
የህግ የበላይነት
ብዙ ምሁራን በየፊናቸው በምርምርና ጥናት ባገኙት እውቀት ተመርኩዘው የህግ የበላይነት መርህ ምንነት፤ ይዘትና ፋይዳውን አስመልክቶ አያሌ ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔዎችን አቅርበዋል፡፡ በአገራችን ደግሞ አባቶችና እናቶች በልባቸው ከተጻፈው እውነትና ከልምድ ከቀዱት ቱባ እውቀት በመነሳት የህግ የበላይነትን ጽንስ ሀሳብ በአንድ አባባል እንዲህ ይገልጹታል፡፡ “በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ያለፍርድ የሄደች ዶሮዬ!” የዚህ ተረትና ምሳሌ አንኳር መልዕክት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተገለጠ ሳይሆን በመላው ማህበረሰብ ዘልቆ የገባ ሀቅ ነው፡፡ እናም ይህን የህግ የበላይነት ፅንሰ ሓሳብን ጠንቅቆ ያወቀው ማህበረሰብ ህግ ሲጣስ፤ ፍትህ ሲጓደል፤ መብት ሲታፈን፤ ስርዓት አልበኝነት ሲነግስ፤ ማን አለብኝነትና በዘፈቀደኝነት ሲንሰራፋ፤ የግሉ የሆነችው ዶሮ ከህግ እና ከፍርድ ውጭ ሲቀማ ድምፁን አጉልቶ ይጮሀል፤ በህግ አምላክ! ይላል፡፡ የጮኸው የዶሮዋ ዋጋ አንገብግቦት አይደለም፡፡ የተወሰደችበት መንገድ እንጂ፡፡ በፍርድ ከሆነ፤ በህጉ መሰረት ከሆነ እንኳንስ ለዶሮ ለበቅሎም ቄብ አይሰጠውም፡፡ በህዝብ አስተዳደር፤ ፖለቲካ ሳይንስ፤ ህግ እና በሌሎችም የጥናት መስኮች የሚገኙ ምሁራን ስለ የህግ የበላይነት ምንነትና ይዘት ያላቸው ግንዛቤና አስተሳሰብ የተራራቀ ከመሆኑ የተነሳ ጽንሰ ሀሳቡ አሁንም ድረስ ቁርጥ ያለ ትርጓሜ አልተገኘለትም፡፡ አንድ የመስኩ ምሁር ይህንን ሀሳብ በማጠናከር እንዳብራራው፤ ‘[T]he rule of law’, like ‘democracy’, has no single meaning: it is not a legal rule, but a moral principle, which means different things to different people according to their particular moral positions.a በዚህ የተነሳ በተለያዩ አገራት የፖለቲካና የህገ መንግስት ስርዓት ውስጥ ይዘቱና አፈጻጸሙ የተለያየ አንዳንዴ የማይጣጣም መልክ በመያዙ መሰረታዊ እሳቤው ወጥነት ርቆታል፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝ አንደኛውና የህግ የበላይነት መገለጫ በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚነሱ ክርክሮች በመደበኛ ፍ/ቤቶች ብቻ መዳኘታቸው ነው፡፡ ያ ማለት በእንግሊዛዊ አይን ፈረንሳይ ውስጥ የህግ የበላይነት የለም እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በፈረንሳይ በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ ክርክሮች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዳኙት ከመደበኛ ፍ/ቤት ትይዩ ራሱን ችሎ በተቋቋመ የአስተዳደር ፍ/ቤት ስርዓት አማካይነት ነው፡፡ በእንግሊዝ ሌላኛው የህግ የበላይነት ትርጉም የግለሰቦች መብትና ነፃነት መደበኛ ፍ/ቤቶች በቀረቡላቸው ተጨባጭ ጉዳዮች የሚሰጡት ውሳኔ ውጤት ነው የሚል ይዘት አለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በእንግሊዝ እውነት ቢሆንም የኛን አገር ጨምሮ የተጻፈ ህገ መንግስት ባላቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት የዜጐች መብቶችና ነፃነቶች በህገ መንግስቱ ላይ በጽሑፍ ይዘረዘራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሊብራል ዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት በህጉ መሰረት ከመግዛትና ከማስተዳደር ባለፈ የህጉ ይዘት (ለምሳሌ ፍትሐዊነቱ፤ የዜጐችን መብት ማክበሩ፣ ህጉ የወጣው ህዝብ ወዶና ፈቅዶ በመረጣቸው ተወካዮች መሆኑ ወዘተ…) ብሎም የገለልተኛና ነፃ ፍ/ቤቶች፤ የዲሞክራዊ ተቋማት፤ ነፃ ፕሬስ ወዘተ… መኖር ሁሉም በህግ የበላይነት ጽንስ ሀሳብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የሊብራል ዲሞክራሲ ጠበል አልተጠመቁም በሚባልላቸው መንግስታት (ለምሳሌ በቻይና) ጽንሰ ሀሳቡ ስልጣን ያለው አካል በሚያወጣቸው ህጐች መሰረት መግዛትና ማስተዳደር ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡ የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ (በተለይ በእንግሊዝ) የተተከለበት መሰረት ነው፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ስራ አስፈፃሚው፣ የአስተዳደር መ/ቤቶች እና የአስተዳደር ጉባዔዎች የሚሰጡት ውሳኔ በህጉ መሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ህጋዊነት የሚሰፍነው ስልጣን የተሰጠው ማናቸውም የመንግስት አካል የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ የሚፈጽማቸው ድርቶች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች እና የሚያወጣቸው ደንብና መመሪያዎች በህግ ጥላ ስር መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡት ውሳኔ በህግ ከተቀመጠው የስልጣን ክልል በላይ ከሆነ ውሳኔው የህግ የበላይነት መርህን እንደሚጥስ ጥርጥር የለውም፡፡ ህጋዊነት መከበሩን ማረጋገጥ ማለት አስተዳደራዊ ድርጊት፣ ውሳኔ፣ እርምጃ፣ ደንብና መመሪያ በህግ በተቀመጠው የስልጣን ገደብ ውስጥ መሆኑን አሊያም አለመሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመደበኛ የፍርድ ቤቶች ተግባር ነው፡፡ ይህንን ተግባር በሚያሳንስ መልኩ በፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ላይ በህግ አውጭው የሚደረግ ገደብ በውጤቱ የህግ የበላይነት መርህን ይሸረሽራል፡፡ ገደቡ በህግ የበላይነት መርህ ላይ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት ያጣብባል፡፡ በተለይም ይህ መብት ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው ከሆነ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን መገደብ ዞሮ ዞሮ የዜጎችን ህገ-መንገስታዊ መብት መገደብ ነው፡፡ የህግ የበላይነት መርህ የአስተዳደር ህግ መሰረት ብቻ ሳይሆን ገደብ ጭምር እንደሆነ ማውሳት ያስፈልጋል፡፡ የውሳኔን ህጋዊነት ማረጋገጥ በይዘቱ ላይ መቆጠብን ያስከትላል፡፡ ፍ/ቤቶች የህግ የበላይነት በማስከበር ሚናቸው የአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ይዘት እንዳያጣሩ ወይም በፖሊሲ ጥያቄዎች ጣልቃ እንዳይገቡ ይገድባቸዋል፡፡