
የስነ ስርዓት ፦
ጉድለት የአስተዳደር ህግ ከይዘት (ውሳኔ) ይልቅ በስነ-ስርዓት (የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት) ላይ የሚያተኩር የህግ ክፍል ስለመሆኑ ከዚህ በፊት ተገልጿል፡፡ የውሳኔ አሰጣጥ ፍትሐዊነት ሲረጋገጥ የአስተዳደር ፍትህ ይሰፍናል፡፡ ህግ አውጭው አንድ ድርጊት ከመፈጸሙ ወይም ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ወይም ስነ-ስርዓቶች በግልጽ ከደነገገ በስልጣኑ ተጠቅሞ እርምጃ የሚወስድ አካል መሟላታቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ በህግ የተደነገገ የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ፍርድ ቤቶች ሆኑ ውሳኔ ሰጪዎች ሊከተሉት የሚገባ አስገዳጅ ደንብ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት ውሳኔ በህግ ፊት ዋጋ ወይም ውጤት ሊኖረው አይገባም፡፡ በእንግሊዝ፣ አሜሪካና የእነሱን የህግ ስርዓት በሚከተሉ አገራት የሚገኙ ፍ/ቤቶች በግልጽ ከሚደነገገው የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ውጭ የግለሰብን መብትና ጥቅም ሊነካ የሚችል ዳኝነታዊ ባህርይ ያለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በህግ ባይቀመጥም እንኳን ፍትሐዊ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መርሆዎችን ተፈፃሚ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም ስልጣን በሰጠው አዋጅ ላይ ባይጠቀስም በአስተዳደራዊ ውሳኔ መብቱ የሚነካ ወገን ከውሳኔው በፊት ራሱን የመከላከል ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ውሳኔ ሰጪውም በተከራካሪዎች የቀረበውን ማስረጃና ህጉን መሰረት አድርጎ ያለ አድልዎ ገለልተኛ ሆኖ ፍትሐዊ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ የገንዘብ፣ በዝምድና አሊያም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ነገር ግምት ውስጥ ገብቶ የተሰጠ ውሳኔ የተዛባና በህግ ፊት ዋጋ የሌለው ውሳኔ ነው፡፡

You must be logged in to post a comment.