የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት አፈፃፀም


የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት አፈፃፀም
ተደጋግሞ እንደተገለፀው የመንግስት ስልጣን በወርድም በቁመትም እየሰፋ በመጣ ቁጥር ለዜጐች መብትና ነፃነት ፀር ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ የስልጣንን አስፈላጊነት አምኖ ተቀብሎታል፡፡ ውጤታማ አስተዳደር እንዲሁም ቀልጣፋ የአገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስር ሳይሆን የሚፈታ ስልጣን ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ከህግና ከህገ መንግስት የሚያፈነግጥ ስልጣን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የበዘፈቀደ ድርጊት፣ ‘እንደፈለግኩኝ እሆናለው እፈልጣለው እቆርጣለው!’ የሚል አካሄድ አቅመ ቢስ የሆነውን ዜጋ የመኖር፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመናገር፣ ሀሳብን የመግለፅና ንብረት የማፍራት መሰረታዊ መብት አለገደብ ይሸረሽራል፡፡ የአስተዳደር ህግ የሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ ረገድ ያለው ሚና የሁለቱን ትስስር በሚገባ ያሳየናል፡፡ ህጉ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አፈፃፀም ላይ ያለውን አዎንታዊ ተፅእኖ በሚገባ ለመረዳት ከሰብዓዊ መብቶች አተገባበር አንፃር የመንግስትን ግዴታ መተንተኑ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ እነዚህም ሚናዎች (ግዴታዎች) የማክበር (respect) የማስከበር (protect) እንዲሁም የመፈጸምና የማስፈፀም (enforcement) ናቸው፡፡ በመጀመሪያው መብቶችን የማክበር የመንግስት ሚና ዜጐች ነፃ ሆነው መብታቸውን ሲጠቀሙ ከየትኛውም የመንግስት አካል የሚመጣ ጣልቃ ገብነትን ይገድባል፡፡ በተለይም መሰረታዊ በሚባሉት በህይወት የመኖር፣ የመፃፍ፣ የመናገር፤ የፈለጉትን ሀይማኖት የመከተል፤ በነፃነት የመዘዋወርና ንብረት የማፍራት መብቶችና ነፃነቶች በተግባር የሚረጋገጡት መንግስት እጁን ሲሰበስብ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በመንግስት በተለይ በስራ አስፈፃሚውና በስሩ ባሉት የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔ፤ ትዕዛዝ፤ ደንብና መመሪያ አማካይነት አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ህገ መንግስቱ የበላይ ህግ እንደመሆኑ ይህን የሚቃረን ህግ፣ ውሳኔና አሰራር ሁሉ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ይህን መሰሉ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ውስጥ አይወድቅም፡፡ ይሁን እንጂ የህገ መንግስታዊነት ብቻ የሚመስል ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ማእቀፍ የሚሸፈንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በአንድ የአስተዳደር ተቋም የወጣ መመሪያ በህግ አውጭው ከተሰጠ የውክልና ስልጣን በማለፍ የዜጐችን ሰብዓዊ መብት የሚገድብ ሆኖ ከተገኘ በውስጡ የህገ መንግስታዊነት (constitutionality) ጥያቄ ያዘለ ቢሆንም በዋናነት ግን የአስተዳደር ህግ ሊመልሰው የሚገባ የህጋዊነት (legality) ጥያቄ ነው፡፡ ልዩነታቸውን የበለጠ መረዳት እንዲያስችልን የሚከተለውን የድሮው የገቢዎች ሚኒስቴር የአሁኑ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያ እንመልከት፡፡ ማንኛውም የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ስልፍና የስራ ማቆም አድማ ማድረግ አይችልም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ለማንኛውም ሰው የተረጋገጠ መብት ነው፡፡ መብቱን የሚያጎናጽፈው የአንቀጽ 30 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲህ ይነበባል፡፡ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ አንድ መመሪያ በስራ አስፈፃሚው አካል ሲወጣ ከህግ አውጭው በግልጽ የተሰጠ የውክልና ስልጣን (Delegation) ሊኖር ይገባል፡፡ መመሪያው የውክልና ስልጣኑን ገደብ ካለፈ ከስልጣን በላይ (Ulta vires) ነው፡፡ ስለሆነም በህግ ፊት ዋጋ አልባ (null and void) ነው፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን መመሪያ ሲያወጣ የስልጣን ምንጩን የጉምሩክ ባለስልጣንን ለማቋቋምና አስራሩን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁ. 368/1995 አንቀጽ 8 (2) (ሐ) እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ይህ የተጠቀሰው የህግ ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል፡፡ የጉምሩክ ህግ እንዲያስከብር ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተመደበን የፖሊስ ኃይል ሚኒስቴሩ የፌደራል ፖሊስ አዋጅን ተከትሎ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በስራ ያሰማራል፡፡ ያስተዳድራል፡፡ ጥፋት ሲገኝም ያሰናብታል፡፡ ይህ አንቀጽ የጉምሩክ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በመመሪያ እንዲከለክል ለገቢዎች ሚኒስቴር ስልጣን አይሰጥም፡፡ ከተወካዮች ምክር ቤት ግልፅ ስልጣን ባልተሰጠበት ሁኔታ የወጣው ይህ መመሪያ ህጋዊነት ሆነ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የአስተዳደር ህግ ይህን መሰል መመሪያዎች በዘፈቀደ እየወጡ የዜጐችን መብትና ነፃነት እንዳይጥሱ በተለያዩ መንገዶች በመቆጣጠር መንግስት ሰብዓዊ መብት የማክበር ግዴታውን እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ የመንግስት የማስፈፀም ኃላፊነት አብዛኛውን ጊዜ ከማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ጋር በቀጥታ ተያይዞ ይነሳል፡፡ መንግስት በዜጐች መብት ላይ ጣልቃ አለመግባቱ ወይም እጁን መሰብሰቡ ብቻ አይበቃም፡፡ ለዜጋው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም ጤና፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ ወዘተ… ካላቀረበ ነፃ መሆን በራሱ ፋይዳ የለውም፡፡ የአስተዳደር ህግ እና የሰብዓዊ መብት ትሰስር ከመንግስት የማስከበር ግዴታ አንጻርም ሊቃኝ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት ሰብዓዊ መብትን በማስከበር ኃላፊነቱ መብት እንዳይጣስ የስልጣን መቆጣጠሪያ ስልቶች በህግ እና በተቋማዊ አደረጃጀት የማጠናከር፣ በመብት መጣስ ጉዳት ለደረሰበት ዜጋ ፈጣን ፍትህ የሚያገኝበትን ስርዓት መዘርጋት አለበት ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መንግስት የዳበረ የአስተዳደር ህግ እና የአስተዳደር ህግ ስርዓት መቅረጽ፣ መትከልና ማጐልበት ይጠበቅበታል፡፡