አዋጅ ቁጥር 668/2002
የሙስና ወንጀልን የሚመለከቱ ሕጎች
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት
አንቀጽ 55 (1)
የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002”
ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፦
‘‘ሀብት‘‘ ማለት ማንኛውም የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ወይም ግዙፍነት ያለው ወይም የሌለው ንብረት ሲሆን የመሬት ይዞታን እና ዕዳን ይጨምራል፤
“ኮሚሽን” ማለት የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ነው፤
‘‘የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል” ማለት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በመንግስት የልማት ድርጅት የስነ-ምግባር ሁኔታን የሚያስተባብርና የሚያማክር አካል ነው፤
‘‘ተሿሚ” ማለት የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡-
የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ ምክትል ሚኒስትሮችን፣ ኮሚሽነሮችን፣ ምክትል ኮሚሽነሮችን፣ ዋና ዳይሬክተሮችንና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮችን፤
የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ከንቲባዎችንና ሌሎች ተሿሚዎችን፤
የመደበኛና የከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶችን፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችንና ዳኞችን፤
የመከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ ተሿሚዎችን፤
አምባሳደሮችን፣ የቆንስላዎችና የሌሎች የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ኃላፊዎችን፤
ዋና ኦዲተርንና ምክትል ዋና ኦዲተርን፤
የብሔራዊ ባንክ ገዥና ምክትል ገዢን፤
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን፣ ሥራ አስኪያጆችንና ምክትል ሥራ አስኪያጆችን፤
የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ፕሬዝዳንቶችንና ምክትል ፕሬዝዳንቶችን።
‘‘ተመራጭ” ማለት የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡-
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሎችን፤
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባሎችን፤ እና
የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ምክር ቤቶች አባሎችን።
‘‘የመንግሥት ሠራተኛ” ማለት የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡-
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመምሪያ ኃላፊነት፣ የዳይሬክተርነት፣ የአገልግሎት ኃላፊነትና ከነዚህ ተመጣጣኝና በላይ ደረጃ ያላቸው ሠራተኞችን፤
የተሿሚዎች አማካሪዎችን፤
ፈቃድ የመስጠት፣ የመቶጣጠር ወይም ግብር የመሰብሰብ ሥራ የሚያከናውኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን፣ ዐቃቤ ሕጎችን፣ መርማሪዎችን፣ የትራፊክ ፖሊሶችን፣ እና
ኮሚሽኑ በሚያወጣው መመሪያ ተለይተው የሚወስኑ ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞችን።
‘‘ቤተሰብ” ማለት የተሿሚ፣ የተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የትዳር ጓደኛ ወይም በሥሩ የሚተዳደር ዕድሜው 18 ዓመት ያልሞላ ልጅ ሲሆን ጋብቻ ሳይፈጽም እንደ ባልና ሚስት አብሮ የሚኖር ሰውን እና የጉዲፈቻ ልጅን ይጨምራል፤
‘‘የቅርብ ዘመድ” ማለት የተሿሚ፣ የተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ወላጆችን፣ ተወላጆችን፣ እህቶችን፣ ወንድሞችን እና ሌሎች እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያላቸው ሰዎችን ያጠቃልላል፤
‘‘የመንግስት መስርያ ቤት” ማለት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግስት በጀት የሚተዳደርና የህግ አውጪነት፣ የዳኝነት እና ወይም አስፈጻሚነት የመንግስት ስራዎች የሚከናወኑበት ማናቸውም መስርያ ቤት ነው፤
‘‘የመንግስት ልማት ድርጅት” ማለት የባለቤትነት ድርሻ በሙሉ ወይም በከፊል ያለበት ማንኛውም የመንግስት የልማት ድርጅት ወይም የአክሲዮን ኩባንያ ነው፤
‘‘ሰው“ ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤
ማንኛውም በወንድ ዖታ የተገለጸ አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡
የተፈጻሚነት ወሰን
ይህ አዋጅ በፌዴራል መንግሥት እና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግስት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ክፍል ሁለት
ሀብትን ስለማሳወቅና ስለማስመዝገብ
የማስመዝገብ ግዴታ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ፡-
በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር የሚገኝ ሀብትን፣ እና
የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጮች፣ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ አለበት፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት ሀብቱን የሚያስመዘግብ ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የራሱንና የቤተሰቡን ሀብትና የገቢ ምንጮች ለየብቻ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ ቅጽ ላይ በመሙላት ትክክለኛነቱን በፊርማው ያረጋግጣል።
በምዝገባ ስለማይካተት ሀብት
የዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ድንጋጌ ቢኖርም የሚከተሉት ሀብቶች አይመዘገቡም፡-
በውርስ ተገኝቶ በጋራ የተያዘና ለወራሾቹ የግል አገልግሎት የሚውል ንብረት፤
የቤት እቃዎችና የግል መገልገያዎች፤
ከጡረታ የሚገኝ ገቢ፡፡
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1//ሀ/ መሠረት በጋራ የተያዘ ንብረት በወራሾች መካከል እንደተከፋፈለ ድርሻውን አሳውቆ ማስመዝገብ አለበት፡፡
ስለመዝጋቢው አካል
የተሿሚዎችን፣ የተመራጮችንና የመንግሥት ሠራተኞችን ሃብት የሚመዘግበው ኮሚሽኑ ይሆናል፡፡
ኮሚሽኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የተሿሚዎችን፣ የተመራጮችን ወይም የመንግሥት ሠራተኞችን ሃብት እንዲመዘግብ እንደሁኔታው በሙሉ ወይም በከፊል የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍልን ሊወክል ይችላል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /2/ መሠረት ውክልና የተሰጠው እያንዳንዱ የሥነ- ምግባር መከታተያ ክፍል በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ /2/ መሠረት የቀረበለትን የሃብት ማስመዝገቢያ ስነድ ምዝገባው በተደረገ በ30 ቀናት ውስጥ ለኮሚሽኑ ያስተላልፋል።
ኮሚሽኑ በዚህ አንቀጽ መሠረት የተከናወኑ የሀብት ምዝገባ ሰነዶች ጠባቂ ሆኖ ያገለግላል። ሃብታቸውን ላስመዘገቡ ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች የምዝገባ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡
ምዝገባ ስለሚካሄድበት ጊዜ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሠራተኛ ይህ አዋጅ ስራ ላይ ከዋለበት ከስድስት ወር በኋላ ባለው ስድስት ወር ውስጥ ሀብቱን ማሳወቅና ማስመዝገብ አለበት፡፡
ማንኛውም አዲስ ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሠራተኛ ሀብቱን የሚያሳውቀውና የሚያስመዘግበው ከተሾመበት፣ ከተመረጠረበት ወይም ከተቀጠረበት ቀን ጀምሮ በ45 ውስጥ ነው፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ ወይም /2/ መሠረት ሀብቱን ያስመዘገበ ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ከዚያ በኋላ ሀብቱን የሚያሳውቀውና የሚያስመዘግበው በየሁለት ዓመቱ ሆኖ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በ30 ቀናት ውስጥ ይሆናል፡፡
የምዝገባ ጊዜን ስለማራዘም
የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምለት የሚጠይቅ ሰው ምዝገባውን ማራዘም ያስፈለገበትን ምክንያት በጽሑፍ በመግለጽ የምዝገባ ጊዜው በተጠናቀቀ በአምስት ቀናት ውስጥ ለኮሚሽኑ ወይም ለሚመለከተው የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ማመልከት ይችላል።
ኮሚሽኑ ወይም ጉዳዩ የሚመለከተው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት የቀረበለት ጥያቄ በበቂ ምክንያት የተደገፈ ሆኖ ሲያገኘው የምዝገባውን ጊዜ ለአንድ ጊዜ እስከ 30 ቀናት ሊያራዝም ይችላል።
የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምለት ለሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ የተደረገበት አመልካች ውሳኔው በደረሰው አምስት ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለኮሚሽኑ ሊያቀርብ ይችላል። ኮሚሽኑ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻ ይሆናል፡፡
ዘግይቶ ስለማስመዝገብ
በመደበኛው ወይም በተራዘመለት የማስመዝገቢያ ጊዜ ውስጥ ሀብቱን ያላስመዘገበ ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ብር አንድ ሺ መቀጫ ከፍሎ በ30 ቀናት ውስጥ ሊያስመዘግብ ይችላል፡፡
ከስንብት በኋላ ስለሚከተሉ ግዴታዎች
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በጡረታ ሲገለል ወይም በማንኛውም ምክንያት አገልግሎቱን ሲያቋርጥ ሁበቱን በ30 ቀናት ውስጥ ለኮሚሽኑ ወይም ለሚመለከተው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል እንዲሁም ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ለኮሚሽኑ ማሳወቅ አለበት፡፡
የምዝገባን ትክክለኛነት ስለማረጋገጥ
ኮሚሽኑ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ /2/ መሠረት በተሿሚ፣ በተመራጭ ወይም በመንግሥት ሠራተኛ በተሞላ መረጃ ያልተሟላ፣ ትክክል ያልሆነ ወይም የሀሰት መረጃ የያዘ መሆኑን ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ሲኖረው ወይም ሀብቱ በትክክል አልተመዘገበም የሚል ጥቆማ ሲቀርብ ወይም በተፈጸመ ወንጀል ምክንያት ምርመራ ሲጀመር የምዝገባውን ትክክለኛነት የማጣራት ተግባር ያከናውናል።
ኮሚሽኑ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት የማጣራት ተግባር ሲያከናውን፡-
ጉዳዩ የሚመለከተው ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ተጨማሪ መረጃ ወይም ማብራሪያ እንዲያቀርብ ሊጠይቀው፣
የተሿሚውን፣ የተመራጩን ወይም የመንግሥት ሠራተኛውን ሀብት የሚመለከት መረጃ ያለው ባንክ፣ የፋይናንስ ተቋም ወይም ማንኛውም ሌላ ሰው መረጃውን እንዲሰጥ ሊያዘው፣ እና
የዋና ኦዲተርን ወይም የሌላ አግባብነት ያለውን አካል ሙያዊ ድጋፍ ሊጠቀም፣
ይችላል።
ኮሚሽኑ ያልተሟላ፣ ትክክል ያልሆነ ወይም የሀሰት መረጃ መቅረቡን በማስረጃ ሲያረጋግጥ ጥፋት በፈጸመው ሰው ላይ በህጉ መሠረት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድበት ያደርጋል፡፡
የምዝገባ መረጃ ተደራሽነት
በኮሚሽኑ እጅ የሚገኝ ማንኛውም የተሿሚ፣ የተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የሀብት ምዝገባ መረጃ ለህዝብ ክፍት ይሆናል፡፡
ስለሀብት ምዝገባ መረጃ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጥያቄውን በጽሁፍ ለኮሚሽኑ ወይም ጉዳዩ ለሚመለከተው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ሊያቀርብ ይችላል።
ኮሚሽኑ ወይም የሚመለከተው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የምዝገባውን መረጃ ለጠየቀው ሰው መስጠት አለበት፡፡
የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች ቢኖሩም የቤተሰብ ሀብትን የሚመለከት የምዝገባ መረጃ ለፍትህ ሥራ ወይም ኮሚሽኑ አስፈላጊ ነው ብሎ ለሚወስነው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሚስጥር የሚያዝ ይሆናል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ አዋጅ መሠረት በየሁለት ዓመቱ ስላከናወነው የሀብት ምዝገባ አጠቃላይ መረጃ በሪፖርት መልክ ያወጣል።
የሃብት አለመመዝገብ የሚያስከትለው ውጤት
በዚህ አዋጅ መሠረት ያልተመዘገበ ማናቸውም የተሿሚ፣ የተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ሀብት ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር ለወንጀል ሕግ አንቀጽ 419/2/ ድንጋጌ አፈጻጸም ሲባል ምንጩ እንዳልታወቀ ንብረት ይቆጠራል።
ክፍል ሶስት
የጥቅም ግጭትን ስለማሳወቅና ስለማስወገድ
መርህ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የያዘውን መንግሥታዊ የሃላፊነት ቦታ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ማዋል አለበት፡፡ በማንኛውም ምክንያት ቢሆን በሥራው አጋጣሚ ያገኘውንና ሕዝብ እንዲያውቀው ያልተደረገን መረጃ ለግል ጥቅሙ ማዋል የለበትም፡፡
ስጦታ፣ መስተንግዶና የጉዞ ግብዣ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የመወሰን ሥልጣኑን የሚፈታተን ወይም የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ስጠታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ መቀበል የለበትም፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ የተደነገገው ቢኖርም የቀረበለትን ስጦታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ ያለመቀበል በስራ ግንኙነት ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ ሲገኝ ስጦታውን፣ መስተንግዶውን ወይም የጉዞ ግብዣውን ለመቀበል ይችላል፡፡ ሆኖም የተቀበለውን ስጦታ አግባብ ላለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ገቢ ማድረግ ወይም መስተንግዶውን ወይም የጉዞ ግብዣውን ለኮሚሽኑ ወይም አግባብ ላለው የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ማሳወቅ አለበት፡፡
የጥቅም ግጭትን ለማስወገድ መወሰድ ስላለበት እርምጃ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በመንግሥት የሥራ ሃላፊነቱና በራሱ ወይም በቅርብ ዘመዱ የግል ጥቅም መካከል ግጭት ሊያስከትልበት የሚችል ጉዳይ ሲያጋጥመው፡-
በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ወይም አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ከኃላፊነቱ ጋር የማይጣጣም ወይም ታማኝነቱን ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ፣ እና
ሁኔታውን ለሚመለከተው የበላይ ኃላፊ ማሳወቅ አለበት፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት የጥቅም ግጭት ሊከሰት መቻሉ የተገለጸለት የበላይ ኃላፊ እንደሁኔታው ተሿሚው፣ ተመራጩ ወይም የመንግሥት ሠራተኛው ጉዳዩን ማየቱን እንዲቀጥል መመሪያ ሊሰጠው ወይም ሌላ ሰው ተተክቶ እንዲያየው ሊያደርግ ይችላል።
የጥቅም ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ስለሚወሰድ እርምጃ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በመንግሥት የሥራ ሃላፊነቱና በራሱ ወይም በቅርብ ዘመዱ የግል ጥቅም መካከል ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በበላይ ኃላፊው ሲጠየቅ ጥፋተኛ መሆኑን በይፋ አምኖ ይቅርታ የመጠየቅ ወይም ራሱን ከኃላፊነት የማግለል ግዴታ አለበት፡፡
ከሥራ መልቀቅ በኋላ ስለሚኖር ክልከላ
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ሥራ በለቀቀ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሲቆጣጠራቸው ከነበረው ሰዎች ጋር ጥቅም የሚያስገኙ ሥራዎች መሥራት የለበትም፡፡ ዝርዝሩ በደንብ እና /ወይም/ በመመሪያ ይገለጻል፡ ፡
የጥቅም ግጭትን የማሳወቅ ግዴታን ስላለመወጣት
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የጥቅም ግጭት መኖሩን በዚህ አዋጅ መሠረት የማሳወቅ ግዴታውን ካልተወጣ አግባብ ባለው የሥነ-ምግባር ደንብ መሠረት ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስድበታል።
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
ጥቆማ ስለማቅረብ
ማንኛውም ሰው ይህንን አዋጅ ጥሷል በሚለው ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ላይ ጥቆማ ማቅረብ ይችላል።
ጥቆማው እስከተቻለ ድረስ ከደጋፊ ማስረጃ ጋር በፅሁፍ ለኮሚሽኑ ወይም አግባብ ላለው የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ይቀርባል፡፡
በቀረበው ጥቆማ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የምርመራ ሂደቱና መዛግብቱ በሚስጥር ተይዘው ይቆያሉ።
በዚህ አንቀጽ መሠረት በቀረበ ጥቆማ የተገኘው መረጃ በወንጀል ህግ አንቀጽ 419(2) የሀብት መወረስ ውሳኔ ለማሰጠት ካስቻለ የተወረሰው ሀብት ከሚያስገኘው ገቢ ውስጥ 25 በመቶ ለጠቋሚው ይከፈላል።
የአዋጁን ተፈጻሚነት ስለማረጋገጥ
ማንኛውም የመንግስት መስርያ ቤት ወይም የመንግስት የልማት ድርጅት የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች በስራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ፡-
ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግስት ሠራተኞች ሀብታቸውን በወቅቱ እንዲያስመዘግቡ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
አግባብ ያላቸው የስነ-ምግባር ደንቦችን አውጥቶ ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡
ቅጣት
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ፡-
ሀብቱን በዚህ አዋጅ መሠረት ለምዝገባ ሳያሳውቅ ከቀረ ወይም ሆን ብሎ ትክክል ያልሆነ የምዝገባ መረጃ ከሰጠ፣ ወይም
የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች በመተላለፍ ስጦታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ ከተቀበለ ወይም የተቀበለውን ስጦታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ ሳያሳውቅ ከቀረ፣
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 417 መሠረት ይቀጣል።
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 20 መሠረት ለኮሚሸኑ ወይም ለሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ጥቆማ አቅርቧል ወይም ምስክርነት ሰጥቷል ወይም ጥቆማ ለማቅረብ ወይም ምስክርነት ለመስጠት ተዘጋጅቷል በሚል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበቀል እርምጃ የወሰደ እንደሆነ በወንጀል ህግ አንቀጽ 444 መሠረት ይቀጣል።
ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የጥቅም ግጭት መኖሩን ሳያሣውቅም ሆነ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ /2/ መሠረት ተፈቅዶለት ሲሠራ የመንግሥት ኃላፊነቱን ተጠቅሞ የራሱን ወይም የቅርብ ዘመዱን የግል ጥቅም ያራመደ እንደሆነ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ ድንጋጌ መሠረት ይቀጣል።
ማንኛውም ሰው በክፉ ልቦና በመነሳሳት ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው ጥቆማ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 20 መሠረት ካቀረበ እስከ ሦስት ዓመት ሊደርስ በሚችል እሥራት ወይም እስከ ብር 2,000 ( ሁለት ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጐች
ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ህግ ወይም ማንኛውም ልማዳዊ አሰራር በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም።
ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል።
ኮሚሽኑ ይህንን አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/ መሠረት የወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል።