የአስተዳደር ህግ ውልደትና ዕድገት በኢትዮጵያ ስለ ኢትዮጵያ


የአስተዳደር ህግ ውልደትና ዕድገት በኢትዮጵያ ስለ ኢትዮጵያ

የአስተዳደር ህግ ብሎም ውልደቱ፣ አነሳሱና ታሪካዊ ዕድገቱ ለመጻፍ ብዕሩን የሚያሾል ጸሐፊ ጭብጥ እንዳጣ የልብለወለድ ደራሲ ከየት ልጀምር? በሚል ጭንቀት ተውጦ ጣራ ላይ ማፍጠጥ አይቀርለትም፡፡ ስራውን ፈታኝ የሚያደርገው በህዝብ አስተዳደር እና በአስተዳደር ህግ ላይ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት፣ የምርምር ጽሑፎችና መጻህፍት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ ለጀማሪ አጥኚ ይህ በራሱ ራስ ምታት ነው፡፡ ከመነሻ ምንጭ እጥረት ባሻገር ሌሎች ዐቢይ ምክንያቶች የአገሪቱን የአስተዳደር ህግ ጉዞ መዘገብ አድካሚ ያደርጉታል፡፡ ለመጥቀስ ያህል፤ የጥናት አድማሱ ወጥነት እና ትኩረት ማጣትa የዲሞክራሲና ህገ መንግስታዊ ዳራውb የፖለቲካና አስተዳደር መደበላለቅc የህግ አውጭውና የፍርድ ቤቶች ሚና ማነስd ባደጉት አገራት የአስተዳደር ህግ ዕድገት ጥርት ባለ መልኩ ራሱን የቻለ የህግ ክፍል ሆኖ ብቅ ማለት የጀመረው የዘመናው ‘የአስተዳደር መንግስት’ (Administrative State) መከሰት ተከትሎ ስለመሆኑ ብዙዎች የመስኩ አጥኚዎች ይስማሙበታል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት ስለ አገራችን አስተዳደር ህግ ታሪካዊ ገጽታዎችና መገለጫዎች ከዘመናዊ አስተዳደር ማቆጥቆጥ ጋር አስታኮ አጠቃላይ ገለጻ መስጠት ይቻላል፡፡ በርካታ የአገራችን ሆኑ የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በአገራን ዘመናዊ አስተዳደር የተተከለው የኃይለስላሴ ዙፋን ላይ መውጣት ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ በተለይም ከኢጣሊያ ወረራ ማብቃትና የንጉሱ ዙፋን መልሶ መረከብ አንስቶ ዘመናዊ አስተዳደር ፈጣን ለውጦች አሳይቷል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ሲወራ የአጼ ቴዎድሮስ ውጥን እና ጥረት ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጦር ለማደራጀት፣ የቤተክስርስትያን የመሬት ይዞታ ለመቆጣጠር፣ የአካባቢ የጦር አበጋዞች በማዕከላዊ መንግስት ስር ለማዋቀር እንዲሁም የመንገድ ግንባታና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ለመዘርጋት ያደረጓቸው ጥረቶች ለቀጣይ ነገስታት መሰረት ጥለዋል፡፡ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለማቆም እና ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል የነበራቸው ህልም፣ ውጥን እና ፖሊሲ እንዲሁም እነዚህን ለመተግበር የወሰዷቸው ስር ነቀል እርምጃዎች የለውጥና የስልጣኔ በር ከፍተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ውልደት ከቴዎድሮስ ይጀምራል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነት እንዲቀረፍና ሹመኞች በህዝብ አገልጋይነታቸው በደል እንዳይፈጽሙ በጊዜው ሲያደርጉት የነበረው ክትትል እና የስልጣን ቁጥጥር በኢትዮጵያ የታሪክ መጻህፍት ጎልቶ ባይወጣም በአንዳንድ ጽሁፎች ተዘግቦ ይገኛል፡፡ በደርግ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ይዘጋጅ የነበረው ሕግና ፍትሕ መጽሔት በመጋቢት 1987 እትሙ አጼ ቴዎድሮስ ሙስና እና የአስተዳደር ብልሹነት እንዲወገድ ሲያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ ሌላ ምንጭ ጠቅሶ እንደሚከተለው ዘግቦታል፡፡e ቴዎድሮስ ወዘልውጥ በመሆንና አልባሌ ልብስ በመልበስ በመንግስቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደር መበላሸት መቆጣጠር፣ ጉቦኞች ሹማምንቶቻቸውን መከታተልና ማጋለጥ ያዘውትሩ ነበር፡፡ በሕዝብ ችግር የጨከኑትን፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የመንግስቱን ስራ የሚበድሉትንና ኅብረተሰቡን ያጉላሉትን ሹማምንት ከስልጣን ወንበራቸው ገልብጠዋል፡፡ አባ ታጠቅ ስልጣን በጨበጡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የጯሂ ጠባቂ (የህዝብ ዕንባ ጠባቂ) ሹማቸው ጉቦ መቀበሉን በማወቃቸውና ራሳቸውም ሲቀበል በማየታቸው በአደባባይ አጋልጠው ሽረውታል፡፡…የጯሂ ጠባቂነቱንም ሥራ ራሳቸው ይዘዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ የመንግስት ስልጣን በህግና በስርዓት እንዲገራ የነበራቸው ቆራጥ አቋም በታሪክ በተዘገቡ ጥቂት የጊዜው ፍርዶች ላይ ይታያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በጳውሎስ ኞኞ ‘አጤ ቴዎድሮስ’ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡፡ ቴዎድሮስ ጋይንት ላይ ሰፍረው ሳለ ወታደሮቻቸውን በባላገሩ ላይ ተሰሪ አስገቡ፡፡ ባላገሩ እንዲቀልብ በየቤቱ ማስገባት ማለት ነው፡፡ ተሰሪ ከገቡት ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን ባላገር ገደለው፡፡ የሟች ወገንም ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ አመለከተ፡፡ ቴዎድሮስም ወታደራቸውን ሁሉ አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን አውጣ ብለው ያዙ፡፡ ወታደሩም በመላው አድሞ ገዳዩን አላየንም እያለ በቄስ እየተገዘተ ወጣ፡፡ የሟች ገዳይ ወታደር በመጥፋቱ ቴዎድሮስ ተናደው ‘ወታደር ብላ፤ ባላገር አብላ ያልሁ እኔ ነኝ፡፡ ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል’ ብለው ብለው ተነስተው ለከሳሹ ነገሩት፡፡ ከሳሹም ‘እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም’ አለ፡፡ ቴዎድሮስም ደም በከንቱ አይቀርም ብለው ለሟቹ ወገን የደም ገንዘብ ዋጋ ሰጥተው ሸኙት፡፡f በሌላ ፍርድ ላይ እንዲሁ ለሁለት ወታደሮቻቸው የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭ ትዕዛዝ የአንደኛውን ወታደር ሞት በማስከተሉ ለሞቱ መከሰት ተጠያቂ ተደርገው ስለተፈረደባቸው በዚያ ንጉስ በማይከሰስበት፤ ሰማይ በማይታረስበት ዘመን ቅጣታቸውን ተቀብለው ፍርዱን ፈጽመዋል፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡ ቴዎድሮስ አንዱን ወታደራቸውን ‘በፍርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ’ ብለው ካዘዙት በኋላ በሌላ ቀን ደግሞ ሌላውን ወታደር ጠርተው ‘ፈረስ እያለዋወጥህ ይህን ወረቀት የጁ ሰጥተህ በአስቸኳይ በስድስት ቀን ውስጥ ተመልሰህ እንድትመጣ’ ብለው ሲልኩት እየጋለበ ሄዶ ፍርቃ በር ላይ ሲደርስ ጠብቅ ከተባለው ወታደር ጋር ‘አልፋለው! አታልፍም!’ እሰጥ አገባ ገጥሙ፡፡ በግዴታ ለማለፍ መንገድ ሲጀምር ዘበኛው ተኩሶ ገደለው፡፡ የንጉስ ትዕዛዝ ሲፈጽም የነበረ የንጉስ መልዕክተኛ በዚህ መልኩ መገደሉ ያንገበገባቸው የሟች ወገኖች ገዳዩን በመክሰስ ከቴዎድሮስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ ቴዎድሮስም ችሎት አስችለው ፍርድ እንዲፈረድ አደረጉ፡፡ በችሎት የተቀመጠው ፈራጅ ሁሉ እየተነሳ ገዳዩን ‘በደለኛ ነህ እምቢ አልፋለው ቢልህስ ለንጉስ ታሰማ ነበር እንጂ ራስህ ፈርደህ እንዴት የንጉስ መልዕክተኛ ትገድላለህ? አሁንም ስትሞት ይታየናል’ እያሉ ፈረዱ፡፡ አንደኛው ፈራጅ ግን ከተቀመጡበት ተነስተው ከሌሎቹ ፈራጆች በመለየት ሁለት ተቃራኒ ንጉሳዊ ትዕዛዝ መስጠት አግባብ ስላልሆነ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሠ ነገሥቱን እንደሆ ከተናገሩ በኋላ ‘ነገር ግን እሳቸው ብርሀን ስለሆኑ ምን ይደረግ?’ በማለት የፍርድ ሀሳባቸውን አሳርገው ተቀመጡ፡፡ አጤ ቴዎድሮስም ይህን የልዩነት የፍርድ ሀሳብ አድንቀው ከተቀመጡበት ተነስተው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ፡፡ በመጨረሻም ፈራጆች በፈረዱት መሰረት በጊዜው የሚከፈለውን የደም ዋጋ አጠፌታውን ብር 500 ከፍለው ጉዳዩ በስምምነት አለቀ፡፡g የቴዎድሮስ ሞትን ተከትሎ የተነሱት ነገስታት ማለትም አጼ ዮሐንስ እና አጼ ምኒልክ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ የውስጥና የውጭ የጦርነት ዘመቻዎች በመጠመዳቸው ዘመናዊ አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ አላሳየም፡፡ ሆኖም ከአድዋ ጦርነት በኋላ ማዕከላዊ መንግስት እየተጠናከረ ሲሄድ የተወሰኑ መሻሻሎች ታይዋል፡፡ በሚኒልክ ዘመነ መንግስት ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በ1900 ዓ.ም. የሚኒስትሮች መሾም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም. የተሰየሙት ሚኒስትሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡h የፍርድ ሚኒስትር የጦር ሚኒስትር የጽህፈት ሚኒስትር የአገር ግዛት ሚኒስትር የገንዘብ ሚኒስትር እና የንግድ ሚኒስትር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእርሻና መስሪያ ሚኒስትር የግቢ ሚኒስትር የመንግስቱን ስራ እንዲሰሩ የተደለደሉት ሚኒስትሮች ስልጣንና ተግባራቸው በዝርዝር ደንብ ተወስኖላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሚኒስትር የሚያስፈጽማቸው የተለያዩ ህጎች ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ህጎች እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ በአጼ ምኒልክና ሀይለስላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩባቸው ዓመታት በግብር ብቻ ተወስኖ የነበረውን የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነት አድማሱን አስፍተውታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የመንግስት ሚና ከጠባቂነት ቀስ በቀስ ወደ የክትትልና ቁጥጥር (regulation) እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅራቢነት ተሸጋግሯል፡፡ በቁጥጥር ረገድ በርካታ የንግድ እና የግብርና ተግባራት በቅድሚያ ከሚመለከተው ሚኒስቴር ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ህጎች ተደንግጓል፡፡ ለአብነት ያህል፤ የወፍጮ መዘውር ማቆምና መፍጨትi ትምባሆ መዝራትና መሸጥj አውሬ ማደን እና ዓሣ መያዝ (ማጥመድ)k በማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ቴሌፎን እና ፖስታ፣ ባቡር እና ሌሎችም ቀስ በቀስ ተስፋፍተዋል፡፡ በ1927 ዓ.ም. የጡረታ ስርዓት ለጉምሩክ ሠራተኞችና የጉምሩክ ወታደሮች (እንደ አሁኑ ፌደራል ፖሊስ ዓይነት) ተዘርግቷል፡፡ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ለወታደሮች ሃምሳ፣ ለሠራተኞች 60 ዓመት ሲሆን ለአበል የሚያበቃው የአገልግሎት ዘመን እንደ ቅደም ተከተሉ ሃያ አምስት እና ሰላሳ ዓመት ነው፡፡l በጊዜው የነበረው የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ከሞላ ጎደል አሁን ካለንበት ዘመን ጋር ተቀራራቢ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በጊዜው የነበረው የጉምሩክ ሹማምንትና ሠራተኞች ዲሲፕሊን አፈጻጸም ለዚህ አባባል ዐቢይ ምስክር ነው፡፡ የጉምሩክ ሠራተኛ በስራው ላይ ጥፋትና የሚጎዳ ነገር ከሰራ በየክፍሉ ያሉ ሹሞች ከስራ አግደው ስራውን በሌላ ሰራተኛ ያሰራሉ፡፡ ሆኖም በራሳቸው የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ስልጣኑ የላቸውም፡፡ ስለ ጥፋቱ አኳኋን መግለጫ አዘጋጅተው ከበላያቸው ላለው ዳይሬክተር ያስታውቃሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደ ጥፋቱ ክብደት እና ድግግሞሽ እስከ አንድ ወር ሙሉ ደመወዝ ‘ቅጣት’ ለመወሰን ስልጣን ነበረው፡፡ ሆኖም ቅጣቱ አስገዳጅ ሳይሆን የውሳኔ ሀሳብ ዓይነት ይዘት ያለው ነው፡፡ ዳይሬክተሩ የወሰነውን ቅጣት እና የጥፋቱን ሁኔታ ገልጾ ማስታወቂያ ለሠራተኛው ከሰጠው በኋላ ሠራተኛው ዋስ ጠርቶ አዲስ አበባ ለነበረው የዋናው ዲሬክተር ጽ/ቤት ይልከዋል፡፡ በመቀጠል ክርክር የሚካሄድበት ቀነ ቀጠሮ ይቆረጣል፡፡ በቀጠሮ ቀን ጥፋት የሚገኝባቸውን ሠራተኞች ሥርዓት ለማየት የተመረጡት ሹማምንት ተሰብስበው ነገሩን ከመረመሩ በኋላ ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ የፍርዱንም ግልባጭ ለሠራተኛው ይሰጠቱታል፡፡ በፍርዱ ቅሬታ ካለው ለንግድ ሚኒስትር ይግባኝ ማሰማት ይችላል፡፡ ሚኒስትሩም ፍርዱንና ነገሩን አይቶ መርምሮ የመጨረሻ ፍርድ ይሰጣል፡፡ ይህ ስርዓት ተፈጻሚነቱ በዋናው ዳይሬክተርና ሚኒስትሩ ለተቀጠሩ የበታች ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡ በንጉሱ አዋጅ ስራ የተቀጠሩ ሠራተኞችና ሹማምንት ጉዳይ የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ የሚያገኘው በሚኒስትሩ ሲሆን ይግባኝ የሚቀርበውና የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው በንጉሱ ችሎት ነው፡፡m ከዲሲፕሊን ጉዳዮች በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮችም የውሳኔ አሰጣጥ እና ቅሬታ አፈታት ስርዓት በዘመኑ ህጎች በስፋት የሚታይ ነበር፡፡ ለምሳሌ በትምባሆ ሬዢ አፈጻጸም ደንብ በ30ኛው ክፍል ደንቡን በመተላለፍ የተቀጣ ሰው እንዳገሩ ርቀት ካንድ ወር እስከ አራት ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርሻ ሚኒስቴር ሊያመልክት እንደሚችልና ሚኒስቴሩም ነገሩን እንደገና እንደሚያደላድለው (ነገሩን ሰምቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ) በደንቡ ላይ ተመልክቷል፡፡n የ1923 ህገ መንግስት ዜጎች የሚደርስባቸውን የአስተዳደር በደል ቅሬታ የማሰማት መብታቸውን ህገ መንግስታዊ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያው ነው፡፡ በአንቀጽ 28 ላይ እንደተደነገገው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለመንግስት አቤቱታ የማቅረብ መብት ተጠብቆላቸዋል፡፡ በተሻሻለው የ1948 ህገ መንግስት ላይም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ድንጋጌ በአንቀጽ 62 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በታወጀው የኢ.ህ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 52 በመንግስት አካላት እና ህዝባዊ ድርጅቶች ላይ ቅሬታ የማሰማት መብት ተጠብቋል፡፡ በተጨማሪም የሚቀርቡ ቅሬታዎች ተመርምረው ምላሽ እንደሚሰጣቸው በድንጋጌው ላይ ተመልክቷል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የተከተለው አቅጣጫ ከባለፉት ይለያል፡፡ አቤቱታ የማሰማት መብትን በተለይ ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ በአንቀጽ 37 የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ደንግጓል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ርዕስና ይዘት በወሰን (scope) አይጣጣሙም፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት ዜጎች ለሚደርስባቸው አስተዳደራዊ በደል በመደበኛ እና ኢ-መደበኛ የፍትሕ ተቋማት ቅሬታ አቅርበው መፍትሄ የማግኘት መብታቸውን ያካትታል፡፡o ይህን መሰረተ ሀሳብ በሚያንጸባርቅ አኳኋን የተቀረጸው የአንቀጽ 37 ርስስ በንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ የሚደነግገው በፍርድ የሚያልቁ ጉዳዮችን ለመደበኛና ፍ/ቤቶች እና ለአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative tribunals) አቅርቦ ዳኝነት የማግኘት መብት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመብቱ ወሰን ለህግ አውጨው፣ ለአስተዳደሩና ለሌሎች ተቋማት (ለምሳሌ እንባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን) ቅሬታ የማሰማት መብትን አይጨምርም፡፡ በአስተዳደር ህግ ታሪካዊ ዕድገት ውስጥ የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative tribunals) ሚና ጉልህ ስፍራ ይይዛል፡፡ በብዙ አገራት እየተለጠጠና እየተወሳሰብ የመጣው የመንግስት አስተዳደር በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚካሄዱ ክርክሮችን ሙሉ በሙሉ በመደበኛ ፍ/ቤቶች አማካይነት መዳኘት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በዚህ የተነሳ የአስተዳደር ጉባዔዎች (Administrative tribunals) አብዛኞቹን ክርክሮች በመዳኘት ውጤታማ የዳኝነት አካላት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ሆኖም በአገራችን በተጨባጭ የሚታይ የረባ ውጤት አላስመዘገቡም፡፡ ድሮም ሆነ ዘንድሮ እነዚህን ተቋማት ከፍትሕ ስርዓቱና ከአስተዳደር ሂደቱ ጋር በማቆራኘት ለማደራጀት ሙከራዎች አልተደረጉም፡፡ የ1923 ህገ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ለአስተዳደር ጉባዔዎች ህገ መንግስታዊ ዕውቅና በመስጠት አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመወሰን ስልጣን እንዳላቸው የደነገገ ቢሆንም በተግባር ግን ተቋማዊ መዋቅር ተዘርግቶላቸው አልተቋቋሙም፡፡ በዚህ ህገ መንግስት አንቀጽ 54 ላይ እንደተመለከተው፤ በማናቸውም በመንግስት ስራ ምክንያት የሚነሡትን ነገሮች የሚፈርዱ በተለይ የቆሙት የፍርድ ቤቶች ናቸው እንጂ ሌሎች ዳኞች እነዚህን ነገሮች ለመፍረድ አይችሉም፡፡ የድንጋጌው ሀሳብ በእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ ግልጽ ተደርጓል፡፡ Special courts shall judge all matters relating to administrative affairs, which are withdrawn from the jurisdiction of other courts. ህገ መንግስቱ በአማርኛው ‘በተለይ የቆሙት ፍርድ ቤቶች’ በእንግሊዝኛው Special courts በሚል በጥቅል የጠቀሳቸው ፍርድ ቤቶች ምን ዓይነት ፍርድ ቤቶች ሊቋቋሙ እንደታሰበ አይጠቁምም፡፡ ሆኖም ስለሚያዩት ጉዳይ የተቀመጠው ገለጻ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ የህገ መንግስቱ ምንጭ ይህንን አባባል የበለጠ ያጠናክራል፡፡ የ1923 የኢትዮጵያ ህገ መንግስቱ በአብዛኛው የተቀዳው በጃፓን እ.ኤ.አ በ1889 ዓም. በይፋ ከታወጀው የመጂ ህገ መንግስት (Meji Constitution) ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የጃፓን ገዢዎች አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ለማግለል የነበራቸውን ጽኑ ፍላጎት የሚደግፍ የአስተዳደር ህግ ስርዓት ሲያጠኑ ከመደበኛ ፍ/ቤት ትይዩ ሆኖ ራሱን ችሎ የተቋቋመው የጀርመን የአስተዳደር ፍ/ቤት ተመራጭ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚሁ መሰረት በመንግስት ላይ የሚቀርቡ ክሶች ከመደበኛው በተለየ በሚቋቋሙ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች እንደሚዳኙ በህገ መንግስታቸው በመደንገግ እ.ኤ.አ በ1890 ላይ ይህን ፍ/ቤት አቋቁመዋል፡፡p በኢትዮጵያ እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ የዳኝነት መብት ከአስተዳደር ስልጣን ጋር የተያያዘ ስለነበር ዳኝነት ሲሰጥ የነበረው በአካባቢው ሹማምንት፣ አገረ ገዢዎችና በራሳቸው በነገስታቱ አማካይነት ነው፡፡q ዳኝነት ከአስተዳደር ተለይቶ መደበኛ ፍ/ቤቶች የተቋቋሙት በ1934 ዓ.ም. ነው፡፡r ዓበይት ህግጋት እስከተጠናቀሩበት እስከ 1950ዎቹ ድረስ እነዚህ ፍ/ቤቶች የሚሰሩባቸው ህጎች ከሞላ ጎደል ልማዳዊ ነበሩ፡፡ ስለሆነም የተጠናከረ አስተዳደር ሆነ ዘመናዊ የህግና የዳኝነት ስርዓት ባልነበረበት በ1923 ዓ.ም. እና ቀጣይ ዓመታት የአስተዳደር ፍ/ቤቶችን አስፈላጊ የሚያደርግ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ አልነበረም፡፡ በተግባር ሲታይም ከወረቀት የዘለለ ህልውና አልነበራቸውም፡፡ እስካሁን ድረስ በአገራችን ራሱን ችሎ በተለይ የቆመ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ የለም፡፡ በንጉሱ ጊዜ እ.አ.አ በ1967 የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ረቂቅ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ከረቂቅነት ደረጃ አላለፈም፡፡ ቀጣይ ሙከራዎች የተደረጉት በ1993 ዓ.ም. እና 2001 ዓ.ም. ሲሆንም በሁለቱም ጊዜያት በፍትሕ እና የህግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት አማካይነት ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህጎች ተዘጋጅተዋል፡፡ እንደባለፈው ሁሉ የእነዚህም እጣ ፈንታ ከረቂቅነት መሻገር አልቻለም፡፡  

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.