ግልጽና ተጓዳኝ ስልጣን


ጽና ተጓዳኝ ስልጣን

ስልጣንአብዛኛውን ጊዜ ለመንግስት አካላት የሚደለደለው ስልጣን አሻሚ ባልሆነ አነጋገር ይገለጻል፡፡ ግልጽና ቀጥተኛ ስልጣን በአስተዳደሩ ውስጥ ህጋዊነትን ያሰፍናል፡፡ በተጨማሪም ስልጣንን በመገልገል ረገድ ጥርጣሬና ብዥታን ያስወግዳል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ለውጤታማ አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑትን ስልጣናትና ተግባራት መዘርዘር ያዳግታል፡፡ ስለሆነም በግልጽ ስልጣን ውስጥ አስፈላጊ የሆነ በዝምታ የሚተላለፍ ተጓዳኝ ስልጣን ይኖራል፡፡ አንድን ድርጊት ለመፈፀም ግልጽ የሆነ ስልጣን ሲሰጥ የድርጊቱ አካል የሆኑና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል በዝምታ የሚሰጥ ስልጣን ስለመኖሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የህጉን ዓላማና ግብ እንዲሁም የህጉን ድንጋጌዎች አነጋገር በጥልቀት መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን መኖሩን ለመወሰን የሚከተሉት ነጥቦች ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡የህጉ አነጋገርይህ የህግ አውጭውን ሀሳብ ለማወቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ለምሳሌ የመንግስት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ኤጀንሲዎች በሚያስፈጽሟቸው አዋጆች መሰረት ለማናቸውም ዓይነት አበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መሟላታቸውን የማረጋገጥና የአበሉን ዓይነትና መጠን የመወሰን ስልጣን አላቸው፡፡ ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በአዋጅ ቁ. 714/2003 እና 715/2003 የተለያዩ ድንጋጌዎች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ እነዚህን ሁኔታዎች መኖራቸውን የመወሰን ስልጣናቸው ክርክር አያስነሳም፡፡ ለምሳሌ በአዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀጽ 41 መሰረት ለሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈለው የጡረታ አበል ሟች ያገኝ ወይም ሊያገኝ ይችል የነበረው የጡረታ አበል 50 በመቶውን ነው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ላይ ባል ወይም ሚስት የጡረታ አበል በመቀበል ላይ እያሉ ጋብቻ ከፈጸሙ አበሉ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች ተመልክተዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መወሰን በኤጀንሲዎቹ ስልጣን ስር ቢሆንም የባልነት ወይም ሚስትነት ጥያቄ በተነሳ ጊዜ ይህንን ማረጋገጥ ከስልጣናቸው ክልል በላይ ነው፡፡ ይህን መወሰን በመደበኛ የዳኝነት አካላት ስልጣን ስር ይወድቃል፡፡ ስለሆነም ‘ለአበል ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች’ የሚለው አነጋገር በሁለቱም አዋጆች ላይ መለኪያና መስፈርት የተቀመጠላቸውን ሁኔታዎች እንጂ በሌሎች ህጎች የሚወሰኑትን አያካትትም፡፡ የህግ አውጨው ሀሳብም ኤጀንሲዎቹ ለአበል ብቁ የሆኑ የሟች ሚስት ወይም ባል የሚከፈላቸውን መጠንና እና ክፍያውን የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች እንዲወስኑ እንጂ ከመነሻው ባልነት ወይም ሚስትነትን በተመለከተ ማስረጃ አሰባስበው ውሳኔ እንዲሰጡ አይደለም፡፡በግልጽ የተሰጠው ስልጣን ወሰን
ስልጣኑ በጠባቡ ከተሰጠ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ በአንጻሩ ሰፊ የሆነ ስልጣን በውስጡ አስፈላጊ የሆኑ ተጓዳኝ ስልጣናትን ያቅፋል፡፡ለምሳሌ በተሽከርካሪ አደጋ የሶስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁ. 799/2005 አንቀጽ 13 ላይ እንደተመለከተው አንድ ተሽከርካሪ የመድን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው የመድን ሽፋን እንደሌለው ስለሚያስቆጥረው የመድን ዋስትና ሰርተፊኬት እስኪመጣ ድረስ ፖሊስ ተሽከርካሪውን ይዞ የማቆየት ስልጣን አለው፡፡ በዚህ ድንጋጌ የፖሊስ የስልጣኑ ወሰን ጠባብ ነው፡፡ መኪናውን ከመያዝና ለማቆያ በተዘጋጀ ስፍራ ላይ ከማስቀመጥ ውጪ ሊወስድ የሚችለው ተጓዳኝ እርምጃ የለም፡፡ይህንን የፖሊስ ስልጣን አካባቢንና ብክለትን የመቆጣጠር ኃላፊነት ካለባቸው አካላት ስልጣን ጋር ብናነጻጽረው ልዩነቱ በግልጽ ይታያል፡፡
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ወይም የሚመለከተው የክልል ባለስልጣን በአካባቢ ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከሚያሰጋ የስራ እንቅስቃሴ ሊመጣ የሚችል ጉዳትን ለመከላከል ድርጅትን እስከ መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡
ድርጅትን እስከመዝጋትና ወደ ሌላ ቦታ እስከማዛወር የሚደርስ ስልጣን ድርጅቱን የማሸግና ሠራተኞች እንዳይገቡ የመከልከል እንዲሁም ጉዳት ለመቀነስ የሚያስፈልጉ ተጓዳኝ እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣን ጭምር ያካትታል፡፡የህጉ ዓላማ የህጉ አጠቃላይ ዓላማና ግብ በግልጽ ከተቀመጠው ስልጣን በተጨማሪ የህጉን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ስልጣናት ስለመኖራቸው አመላካች ነው፡፡ ተጓዳኝ ስልጣን ሳይኖር የህጉን ዓላማ በተግባር ማሳካት የማይቻል ከሆነ በዝምታ የተሰጠ ስልጣን ስለመኖሩ ግምት ይወሰድበታል፡፡የድርጊቱ ዓይነትና /ባህርይ/ ይዘትበግልጽ የተሰጠው ስልጣን ማዕቀብ የሚጥል ድርጊት ወይም እርምጃ ከሆነ ተጓዳኝ ስልጣን ስለመኖሩ በጠባቡ መተርጐም ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የመቆጣጠር ስልጣን በውስጠ ታዋቂነት የመከልከል ስልጣንን አይጨምርም፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.