የአስተዳደር ህግና ህገመንግስታዊ መርሆዎች/እና የህግ የበላይነት


የአስተዳደር ህግ እና ህገ መንግስታዊ መርሆዎች የአስተዳደር ህግ እና የህገ መንግስት ትስስር እና ተዛምዶ የአስተዳደር ህግ ጽንስቱ ሆነ ውልደቱ.

ሁለቱም የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነትን በሚመራው ‘የህዝብ አስተዳደር ህግ’ ተብሎ በሚጠራው የህግ ክፍል ውስጥ ይመደባሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄዎችን ያስነሳሉ፡፡ የአስተዳደር ህግን በጥልቀት ለመረዳት ከተፈለገ ሂደቱ መጀመር ያለበት ህገ መንግስትን በማጥናት ነው፡፡ በምሁራኑ አንደበት ይኸው እውነታ እንዲህ ይገለፃል፡፡ የአስተዳደር ህግ ከህገ መንግስታዊ መሰረቱ ተለይቶ በደንብ ሊታወቅ ሆነ ሊጠና አይችልም፡፡ የአስተዳደር ህግ በህገ መንግስት ማስፈጸሚያ መሳሪያነቱ የዝምድናቸውን ገጽታ በሚገባ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ በዚህ የተግባሪነት ሚናው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ የተቀመጡትን የህገ መንግስታዊነትና የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች እንዲሁም የግለሰቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተጨባጭ እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን በማስፈጸም ረገድ እንደ አንድ መሳሪያ ያገለግላል፡፡ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም. የጀርመን የፌደራል አስተዳደር ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እንደተናገሩት የአስተዳደር ህግ ‘ተጨባጭ ህገ መንግስት’ ማለትም በተግባር የሚታይ ህገ መንግስት ነው፡፡a የአንድ አገር ህገ መንግስት በዋነኛነት የዜጐችን ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ይደነግጋል፡፡ የዜጐች መብት በሌላ ግለሰብ፣ ማህበር ወይም የንግድ ድርጅት ሊጣስ ይችላል፡፡ ትልቁ አደጋ ያለው ግን ከመንግስት በተለይም ከስራ አስፈፃሚው አካል በኩል ነው፡፡ መብቶች በሚገባ እንዲጠበቁ የመንግስት አስተዳደር ልኩ ተለይቶ በታወቀ የስልጣን ገደብ ውስጥ ሊከናወን ይገባል፡፡ ሆኖም ስልጣን ሁልጊዜ በህጉ መሰረት ግልጋሎት ላይ ይውላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የግድ በአግባቡ ሊገራና ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡ የአስተዳደር ህግ የስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ በዚህ ተግባሩ ውጤታማ የስልጣን ቁጥጥር የዜጐች ህገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ዋስትና ይሰጣል፡፡ መንግስቱን በተግባር እንዲተረጐም የሚደርገውም በዚህ መንገድ ነው፤ ስልጣንን በመቆጣጠር የዜጐችን መብት በተጨባጭ ማቀዳጀት፡፡ ይህ ሚናውን በሌሎች ህገ መንግስታዊ መርሆዎች አንጻርም ጎልቶ ይታያል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በዋነኛነት ከሚደነግጋቸው የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች መካከል ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎ ይገኙበታል፡፡b ግልጽነት እውን የሚሆነው የመንግስት ባለስልጣናትና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ለዜጐች መረጃ የመስጠት ግዴታቸው ከነዝርዝር አፈፃፀሙ ጭምር በህግ ተደንግጐ ሲገኝ ነው፡፡ ተጠያቂነት፤ ጠያቂውና ተጠያቂው ተለይቶ የተጠያቂነት ስልቱ በዝርዝር ህግ ካልተቀመጠ በተግባር አይረጋገጥም፡፡ የህዝብ ተሳትፎ እንዲሁ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት ውሳኔ በተለይም ደንብና መመሪያ ሲያወጡ በጉዳዩ ጥቅም ካላቸው ወገኖች ሀሳብና አስተያየት እንዲቀበሉ የሚያስገድድ የህግ ድንጋጌ ከሌለ የህዝብ ተሳትፎ በተጨባጭ አይታይም፡፡ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትንና የህዝብ ተሳትፎን በተግባር ለማረጋገጥ የሚወጡ ህጐች በአስተዳደር ህግ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ህጉ እነዚህ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች በተግባር እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን ያስፈጽማል፡፡ በህገ መንግስትና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት ልዩነታቸው የላላ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሊጠቀስ የሚችል ቀጭን ልዩነት ቢኖር የወሰን እና የህጎች የተፈጻሚነት ደረጃ (Hierarchy of Laws) ልዩነት ነው፡፡ ከወሰን አንፃር ህገ መንግስት አጠቃላዩን የመንግስት አወቃቀርና የሶስቱን የመንግስት አካላት ብሎም በፌደራልና በክልል መንግስታት ያለውን የስልጣን ክፍፍል ስለሚወስን በይዘቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በአንፃሩ የአስተዳደር ህግ የአንደኛውን የመንግስት አካል ማለትም የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን፣ ግዴታና ተግባር ብሎም የውሳኔዎቹን ህጋዊነት የሚመለከት ህግ ነው፡፡ በህግ አውጭው የሚወጣ ህግ እና ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ህገ መንግስታዊነት ከጥናት አድማሱ በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ከወሰናቸው አንጻር ህገ መንግስት መስፋቱ የአስተዳደር ህግ መጥበቡ እንደ አንድ የልዩነት ነጥብ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ልዩነት የህጎች መሰላል (Hierarchy of Laws) ሲሆን በህጐች መካከል ያለውን የደረጃ ዝምድና ይመለከታል፡፡ ህገ መንግስት የአንድ አገር የበላይ ህግ እንደመሆኑ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ልምዶች ዋጋ የላቸውም፡፡ የአስተዳደር ህግ በደረጃው ከህገ መንግስት ዝቅ ብሎ የሚገኝ እንደመሆኑ መቼም ቢሆን ከህገ መንግስቱ ጋር መጣጣም አለበት፡፡ ግጭት በተነሳ ጊዜ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ሁልጊዜ ተፈፃሚነት አለው፡፡

የህግ የበላይነት ብዙ ምሁራን በየፊናቸው በምርምርና ጥናት ባገኙት እውቀት ተመርኩዘው የህግ የበላይነት መርህ ምንነት፤ ይዘትና ፋይዳውን አስመልክቶ አያሌ ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔዎችን አቅርበዋል፡፡ በአገራችን ደግሞ አባቶችና እናቶች በልባቸው ከተጻፈው እውነትና ከልምድ ከቀዱት ቱባ እውቀት በመነሳት የህግ የበላይነትን ጽንስ ሀሳብ በአንድ አባባል እንዲህ ይገልጹታል፡፡“በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ያለፍርድ የሄደች ዶሮዬ!”የዚህ ተረትና ምሳሌ አንኳር መልዕክት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተገለጠ ሳይሆን በመላው ማህበረሰብ ዘልቆ የገባ ሀቅ ነው፡፡ እናም ይህን የህግ የበላይነት ፅንሰ ሓሳብን ጠንቅቆ ያወቀው ማህበረሰብ ህግ ሲጣስ፤ ፍትህ ሲጓደል፤ መብት ሲታፈን፤ ስርዓት አልበኝነት ሲነግስ፤ ማን አለብኝነትና በዘፈቀደኝነት ሲንሰራፋ፤ የግሉ የሆነችው ዶሮ ከህግ እና ከፍርድ ውጭ ሲቀማ ድምፁን አጉልቶ ይጮሀል፤ በህግ አምላክ! ይላል፡፡ የጮኸው የዶሮዋ ዋጋ አንገብግቦት አይደለም፡፡ የተወሰደችበት መንገድ እንጂ፡፡ በፍርድ ከሆነ፤ በህጉ መሰረት ከሆነ እንኳንስ ለዶሮ ለበቅሎም ቄብ አይሰጠውም፡፡በህዝብ አስተዳደር፤ ፖለቲካ ሳይንስ፤ ህግ እና በሌሎችም የጥናት መስኮች የሚገኙ ምሁራን ስለ የህግ የበላይነት ምንነትና ይዘት ያላቸው ግንዛቤና አስተሳሰብ የተራራቀ ከመሆኑ የተነሳ ጽንሰ ሀሳቡ አሁንም ድረስ ቁርጥ ያለ ትርጓሜ አልተገኘለትም፡፡ አንድ የመስኩ ምሁር ይህንን ሀሳብ በማጠናከር እንዳብራራው፤‘[T]he rule of law’, like ‘democracy’, has no single meaning: it is not a legal rule, but a moral principle, which means different things to different people according to their particular moral positions.aበዚህ የተነሳ በተለያዩ አገራት የፖለቲካና የህገ መንግስት ስርዓት ውስጥ ይዘቱና አፈጻጸሙ የተለያየ አንዳንዴ የማይጣጣም መልክ በመያዙ መሰረታዊ እሳቤው ወጥነት ርቆታል፡፡ለምሳሌ በእንግሊዝ አንደኛውና የህግ የበላይነት መገለጫ በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚነሱ ክርክሮች በመደበኛ ፍ/ቤቶች ብቻ መዳኘታቸው ነው፡፡ ያ ማለት በእንግሊዛዊ አይን ፈረንሳይ ውስጥ የህግ የበላይነት የለም እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በፈረንሳይ በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ ክርክሮች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዳኙት ከመደበኛ ፍ/ቤት ትይዩ ራሱን ችሎ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ስርዓት አማካይነት ነው፡፡ በእንግሊዝ ሌላኛው የህግ የበላይነት ትርጉም የግለሰቦች መብትና ነፃነት መደበኛ ፍ/ቤቶች በቀረቡላቸው ተጨባጭ ጉዳዮች የሚሰጡት ውሳኔ ውጤት ነው የሚል ይዘት አለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በእንግሊዝ እውነት ቢሆንም የኛን አገር ጨምሮ የተጻፈ ህገ መንግስት ባላቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት የዜጐች መብቶችና ነፃነቶች በህገ መንግስቱ ላይ በጽሑፍ ይዘረዘራል፡፡ከዚህ በተጨማሪ በሊብራል ዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት በህጉ መሰረት ከመግዛትና ከማስተዳደር ባለፈ የህጉ ይዘት (ለምሳሌ ፍትሐዊነቱ፤ የዜጐችን መብት ማክበሩ፣ ህጉ የወጣው ህዝብ ወዶና ፈቅዶ በመረጣቸው ተወካዮች መሆኑ ወዘተ…) ብሎም የገለልተኛና ነፃ ፍ/ቤቶች፤ የዲሞክራዊ ተቋማት፤ ነፃ ፕሬስ ወዘተ… መኖር ሁሉም በህግ የበላይነት ጽንስ ሀሳብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የሊብራል ዲሞክራሲ ጠበል አልተጠመቁም በሚባልላቸው መንግስታት (ለምሳሌ በቻይና) ጽንሰ ሀሳቡ ስልጣን ያለው አካል በሚያወጣቸው ህጐች መሰረት መግዛትና ማስተዳደር ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ (በተለይ በእንግሊዝ) የተተከለበት መሰረት ነው፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ስራ አስፈፃሚው፣ የአስተዳደር መ/ቤቶች እና የአስተዳደር ጉባዔዎች የሚሰጡት ውሳኔ በህጉ መሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ህጋዊነት የሚሰፍነው ስልጣን የተሰጠው ማናቸውም የመንግስት አካል የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ የሚፈጽማቸው ድርቶች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች እና የሚያወጣቸው ደንብና መመሪያዎች በህግ ጥላ ስር መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡት ውሳኔ በህግ ከተቀመጠው የስልጣን ክልል በላይ ከሆነ ውሳኔው የህግ የበላይነት መርህን እንደሚጥስ ጥርጥር የለውም፡፡ ህጋዊነት መከበሩን ማረጋገጥ ማለት አስተዳደራዊ ድርጊት፣ ውሳኔ፣ እርምጃ፣ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ መሆኑን አሊያም አለመሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመደበኛ የፍርድ ቤቶች ተግባር ነው፡፡ ይህንን ተግባር በሚያሳንስ መልኩ በፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ በህግ አውጭው የሚደረግ ገደብ በውጤቱ የህግ የበላይነት መርህን ይሸረሽራል፡፡ ገደቡ በህግ የበላይነት መርህ ላይ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ያጣብባል፡፡ በተለይም ይህ መብት ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው ከሆነ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን መገደብ ዞሮ ዞሮ የዜጎችን ህገ-መንገስታዊ መብት መገደብ ነው፡፡የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ መሰረት ብቻ ሳይሆን ገደብ ጭምር እንደሆነ ማውሳት ያስፈልጋል፡፡ የውሳኔን ህጋዊነት ማረጋገጥ በይዘቱ ላይ መቆጠብን ያስከትላል፡፡ ፍ/ቤቶች የህግ የበላይነት በማስከበር ሚናቸው የአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ይዘት እንዳያጣሩ ወይም በፖሊሲ ጥያቄዎች ጣልቃ እንዳይገቡ ይገድባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.