አስተዳደራዊ ስልጣን


አስተዳደራዊ ስልጣን

ደንብና መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ህግ አስፈፃሚ አካላት ህግና ፖሊሲን ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው

አስተዳደራዊ ስልጣን

ደንብና መመሪያ ማውጣት እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ መውሰድ ህግ አስፈፃሚ አካላት ህግና ፖሊሲን ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው፡፡ የእነዚህ አካላት ዋነኛ ስልጣንና ተግባር ህግ ማውጣት አሊያም ዳኝነት መስጠት ሳይሆን ማስተዳደር ነው፡፡ አስተዳደራዊ ስልጣን ከህግ ማውጣት እና ዳኝነት መስጠት ውጪ ያሉትን ተግባራት በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ የአስተዳደር /ቤቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ይህን የእለት ተእለት የአስተዳደር ስራ በማከናወን ነው፡፡
በዚህ ስልጣን ስር ከሚወድቁ በርካታ ምሳሌዎችን መካከል ሪፖርት ማቅረብ፣ ፓስፖርት መስጠት፣ ፍቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ፀጥታ ማስከበር፣ ክስ መመስረት፣ እድገትና ሹመት መስጠት፣ ምርመራ፤ ቁጥጥርና ክትትል ማካሄድ የምክር ሀሳብ መስጠት ወዘተ ሁሉም የአስተዳደር /ቤቶች አስተዳደራዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም የሚያከናውኗቸው ስራዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ተግባራት የህግ መጣስ መኖርን አለመኖሩን ለማረጋገጥ መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የመረጃ አሰባሰብና ጥንቅር ስርዓት የንግድ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የመረጃ አሰባሰብ ስርዓቱ በአካል ተገኝቶ ቀጥተኛ እና የአካባቢ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ እና የማጣራት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የመርማሪነት ስራ ህጉ ልዩ ስልጣን በሰጣቸው መርማሪዎች የሚከናወን ሲሆን የምርመራ ሂደቱም በህግ ማእቀፍ ውስጥ ይመራል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የፖሊስ የምርመራ ተግባር ነው፡፡ ፖሊስ ወንጀል ሲፈጸም ወይም ተፈጽሟል የሚል መረጃ ከደረሰው አሊያም ተገቢ ጥርጣሬ ካደረበት የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ በአካል በመገኘት ተጨባጭ ማስረጃዎችን የመሰብሰብ እና ተጠርጣሪውን የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ስልጣናት አሉት፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአስተዳደር /ቤቶች የመርማሪነት፣ የቁጥጥርና ክትትል ስልጣን በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህጉ ለፖሊስ ከተሰጠው ስልጣን ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡
በአስረጂነት በተወሰኑ ህጎች ለተቆጣጠሪዎች የተሰጣቸው መጠነ ሰፊ ስልጣን በማጣቀሻነት እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
የአካባቢ ተቆጣጣሪዎች ስልጣንa
ሳያሳውቁ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይዙ በማንኛውም ተገቢ መስሎ በሚታያቸው ጊዜ ወደ ማንኛውም ቦታ ወይም ቅጥር ግቢ መግባት
ማንኛውንም ሰው ብቻውን ወይም በምስክር ፊት የመጠየቅ
ከብክለት ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ወረቀት፣ ማህደር ወይም ሌላ ሰነድ መፈተሽ፣ መገልበጥ ወይም ለይቶ መቅዳት
የማንኛውንም ቁስ ናሙናዎች እንደአስፈላጊነቱ ያለክፍያ መውሰድና በአካባቢ ወይም በህይወት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ አለመሆኑን ለመወሰን መመርመር ወይም ማስመርመር
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 300/1995 ወይም ሌላ ህግ መከበሩን ለማረጋገጥ ሸቀጥን፣ የአመራረት ሂደትን ወይም መገልገያን በፍቶግራፍ ማንሳት፣ መለካት፣ መሳል ወይም መፈተሽ
አዋጁን ወይም አግባብ ያለውን ሌላ ህግ በመተላለፍ ጥፋት ተፈጽሞበታል የተባለ መሳሪያን ወይም ሌላ ነገርን መያዝ
የዱር እንስሳት ቁጥጥር ሠራተኛ
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶች ተደብቀዋል ብሎ ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖር ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ማንኛውም ሰው መሬት፣ ህንጻ፣ ድንኳን፣ ተሸከርካሪ፣ የአየር መንኮራኩር ወይም ጀልባ ውስጥ የመግባትና የመፈተሸ እንዲሁም ሻንጣ ወይም እሽግ የመፈተሸ
ሕግን በመተላለፍ በይዞታ ስር የተደረጉ የዱር እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት ውጤቶችን እንዲሁም ጥፋቱ የተፈጸመባቸውን መሳሪያዎች እንዲወረሱ ለማድረግ እንዲቻል በቁጥጥር ስር የማድረግና የሚመለከተው አካል ባወጣው የመመዝገቢያ ቅፅ መሰረት ተገቢውን ደረሰኝ ሰጥቶ የመረከብ
የዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ማፅደቂያ አዋጅ ቁ. 541/1999 አንቀጽ 16 ድንጋጌዎች በመተላለፍ ጥፋት ሲፈጽም የተገኘን ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዞ ለሚመለከተው ህግ አስከባሪ አካል ማስረከብ
የደን ውጤት ተቆጣጣሪ
የደን ውጤቶችን የጫነ ወይም ለመጫኑ የሚጠረጠርን ማናቸውንም ማጓጓዣ በደን መግቢያና መውጫዎች እንደአስፈላጊነቱ በሚመረጡ የሀገር ውስጥ እና የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ አስቁሞ መፈተሸ
የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁ. 542/1999 በመተላለፍ ተዘጋጅተው ሲጓጓዙ ወይም ተከማችተው የተገኙ የደን ውጤቶችን ከድርጊቱ ተጠያቂዎች ጋር የመያዝ
የቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁ. 602/2000 ለማስፈጸም የሚወጡ ደንብና መመሪያዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ቡና ሊገኝበት ይችላል ተብሎ የሚገመትን መጋዘን፣ መኖሪያ ቤት፣ የመንግስት ድርጅት፣ ማጓጓዣ ወይም ማናቸውም ሌላ ቦታ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የመፈተሽ፣ህገ ወጥ ቡና ሲያዝ የማሸግ፣ ምርቱን የማገድ፣ የመያዝ፣ ህገ ወጥነታቸው የማያጠራጥር ሲሆን የቡናው ባለቤት ለፍርድ ቤት ቅሬታ የማቅረብ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የመውረስና የመሸጥ.

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.