
የአስተዳደር ህግ ውልደትና ዕድገት በኢትዮጵያ
ስለ ኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ብሎም ውልደቱ፣ አነሳሱና ታሪካዊ ዕድገቱ ለመጻፍ ብዕሩን የሚያሾል ጸሐፊ ጭብጥ እንዳጣ የልብለወለድ ደራሲ ከየት ልጀምር? በሚል ጭንቀት ተውጦ ጣራ ላይ ማፍጠጥ አይቀርለትም፡፡ ስራውን ፈታኝ የሚያደርገው በህዝብ አስተዳደር እና በአስተዳደር ህግ ላይ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት፣ የምርምር ጽሑፎችና መጻህፍት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ ለጀማሪ አጥኚ ይህ በራሱ ራስ ምታት ነው፡፡ ከመነሻ ምንጭ እጥረት ባሻገር ሌሎች ዐቢይ ምክንያቶች የአገሪቱን የአስተዳደር ህግ ጉዞ መዘገብ አድካሚ ያደርጉታል፡፡ ለመጥቀስ ያህል፤
የጥናት አድማሱ ወጥነት እና ትኩረት ማጣት።
የዲሞክራሲና ህገ መንግስታዊ ዳራው።
የፖለቲካና አስተዳደር መደበላለቅ።
የህግ አውጭውና የፍርድ ቤቶች ሚና ማነ።
ባደጉት አገራት የአስተዳደር ህግ ዕድገት ጥርት ባለ መልኩ ራሱን የቻለ የህግ ክፍል ሆኖ ብቅ ማለት የጀመረው የዘመናው ‘የአስተዳደር መንግስት’ (Administrative State) መከሰት ተከትሎ ስለመሆኑ ብዙዎች የመስኩ አጥኚዎች ይስማሙበታል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት ስለ አገራችን አስተዳደር ህግ ታሪካዊ ገጽታዎችና መገለጫዎች ከዘመናዊ አስተዳደር ማቆጥቆጥ ጋር አስታኮ አጠቃላይ ገለጻ መስጠት ይቻላል፡፡
በርካታ የአገራችን ሆኑ የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በአገራን ዘመናዊ አስተዳደር የተተከለው የኃይለስላሴ ዙፋን ላይ መውጣት ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ በተለይም ከኢጣሊያ ወረራ ማብቃትና የንጉሱ ዙፋን መልሶ መረከብ አንስቶ ዘመናዊ አስተዳደር ፈጣን ለውጦች አሳይቷል፡፡
ስለ ኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ሲወራ የአጼ ቴዎድሮስ ውጥን እና ጥረት ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጦር ለማደራጀት፣ የቤተክስርስትያን የመሬት ይዞታ ለመቆጣጠር፣ የአካባቢ የጦር አበጋዞች በማዕከላዊ መንግስት ስር ለማዋቀር እንዲሁም የመንገድ ግንባታና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ለመዘርጋት ያደረጓቸው ጥረቶች ለቀጣይ ነገስታት መሰረት ጥለዋል፡፡ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለማቆም እና ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል የነበራቸው ህልም፣ ውጥን እና ፖሊሲ እንዲሁም እነዚህን ለመተግበር የወሰዷቸው ስር ነቀል እርምጃዎች የለውጥና የስልጣኔ በር ከፍተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ውልደት ከቴዎድሮስ ይጀምራል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነት እንዲቀረፍና ሹመኞች በህዝብ አገልጋይነታቸው በደል እንዳይፈጽሙ በጊዜው ሲያደርጉት የነበረው ክትትል እና የስልጣን ቁጥጥር በኢትዮጵያ የታሪክ መጻህፍት ጎልቶ ባይወጣም በአንዳንድ ጽሁፎች ተዘግቦ ይገኛል፡፡ በደርግ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ይዘጋጅ የነበረው ሕግና ፍትሕ መጽሔት በመጋቢት 1987 እትሙ አጼ ቴዎድሮስ ሙስና እና የአስተዳደር ብልሹነት እንዲወገድ ሲያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ ሌላ ምንጭ ጠቅሶ እንደሚከተለው ዘግቦታል፡፡e
ቴዎድሮስ ወዘልውጥ በመሆንና አልባሌ ልብስ በመልበስ በመንግስቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደር መበላሸት መቆጣጠር፣ ጉቦኞች ሹማምንቶቻቸውን መከታተልና ማጋለጥ ያዘውትሩ ነበር፡፡ በሕዝብ ችግር የጨከኑትን፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የመንግስቱን ስራ የሚበድሉትንና ኅብረተሰቡን ያጉላሉትን ሹማምንት ከስልጣን ወንበራቸው ገልብጠዋል፡፡ አባ ታጠቅ ስልጣን በጨበጡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የጯሂ ጠባቂ (የህዝብ ዕንባ ጠባቂ) ሹማቸው ጉቦ መቀበሉን በማወቃቸውና ራሳቸውም ሲቀበል በማየታቸው በአደባባይ አጋልጠው ሽረውታል፡፡…የጯሂ ጠባቂነቱንም ሥራ ራሳቸው ይዘዋል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ የመንግስት ስልጣን በህግና በስርዓት እንዲገራ የነበራቸው ቆራጥ አቋም በታሪክ በተዘገቡ ጥቂት የጊዜው ፍርዶች ላይ ይታያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በጳውሎስ ኞኞ ‘አጤ ቴዎድሮስ’ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡፡
ቴዎድሮስ ጋይንት ላይ ሰፍረው ሳለ ወታደሮቻቸውን በባላገሩ ላይ ተሰሪ አስገቡ፡፡ ባላገሩ እንዲቀልብ በየቤቱ ማስገባት ማለት ነው፡፡ ተሰሪ ከገቡት ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን ባላገር ገደለው፡፡ የሟች ወገንም ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ አመለከተ፡፡ ቴዎድሮስም ወታደራቸውን ሁሉ አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን አውጣ ብለው ያዙ፡፡ ወታደሩም በመላው አድሞ ገዳዩን አላየንም እያለ በቄስ እየተገዘተ ወጣ፡፡ የሟች ገዳይ ወታደር በመጥፋቱ ቴዎድሮስ ተናደው ‘ወታደር ብላ፤ ባላገር አብላ ያልሁ እኔ ነኝ፡፡ ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል’ ብለው ብለው ተነስተው ለከሳሹ ነገሩት፡፡ ከሳሹም ‘እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም’ አለ፡፡ ቴዎድሮስም ደም በከንቱ አይቀርም ብለው ለሟቹ ወገን የደም ገንዘብ ዋጋ ሰጥተው ሸኙት፡፡f
በሌላ ፍርድ ላይ እንዲሁ ለሁለት ወታደሮቻቸው የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭ ትዕዛዝ የአንደኛውን ወታደር ሞት በማስከተሉ ለሞቱ መከሰት ተጠያቂ ተደርገው ስለተፈረደባቸው በዚያ ንጉስ በማይከሰስበት፤ ሰማይ በማይታረስበት ዘመን ቅጣታቸውን ተቀብለው ፍርዱን ፈጽመዋል፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡
ቴዎድሮስ አንዱን ወታደራቸውን ‘በፍርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ’ ብለው ካዘዙት በኋላ በሌላ ቀን ደግሞ ሌላውን ወታደር ጠርተው ‘ፈረስ እያለዋወጥህ ይህን ወረቀት የጁ ሰጥተህ በአስቸኳይ በስድስት ቀን ውስጥ ተመልሰህ እንድትመጣ’ ብለው ሲልኩት እየጋለበ ሄዶ ፍርቃ በር ላይ ሲደርስ ጠብቅ ከተባለው ወታደር ጋር ‘አልፋለው! አታልፍም!’ እሰጥ አገባ ገጥሙ፡፡ በግዴታ ለማለፍ መንገድ ሲጀምር ዘበኛው ተኩሶ ገደለው፡፡ የንጉስ ትዕዛዝ ሲፈጽም የነበረ የንጉስ መልዕክተኛ በዚህ መልኩ መገደሉ ያንገበገባቸው የሟች ወገኖች ገዳዩን በመክሰስ ከቴዎድሮስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ ቴዎድሮስም ችሎት አስችለው ፍርድ እንዲፈረድ አደረጉ፡፡
በችሎት የተቀመጠው ፈራጅ ሁሉ እየተነሳ ገዳዩን ‘በደለኛ ነህ እምቢ አልፋለው ቢልህስ ለንጉስ ታሰማ ነበር እንጂ ራስህ ፈርደህ እንዴት የንጉስ መልዕክተኛ ትገድላለህ? አሁንም ስትሞት ይታየናል’ እያሉ ፈረዱ፡፡ አንደኛው ፈራጅ ግን ከተቀመጡበት ተነስተው ከሌሎቹ ፈራጆች በመለየት ሁለት ተቃራኒ ንጉሳዊ ትዕዛዝ መስጠት አግባብ ስላልሆነ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሠ ነገሥቱን እንደሆ ከተናገሩ በኋላ ‘ነገር ግን እሳቸው ብርሀን ስለሆኑ ምን ይደረግ?’ በማለት የፍርድ ሀሳባቸውን አሳርገው ተቀመጡ፡፡ አጤ ቴዎድሮስም ይህን የልዩነት የፍርድ ሀሳብ አድንቀው ከተቀመጡበት ተነስተው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ፡፡ በመጨረሻም ፈራጆች በፈረዱት መሰረት በጊዜው የሚከፈለውን የደም ዋጋ አጠፌታውን ብር 500 ከፍለው ጉዳዩ በስምምነት አለቀ፡፡g
የቴዎድሮስ ሞትን ተከትሎ የተነሱት ነገስታት ማለትም አጼ ዮሐንስ እና አጼ ምኒልክ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ የውስጥና የውጭ የጦርነት ዘመቻዎች በመጠመዳቸው ዘመናዊ አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ አላሳየም፡፡ ሆኖም ከአድዋ ጦርነት በኋላ ማዕከላዊ መንግስት እየተጠናከረ ሲሄድ የተወሰኑ መሻሻሎች ታይዋል፡፡ በሚኒልክ ዘመነ መንግስት ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በ1900 ዓ.ም. የሚኒስትሮች መሾም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም. የተሰየሙት ሚኒስትሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡h
የፍርድ ሚኒስትር
የጦር ሚኒስትር
የጽህፈት ሚኒስትር
የአገር ግዛት ሚኒስትር
የገንዘብ ሚኒስትር እና የንግድ ሚኒስትር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የእርሻና መስሪያ ሚኒስትር
የግቢ ሚኒስትር
የመንግስቱን ስራ እንዲሰሩ የተደለደሉት ሚኒስትሮች ስልጣንና ተግባራቸው በዝርዝር ደንብ ተወስኖላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሚኒስትር የሚያስፈጽማቸው የተለያዩ ህጎች ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ህጎች እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ በአጼ ምኒልክና ሀይለስላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩባቸው ዓመታት በግብር ብቻ ተወስኖ የነበረውን የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነት አድማሱን አስፍተውታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የመንግስት ሚና ከጠባቂነት ቀስ በቀስ ወደ የክትትልና ቁጥጥር (regulation) እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅራቢነት ተሸጋግሯል፡፡
በቁጥጥር ረገድ በርካታ የንግድ እና የግብርና ተግባራት በቅድሚያ ከሚመለከተው ሚኒስቴር ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ህጎች ተደንግጓል፡፡ ለአብነት ያህል፤
የወፍጮ መዘውር ማቆምና መፍጨትi
ትምባሆ መዝራትና መሸጥj
አውሬ ማደን እና ዓሣ መያዝ (ማጥመድ)k
በማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ቴሌፎን እና ፖስታ፣ ባቡር እና ሌሎችም ቀስ በቀስ ተስፋፍተዋል፡፡ በ1927 ዓ.ም. የጡረታ ስርዓት ለጉምሩክ ሠራተኞችና የጉምሩክ ወታደሮች (እንደ አሁኑ ፌደራል ፖሊስ ዓይነት) ተዘርግቷል፡፡ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ለወታደሮች ሃምሳ፣ ለሠራተኞች 60 ዓመት ሲሆን ለአበል የሚያበቃው የአገልግሎት ዘመን እንደ ቅደም ተከተሉ ሃያ አምስት እና ሰላሳ ዓመት ነው፡፡l
በጊዜው የነበረው የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ከሞላ ጎደል አሁን ካለንበት ዘመን ጋር ተቀራራቢ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በጊዜው የነበረው የጉምሩክ ሹማምንትና ሠራተኞች ዲሲፕሊን አፈጻጸም ለዚህ አባባል ዐቢይ ምስክር ነው፡፡
የጉምሩክ ሠራተኛ በስራው ላይ ጥፋትና የሚጎዳ ነገር ከሰራ በየክፍሉ ያሉ ሹሞች ከስራ አግደው ስራውን በሌላ ሰራተኛ ያሰራሉ፡፡ ሆኖም በራሳቸው የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ ስልጣኑ የላቸውም፡፡ ስለ ጥፋቱ አኳኋን መግለጫ አዘጋጅተው ከበላያቸው ላለው ዳይሬክተር ያስታውቃሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደ ጥፋቱ ክብደት እና ድግግሞሽ እስከ አንድ ወር ሙሉ ደመወዝ ‘ቅጣት’ ለመወሰን ስልጣን ነበረው፡፡ ሆኖም ቅጣቱ አስገዳጅ ሳይሆን የውሳኔ ሀሳብ ዓይነት ይዘት ያለው ነው፡፡ ዳይሬክተሩ የወሰነውን ቅጣት እና የጥፋቱን ሁኔታ ገልጾ ማስታወቂያ ለሠራተኛው ከሰጠው በኋላ ሠራተኛው ዋስ ጠርቶ አዲስ አበባ ለነበረው የዋናው ዲሬክተር ጽ/ቤት ይልከዋል፡፡ በመቀጠል ክርክር የሚካሄድበት ቀነ ቀጠሮ ይቆረጣል፡፡
በቀጠሮ ቀን ጥፋት የሚገኝባቸውን ሠራተኞች ሥርዓት ለማየት የተመረጡት ሹማምንት ተሰብስበው ነገሩን ከመረመሩ በኋላ ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ የፍርዱንም ግልባጭ ለሠራተኛው ይሰጠቱታል፡፡ በፍርዱ ቅሬታ ካለው ለንግድ ሚኒስትር ይግባኝ ማሰማት ይችላል፡፡ ሚኒስትሩም ፍርዱንና ነገሩን አይቶ መርምሮ የመጨረሻ ፍርድ ይሰጣል፡፡
ይህ ስርዓት ተፈጻሚነቱ በዋናው ዳይሬክተርና ሚኒስትሩ ለተቀጠሩ የበታች ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡ በንጉሱ አዋጅ ስራ የተቀጠሩ ሠራተኞችና ሹማምንት ጉዳይ የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ የሚያገኘው በሚኒስትሩ ሲሆን ይግባኝ
