የአስተዳደር ህግ እና የህገ መንግስት ትስስር እና ተዛምዶ


የአስተዳደር ህግ እና የህገ መንግስት ትስስር እና ተዛምዶ

የአስተዳደር ህግ ጽንስቱ ሆነ ውልደቱ ከህገ መንግስት እንደመሆኑ ከዚህ የህግ ክፍል ጋር ብዙ ባህርያትን ይጋራል፡፡ ሁለቱም የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነትን በሚመራው ‘የህዝብ አስተዳደር ህግ’ ተብሎ በሚጠራው የህግ ክፍል ውስጥ ይመደባሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የአስተዳደር ህግ ጥያቄዎች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄዎችን ያስነሳሉ፡፡ የአስተዳደር ህግን በጥልቀት ለመረዳት ከተፈለገ ሂደቱ መጀመር ያለበት ህገ መንግስትን በማጥናት ነው፡፡ በምሁራኑ አንደበት ይኸው እውነታ እንዲህ ይገለፃል፡፡ የአስተዳደር ህግ ከህገ መንግስታዊ መሰረቱ ተለይቶ በደንብ ሊታወቅ ሆነ ሊጠና አይችልም፡፡ የአስተዳደር ህግ በህገ መንግስት ማስፈጸሚያ መሳሪያነቱ የዝምድናቸውን ገጽታ በሚገባ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ በዚህ የተግባሪነት ሚናው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ የተቀመጡትን የህገ መንግስታዊነትና የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች እንዲሁም የግለሰቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተጨባጭ እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን በማስፈጸም ረገድ እንደ አንድ መሳሪያ ያገለግላል፡፡ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም. የጀርመን የፌደራል አስተዳደር ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እንደተናገሩት የአስተዳደር ህግ ‘ተጨባጭ ህገ መንግስት’ ማለትም በተግባር የሚታይ ህገ መንግስት ነው፡፡a የአንድ አገር ህገ መንግስት በዋነኛነት የዜጐችን ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ይደነግጋል፡፡ የዜጐች መብት በሌላ ግለሰብ፣ ማህበር ወይም የንግድ ድርጅት ሊጣስ ይችላል፡፡ ትልቁ አደጋ ያለው ግን ከመንግስት በተለይም ከስራ አስፈፃሚው አካል በኩል ነው፡፡ መብቶች በሚገባ እንዲጠበቁ የመንግስት አስተዳደር ልኩ ተለይቶ በታወቀ የስልጣን ገደብ ውስጥ ሊከናወን ይገባል፡፡ ሆኖም ስልጣን ሁልጊዜ በህጉ መሰረት ግልጋሎት ላይ ይውላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የግድ በአግባቡ ሊገራና ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡ የአስተዳደር ህግ የስልጣን መቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ በዚህ ተግባሩ ውጤታማ የስልጣን ቁጥጥር የዜጐች ህገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ዋስትና ይሰጣል፡፡ መንግስቱን በተግባር እንዲተረጐም የሚደርገውም በዚህ መንገድ ነው፤ ስልጣንን በመቆጣጠር የዜጐችን መብት በተጨባጭ ማቀዳጀት፡፡ ይህ ሚናውን በሌሎች ህገ መንግስታዊ መርሆዎች አንጻርም ጎልቶ ይታያል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በዋነኛነት ከሚደነግጋቸው የመንግስት አስተዳደር መርሆዎች መካከል ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ ተሳትፎ ይገኙበታል፡፡b ግልጽነት እውን የሚሆነው የመንግስት ባለስልጣናትና የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ለዜጐች መረጃ የመስጠት ግዴታቸው ከነዝርዝር አፈፃፀሙ ጭምር በህግ ተደንግጐ ሲገኝ ነው፡፡ ተጠያቂነት፤ ጠያቂውና ተጠያቂው ተለይቶ የተጠያቂነት ስልቱ በዝርዝር ህግ ካልተቀመጠ በተግባር አይረጋገጥም፡፡ የህዝብ ተሳትፎ እንዲሁ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት ውሳኔ በተለይም ደንብና መመሪያ ሲያወጡ በጉዳዩ ጥቅም ካላቸው ወገኖች ሀሳብና አስተያየት እንዲቀበሉ የሚያስገድድ የህግ ድንጋጌ ከሌለ የህዝብ ተሳትፎ በተጨባጭ አይታይም፡፡ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትንና የህዝብ ተሳትፎን በተግባር ለማረጋገጥ የሚወጡ ህጐች በአስተዳደር ህግ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ህጉ እነዚህ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች በተግባር እንዲረጋገጡ በማድረግ ህገ መንግስቱን ያስፈጽማል፡፡ በህገ መንግስትና በአስተዳደር ህግ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት ልዩነታቸው የላላ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሊጠቀስ የሚችል ቀጭን ልዩነት ቢኖር የወሰን እና የህጎች የተፈጻሚነት ደረጃ (Hierarchy of Laws) ልዩነት ነው፡፡ ከወሰን አንፃር ህገ መንግስት አጠቃላዩን የመንግስት አወቃቀርና የሶስቱን የመንግስት አካላት ብሎም በፌደራልና በክልል መንግስታት ያለውን የስልጣን ክፍፍል ስለሚወስን በይዘቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በአንፃሩ የአስተዳደር ህግ የአንደኛውን የመንግስት አካል ማለትም የስራ አስፈፃሚውን ስልጣን፣ ግዴታና ተግባር ብሎም የውሳኔዎቹን ህጋዊነት የሚመለከት ህግ ነው፡፡ በህግ አውጭው የሚወጣ ህግ እና ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ህገ መንግስታዊነት ከጥናት አድማሱ በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ከወሰናቸው አንጻር ህገ መንግስት መስፋቱ የአስተዳደር ህግ መጥበቡ እንደ አንድ የልዩነት ነጥብ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ልዩነት የህጎች መሰላል (Hierarchy of Laws) ሲሆን በህጐች መካከል ያለውን የደረጃ ዝምድና ይመለከታል፡፡ ህገ መንግስት የአንድ አገር የበላይ ህግ እንደመሆኑ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ልምዶች ዋጋ የላቸውም፡፡ የአስተዳደር ህግ በደረጃው ከህገ መንግስት ዝቅ ብሎ የሚገኝ እንደመሆኑ መቼም ቢሆን ከህገ መንግስቱ ጋር መጣጣም አለበት፡፡ ግጭት በተነሳ ጊዜ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ሁልጊዜ ተፈፃሚነት አለው፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.