር ይስማማል፡፡ ይህ ከተባለ በኋላ ግን ከላይ በቀረበው ዝርዝር ውስጥ ህግ አውጭው የወሰነው የዳኝነት ስልጣን ምን መልክ እንዳለው መለየት ያስፈልጋል፡፡ራሱን የቻለ የአስተዳደር ህግ ስርዓት ባላቸው አገራት በፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮች ሶስት ዓይነት ናቸው፤ የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እና የአስተዳደር፡፡ በፈረንሳይ የአስተዳደር ክርክሮች ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ተለይተው በተቋቋሙ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች አማካይነት ይዳኛሉ፡፡ በጀርመን ራሱን ችሎ በተለይ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ይታያሉ፡፡ ከስልጣን ክፍፍል አንጻር መደባቸው ሲታይ የአስተዳደር ፍ/ቤቶች በፈረንሳይ በስራ አስፈፃሚው ስር የሚገኙ ሲሆን በጀርመን ግን በዳኝነት አካሉ የታቀፉ ናቸው፡፡ በእንግሊዝ የፍትሐብሔር ክርክሮችን የሚያስተናግዱት መደበኛ ፍ/ቤቶች የአስተዳደር ክርክሮችንም ደርበው ይዳኛሉ፡፡ በእርግጥ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች የሚቀርቡት ለከፍተኛው ፍ/ቤት ቢሆንም ፍ/ቤቱ ራሱን የቻለ የተለየ መዋቅር የለውም፡፡ በሶስቱም አገራት በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚካሄዱ ክርክሮች የሚዳኙበት መንገድ ቢለያያም አንድ ነገር ያመሳስላቸዋል፡፡ ይኸውም የዳኝነት ስልጣናቸው ዓይነት አጣሪነት (supervisory) ነው፡፡ የዚህ ስልጣን ወሰን የአስተዳደሩን ተግባራት ህጋዊነት ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ያለፉ የፍትሐብሔር ክርክሮችን መደበኛ ፍ/ቤቶች ይረከባሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የአስተዳደር ተቋም ከህግ የመነጨ ስልጣኑን በመጠቀም እርምጃ ሲወስድ ክርክሩ በአጣሪነት ዳኝነት ስር ይወድቃል፡፡ እንደማንኛውም ግለሰብ በሚፈጽማቸው የግል ተግባራት ሲከሰስ (ለምሳሌ የተቋሙ መኪና በአካል ወይም ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት ካሳ ሲጠየቅ) ደግሞ መደበኛ ፍ/ቤቶች በፍትሐብሔር የዳኝነት ስልጣናቸው ያዩታል፡፡በከተማ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ስር ከተዘረዘሩት መካከል የይዞታ ባለመብትነትን በምሳሌነት ብንወስድ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ጉዳዩ የሚታይበት ፍ/ቤት የሚለየው በክሱ ይዘት ነው፡፡ ከፍትሐብሔር ውጭ በአስተዳደሩ ላይ ሊቀርብ የሚችለው ክስ ህጋዊነት የሚጣራበት ክስ ነው፡፡ ይህም የሚያደርሰን መደምደሚያ የከተማ ፍርድ ቤቶች በህግ የተወሰነላቸው የዳኝነት ስልጣን ዓይነት የአጣሪ ዳኝነት (judicial review) ስልጣን እንደሆነ ነው፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.