የአስተዳደር ጉባዔስያሜና ትርጓሜ


የአስተዳደር ጉባዔ


ስያሜ አስተዳደር ጉባዔ (Administrative Tribunal) ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ ያለ ገለልተኛ የዳኝነት አካል ነው። ከተግባራዊ እይታ አንፃር ከመደበኛ ፍርድ ቤትና ከአስተዳደር መስሪያ ቤት ከፊል ባህሪያትን ይጋራል። ሁለት ባህሪያትን በአንድ ጊዜ ቀይጦ በመያዙ ሙሉ በሙሉ ‘እዚህ ወይም እዚያ’ ብሎ መፈረጅ ይከብዳል። ከፊል ጎኑ አስተዳደራዊ ከፊሉ ደግሞ ዳኝነታዊ በመሆኑ ቁርጥ ያለ መደብ የለውም።a
ይህን ድርብ መልኩን የሚያንፀባርቅ ትርጓሜ ከማየታችን በፊት ‘የአስተዳደር ጉባዔ’ የሚለው አገላለጽ ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር በዚህ መጽሐፍና በሌሎች አገራት ግልጋሎት ላይ የዋለበትን መንገድ በጥቂቱ ማውሳት ያስፈልጋል። በአገራችን በተለምዶ ‘የአስተዳደር ፍርድ ቤት’ ስንል በእንግሊዝ፣ በአውስትራሊያና በሌሎች አገራት Administrative Tribunal በመባል የሚታወቀውን ከላይ የተጠቀሰውን ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ ያለ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ለመዳኘት የተቋቋመ አካል ማለታችን ነው። ሆኖም አማርኛውን ከእንግሊዝኛው ጋር ስናዛምደው የአስተዳደር ፍርድ ቤት እና Administrative Tribunal አቻ መልዕክት አያስተላልፉም። የአስተዳደር ፍርድ ቤትን በትክክል የሚገልጸው እንግሊዝኛ Administrative Court ሲሆን የእንግሊዝኛውን ‘Administrative Tribunal’ የሚወክል የአማርኛ ቃል ደግሞ ‘የአስተዳደር ጉባዔ ነው።
Administrative Court በእንግሊዝ አጣሪ ዳኝነት ስልጣን ያለውን የከፍተኛውን ፍርድ ቤት የሚጠቁም ሲሆን ‘የአስተዳደር’ የሚለው ቅጥያ የተጨመረበት በአጣሪ ዳኝነት (Judicial Review) ስልጣኑ እንጂ ከአስተዳደሩ (ከስራ አስፈፃሚው) የመንግስት አካል ጋር ቅርበት ሆነ ግንኙነት ስላለው አይደለም። ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ መደበኛ ፍርድ ቤት ነው። በጀርመን ‘Administrative Court’ የሚለው መጠሪያ ከታች ወደ ላይ ራሳቸውን ችለው ከተቋቋሙት አምስትb ዓይነት መደበኛ ፍርድ ቤቶች መካከል አንደኛው ነው።c ወደ ፈረንሳይ ስንመጣ Administrative Court በብዙ መልኩ ‘ፀጉረ-ልውጥ’ ፍርድ ቤት ነው። በአወቃቀሩ የሥራ አስፈፃሚው አካል ሲሆን በዳኝነት ተግባሩ ከመደበኛው ፍ/ቤት ጋር የሚስተካከል ነጻነት ያለው ገለልተኛ የዳኝነት ተቋም ነው። በአደረጃጀቱ የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮችን እንደሚያዩት መደበኛ ፍርድ ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ፣ የይግባኝ ሰሚ እና የሰበር ስልጣን ያላቸው የፍርድ ቤት ሰንሰለቶች አሉት።
በዚህ መጽሐፍ ‘የአስተዳደር ጉባዔ’ የሚለው አገላለጽ ጥቅም ላይ የዋለው በእንግሊዝ፣ በጀርመንን አሊያም በፈረንሳይ ያለውን Administrative Court በማመልክት ሳይሆን በተቃራኒው የእንግሊዝኛውን Administrative Tribunal አቻ ትርጉም በመወከል ነው።
ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ምሁራን ከተግባራቱ አንጻር በሚከተለው መልኩ ገልጸውታል።
Broadly, a tribunal is an adjudicative body, empowered to hear and decide disputes in particular circumstances. Tribunals are sometimes referred to as court substitutes, in that they have the power to make legally enforceable decisions, but they are regarded as having the advantages over courts of speed, cheapness, informality, and expertise.d
Tribunal ቃሉ ሲተረጎም ‘ችሎት’ ወይም ‘ዳኛው የሚያስችልበት ቦታ’ (seat of the judge)፣ ጉባዔ፣ ሸንጎ ማለት ነው። ስለሆነም የአስተዳደር ጉባዔ (Administrative Tribunal) ማለት በህግ ተለይተው የተደነገጉ የአስተዳደር ክርክሮችን ሰምቶ የመወሰን ስልጣን ያለው የዳኝነት አካል ማለት ነው። በስልጣኑ ስር የሚያያቸው ጉዳዮች በዋነኛነት በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ ክርክሮችን ቢሆንም አልፎ አልፎ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ክርክሮችን (ለምሳሌ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ) ይዳኛል።
አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ
እንደ ፕሮፌሰር ዌድና ፎርሲይዝ እይታ አስተዳደራዊ ደንብና መመሪያ የመደንገግ ስልጣን የአስተዳደር ህግ ዋነኛ መገለጫ ነው።e የአስተዳደር ጉባዔዎች ከሚሰጡት ግልጋሎትና እያሳዩት ካለው ፈጣን ዕድገት አንጻር በሁለተኛነት የህጉ መገለጫ አድርገን ብንወስዳቸው አንሳሳትም። እነዚህ የዳኝነት ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥርና በዓይነት እየበዙ መምጣታቸውና የዳኝነት ስልጣናቸው ክልል እየሰፋ መሄዱ የአስተዳደር ህግ ትልቁ ስኬት እንደሆነ የመስኩ ምሁራን በአፅንኦት የሚገልፁት ጉዳይ ሆኗል።f ፒተር ኬን ይህን ስኬት እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
One of the most significant, large-scale and enduring constitutional developments of the past 150 years has been the creation of a set of governmental institutions known, in major common law jurisdictions outside the United States, as ‘tribunals’.g
የአስተዳደር ጉባዔዎች የመፈጠራቸው ዋነኛ ምክንያት ዜጎች በአነስተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው። በብዙ አገራት (ለምሳሌ በእንግሊዝና አውስትራሊያ) እነዚህ የዳኝነት አካላት ከሞላ ጎደል ይህን ዓላማቸውን ከግብ በማድረስ ውጤታማ ሆነዋል። በህግ የሚሰጣቸው የዳኝነት የስልጣን ክልል ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች አንጻር ውስን ቢሆንም በመንግስትና በግለሰብ ብሎም በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ጉዳዮችን ለምሳሌ በጤና፣ በትምህርት፣ በጨረታ፣ በፈቃድ አሰጣጥ፣ ስደተኞችና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት በመስጠት እንደ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገድ ውጤታማና ፍሬያማ ለመሆን በቅተዋል።
ስለ አስተዳደር ጉባዔ ስኬትና ውጤታማነት ስንነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ የምናገኘው እውነታ የዚህ ተቃራኒ ነው። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በዋነኛነት ግን ሁለቱን ማንሳቱ አግባብነት አለው። የመጀመሪያው ዋነኛ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ጉባዔዎች በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መዘንጋታቸውና ህገ መንግስታዊ ቦታቸው ጥርት ብሎ አለመታወቁ በዚህም ምክንያት ወጥ፣ ነፃና ውጤታማ አደረጃጀት የሌላቸው መሆኑ ነው።h
በሁለተኛነት ስለ አስተዳደር ፍርድ ቤት ያለው ግንዛቤና እይታ ራሳቸውን እንደቻሉ የፍትህ ስርዓቱ ተጓዳኝ ተቋማት ሳይሆን በአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ስር ያሉ ቅሬታ ሰሚ አካላት ተደርገው መቆጠራቸው ነው።
ከጠቀሜታቸው አንጻር በአነስተኛ ወጪ፣ ቀላል በሆነ የክርክር ስነ ስርዓት፣ ፈጣን የአስተዳደር ፍትህ በመስጠት ለዜጎች የሚያበረከረቱት አስተዋፅኦ እጅጉን የጎላ ነው።i በተለይ በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚነሱ እጅግ በርካታ አስተዳደራዊ ክርክሮችን በተሻለና ውጤታማ በሆነ መንገድ በመፍታት የፍርድ ቤቶችን ጫና ያቃልላሉ።
በፍርድ ቤት ያለው የክስ ሂደት የተንዛዛ ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ በተለይ ለድሃው የህብረተሰብ ክፍል በቀላሉ ፍትህ ማጎናፀፍ ይሳነዋል። ይህም ከአስተዳደሩ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ክርክሮች ሁለት ጉዳቶችን ያስከትላል። በአንድ በኩል በተንዛዛ ክርክር ምክንያት ውጤታማ አስተዳደር አይኖርም። በሌላ በኩል ዜጎች በፍትህ እጦት ይንገላታሉ።
ሌላው ጠቀሜታ ልዩ ዕውቀት ያካበተ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የሙያ ክህሎትን ማጎልበታቸው ላይ ነው። አብዛኛዎቹ ጉባዔዎች የሚያዩት ጉዳይ ውስን ከመሆኑ አንጻር ተደጋጋሚ ጉዳዮች ቀርበው መወሰናቸው የአስተዳደር ዳኛው በመስኩ ሰፊ ተሞክሮና ዕውቀት እንዲቀስም ያስችለዋል። በተጨማሪ የአስተዳደር ክርክሮችን የሚያየው ዳኛ በቦታው ሲሾም ከህግ ዕውቀት በተጨማሪ ስለሚያየው ጉዳይ ልዩ እውቀት ስለሚኖረው የህግ ዕውቀት ብቻ ኖሮት የተለያዩ ዓይነት ጉዳዮችን ከሚያየው የመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በተሻለ መልክ ውጤታማ ውሳኔ ለመስጠት ተመራጭ ያደርገዋል። የአስተዳደር ዳኞች ከህግ ዕውቀት በተጨማሪ ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን ሙያ የጨበጡ በመሆኑ በክርክር ወቅት ሊነሱ የሚችሉ ህግ ነክ ያልሆኑ ጭብጦችን በቀላሉ ተረድተው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያስችላቸዋል።
ለማጠቃለል ያህል የሚከተሉትን ነጥቦች እንደ አስተዳደር ጉባዔ ጠቃሜታዎች መጥቀስ እንችላለን።
ጉዳዩን ሰምቶ ለመወሰን አጭር ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ ያለ ረጅም ቀጠሮ ፈጣን ውሳኔ ይሰጣል።
በአስተዳደር ክርክር አብዛኛውን ጊዜ ጠበቃ ማቆም አስፈላጊ ባለመሆኑና መዝገብ ለማስከፈት መጠነኛ ወይም ከነጭራሹ ክፍያ ስለማይኖር የተከራካሪዎችን ወጪ ይቆጥባል።
በቦታው የሚቀመጠው የአስተዳደር ዳኛ ለጉዳዩ ልዩ እውቀት ያለው በመሆኑ የተሻለ ውሳኔ ይሰጣል።
መደበኛውን ስነ ስርዓትና የማስረጃ ህግ የመከተል ግዴታ ሳይኖርበት እንደየሁኔታው ተፈጻሚ የሚሆኑ ኢ-መደበኛ የስነ ስርዓት ደንቦች ላይ ተመርኩዞ ክርክሩን በመምራት የተንዛዛ የክርክር ስርዓትን ያስቀራል።
አስፈላጊነቱና ጠቀሜታው እንዳለ ሆኖ ደካማ ጎኑንም በጥቂቱ መዳሰሱ ጥቅምና ጉዳቱን ከመመዘን አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው። ከደካማ ጎኖች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
በጊዜ ሂደት የተወሰኑ የአስተዳደር ጉባዔዎች መለያቸው የሆነውን ኢ-መደበኛ ስነ ስርዓት በመተው ጥብቅ የስነ ስርዓት ደንቦች የሚከተሉ ፍርድ ቤቶች እየሆኑ መጥተዋል።
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በስራ አስፈፃሚው እጅ ስለሚወድቁ ነፃና ገለልተኛ አካላት አይደሉም።
አንዳንዶቹ የሰለጠነ የሰው ኃይል የላቸውም። ለውሳኔያቸው በቂ ምክንያት አይሰጡም።
በአስተዳደር ፍርድ ቤት ተከራካሪ የሆነ ባለ ጉዳይ የህግ እርዳታ አያገኝም።
መለያ ባህሪያት
የአስተዳደር ጉባዔን ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር የሚያመሳስለው ነጥብ ቢኖርም ከፊል ጎኑ አስተዳደራዊ እንደመሆኑ የራሱ ባህርያት አሉት። በአጠቃላይ መለያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ መሰረታዊ መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው።
በህግ መቋቋም
የአስተዳደር ጉባዔ ሊቋቋም የሚችለው ፓርላማው (የተወካዮች ምክር ቤት) በሚያወጣው አዋጅ ነው። ህግ አውጪው አንድን የአስተዳደር ፍርድ ቤት ሲያቋቁም ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ምክንያት ተንተርሶ ሲሆን ይህም የመንግስት አስተዳደርን ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ ወይም ዜጎች በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ርትዐዊ ዳኝነትና አስተዳደራዊ ፍትህ እንዲያገኙ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገድ ማቅረብ ሊሆን ይችላል። በዚህ መሰረት በኢትዮጵ ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ጉባዔዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ከፊሎቹ እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ።
የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ
ስለ አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ የወጣ አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 145/1/ እና /2/
የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን
የፌደራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁ. 983/2008 አንቀጽ 86/1/
የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍ/ቤት
የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁ.1064/2010 አንቀጽ 79
የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ
የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁ. 714/2003 አንቀጽ 57
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁ. 813/2006 አንቀጽ 33
የስደተኞች ጉዳይ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ
የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1110/2011 አንቀጽ 17
የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ
የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ አዋጅ ቁ. 818/2006
የአእምሯዊ ንብረት ትሪቡናል
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁ. 872/2007
የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ
የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006 አንቀጽ 48
የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ ቁ. 721/2004 አንቀጽ 30
የፌደራል ዓቃብያነ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ
የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 943/2008 አንቀጽ 12/1/
የህንፃ ግንባታ ይግባኝ ሰሚ ቦርድ
ደንብ ቁ. 243/2003 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህንፃ ደንብ አንቀጽ አንቀጽ 21/1/
የምርት ገበያ ባለስልጣን
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁ. 551/1999 አንቀጽ 7
የኢንቨስትመንት ቦርድ
ደንብ ቁ. 313/2006 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድንና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ
የመንግስት ግዥና አቤቱታ አጣሪና ዉሳኔ ሰጪ ቦርድ
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 ዓ.ም አንቀጽ 70/1/
የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማኅበር የክርክር አወሳሰን ኮሚቴ
የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 841/2006 አንቀጽ 56
የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ
የከተማ መሬት ይዞታ ማረጋገጥ እና ምዝገባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 324/2006 አንቀጽ 22
የክሪፕቶ መሠረተ ልማት ካውንስል
የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁ. 1072/2010 አንቀጽ 50
አስገዳጅ ውሳኔ
የአስተዳደር ጉባዔዎች ክርክሩን ሰምተው የሚሰጡት ውሳኔ እንደማንኛውም የመደበኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈፃሚነት ያለው አስገዳጅ ወይም አሳሪ ውሳኔ ነው። ተፈፃሚና አሳሪ የሆነ ውሳኔ የማይሰጥ አካል እንደ አስተዳደር ጉባዔ ለመቁጠር ያስቸግራል። ስለሆነም የዲሲፕሊን ኮሚቴዎችና ሌሎች በህግ ወይም በየመ/ቤቱ የሚቋቋሙ አጣሪና መርማሪ አካላት ከአስተዳር ጉባዔ ማእቀፍ ውጪ ናቸው። የጠበቆች ዲሲፕሊን ጉባዔj ከአገር ማስወጫ ትዕዛዝ ላይ አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴk የይቅርታ ቦርድl የጤና ሙያ ስነ ምግባር ኮሚቴm የቱሪስት አገልግሎት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴn የአመክሮ ኮሚቴo የደህንነተ ህይወት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴp ሁሉም የመወሰን ስልጣን ላለው ሚኒስቴር ወይም የበላይ አካል የውሳኔ ሀሳብ ከማቅረብ በስተቀር አስገዳጃ ውሳኔ ማስተላለፍ የማይችሉ በመሆኑ እንደ አስተዳደር ጉባዔ አይፈረጁም።
ስነ-ስርዓት
የአስተዳደር ጉባዔ የመቋቋሙ ዐቢይ ምክንያት በአነስተኛ ወጪና ቀላል የክርክር ስርዓት ቀልጣፋ ፍትህ መስጠት በመሆኑ በመደበኛው ፍ/ቤት የክርክር ሂደት ተፈፃሚ የሚሆኑት ጥብቅና የማያወላዱ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ አይሆኑበትም። ሆኖም ለመሰረታዊ የስነ-ስርዓት ደንቦች ተገዢ መሆን አለበት።
ተፈጻሚ የሚሆኑት የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎች አልፎ አልፎ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ የሚዘረዘሩ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ግን ጉባዔው የራሱን ስነ-ስርዓት በውስጠ ደንብ እንዲወስን ስልጣን ይሰጠዋል። ከአነስተኛ መሰረታዊ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የተከራካሪ ወገኖች ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ፣ (የመሰማት መብት) አድሎአዊ ያልሆነ ውሳኔ ወይም ፍትህዊ ውሳኔ መስጠት እንዲሁም በማስረጃና በምክንያት የተደገፈ ውሳኔ መስጠት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
የአስተዳደር ጉባዔን ከመደበኛው ፍ/ቤት በስነ-ስርዓት ረገድ የተለየ የሚያደርገው ለፍትሀዊ ስነ-ስርዓት ህጉ ተገዢ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ባመቸው መንገድ የሚመራበትን ስነ-ስርዓት በራሱ ለመወሰን ስልጣን የተሰጠው መሆኑ ጭምር ነው። ይህም በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ የተለያየ ስነ-ስርዓት ተፈፃሚ በማድረግ እንደየሁኔታው እንዲለጠጥ ይረዳዋል። ተለጣጭነቱ ግን ወጥ አሰራርን ጨርሶ በማጥፋት ወደ በዘፈቀደ አካሄድ የሚያመራ መሆን የለበትም። ከጉዳይ ጉዳይ ቢለያይም በተለጣጭነት እና ወጥ አሰራር መካከል ሚዛኑን የሚጠብቅ መስመር ሊኖር ይገባል። ጠቅለል ባለ አነጋገር የመደበኛ ፍ/ቤቶች የማያወላዳ ግትር የስነ-ስርዓት አካሄድ በአስተዳደር ፍ/ቤቶች ተፈፃሚ አለመሆኑ በአካሄዳቸው ተለጣጭነት ውጤታማ እንዲሆኑ የተመቻቸ እድል ይሰጣቸዋል።
የዳኞች ሚና
በስነ-ስርዓት ረገድ በኮመን ሎው እና ሲቪል ሎው አገራት መካከል ያለው የመርማሪ (inquistiorial) እና የሙግታዊ (adversarial) አቀራረብ የአስተዳደር ጉባዔና የመደበኛ ፍ/ቤት የልዩነት ነጥብ ተደርጐ ይወሰዳል። በሁለቱ የህግ ስርዓቶች ጉባዔዎች በጉዳዩ ወይም በክርክሩ ላይ ካላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ አንጻር አካሄዳቸው የመርማሪነት እንደሆነ ስምምነት አለ። ከስምምነቱ ባሻገር ብዙዎቹ የመስኩ ባለሙያዎች የአስተዳደር ጉባዔ ይህን መርማሪ አካሄድ መከተል እንዳለበት ጠንካራ መከራከሪያ ያቀርባሉ።
እንደ ፒተር ሌይላንድ እና ቴሪውድስ ገለጻ፤
የአስተዳደር ጉባዔ መርማሪ የስነ-ስርዓት አቀራረብ መከተል ይኖበታል። ይህ ሲሆን ነው በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ምርመራ በማድረግ ፍትህ መሰራቱን ማረጋገጥ የሚችለው።
መርማሪ በሆነው አካሄድ እውነትን ፈልፍሎ ማውጣት ለተከራካሪ ወገኖች ብቻ የሚተው ሳይሆን ችሎቱን የሚመራው ዳኛም በንቃት ይሳተፍበታል። ይህ መርማሪ የክርክር አመራር ስርዓት በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሙግት ላይም የሚታይ ቢሆንም በገዘፈ መልኩ በተጨባጭ የሚንፀባረቀው ግን በአስተዳደር ጉባዔ በሚካሄዱ ክርክሮች ላይ ነው።
ቁጥብነት
ቁጥብነት የአስተዳደር ጉባዔ ዋነኛ መገለጫው ነው። የክርክር ሂደቱ እንደ መደበኛው ፍ/ቤት ከፍተኛ ወጪን አይጠይቅም። ተከራካሪ ወገኖች ለሚያቀርቡት አቤቱታ በመደበኛው ታሪፍ መሰረት ዳኝነት አይከፍሉም። አብዛኛውን ጊዜ የጠበቃ ውክልና አስፈላጊ ስለማይሆን ተጨማሪ ወጪ አይኖርም። ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ ወጪና ኪሳራ በማቻቻል የሚታለፍ ሲሆን አልፎ አልፎ አነስተኛ ኪሳራ ሊወሰን ይችላል።
ስልጣንና ተግባር
የአስተዳደር ጉባዔዎች የዳኝነት የስልጣን ክልል (Judicial Jurisdiction) ጠባብና በህግ ተለይተው በተጠቀመጡ ውሱን ጉዳዮች ላይ ብቻ የተገደበ ነው። በአንጻሩ መደበኛ ፍ/ቤቶች እርስ በርሳቸው የይዘት ቅርበትና ዝምድና የሌላቸውን የተለያዩ የህግ ክፍሎችን የሚመለከቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን አላቸው። ጠባብ የሆነው የዳኝነት ስልጣን ልዩ እውቀትን በማጐልበት ረገድ የጐላ አሰተዋጽኦ ያበረክታል። ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የዳኝነት ስልጣን በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚነሱ የወል የስራ ክርክሮች ላይ ብቻ ነው።q የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እንዲሁ የግብር አሰባሰብና ጉምሩክን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ ሲሆን የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ከጡረታ መብትና ጥቅም ጋር በተያያዘ የዳኝነት ስልጣን አለው።
ምንም እንኳን የጉባዔዎች የዳኝነት ስልጣን በጥቅሉ ሲቀመጥ ጠባብ ቢመስልም በስራቸው ከሚወድቁት ጉዳዮች ብዛትና ከሚነሱት ጭብጦች ዓይነት አንጻር ስልጣናቸው ትንሽ የሚባል አይደለም። ለአብነት ያህል የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምንም እንኳን የስልጣኑ ክልል የጡረታ መብትና ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ቢሆንም ጉባዔው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ጡረተኛ የሚያቀርበውን ይግባኝ ስለሚሰማ በአይነት ሆነ በቁጥር በርካታ ጉዳዮችን ያስተናግዳል።
ከዳኝነት ስልጣን በተጨማሪ በክርክሩ ሂደት የሚኖረው ስልጣን ከባህርያቱ አንጻር መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ነው። የአስተዳደር ጉባዔ ከፊል የዳኝነት አካል እንደ መሆኑ ከሞላ ጐደል መደበኛ ፍርድ ቤት የሚኖሩትን ስልጣንና ተግባራት ይጋራል። ስለሆነም በማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተለይቶ በግልፅ ቢመለከትም ባይመለከትም እንደ ማንኛውም ፍ/ቤት ተከራካሪ ወገኖችና ምስክሮች እንዲቀርቡ ወይም ቃላቸውን እንዲሰጡ የማድረግ፣ የመሀላ ወይም የማረጋገጫ ቃል የመቀበል፣ ለክርክሩ በማስረጃነት አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ከሚመለከተው ሰው ወይም ድርጅት እንዲቀርቡ የማድረግ ብሎም በማናቸውም ድርጅት ውስጥ ገብቶ አስፈላጊ መረጃዎችን የመሰብሰብና ምስክሮችን የመስማት የመሳሰሉ ተግባራትን ለማከናወን ስልጣን አለው። በተጨማሪም በክርክሩ ወቅት የሚያስተላልፋቸው ትእዛዞችና ውሳኔዎች አስገዳጅ ተፈጻሚነት አላቸው።
የእነዚህ ባህሪያት መኖር ከመደበኛ ፍ/ቤት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ሁለት ጭብጦች የጠራ መልስ ይሰጠናል። የመጀመሪያው በክርክር ሂደት ፍ/ቤት የመድፈር ውጤትን ይመለከታል። የአስተዳደር ጉባዔ በያዘው ጉዳይ ላይ በክርክር ወቅት የፍ/ቤት መድፈር ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ወዲያውኑ ቅጣት ማስተላለፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ዳኝነታዊ የሆነው ባህርዩ አዎንታዊ መልስ ይሰጠናል። በወንጀል ህግ አንቀጽ 449 ላይ የተመለከተው ፍ/ቤትን የመድፈር ወንጀል ከሚያቋቁሙት ህጋዊ ክፍሎች መካከል በድንጋጌው ላይ ከተመለከቱት ድርጊቶች መኖር በተጨማሪ ድርጊቱ በፍ/ቤት፣ ምርመራ ወይም የዳኝነት ስራ በሚከናወንበት ወቅት መሆን አለበት። የአስተዳደር ጉባዔ በከፊልም ቢሆን ዳኝነታዊ ስልጣን ያለው የዳኝነት አካል እንደመሆኑ የጉባዔው ዳኛ ላይ ማፌዝ፣ መዛት፣ መሳደብ ወይም በማናቸውም መንገድ ስራውን ማወክ የፍ/ቤት የመድፈር ወንጀል ነው። ስለሆነም ድርጊቱ በተፈፀመ ጊዜ ዳኛው ወዲያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስንበት ይችላል።
በሁለተኛነት ተያይዞ የሚነሳው ጭብጥ በጉባዔ ፊት ሀሰተኛ ቃል ወይም ምስክርነት መስጠት በወንጀል የማስቀጣቱ ሁኔታ ነው። በወንጀል ህግ አንቀጽ 425 እና 453 ላይ ተከራካሪ ወገን የሚሰጠው ሀሰተኛ ቃል እና ሀሰተኛ የምስክርነት ቃል፣ አስተያየት ወይም ትርጉም በመደበኛ ፍ/ቤት ፊት ብቻ ሳይሆን የዳኝነት ነክ ስልጣን ባለው አካል ፊት የተፈፀመ ከሆነ በወንጀል ያስቀጣል። ምንም እንኳን የወንጀል ህጉ በግልፅ ስለ አስተዳደር ጉባዔ ባያወራም ‘የዳኝነት ነክ ስልጣን ያለው አካል’ ከፊል የዳኝነት ስልጣን ያለውን የአስተዳደር ጉባዔን እንደሚጨምር ግልፅ ነው።
አመዳደብ
ጉባዔዎች እንደ ቅርጻቸው፣ ስልጣናቸውና አወቃቀራቸው የተለያየ መልክ ይዘው ይቋቋማሉ። አንድ የመስኩ ምሁር ከዳኝነት ስልጣናቸው እና መዋቅራቸው አንጻር በአራት መንገዶች እንደሚከተለው ይከፋፍላቸዋል።r ይኸውም፤
ልዩ (ውስን) እና ሁሉን አቀፍ (ሁለገብ ወይም ዘርፈ ብዙ)
ነጠላ እና ድርብ (አንድ እርከን እና ሁለት እርከን)
የግል እና የአስተዳደር ክርክር ሰሚ
የመጀመሪያ ደረጃ እና አጣሪ
ልዩ እና ሁሉን አቀፍ
ልዩ የአስተዳደር ጉባዔ ስልጣኑ በአንድ ውስን ዘርፍ ላይ ብቻ የተገደበ ነው። በእኛ አገር የሚገኙት ጉባዔዎች ሁሉም በልዩ የአስተዳደር ጉባዔ ስር ይመደባሉ። ለምሳሌ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሚያያቸው ጉዳዮች የወል ስራ ክርክሮችን ብቻ ሲሆን የመንግስት ሰራተኞች የአስተዳደር ፍ/ቤት በበኩሉ በመንግስት ሰራተኞች የሚቀርቡ የስራ ክርክር ቅሬታዎችን ተቀብሎ ዳኝነት ይሰጣል።
ሁሉን አቀፍ የሚባለው ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ ሳይወሰን ተቀራራቢነት የሌላቸው ዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ክርክሮችን ለማየትና ለመዳኘነት ሰፊ ስልጣን ተሰጥቶት የሚቋቋም የአስተዳደር ጉባዔ ነው። ስለሆነም ከንግድ ፈቃድ መሰረዝ አንስቶ እስከ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መባረር፣ የንግድ ድርጅት መዘጋት፣ ከአገር የማስወጣት እርምጃ፣ የጡረታ መብት አወሳሰን ወዘተ…ሁሉንም ጠቅልሎ በመያዝ በተለያዩ የአስተዳደር ክርክሮች ላይ ዳኝነት ይሰጣል። ይህን መሰሉ የአስተዳደር ጉባዔ በመዋቅርና በአደረጃጀት ራሱን የቻለ ህጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሆኖ የሚቋቋም ሲሆን በስሩም የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያዩ ችሎቶች ይኖሩታል፡
አሀዳዊ ቅርጽ ይዞ የሚቋቋም ሁሉን አቀፍ የአስተዳደር ጉባዔ ከውጤታማነት አንጻር ሲታይ በብዙ መልኩ ተመራጭነት አለው። በመጀመሪያ በወጪ እና በሰው ኃይል ረገድ ውጤታማ አጠቃቀም ያዳብራል። ለምሳሌ ያህል ለጉባዔው ስራ የሚያስፈልጉ ሬጅስትራሮች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቁጥር ይቀንሳል። ምናልባትም ሁሉንም ስራዎች በአንድ ሬጅስትራር ማከናወን ይቻላል። ለሌሎች ግብዓቶች (ቤተ-መጻህፍት፣ መኪና፣ ኮምፒውተር ወዘተ…) የሚወጣው ወጪም በእጅጉ ይቀንሳል። በተጨማሪም ሁሉም የአስተዳደር ዳኞች በአንድ ተቋም ውስጥ ስለሚታቀፉ በተለያዩ ችሎቶች እያዘዋወወሩ ለማሰራት አመቺ ያደርገዋል። ዳኞች በየችሎቱ እየተዘዋወሩ ሲሰሩ በተለያዩ የአስተዳደር ክርክሮች በሚነሱ የህግ እና ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሰፋ አመለካከት እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣቸዋል።
ነጠላ እና ድርብ
የአስተዳደር ጉባዔ ውሳኔ በሌላ ይግባኝ ሰሚ የአስተዳደር ጉባዔ በድጋሚ በይግባኝ ሊታይ ይችላል። በዚህ መልኩ በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ የተዋቀረ የአስተዳደር ጉባዔ ድርብ (ባለ ሁለት እርከን) በሚል ይመደባል። በአንጻሩ የስር የአስተዳደር ጉባዔ ውሳኔን በይግባኝ ሰምቶ ዳኝነት የሚሰጥ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ከሌለ ነጠላ (አንድ እርከን) ተብሎ ይጠራል። በአገራችን የሚገኙት የአስተዳደር ጉባዔዎች በሙሉ የተዋቀሩት በአንድ እርከን ነው። ምንም እንኳ የተወሰኑት ‘ይግባኝ ሰሚ’ የሚል ቅጥያ ቢይዙም አንዳቸውም በስራቸው ከሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ካለው ጉባዔ ይግባኝ አይሰሙም። ‘ይግባኝ’ የሚለው አገላለፅ ጉባዔው በአንድ የአስተዳደር መስሪያ ቤት የተሰጠ ውሳኔ እንደገና የማየትና የማጣራት የዳኝነት ስልጣን እንዳለው ለማመልከት ነው። የጉባዔው ውሳኔ በይግባኝ የሚታየው በመደበኛ ፍርድ ቤት እንጂ በሌላ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ አይደለም።
የግል እና የአስተዳደር ክርክር ሰሚ
በግል ክርክር ሰሚ እና የአስተዳደር ክርክር ሰሚ ጉባዔዎች መካከል ያለው ልዩነት ከሚያዩት ጉዳይ ጋር ይያያዛል። በሁለተኛው ረድፍ ውስጥ የሚወድቁት በመንግስትና በግለሰብ መካከል የሚነሱ የአስተዳደር ክርክሮችን ይዳኛሉ። ጉዳዩ በግለሰቦች መካከል የሚነሳ ክርክር በሚሆንበት ጊዜ የግል ክርክር ሰሚ የአስተዳደር ጉባዔ /ወይም ባጭሩ የግል የአስተዳደር ጉባዔ/ በሚል ይመደባል። በአገራችን የግል ተብለው ሊጠሩ ከሚችሉ የአስተዳደር ጉባዔዎች መካከል የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ፤ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት እና በመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማኅበራት አዋጅቁጥር 841/2006 የተቋቋመው የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማኅበር የክርክር አወሳሰን ኮሚቴ ተጠቃሽ ናቸው። የአስተዳደር ተብለው ከሚመደቡት መካከል ደግሞ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን፣ የመንግስት ሠራተኞች የአስተዳደር ፍ/ቤት እና የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ይጠቀሳሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ
የአስተዳደር ጉባዔ የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ሰምቶ በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኑ በቀረበለት ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ውሳኔ ሰጪ አካል ሆኖ ሊቋቋም ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በአንድ አስተዳደር መስሪያ ቤት የተሰጠን ውሳኔ እንደገና የሚመረምርና የሚያጣራ ቅሬታ ወይም ይግባኝ ሰሚ አካል ሆኖ ሊቋቋም ይችላል። የፌደራል ዓቃብያነ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኑ በዓቃቤ ህግ ላይ የሚቀርብን ክስ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል። የውሳኔ ሰጭነት ስልጣን ባይኖረውም የጠበቆች ዲሲፕሊን ጉባዔ የመጀመሪያ ደረጃ ሲሆን የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን፣ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ እና የመንግስት ሠራተኞች የአስተዳደር ፍርድ ቤት ሁሉም አግባብነት ያለው መስሪያ ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን የሚያዩ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔዎች ናቸው። የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እንዲሁ የአሠሪውን ውሳኔ ህጋዊነትና አግባብነት የሚያጣራ ጉባዔ ነው።
መዋቅርና አደረጃጀት፡ ንጽጽራዊ እይታ
የአስተዳደር ጉባዔ አደረጃጀት በተለያዩ አገራት የተለያየ ቅርፅ ይይዛል። ጠቅለል ባለ አነጋገር የፈረንሳይን የአስተዳደር ህግ በሚከተሉት እና በተቃራኒው የእንግሊዝ የህግ ስርዓት በሚከተሉት አገራት መካከል የሰፋ ልዩነት ይታይል።
ለንፅፅር እንዲረዳን የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝና አውስትራሊያ የአስተዳደር ጉባዔዎች ያላቸውን አደረጃጀትና መዋቅር በቅደም ተከተል እናያለን። በየአገራቱ ያለው አደረጃጀት የተቃኘው እንደሚከተሉት የህግ ስርዓት በተለይም የአስተዳደር ህግ ስርዓት እንዲሁም ነባራዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ቢሆንም ንጽጽሩ በአገራችን ውጤታማ የአስተዳደር ጉባዔ ስርዓት በመዘርጋት ረገድ ጠቃሚ ግብዓት ሊሆን ይችላል።
በፈረንሳይ
በፈረንሳይ የአስተዳደር ፍርድ ቤትs ሲወሳ መነሻችን የፈረንሳይ የአስተዳደር ህግ (droit administratif) ነው። ፈረንሳይ የምትከተለው የአስተዳደር ህግ የታሪካዊ ክስተት ውጤት ሲሆን የራሱ መገለጫ ባህሪያት አሉት። በዋነኛነት ግን ሁለት ራሳቸውን የቻሉ የፍ/ቤት ስርዓት ያላት መሆኑ ለአስተዳደር ህጉ መሰረታዊ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
በአንድ በኩል በግለሰቦች መካከል የሚነሱ የፍትሐብሔር ክርክሮችን የሚያይ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ የተዘረጋ መደበኛ የፍርድ ቤት ስርዓት ሲኖር በሌላ በኩል በግለሰብና በአስተዳደሩ የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ውሳኔ የሚሰጥ ራሱን የቻለ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ስርዓት ተዘርግቷል። በዚህ መዋቅር ውስጥ Conseil d’Etat (የመንግስት ምክር ቤት በእንግሊዝኛው Council of State) የበላይ የአስተዳደር ፍ/ቤት ሲሆን አስተዳደራዊ ክርክሮችን በተመለከተ የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን አለው። ይህም ማለት በግለሰብና በመንግስት የሚነሱ የአስተዳደር ክርክሮች በመደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሆነ በሌላ መንገድ የሚስተናገዱበት አጋጣሚ የለም።
የዚህ የድርብ ወይም የሁለትዮሽ የፍርድ ቤት ስርዓት ጠንሳሽና ቀያሽ የ17ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ንጉስ የነበረው ናፓሊዮን ቦናፓርቴ ነው። ናፓሊዮን በስልጣን በነበረበት ወቅት በፓርላማው ሆነ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ላይ እምነት አልነበረውም። ስለሆነም በወቅቱ በፖለቲከኞችና ምሁራን ዘንድ በስፋት የሚቀነቀነውን የስልጣን ክፍፍል መርህ ለጥጦ በመተርጎም አስተዳደሩ በስሩ የሚነሱትን ክርክሮች በራሱ በአስተዳደሩ ማለቅ አለባቸው ወደ ሚል ድምዳሜ አድርሶታል። በዚህ መሰረት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለአስተዳደሩ በአማካሪነት ሚና ብቻ ተወስኖ የነበረውን conseil detat የዳኝነት ስልጣን በመስጠት እንደ የበላይ የአስተዳደር ችሎት ማቋቋም ችሏል። ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ1799 ዓ.ም. ሲሆን conseil detat ከሁለት ክፍለ ዘመናት በላይ ባስቆጠረው እድሜው ውጤታማነቱን በማስመስከር የፈረንሳይ ኩራት ከመሆን አልፎ በብዙ አገራት የሚደነቅና በአምሳያነት በህግ ስርዓታቸው የሚታቀፍ ተቋም ሆኗል።t
በአሁን ወቅት በፈረንሳይ ያለው የአስተዳደር ፍ/ቤት ስርዓት በሶስት ደረጃዎች የተከፋፈለ ነው። በደረጃው መነሻ ላይ የሚገኙት የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች (tribunaux administratifs) ሲሆኑ በግለሰብና በአስተዳደሩ መካከል የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን አይቶ የመወሰን የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን አላቸው።u በመቀጠልም የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔዎችን በይግባኝ የሚያይ የአስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት (Administratifs d’appeal) ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመጨረሻ ደረጃ ላይ ከይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በይግባኝ ስልጣኑ ከተሰጠ ውሳኔ ላይ የመጨረሻ የይግባኝ ስልጣን እንዲሁም የሰበር እና የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ያለው Consei detat በመባል የሚጠራው ተቋም በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የመጨረሻና የበላይ የዳኝነት አካል ነው።v
በእንግሊዝ
እ.ኤ.አ ከ1974 ዓ.ም ወዲህ በእንግሊዝ አስተዳደራዊ ክርክሮችን የሚዳኙ የአስተዳደር ጉባዔዎች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል። የመንግስት ሚና ወደ ማህበራዊ አገልግሎት አቅራቢነት እየተለወጠ መምጣቱና በዚህም የመንግስትና የግለሰብ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እየሰፋ መሄዱ ከግንኙነቱ የሚመነጩ ክርክሮችን በአማራጭ ለመፍታት የተለያዩ የአስተዳደር ጉባዔዎችን (Administrative tribunals) ማቋቋም አስፈልጓል። ይኸው ምክንያት ለቁጥራቸው ማደግ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል። እንደዛም ሆኖ በእንግሊዝ የአስተዳደር ጉባዔዎች ሊከተሉት ስለሚገባ ስርዓት በተመለከተ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ አልነበረም።
በእርግጥ አደረጃጀታቸውን በተመለከተ ያለው ችግር ገንኖ የወጣው ሎርድ ሄዋርድ በ1929 ዓ.ም. ‘አዲሱ አምባገነንነት’ (The New Despotism) በሚለው መጽሐፋቸው መነሻ ነበር። ይህ መጽሐፉ በወቅቱ በጣም እያደገ የመጣውን የአስተዳደር መ/ቤቶች ሰፊ ስልጣን የሚተነትንና ይህም ገደብ ካልተደረገበት ቅልጥ ያለ አምባገነንት እንደሚያስከትል ተጨባጭ ስጋት አንጸባርቋል። በምላሹም የእንግሊዝ ፓርላማ የሚኒስትሮችን ስልጣን የሚመረምር ኮሚቴ በማቋቋም እ.ኤ.አ. በ1932 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ስልጣን ኮሚቴ ሪፖርት (Report of the Committee of Ministers Powers) ለህዝብ ይፋ ሆነ።w የሪፖርቱ ይዘት በጠቅላላው እያደገ የመጣውን የስራ አስፈፃሚ ስልጣን የሚመለከት እንጂ ስለ የአስተዳደር ጉባዔዎች ዝርዘር ጥናት አላካተተም።
እ.ኤ.አ. በ1957 ዓ.ም. የተቋቋሙው የፍራንክ ኮሚቴ (Franks Coomittee) የአስተዳደር ጉባዔዎችን የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት፣ አደረጃጀትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር ምርመራና ጥናት አድርጐ ሪፖርቱ በዚሁ ዓመት ይፋ ሆኖ ታተመ። የኮሚቴውን ሪፖርት እንደ መነሻ በመውሰድ ከአንድ ዓመት በኋላ እ.ኢ.አ. በ1958 የወጣው የአስተዳደር ጉባዔዎችና መርማሪ አካላት አዋጅ (Tribunals and Inquiries Act 1958) ተብሎ የሚጠራውን ህግ ለአስተዳደር ፍ/ቤቶች ዘላቂ አደረጃጀት መሰረት ሆኗል። በመቀጠልም እ.ኢ.አ. በ1992 አዋጁ የተወሰኑ ማሻሻያ ታክለውበት እንደገና ህግ ሆኖ ወጥቷል።
በዚሁ መሰረት የተሻሻለው አዋጅ በተለያዩ አስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን ያላቸውን ጉባዔዎች በመዘርዘር አቋቁሟል። ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ተመሳሳይ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን ያላቸው የአስተዳደር ጉባዔዎች ደግሞ በሌላ በልዩ ህግ ተቋቁመዋል። የእነዚህ ጉባዔዎች ባህርያት በጥቅሉ ሲታይ ሁሉም ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ እንጂ የጐንዮሽ እና ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም። ይህም ማለት ሁሉንም በበላይነት የሚያስተዳድርና የሚመራ ፕሬዝዳንት ሆነ ሊቀመንበር የለም። በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ የሚከተሉት ስነ-ስርዓት ወጥነት የለውም። ሁሉም ለጉዳዩ አመቺ የሆነ ዝርዝርና ልዩ ስነ-ስርዓት ተፈፃሚ ያደርጋሉ። የሚከተሉት ስነ-ስርዓት የተለያየ ቢሆንም ባይሆንም ሁሉም በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ የተፈጥሮ ፍትህ መሰረት ሀሳቦችን ማለትም የመሰማት መብት እና የኢ አድሎአዊነት መርህ ወጥ በሆነ መልኩ የመከተል ግዴታ አለባቸው።
የእንግሊዝ የአስተዳደር ጉባዔዎች በአንድ ጥላ ስር አለመደራጀታቸው ዝብርቅርቅ ስነ-ስርዓት በመፍጠር ከወጪ አንፃር አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድርና ይህም በውጤታማነታቸው ላይ ክፍተት እንደሚፈጥር እሙን ነው። ይህን ችግር በከፊልም ቢሆን ለማስወገድ እ.ኤ.አ. በ1992 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው አዋጅ አሰራርና አደረጃጀታቸውን የሚከታተል የአስተዳደር ጉባዔዎች ካውንስል የተባለ ራሱን የቻለ አካል በማቋቋም በተግባርም የተሻለ ውጤት እንዲመጣ አድርጓል።
ይህ ተቋም ምንም አይነት የዳኝነት ስልጣን የለውም። ሆኖም የጉባዔዎችን አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ እርምጃዎች የመውሰድ ወይም እንዲወሰዱ የማድረግ ስልጣናት ነበሩት። ለምሳሌ ያህል የሚመሩበት ስነ-ስርዓት በየትኛውም አካል ከመውጣቱ በፊት በቅድሚያ ካውንስሉን ማማከር ያስፈልጋል። የዳኞችን ሹመት በተመለከተም ለሚመለከተው አካል ሀሳብ መስጠት ይችላል። በተጨማሪም አጠቃላይ አሰራራቸውን በተመለከተ በየአመቱ ሪፖርት ያቀርባል። በተጨማሪም ስልጠና እና ትምህርት በማዘጋጀት አቅማቸውን በማጐበት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
እ.ኤ.አ እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ጉባዔዎች አደረጃጀት ወጥነት እንዳልነበረው ሁሉ የይግባኝ ስርዓቱም ወጥ ስርዓት ሲከተል አልነበረም። አንዳንድ ጉባዔዎች በመጀመሪያና በይግባኝ ቢደራጁም የተቀሩት ግን የይግባኝ ስርዓት አልተዘረጋላቸውም።
እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. የአስተዳደር ጉባዔዎችን በአዲስ መልክ ያቋቋመው Tribunals, Courts and Enforcement Act 2007 (TCE Act) ተሰበጣጥረው የነበሩትን ሁሉንም ጉባዔዎች አንድ ላይ አዋህዷቸዋል። በዚሁ መሰረት ገለልተኛና ነጻ ጉባዔዎች በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ ሰሚ ተዋቅረዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ጉባዔዎች በአስተዳደር አካላት የተሰጡ ማናቸውንም ውሳኔዎችና እርምጃዎች በመቃወም የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በህግና በፍሬ ነገር ላይ የዳኝነት ስልጣን ያላቸው ሲሆን በይግባኝ ሰሚነት የተዋቀሩት ደግሞ በህግ ጉዳይ ላይ አከራክሮ የመወሰን ስልጣን አካቸው። በተጨማሪም ውስን በሆኑ ጉዳዮች በቀጥታ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።x
በአውስትራሊያ
የአውስትራሊያ የአስተዳደር ጉባዔዎች ስርዓት ከሞላ ጐደል በእንግሊዝ ስርዓት መሰረት የተቀረጸ ቢሆንም የራሱ የሆኑ ልዩ ባህርያት አሉት። በአውስትራሊያ የአስተዳደር ጉባዔ ጽንሰ ሀሳብ ከመነሻው ከእንግሊዝ በውሰት የተወሰደ ቢመስልም የራሱን ልዩ መገለጫዎች በመያዝ በየጊዜው በለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈ በተለያየ ቅርጽና አወቃቀር ውስጥ እየተፈተነ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንደ እንግሊዝ ሁሉ የአውስትራሊያ የአስተዳደር ጉባዔዎች ስርዓት ሊይዝ ስለሚገባው ቅርጽና ገጽታ በተመለከተ በተለያዩ አጥኒ ቡድኖች ስፊ ጥናትና ዳሰሳ ከተሄደበት በኋላ አብዛኛዎቹ ከጥናቱ የተገኙ የመፍትሔ ሀሳቦች በህግ ማእቀፍ ውስጥ ተካትተዋል። የእነዚህ ጥናቶች ዋና አላማ በመንግስት አስተዳደር በደል የደረሰባቸው ዜጐች የአስተዳደር ፍትህ ማጐናጸፍ ነው። ጥናቶቹ ወጥነት በሌለው መልኩ ተሰበጣጥረው የነበሩትን ጉባዔዎች ሁሉን አቀፍ አሀዳዊ ስርዓት እንዲከተሉ የጐላ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ወጥነት ያለው ሁሉን አቀፍ የአስተዳደር ጉባዔ አስፈላጊነቱ በየጊዜው እየታመነበት በዚህ አቅጣጫ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገ ቢኖርም የመጀመሪያ ደረጃ ጉባዔዎችን በአንድ ጥላ ስር የሚያዋቅር ስርዓት አሁንም ድረስ በአውስትራሊያ በፌደራል መንግስቱ ደረጃ አልተዋቀረም። በእርግጥ እ.ኤ.አ. በ2000 ዓ.ም. ረቂቁ ለፓርላማ የቀረበ ቢሆንም ህግ ሆኖ ገና አልፀደቀም።
ከዚህ በተቃራኒ ከእነዚህ የተለያዩ የአስተዳደር ጉባዔዎች የተሰጡ ውሳኔዎች በይግባኝ የሚዳኙት ወጥ በሆነ አንድ የይግባኝ ሰሚ አስተዳደር ጉባዔ ስር ነው። በዳኝነት ስልጣኑ የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ጉባዔዎች በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ላይ በፍሬ ነገር እና በህግ ጉዳይ ላይ ይግባኝ ይሰማል።
በአገራችን የአስተዳደር ጉባዔዎች መዋቅርና አደረጃጀት
በአትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ጉባዔዎች አደረጃጀት ወጥነት አይታይበትም። ማቋቋሚያ አዋጁ ለአንዳንዶቹ በግልጽ የህግ ሰውነት ሲሰጥ ሌሎቹን ግን ከማቋቋም ባለፈ ከአስተዳደር መ/ቤቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና የህግ ሰውነት በግልጽ አይለይም። ሁሉም ጉባዔዎች ራሳቸው ችለው በተናጠል የተቋቋሙ ሲሆን እርስ በርስ የጐንዮሽ ግንኙነት የላቸውም። በተጨማሪም በአሰራር፣ በስነ-ስርዓት፣ የዳኞች ምልመላ፣ ሹመትና ሽረት ከበላይ ሆኖ የሚያስተዳድርና የሚመራና አንድ ወጥ አካል የለም።
የይግባኝ ስርዓቱም እንዲሁ ወጥነት ርቆታል። ሁሉም የአስተዳደር ጉባዔዎች የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ብቻ ያላቸው ሲሆን በአንድ ጉባዔ የተወሰነን ጉዳይ ይግባኝ የሚሰማ ይግባኝ ሰሚ ጉባባዔ የለም። ለምሳሌ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የተወሰነ ጉዳይ ይግባኙ የሚሰማው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትy ሲሆን በመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍ/ቤትz እና በማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔa የተወሰነ ጉዳይ ይግባኙ የሚቀርበው ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ነው። በታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የሚሰጡ ውሳኔዎች ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍ/ቤት በይግባኝ ይታያሉ።b
የአስተዳደር ጉባዔዎች ሁሉን አቀፍ መልክ ይዘው በአንድ ጥላ ስር አለመደራጀታቸው ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳረግ ከመሆኑም በላይ በተሰበጣጠረ ቦታ መገኘታቸውና ወጥ ስነ-ስርዓት አለመከተላቸው ተደራሽነታቸውን ሩቅ አድርጐታል። አብዛኛዎቹ በአስተዳደር መ/ቤቱ ህንፃ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከጸሐፊ ጀምሮ ለስራ አስፈላጊ ቁሳቁሶች በመ/ቤቱ በጀት ይመደብላቸዋል። ይህም ገለልተኛነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። በተግባር እንደሚታየው ስለ አስተዳደር ጉባዔዎች ያለው እይታ በመ/ቤቱ ውስጥ እንደተቋቋሙ ቅሬታ ሰሚ አካላት እንጂ ራሳቸውን እንደቻሉ ፍትህ ሰጪ ተቋማት አይደለም። ይህም በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እና ተቀባይነታቸውን አውርዶታል ማለት ይቻላል።
የ1967ቱ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ወጥ የአደረጃጀት ስርዓት ለመዘርጋት በመሞከር የመጀመሪያው ነው። ረቂቁ በአንቀጽ 23 ላይ የጠቅላይ ፍ/ቤት (Imperial supreme court) አካል (Division) የሆነ ጠቅላይ የአስተዳደር ፍ/ቤት ያቋቁማል። ይህ ፍ/ቤት በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ይግባኝ የመስማት ብቸኛ የዳኝነት ስልጣን (exclusive jurisdiction) አለው። ይህ ስርዓት የፈረንሳይ የአስተዳደር ፍ/ቤትን አደረጃጀት የሚከተል ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህን ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ መቀበል ያስቸግራል።
ጠቅላይ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ የጠቅላይ ፍ/ቤት አንድ ክፍል ተደርጐ መቆጠሩ ራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው የአስተዳደር ፍ/ቤት አለመኖሩንና የሁለትዮሽ ስርዓት ተፈፃሚ አለመሆኑ ያሳየናል። በአቋሙ ሲታይ እንደፈረንሳይ ኮንሲል ዴታ (Conseil d’Etat) በአስተዳደራዊ ጉዳዮች የመጨረሻ ስልጣን ያለው ፍ/ቤት ይመስላል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጠቅላይ የአስተዳደር ፍ/ቤት ስር አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንና በይግባኝ የሚያዩ የአስተዳደር ጉባዔዎች አልተቋቋሙም። ስለዚህ ምንም እንኳን ‘ይግባኝ’ የሚለው ቃል በአንቀጽ 25 ላይ ቢጠቀስም ጠቅላይ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ አስተዳደራዊ ክርከሮችን በቀጥታ የሚያይ የመጀመሪያ ደረጃ የአስተዳደር ፍ/ቤት ነው። ከአስተዳደራዊ ፍትህ አንፃር ሲታይ በዚህ ፍ/ቤት የሚታይ ጉዳይ ለበላይ አስተዳደር ፍ/ቤት ሆነ ለመደበኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ስለማይቀርብ የዜጐችን አስተዳደራዊ ፍትህ የማግኘት መብት በእጅጉ ያጣብባል።
በ2001 ዓ.ም. የተዘጋጀው ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ በ1967ቱ ላይ የሚንጸባረቀውን የተምታታ አደረጃጀት በማስወገድ ከሞላ ጐደል የእንግሊዝ የአስተዳደር ጉባዔ ስርዓት የመሰለ አደረጃጀት ተፈፃሚ ያደርጋል። በረቂቁ አንቀጽ 17 ላይ እንደተመለከተው ከመደበኛ ፍ/ቤት ውጪ የሆነ ራሱን የቻለ የፌደራል የአስተዳደር ቅሬታዎች ይግባኝ ፍ/ቤት የተባለ አካል ይቋቋማል። ፍ/ቤቱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን የሚመራ የራሱ ፕሬዚደንትና ምክትል ፕሬዚደንት የሚኖሩት ሲሆን የሚሾሙትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በተወካዮች ም/ቤት ይሆናል። ረቂቅ አዋጁ ሁሉንም የአስተዳደር ችሎቶች በአንድ ጥላ ስር በማደራጅት ሁሉን አቀፍ የአስተዳደር ጉባዔ ስርዓት (generalized tribunal) መከተሉ ከስነ-ስርዓት ወጥነት፣ ተደራሽነትና ወጪ ቆጣቢነት አንጻር ተመራጭነት አለው።
ረቂቁ በተጨማሪ ከእንግሊዙ የአስተዳደር ጉባዔ ም/ቤት (Council on Tribunals) ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምክር ቤት ያቋቁማል። ሆኖም በይዘትና በስልጣን ረገድ የተከተለው አካሄድ የተለየ ያደርገዋል። የዚህ ም/ቤት ስልጣን ለአስተዳደር ፍ/ቤት ዳኞች ስልጠና በማዘጋጀት፣ በማመቻቸት እንዲሁም በቀጥታ በመስጠትና ሪፖርት በማቅረብ ላይ የተገደበ ሳይሆን በፕሬዝዳንቱ የሚቀርቡትን እጩ ዳኞች መርጦ የመሾም፣ የዲሲፕሊን እርምጃ የመውሰድ፣ ስነ-ስርዓትን ጨምሮ ፍ/ቤቱ ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ የሚረዳ መመሪያ የማውጣት እንዲሁም አስተዳደራዊ ፍትህን ለማስፈን የሚረዱ አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ የመወሰን ስፊ ተግባራዊ ስልጣን ተሰጥቶታል። ምክር ቤቱ ስፊ ስልጣን ማግኘቱ የአስተዳደር ፍ/ቤቱ በየጊዜው የሚያጥሙትን ችግሮች በቅርበት እየተከታተለ ለመፍታት ያስችለዋል።
ከይዘቱ አንፃር ግን የተለያዩ አስተዳደር ፍ/ቤቶች ሆነ የሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ውክልና አለማግኘቱ የችሎቶቹን ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከመሆኑም በላይ የአስተዳደር ፍ/ቤቱን ኢ-መደበኛ ባህርይ ያጠፋዋል።
በረቂቁ አንቀጽ 19 መሰረት ም/ቤቱ የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል።
የተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ……………ሊቀመንበር
የፌደሬሽን ም/ቤት አፈ- ጉባኤ…………………አባል
የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት…………አባል
ዋና እንባ ጠባቂ………………………………አባል
የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ዋና ኮሚሽነር………አባል
የፍትህ ሚኒስትር (በአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ)………አባል
የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት………………………አባል
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት………………. አባል
በዚህ መልኩ የሚዋቀረው ም/ቤት በአስተዳደር ፍ/ቤቱ ዳኞች ሹመት ላይ የመወሰን ስልጣን አለው። በተጨማሪም ችሎቶቹን ያደራጃል። ይመድባል።
ከፌደራል የአስተዳደር ቅሬታዎች ይግባኝ ፍ/ቤት በሚሰጥ ውሳኔ ላይ ስለሚኖረው የይግባኝ ስርዓት እንደበፊቱ ረቂቅ ሁሉ በፌደራሉ ረቂቅ ላይም በዝምታ ታልፏል። ምንም እንኳን ይህ ፍርድ ቤት ‘የይግባኝ ፍ/ቤት’ የሚል ስያሜ ቢሰጠውም በተግባር ግን በአሰተዳደር መ/ቤቱ በሚሰጡ የመጨረሻ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ በፍሬ ነገርና በህግ ጉዳይ ላይ አከራክሮ ውሳኔውን የመለወጥ፣ የማጽደቅ ወይም ቅጣቱን የመቀነስ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ያለው የአስተዳደር ፍ/ቤት ነው።
በረቂቁ መሰረት ስራ ላይ ያሉት ጥቂት የአስተዳደር ጉባዔዎች እጣ ፋንታ አልለየለትም። እነዚህ ጉባዔዎች ታጥፈው በረቂቁ መሰረት በሚቋቋሙት ችሎቶች የሚተኩ ከሆነ ረቂቁ ይህንን የሚያጣጥም ድንጋጌ ሊኖረው ይገባል።
የዳኞች ሹመት እና ሽረት
በአስተዳደር ጉባዔ የሚያስችሉ ዳኞች የሹመት ስርዓትና የብቃት መመዘኛ እንደ ክርክሩ አይነት ይለያያል። ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው በብዙ አገራት ተቀባይነት ያገኘው ስርዓት ‘ሚዛናዊ የአስተዳደር ጉባዔ’ (balanced tribunal) ተብሎ የሚጠራው ሲሆን በገለልተኛ አካል የሚሾም አንድ ሊቀመንበርና የተለያዩ ጐራዎችን ጥቅም የሚወክሉ ሁለት አባላት ይኖሩታል። የዚህ ስርዓት ዋና ዓላማ በክርክሩ ተካፋይ የሆነ ወገን የእርሱን ጉዳይ በወጉ የሚረዳ ቢያንስ አንድ አባል እንዲኖረው በማድረግ ፍትሐዊነቱን ማረጋገጥ ነው።
በአገራችን የአስተዳደር ጉባዔዎች ከሞላ ጐደል ይህንኑ ስርዓት ይከተላሉ። የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ቦርድ በችሎት የሚሰየም አንድ ሰብሳቢ እና ከአሰሪ ማህበራት የሚወክሉ ሁለት አባላት እንዲሁም ከሰራተኞች ማህበራት የሚወክሉ ሁለት አባላት ይኖሩታል። የቦርዱ ተተኪ አባላትም ከሰራተኛና አሰሪ ማህበራት የሚወከሉ አንድ አንድ አባላት ይሆናሉ።
በሁሉም የአስተዳደር ጉባዔዎች ሰብሳቢው ወይም ሊቀመንበሩ በስራ አስፈፃሚው ይሾማል። የችሎቱ አባላት ከችሎት የሚነሱትም ሹመቱን ባጸደቀው ሚኒስትር ወይም ባለስልጣን ሲሆን በተለይ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን በተመለከተ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰራተኛ ወይም አሰሪ ማህበራት የተወከሉ አባላትን ሳይቀር የመሻርና በሌላ የመተካት ስልጣን አለው። ሹመትና ሽረት የሚፈጸመው በአንድ ሰው መሆኑ ሳያንስ ሚኒስቴሩ ያልሾመውን አባል ጭምር የመሻር ስልጣን ማግኘቱ የቦርዱንን ነፃነትና ገለልተኝነት በእጅጉ ይጋፋል።
በአስተዳደር ጉባዔ የሚሰየሙ ዳኞች በሚያዩት ጉዳይ ላይ የተካነ እውቀት እንዲኖራቸው እንጂ የግድ የህግ እውቀት አያስፈልጋቸውም። ሆኖም አንዳንድ የተወሳሰቡ የአስተዳደር ክርክሮች የህግ ባለሙያ እገዛ ስለሚጠይቁ ቢያንስ የተወሰኑ አባላት የህግ እውቀት ቢኖራቸው ይመረጣል። በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ከሚሾሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ ስለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ብቃትና ልምድ ሊኖራቸው ይገባል። ሁሉም የቦርዱ አባላትና ተተኪ አባላት የአገልግሎት ዘመናቸው ሶስት ዓመት ሲሆን የስራ ጊዜያቸውም ‘የትርፍ ጊዜ’ (part-time) ሆኖ በቦርድ ስብሰባ ለተገኘ አባል በሚኒስትሩ ከሚወሰን አበል በስተቀር ቋሚ ደመወዝ አይከፈላቸውም።
በፌደራሉ ረቂቅ አዋጅ (2001 ዓ.ም.) መሰረት በችሎቱ የሚሰየሙ አባላት ሹመትና ሽረት በረቂቁ በሚቋቋመው ም/ቤት አማካይነት የሚከናወን ሲሆን ይህም የፍ/ቤቱን ገልተኛነት በሚገባ ያረጋግጣል። የችሎቱ አባላት የስራ ዘመን ለአምስት ዓመት ሆኖ በድጋሚ ከመሾም ገደብ አይደረግባቸውም። የስራ ጊዜያቸው ሙሉ ወይም ከፊል የስራ ሰዓት ስለመሆኑ ባይመለከትም ፍ/ቤቱ ራሱን ችሎ እንደ ተቋም የተደራጀ ከመሆኑ አንጻር የሙሉ ሰዓት ዳኞች እንደሆኑ መገመት ይቻላል። ለዳኞች የሚከፈለው ክፍያ መጠን በምክር ቤቱ በሚወሰነው መሰረት ይሆናል።
የዳኞች ብቃት መለኪያ እንደሚቋቋሙት ችሎቶቸ የሚቀያየር ሳይሆን ወጥነት ባለው መልኩ የተቀመጠ ነው። እያንዳንዱ ችሎት ሶስት አባላት ሲኖሩት ሰብሳቢው በህግ ትምህርት ስልጠና ያለው ወይም በህግ መስክ በቂ ልምድ ያለው ሰው መሆን ይኖርበታል። በዚህ መመዘኛ መሰረት ከስልጠና ወይም ልምድ በስተቀር በመደበኛ የህግ ትምህርት ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ መያዝን አይጠይቅም። የተቀሩት ሁለት አባላት ‘መልካም ስምና ክብር ከበቂ የአስተዳደር ተግባራት እውቀትና ልምድ’ ጋር ሊኖራቸው እንደሚገባ በረቂቁ አንቀጽ 46/2/ ተመልክቷል። ይህ መለኪያ ግልጽነት የሚጎድለው እንደመሆኑ ‘የአስተዳደር ተግባራት’ የሚለው ‘በህዝብ አስተዳደር’ በሚል ቢተካ የተሻለ ነው። ይህም ቢሆን ጥቅል ሀሳብ ያዘለ እንደመሆኑ መጠን የአስተዳደር ዳኞች እንደ ክርክሩ አይነት ልምድና እውቀታቸው እየተመዘነ በዳኝነት ቢሾሙ ሊቋቋም የታሰበው የአስተዳደር ፍ/ቤት እንደሌሎች አገራት ሁሉ ውጤታማነቱን በማስመስከር በአስተዳደር በደል ለተጠቃው ዜጋ የአስተዳደር ፍትህ ለማስፈን ብቃት ይኖረዋል።

One thought on “የአስተዳደር ጉባዔስያሜና ትርጓሜ”

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.