በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች


በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ በፍርድ ቤቶችና በህግ ምሁራን ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ ይዘት አያንጸባርቅም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12a በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው፡፡ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15b በተሰጠ የህግ ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል፡፡በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ይዋልላል፡፡
ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን አይመለከትም፡፡
ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን አለው ነገር፡፡ ግን ጉዳዩን ለመፍታት ተቋማዊ ብቃት የለውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ስልጣንም ብቃትም አለው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በዳኝነት ለመጨረስ ህገ መንግስታዊ ተገቢነት የለውም፡፡ጉዳዩ ገና ያልበሰለ ነው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤት ጣልቃ አይገባበትም፡፡ፍርድ ቤቱ ህጋዊነትን ከማጣራት አልፎ የጉዳዩን ይዘት (merit) ሳይፈትሽ በአጣሪ ዳኝነት ሊመረምር የሚችልበት በቂ ምክንያት (grounds of judicial review) የለም፡፡ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመወሰን የሚያስችል ቅቡልነት ያለው ማስረጃ ማግኘት ወይም ማስቀረብ አልቻለም፡፡cከዝርዝሮቹ መካከል በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ በሚገባ የተገለጸው በ3ኛ እና 4ኛ ላይ ነው፡፡ የዳኝነት ስልጣን ጉዳዩን ለመዳኘት ካለመቻል የሚመነጭ ባህርይ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ስልጣን ላይ በህግ የተቀመጠ ገደብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ እንዲያይ ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የይግባኝ ስልጣኑ ለሌላ አካል ከተሰጠ የስረ-ነገር የዳኝነት ስልጣን ያጣል፡፡ በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ በከፊል ስልጣን አግኝቶ ከሆነም በፍሬ ነገር ረገድ የሚደርስበት ድምዳሜ የስልጣኑን ልክ ያልፋል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ራሱን ችሎ የቆመ ሀሳብ በመሆኑ ከጉዳዩ ለመዳኘት አለመቻል ጋር ሊቀላቀል አይገባውም፡፡በዝርዝሩ 2ኛ ላይ የተጠቀሰው ‘ህዝባዊ ስልጣን’ ጉዳዩ የአስተዳደር ህግ ጥያቁ እንደማያስነሳ ያመለክታል፡፡ ሁለት የተለያየ የአስተዳር ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስርዓት ላለቸው አገራት ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ መነሻው መንግስት እንደ ግለሰብ ያሉትን መብቶች ተጠቅሞ የፈጸመው ድርጊት ከሆነ በአጣሪ ዳኝነት አይስተናገድም፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነት ወይም ከውል በሚመነጭ ግዴታ መንግስት ተጠያቂነት ካለበት ጉዳዩ ከመነሻው የአጣሪ ዳኝነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡የጉዳዩ አለመብሰል እና የይዘት ጥያቄ የአስተዳደር ህግ ወሰንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩ ገና ውሳኔ ላይ ያልደሰበትን ጉዳይ የማያዩት ህጋዊነቱን የሚመዝኑበት በቂ ምክንያት ስለማያገኙ ነው፡፡ የውሳኔው ይዘት ማለትም ትክክለኛነቱ እንዲሁ ከህግ አንጻር የሚጣራበት መሰረት የለም፡፡ በመጨረሻም ማስረጃ ሊገኝ አለመቻሉ ወይም እንዲቀርብ የታዘዘው ማስረጃ ሚስጥራዊ ተብሎ በመፈረጁ የተነሳ ፍርድ ቤቱ እልባት ለመስጠት አለመቻሉ ጉዳዩ ከመነሻው በፍርድ እንደማይዳኝ አያመለከትም፡፡በዝርዝሮቹ 3ኛ እና 4ኛ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በከፊል በሚያቅፍ መልኩ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ምን እንደሆነ ትክክለኛ ትርጓሜ የተሰጠው በሰ/መ/ቁ. 42150 ቅጽ 12d ከአብላጫው ድምጽ በተለየው ሀሳብ ላይ ነው፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው የሚባለው የክርክሩ መሠረታዊ ባህሪ በፍርድ ለመጨረስ አመች የሆነ ሲሆንና ተከራካሪዎቹ የሚከራከሩበት ጉዳይ ንድፈ ሃሳባዊ ወይም ምናባዊ የፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሣይሆን በነባራዊ ዕውነታና ተጨባጭ በሆነ ችግር ወይም ክስተት መሠረት ያደረገ የመብት ወይም የሃላፊነት ጥያቄ ሲሆን እንደሆነ ነው፡፡በአብላጫው ድምጽ ላይ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ከከሳሽነት ብቃት ጋር ተምታቷል፡፡ በአብላጫው አስተያየት አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው ሊባል የሚችለው፤…የክርክሩ መሠረት በሕግ ጥበቃ ያገኘ መብት ወይም ግዴታ ሲሆን ወይም ለመብቱ ወይም ግዴታው መሠረት የሚሆን ውል መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ይሁን እንጂ ‘ያለመዳኘት’ ከጉዳዩ ባህርይ እንጂ ከተከራካሪ ወገኖች ብቃት ወይም መብት አይመነጭም፡፡ ከባህርያቱ አንጻር ሲቃኝ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊዳኝ አይችልም የሚባለው አንድም ከፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ብቃት አንጻር በፍርድ ለማለቅ አመቺ ባለመሆኑ አሊያም ከህግ መንግስታዊው የስልጣን ክፍፍል አንጻር ዳኝነት መስጠት ተገቢ ስለማይሆን ነው፡፡ከተቋማዊ ብቃት አንጻር አንዳንድ ጉዳዮች የብዙ ወገኖች ተጻራሪና ተነጻጻሪ ጥቅም ያዘሉ (polycemtric) በመሆናቸው በባህርያቸው በፍርድ ቤት ሙግት ለማለቅ አያመቹም ወይም አይመቹም፡፡ እንደ ፒተር ኬን ገለጻ፤
A polycentric issue is one which involves a large number of interlocking and interacting interests and considerations.e
የፍርድ ቤት የሙግት ስርዓት ተጻራሪ የጥቅም ግጭት ያለባቸውን ጉዳዮች በወጉ ለመፍታት አያመችም፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት ጥብቅ የሙግት ስነ ስርዓት ብሎም የሚመደብላቸው ውስን የገንዘብና የሰው ኃይል ቴክኒካልና ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሆነ ተጻራሪ ጥቅሞችን በማቻቻል ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ አያስችልም፡፡ በአጭር አነጋገር እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት ተቋማዊ ብቃታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡በፍርድ ለመዳኘት ህገ መንግታዊ ተገቢነት የሌላቸው ጉዳዮች በፈራጆች ውሳኔ ሳይሆን በተመራጮችና ፖለቲከኞች ጥበብና ብልሀት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዳኞች ተሿሚዎች እንጂ ተመራጮች አይደሉም፡፡ ለመራጩ ህዝብም ቀጥተኛ ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ እንዲሁም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ዳኝነት መስጠት ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና አንጻር ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት መዋዋል፣ የሚኒስትሮች ሹመትና ሽረት፣ ፓርላማ የመበተን ስልጣን፣ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ፣ መንግስት በአንድ አካባቢ መሰረት ልማት ለመዘርጋት የሚደርስበት ውሳኔ በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ውሳኔ ፖለቲካዊ ተገቢነት መዝኖ ፍርድ ማሳረፍ የዳኝነት አካሉ ሚና አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዳኝነት ማየት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳል፡፡ ውሳኔ ሰጪው ፈቃደ ስልጣን የሚወሰኑ ጉዳዮች እንዲሁ በፍርድ ለማለቅ አመቺ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስራ ፈቃድ ወይም የግንባታ ቦታ ጥያቄዎች ተገቢነት በፍርድ ቤት ጭብጥ ተይዞበት የሚወሰን አይደለም፡፡ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንድ ጉዳይ በፍርድ የማይዳኘው የክሱ ምክንያት በይዘቱ ዳኝነት ለመስጠት አመቺ ሳይሆን እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ተገቢነት ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክርክሩ መነሻ የሆነው አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድርጊት ‘የጀርባ ምክንያት’ ፖለቲካዊ ነክ መሆኑ ፍርድ ቤቶች አከራክረው ውሳኔ ከመስጠት አያግዳቸውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48217f አመልካች በህጋዊ መንገድ ተመርተው የሰሩት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ተነጥቀው ለ2ኛ ተጠሪ እንደተሰጠባቸው በመግለጽ እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቤቱ አሰጣጥ መነሻ አመልካች በጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረት ስለወደመባቸው ለተፈናቃዮች ምትክ ቦታና ገንዘብ እንዲሰጥ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ አመልካች በዚሁ መሰረት የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ቤቱን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ‘ኤርትራዊ ነሽ’ በሚል ምክንያት 1ኛ ተጠሪ ቤታቸውን ነጥቆ ለ2ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡
ክሱ በቀረበበት ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ የቤቱ አሰጣጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይዳኝ የመጀሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያነሳ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሆኖም ክርክሩን በይግባኝና በሰበር ያዩት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ በአስተዳደር እንጂ በፍርድ እንደማያልቅ አቋም በመያዛቸው የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት በበኩሉ በድርጊቱ ይዘት ላይ በማተኮር የአመልካች የክስ ‘አለአግባብ ቤቴን ተነጠቅኩኝ’ በሚል የቀረበ እንደሆነ በመጠቆም ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ እንደሚችል ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
የአገራችን ፍርድ ቤቶች በፍርድ አይዳኙም በሚል በራቸውን የሚዘጉባቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የተቋማዊ ብቃት ሆነ የፖሊሲ ጥያቄ አያስነሱም፡፡ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸው በሰበር ችሎት ከታረሙ አንዳንድ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ‘በፍርድ የማይዳኙት’ ውስጥ የመፈረጅ አዝማሚያ በፍርድ ቤቶቻችን ዘንድ ሰፍኖ ይታያል፡፡በሰ/መ/ቁ. 75414 ቅጽ 14g የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታ ‘በፍርድ አይዳኝም’ በሚል በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሰበር ችሎት የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ሽሮታል፡፡የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ቀሪ ነው፤ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚቀርብ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1196 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት በፍ/ቤት ሊረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት የሚያበቃ አይደለም፡፡

የከሳሽነት ብቃት
‘አንድን የአስተዳደር ተግባር በፍርድ ቤት ወይም በሌላ የዳኝነት ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት መሞገት የሚችለው ማነው?’ የሚለው ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ውስጥ መልስ አሁንም ድረስ መቋጫ የሌለው አንዳንዴም ውሉ የጠፋበት የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በየአገራቱ ያለው ተሞክሮ ሆነ በአንድ አገር ውስጥ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚያዘው አቋም እንዲሁ ወጥነት አይታይበትም፡፡ የጽንሰ ሀሳቡን ምንነት እና ዘርፈ ብዙ ስለሆኑት መልኮቹ ከመቃኘታችን በፊት የቋንቋ አጠቃቀም ራሱን የቻለ እክል እንደሚፈጥር ማውሳት ያስፈልጋል፡፡ አንድን የህግ ጽንሰ ሃሳብ በጥልቀት ለመረዳት መጀመሪያ ጽንሰ ሀሳቡ የሚገለጽበት ቋንቋ አብዛኛው ሰው የሚረዳው ስያሜ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‘ለ’ Judicial Review አንድ ወጥ የአማርኛ ፍቺ አለመኖሩ ፅንሰ ሀሳቡ በአገራችን ውስጥ ያሉትን ገጽታዎችና የተፈጻሚነት ወሰኑን በተመለከተ የተሟላ ትንተና ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ያደበዝዘዋል፡፡በእንግሊዘኛ Standing በላቲን ደግሞ Locus Standi በመባል የሚታወቀው ቃል በኢትዮጵያ የህግ ስነ ጽሁፍ ውስጥ ገና መደበኛ ስያሜውን አላገኘም፡፡ ‘የመክሰስ መብት’፣ ‘የመክሰስ ችሎታ’ የሚሉት አገላለጾች አሁን አሁን በከፊልም ቢሆን ተቀባይነት እያገኙ ነው፡፡ ‘በጉዳዩ የሚያገባው ወገን’፣ ‘በጉዳዩ ጥቅም ያለው ወገን’፣ ‘ጉዳት የደረሰበት ወገን’ ወዘተ…የሚሉት አጠራሮችም በአቻነት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡‘የመክሰስ መብት’ በጥሬ ትርጉሙ የወሰድነው እንደሆነ ከህግ ወይም ከህገ-መንግስት የመነጨ መብት መኖርን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ስለሆነ ፍቺ ሆኖ መቅረቡ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥቅል የሆነ መብትን እንጂ በአንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአግባቡ አያመለክትም፡፡ በመርህ ደረጃ ማንም ሰው የመክሰስ መብት አለው፡፡ ይህን መብቱን በተግባር ሊገለገልበት የሚችለው ግን ለመክሰስ የሚያበቃው ሁኔታ በህግ ተሟልቶ ሲገኝብቻ ነው፡፡በሌላ በኩል ‘የመክሰስ ችሎታ’ በተለመደው የቋንቋ አጠቃቀም ወይም በመደበኛ ፍቺው ‘ለ’ Standing ወካይ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ የመክሰስ ችሎታ የሚመጣው ‘የ’ Standing ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ አንድ ሰው ‘የመክሰስ ችሎታ የለውም’ የሚባለው ህጋዊ ሰውነት ወይም ውክልና በማጣቱ እንዲሁም በእድሜው ወይም በአእምሮ ጤንነቱ ምክንያት በፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር Standing ኖሮት ችሎታ ግን ላይኖረው ይችላል፡፡ በጉዳዩ የሚያገባው፣ በጉዳዩ ጥቅም ያለው፣ ጉዳት የደረሰበት፣ የሚሉት አገላለጾችም ፅንሰ ሀሳቡን አለአግባብ የማጥበብ ወይም የማስፋት እንደምታ ያዘሉ በመሆኑ በአቻ ትርጉም ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በዚህ መጽሐፍ Standing የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ‘የከሳሽነት ብቃት’ በሚል ተተርጉሟል፡፡ አንድ ሰው በፍትሐብሔር ሆነ በአስተዳደር ክርክር ከሳሽ ሆኖ ለመሟገት እንዲፈቀድለት በቅድሚያ ክሱን ለማቅረብ ብቁ የሚያደርጉት የህግ ሁኔታዎች መሟላታቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ብቃት እንዳለው የሚወሰነው በከሳሹና ክስ ባቀረበበት ጉዳይ መካከል በበቂ ሁኔታ የሚታይ ግንኙነት (nexus) ሲኖር ነው፡፡የግንኙነቱ ገመድ በህግ ማዕቀፍ የሚገለጽበት መንገድ ከአገር አገር ይለያያል፡፡ በብዙ የካሪቢያን አገራት በአስተዳራዊ ድርጊት ወይም አልድርጊት (omission) መብትና ጥቅሙ የተጎዳ ሰው የከሳሽነት ብቃት የሚኖረው ሲሆን በተወሰኑ ሁኔታዎች ከግላዊ ጥቅሙ ባሻገር ህዝባዊ ጥቅሙን ለማስከበር ክስ ለማቅረብ ይፈቀድለታል፡፡a በአውስትራሊያ እንደሚጠየቀው የመፍትሔ ዓይነት ይለያያል፡፡ የዕግድ እና የማስገደጃ ትዕዛዞችን ለመጠየቅ የተፈጸመው ወይም ያልተፈጸመው ተግባር ግላዊ ጥቅም ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚጋራው ሕዝባዊ ጥቅም በሚሆንበት ጊዜ ግን ከሳሽ ለመሆን የሚፈቀድለት በጉዳዩ የተለየ ጥቅም እንዳለው ማሳየት ከቻለ ነው፡፡b የመሻሪያ (Certiorari)፣ የክልከላ (Prohibition) እና አካልን ነጻ የማውጣት (Habeas Corpus) ዳኝነት ለመጠየቅ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው ከሳሽ የመሆን ብቃት አለው፡፡በአገራችን በፍትሐብሔር እና በአስተዳደር ክርክሮች የከሳሽነት ብቃት የሚወሰነው በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህጉ ድንጋጌዎች ነው፡፡ ይህ ጠቅላላ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ የከሳሽነት ብቃት ገደቦችን የሚያስቀሩ በጣት የሚቆጠሩ ልዩ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 402/2/ ሲሆን እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ከዚህ በላይ ባለው ቁጥር [401] የተመለከተውን ፈራሽነት ማንኛውም ባለጉዳይ ሁሉ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.