የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርህ እና ስርዓትአስተዳደራዊ ውሳኔ ምንድነው?


የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርህ እና ስርዓት
አስተዳደራዊ ውሳኔ ምንድነው?

‘አስተዳደራዊ ውሳኔ’ በአስተዳር ህግ ውስጥ ከቃል አጠቃቀም፣ ከይዘትና ከወሰን አንጻር ቁርጥ ያለ መደብ ከሌላቸው ፅንሰ ሀሳቦች መካከል ጎልቶ ይወጣል። ውስብስብነቱ ከፅንሰ ሀሳቡ ወካይ ስያሜ ይጀምራል። ‘አስተዳደራዊ ውሳኔ’ በሚል እዚህ ላይ መጠቀሱም በአገራችን የአስተዳደር ህግ ውስጥ መደበኛ መጠሪያው ቢሆን ይበጃል በሚል ብቻ ነው። ጀርመኖች እንኳን የራሳቸውን ወካይ ቃል መፍጠር ተስኗቸው አሁን ላይ በአስተዳደር ህጋቸው ዐቢይ ስፍራ ይዞ የሚገኘውን ‘Administrative act’ (Verwaltungsakt) በሚል የሚጠሩትን ፅንሰ ሀሳብ ለማዳበር ከፈረንሳዮች acte administrative ለመዋስ ተገደዋል።
‘Administrative act’ (Verwaltungsakt) is a core concept of the German administrative law. It covers most of the actions of the administrative authorities through which they affect the legal interests of an individual. The origin of this concept is traced from the French concept of acte administratif from which it was borrowed by the German jurists and developed into a German concept since 1826 onwards.a
በእንግሊዝኛው ፍቺ ከወሰድነው Administrative Decision በይዘቱ Administrative Act ውስጥ የሚጠቃለል ሲሆን ዘርፈ ብዙ መልክ ካላቸው አስተዳደራዊ ተግባራት መካከል አንድ ነጠላ ተግባርን ብቻ ይወክላል። ሆኖም ለአገራችን የአስተዳደር ህግ ‘አስተዳደራዊ ተግባር’ ወይም ‘አስተዳደራዊ ድርጊት’ የሚለውን ቃል ብንጠቀም ገላጭነቱ አይጎላም። ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደራዊ ድንጋጌ ማውጣት እንዲሁም ምርመራ፣ ቁጥጥርና ክትትል ሁሉም የአስተዳደር ተግባራት እንደመሆናቸው ዳኝነታዊ ባህርይ ያላቸውን ተግባራት ለይቶ ለማመልከት ውስን ይዘት ያለውን ቃል መጠቀም ያስፈልጋል።

ከዚህ አንጻር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‘የአስተዳደር ውሳኔ’ ወይም ‘አስተዳደራዊ ውሳኔ’ የሚለው ቃል ዳኝነታዊ ባህርይ ያላቸውን ተግባራት ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል። ሆኖም በመደበኛ ትርጓሜው አደናጋሪ መልዕክት ስለሚፈጥር ይዘቱንና ፍቺውን በቅድሚያ መወሰን ያስፈልጋል።
እ.ኤ.አ. በ1976 ዓ.ም. በወጣው የጀርመን የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ የአስተዳደር ተግባር (Administrative act) የሚከተለው ፍቺ ተሰጥቶታል።
Administrative act is every order, decision or other sovereign measure taken by an authority for the regulation of a particular case in the sphere of public law and directed at immediate external legal consequences.b
ወደ አማርኛ ስንመልሰው፤
የአስተዳደር ተግባር ማለት ቅርብና ውጫዊ የህግ ውጤት የሚያስከትል በህዝብ አስተዳደር ህግ ማዕቀፍ ውስጥ አንድን ልዩ ሁኔታ ለመቆጣጠር ሲባል ስልጣን ያለው አካል የሚሰጠው ትዕዛዝ፣ ውሳኔ ወይም ሌላ ማናቸውም ሌላ ሉዓላዊ እርምጃ ነው።
በትርጓሜው ውስጥ ተጨማሪ ሰፊ ማብራሪያ የሚሹ ንዑስ ሀሳቦች ታጭቀዋል። ሆኖም በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል በጀርመን የአስተዳደር ህግ የአስተዳደር ተግባር ማለት ህግ ለማስፈጸምና የአስተዳደር ስራ ለማከናወን ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ይህን ህዝባዊ ስልጣናቸውን (public functions) በመገልገል የሚሰጡትን ትዕዛዝ፣ ውሳኔ ወይም ማናቸውም በማድረግ፣ ባለማድረግ የሚገለጽ እርምጃ ሁሉ ያጠቃልላል። ይህም ማለት በውል ወይም ከውል ውጪ ኃላፊነት ህጎች ስር የሚሸፈኑ ግላዊ ድርጊቶች፣ ውሳኔዎች፣ እርምጃዎች ወዘተ…በአስተዳደር ተግባር ስር አይሸፈኑም።
በትርጓሜው ላይ ‘ልዩ ሁኔታ ለመቆጣጠር’ ሲባል ተግባሩ ህጋዊ ውጤት እንደሚያስከትል ወሰኑም በአንድ ልዩ ሁኔታ ላይ ያነጣጠረ እንጂ ጠቅላላ ተፈጻሚነት እንደሌለው ያመለክታል። ስለሆነም የበታች ሠራተኛ ለበላይ ኃላፊ የሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ፣ ሪፖርት ወይም የምርመራ ውጤት ራሱን ችሎ ህጋዊ ውጤት የማይከተለው በመሆኑ እንደ አስተዳደራዊ ተግባር አይቆጠርም። በአንድ ዘርፍ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ (ለምሳሌ ስጋ ሻጮች ማሟላት ያለባቸው የጥራት ደረጃ) ከላይ በተቀመጠው ትርጓሜ ውስጥ አይወድቅም። ምክንያቱም ተፈጻሚነቱ ሁሉንም የዘርፍ ነጋዴዎች ስለሚያቅፍ ጠቅላላነት ይታይበታል። በመጨረሻም ህጋዊ ውጤቱ በአስተዳደሩ ውስጣዊ መዋቅር ተወስኖ የሚቀር (ለምሳሌ በአንድ ነጋዴ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የበላይ ኃላፊው ለበታች ሠራተኛ የሚያስተላልፈው ማሳሰቢያ) ከሆነ በአስተዳደራዊ ተግባር ውስጥ አይመደብም።
የአሜሪካው የፌደራል አስተዳር ስነ ስርዓት ህግ ተፈጻሚነቱ አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት (rule making) እና አስተዳደራዊ ዳኝነት (adjudication) የመስጠት ሂደቶች ላይ ነው። በህጉ ላይ በተሰጠው ፍቺ አስተዳደራዊ ዳኝነት ማለት በውጤቱ ‘ትዕዛዝ’ የሚያቋቁም የአስተዳደር ሂደት (agency process for the formulation of an order) ነው። ትዕዛዝ የሚለው ቃል በአስተዳደር ስነ ስርዓት ህጉ ላይ ፍቺ የተሰጠው ሲሆን ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል።
order means the whole or a part of a final disposition, whether affirmative, negative, injunctive, or declaratory in form, of an agency in a matter other than rule making but including licensing.c
‘ትዕዛዝ’ ከጀርመኑ ‘የአስተዳደር ተግባር’ ጋር ሲነጻጸር መሰረታዊ ልዩነት አይታይበትም። ጉዳዩን የሚቋጭ የመጨረሻ መሆኑ ህጋዊ ውጤት እንደሚከተለው ይጠቁመናል። በይዘቱ አንድ ድርጊት እንዳይፈጸም፣ እንዲፈጸም ወይም የአንድ ሁኔታ (መብት) መኖር/አለመኖር የሚያረጋግጥ መግለጫ ወይም ከአስተዳደራዊ ድንጋጌ ማውጣት ውጪ ያለ ማንኛውም የመጨረሻ እልባት የሚሰጥ ነው።
በመቀጠል የአገራችን የፌደራል ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ (1993) የተጠቀመውን ቃል እና አፈታቱን እናያለን። በረቂቅ አዋጁ የትርጓሜ ክፍል አንቀጽ 2 /2/ እንደተመለከተው አስተዳደራዊ ውሳኔ ማለት፤
ማናቸውም አስተዳደራዊ ባህርይ ያለውን ተግባር ወይም ነገር ከመፈጸም ጋር የተያያዘ ውሳኔ ወይም ውሳኔ አለመስጠትን ጨምሮ ቅጣትን ለመጣል፣ ወይም መፍትሔ ለመስጠት ወይም የመከላከል ዓላማ ወይም ውጤት ያለው በአስተዳደር ተቋማት የሚሰጥ ማናቸውም ውሳኔ፣ ትዕዛዝ ወይም ብይን [ነው።]
የትርጓሜውን ይዘት ይበልጥ ለመረዳት የእንግሊዝኛውን ቅጂ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።
Administrative Decision means any decision, order or award of an agency having as its object or effect the imposition of a sanction or the grant or refusal of relief, including a decision relating to doing or refusing to do any other act or thing of an administrative nature, or failure to take a decision
በቀጣይ በ2001 ዓ.ም. በተዘጋጀው ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ አዋጅ አርቃቂዎቹ የተለየ አገላለጽ መጠቀም መርጠዋል። በረቂቁ አንቀጽ 2/2/ ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደሚከተለው ተተርጉሟል።
አስተዳደራዊ ውሳኔ ማለት ተጨባጭ ሕጋዊ ግንኙነቶችን ለመመስረት፣ ለማሻሻል፣ በምርመራ ለማረጋገጥ ወይም የተሟላ ለማድረግ ለአንድ ጉዳይ የተወሰነ መፍትሔ የመስጠት ዓላማ ያለውና በግለሰብ ወይም በተወሰኑ ሰዎች ላይ ተፈጻሚነት ያለው በተቋሙ የሚሰጥ ሕጋዊ ውሳኔ ሲሆን፣ አስተዳደራዊ ባህርይ ባለው ተግባር ወይም ጉዳይ ላይ ውሳኔ አለመስጠትንም ይጨምራል።
በሁለቱም ረቂቆች ላይ የሚታየው ገላጭነት የጎደለው የቋንቋ አጠቃቀም አብዛኛው ሰው በቀላሉ አይረዳውም። ከዚህም አልፎ የህግ ባለሞያዎች፣ ዳኞች እና አስተዳዳሪዎች በጋራ የሚያግባባ አገላለጽ አልያዘም። ለምሳሌ በተለምዶ ሰርኩላር በሚል ስያሜ ጠቅላላ ተፈጻሚነት ኖሯቸው የሚተላፉ ትዕዛዞች የአስተዳደራዊ ውሳኔና የአስተዳደራዊ ድንጋጌ ከፊል ባህርያት ይጋራሉ። ሆኖም በአንደኛው ስር ለመፈረጅ ሁለቱም ትርጓሜዎች ግልጽ መለያ መስፈርት አላካተቱም። ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ትርጓሜ ለማበጀት ጥሩ መነሻ የሚሆነው የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው። ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ብዙ ነጥቦች አሉ። አስተዳደራዊ ሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሁለቱም ምንጫቸው ዳኝነታዊ ስልጣን ነው። በዳኝነት ፍሬ ነገሩን የማረጋገጥና በተረጋገጠው ፍሬ ነገር ላይ ህጉን ተፈጻሚ የማድረግ ተግባራት ይከናወናሉ። ዓላማው አከራካሪ የሆነ አንድ ተለይቶ የታወቀ ጉዳይ (particular case) መቋጨት ነው። ጉዳዩን በመቋጨት የሚነገረው ትዕዛዝ፣ ብይን ወይም ውሳኔ በባለጉዳዮች ወይም ሶስተኛ ወገኖች ላይ ህጋዊ ውጤት ያስከትላል። እነዚህ ወሳኝ ባህርያት በጀርመኑ እና የአሜሪካው የአስተዳደር ህጎች ላይ በግልጽ ተለይተዋል።
የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ቁ. 1183/2012 ለአስተዳደር ውሳኔ ፍቺ የሰጠበት መንገድ የቀድሞዎቹን ረቂቆች ችግር ከማስተካከል ይልቅ የባሰ ተጨማሪ ችግሮች ይዞ መጥቷል። በአንቀጽ 2/3/ ላይ ትርጓሜው እንደሚከተለው ይነበባብል።
የአስተዳደር ውሳኔ ማለት መመሪያ ማውጣትን ሳይጨምር የአስተዳደር ተቋም በዕለት ተዕለት ተግባሩ በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ የሚሰጠው የአስተዳደር ውሳኔ ነው።
የትርጓሜ አለአግባብ መለጠጥ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ከመመሪያ ማውጣት ያሉ የአስተዳደር ተግባራት በትርጓሜው ስር እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። ምንም እንኳን በአቀራረቡ የአሜሪካውን የአስተዳደር ስነ-ስርዓት የተከተለ ቢመስልም በአዋጁ ውሳኔዎች አዎንታዊ መልክ ብቻ እንዲኖራቸው ነው የተደረገው። ለምሳሌ ተቋሙ ‘የማይሰጠውን ውሳኔ’ ማለትም ግዴታን አለመወጣት በትርጓሜው ላይ አይነበብም።
በአንድ የአስተዳደር መ/ቤት የተፈጸመ ተግባር የአስተዳደር ውሳኔ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ በአስተዳደር ህግ ውስጥ መሰረታዊ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። ጥያቄው ተቋሙ ካሉት ጠቅላላ የማስተዳደር (ህግ ማስፈጸም)፣ ከፊል የህግ አውጭነት እና ከፊል የዳኝነት ስልጣናት መካከል የትኛውን እየተገለገለ እንደሆነ የሚለይበት ነው። የጥያቄው ሌላ መልክ ሲታይ ተቋሙ የፈጸመው ተግባር በባህርዩ ዳኝነታዊ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። የውሳኔ ሰጭውን የስልጣን እና የተግባር ዓይነት መለየት በህጉ የአፈጻጸም ወሰን ላይ የራሱ ጉልህ እንደምታዎች አሉት። ጠቅለል ባለ አነጋገር የአስተዳደር መ/ቤቶች ዳኝነታዊ ወይም የህግ አውጭነት ስልጣናቸውን በሚገለገሉበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ በሙሉ በአስተዳደር ስልጣን ውስጥ የሚወድቁት ድርጊቶች በመደበኛ ፍ/ቤቶች ቁጥጥር ሊደረግባቸው አይችልም። በሌላ አነጋገር አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድንጋጌ ባልሆነ ጉዳይ ላይ የአጣሪ ዳኝነት ስልጣን አይኖራቸውም። የአስተዳደር መ/ቤቶች ዳኝነታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጡ መሰረታዊ የውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች ተፈጻሚ መሆን ይጀምራሉ።
የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች
ከስነ-ስርዓት አካሄድ አንጻር ውሳኔ ሰጪ የሆነ የመንግስት አካል በቅን ልቦና ተመርቶ አድሎአዊ ያልሆነ ውሳኔ መስጠትና ከሁሉም በላይ በውሳኔው መብቱ ወይም ጥቅሙ ሊነካ ለሚችል ለማንኛውም ግለሰብ ከውሳኔው በፊት የመሰማት መብቱን ሊጠብቅለት ይገባል።
የአስተዳደር ውሳኔ ፍትሐዊነት በዋነኛነት ሁለት መሰረታዊ መርሆዎችን ያቅፋል። አንደኛው የመሰማት መብት ሲሆን (The right to fair hearing) በላቲን audi alteram partem ተብሎ ሲጠራ አንዳንዴ ‘ተቃራኒውን ወገን ሰማው’ ወይም ‘ማንም ሰው መከላከያው ሳይሰማ እርምጃ ሊወሰድበት አይገባም’ (no one should be condemned unheard) በሚል ይገለጻል።d
ሁለተኛው የኢ-አድሎአዊነት መርህ (The rale against bias) ነው። በላቲን nemo judex in causa sua የሚለውን የህግ አባባል / legal maxim/ ይወክላል። ወደ አማርኛው ስንመልሰው ‘አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ራሱ ዳኛ ሊሆን አይገባም’ የሚል መልዕክት አለው።e በእንግሊዝ እነዚህ ሁለት መርሆዎች ‘የተፈጥሮ ፍትሕ’ የሚባለውን በዳኞች የዳበረ ፅንሰ ሀሳብ የሚወክሉ ሲሆን የህጉ የመሰረት ድንጋይ ተደርገው ይቆጠራሉ።
የመሰማት መብት
በተከሰሰበት ጉዳይ መልስ ሳይሰጥ እንዲሁም ማስረጃውን ሳያሰማ የንግድ ፍቃዱ የተሰረዘበት ነጋዴ፣ የቤት ካርታው የመነከበት ግለሰብ፣ ከዩኒቨርሲቲ የተባረረ ተማሪ… ሁሉም የአስተዳደር በደል ሰለባዎች ናቸው። የአንድን ግለሰብ መብትና ጥቅም ሊጐዳ የሚችል ማንኛውም አስተዳደራዊ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ግለሰቡ የመሰማት ዕድል ሊያገኝ ይገባል። የመሰማት መብት በዘፈቀደ በሚወሰድ አስተዳደራዊ እርምጃ የተነሳ ዜጎች ህይወታቸውና ንብረታቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ ይከላከላል።
መሰማት ሲባል ከክስ እስከ ውሳኔ ድረስ ያሉ ዝርዝር የክርክር ሂደቶችን ያቅፋል። እያንዳንዱ ሂደት በራሱ ካልተሟላ በቂ የመሰማት ዕድል እንዳልተሰጠ ይቆጠራል። በአስተዳደር ዳኝነት ውስጥ የዚህ መብት ዝርዝር ሂደቶችና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በዋነኛነት የሚከተሉትን ያካትታል።

ቅድመ-ክስ ማስታወቂያ

የክስ መሰማት ውሳኔ ሰጭው ባለስልጣን ለባለጉዳዩ /ለተከሳሹ/ በሚሰጠው የክስ ማስታወቂያ ይጀመራል። ማስታወቂያ ተከራካሪው እንዲቀርብ የሚሰጥ መጥሪያ ነው። በይዘቱ ባለጉዳዩ የቀረበበትን ክስ በሚገባ ተረድቶ መልሱን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ የሚያስችለው በቂ ማስታወቂያ መሆን አለበት። ተከራካሪው ራሱን ለመከላከል የሚችለው የተከሰሰበትን ጉዳይ በማያሻማ ሁኔታ የተገለጸለት እንደሆነ ነው።f ከዚህ አንጻር የክሱ ዓይነትና ምክንያት ቀጥተኛና ግልጽ በሆነ መንገድ በማስታወቂያው ላይ መስፈር ይኖርበታል። ለምሳሌ እንዲቀርብ የተጠራው ባለጉዳይ የመንግስት ሰራተኛ ወይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆነ በደፈናው ‘የዲሲፕሊን ክስ ስለቀረበብህ እንድትቀርብ!’ የሚል መጥሪያ ግልጽነት ይጐድለዋል። በተጨማሪም ከአንድ በላይ ክስ በቀረበ ጊዜ እያንዳንዱ ክስ በዝርዝር ሊገለጽ ይገባል። በሌላ መልኩ በክስ ማስታወቂያው ላይ የቀረበው የክስ አይነት ክሱ በሚሰማበት ቀን የተቀየረ እንደሆነ ክሱ እንዳልተገለጸ ወይም በቂ ማስታወቂያ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል። በስርቆት ተከሶ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ፊት እንዲቀርብ የተጠራ ተማሪ ክሱ በሚሰማበት ቀን የመጀመሪያው ክስ ተቀይሮ ‘በፈተና ማጭበርበር’ ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ተማሪው የተቀጣው በቂ ማስታወቂያ ሳይሰጠው እንደመሆኑ ቅጣቱ መሰረታዊ የሆነውን የመሰማት መብት ይጻረራል።
ክሱ የሚሰማበት ጊዜና ቦታ
‘በቂ’ ሊባል የሚችል የክስ ማስታወቂያ መለኪያ ባለጉዳዩ ራሱን በሚገባ እንዲከላከል በሚያስችል መልኩ በቂ መረጃና ጊዜ የሰጠ እንደሆነ ነው። ክርክሩን ለማካሄድ ስልጣን የተሰጠው አካል ተከራካሪዎች የሚመቻቸውን ጊዜ በመወሰን ክሱ ስለሚሰማበት ቦታ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ መጥሪያውን መላክ ይጠበቅበታል። ጊዜው ሲገለጽ ትክክለኛው ሰዓት ጭምር መገለጽ አለበት። ቦታውም እንዲሁ ትክክለኛ መለያ አድራሻውን በመጥቀስ ለባለጉዳዩ/ለተከሳሹ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
ከጊዜ ጋር በተያያዘ መልስ ለማቅረብ የሚሰጠው የዝግጅት ጊዜ እንደክሱ ክብደትና ውስብስብነት ሚዛናዊ የጊዜ መጠን መሆን ይኖርበታል። ዛሬ ክሱ ተሰጥቶት ለነገ መልስ መጠበቅ በተዘዋዋሪ የመሰማት መብትን እንደመንፈግ ይቆጠራል። በመጨረሻም ክሱን የሚሰማው አካል ትክክለኛ ማንነት በማስታወቂያው ላይ መመልከት ይኖርበታል።
የክስ ማስታወቂያ በአካል ስለመስጠት
የጥሪ ማስታወቂያው በይዘቱ በቂ ሊባል የሚችል ቢሆንም ለባለጉዳዩ በአግባቡ እስካልዳረሰው ድረስ የመሰማት መብቱ ተጓድሏል። ባለጉዳዩ በቅርብ የሚገኝ ከሆነ በተቻለ መጠን መጥሪያው ለራሱ በአካል ሊሰጠው ይገባል። ከተገቢ ጥረት በኋላ ለማግኘት የማይቻል ከሆነ ማስታወቂያውን ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ መለጠፍና ለተወሰነ ጊዜ በተለጠፈበት ቦታ እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል። ጉዳዩ በሚሰማበት ቀን አለመቅረብ ክርክሩ በሌለበት እንዲቀጥል የሚያደረግ በመሆኑ የመጥሪያ በአግባቡ መድረስ የመስማት መብት አካል ተደርጐ መቆጠር ይኖርበታል።ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ መብት
ክስ የቀረበበት (ባለጉዳይ) ጉዳዩ በተቀጠረበት ቀን በአካል ወይም በወኪሉ ተገኝቶ ክርክሩን የመከታተል፤ መልስ፣ ክርክርና ማስረጃ የማቅረብ ዕድል ሊያገኝ ይገባል። ይህ መፈጸሙን ማረጋገጥ ክርክሩን የሚሰማው አካል ግዴታ ነው። መልሱ የሚቀርብበት መንገድ እንደየሁኔታው በቃል ወይም በጽሑፍ ሊሆን ይችላል። የሚቀርበው የማስረጃ ዓይነት የቃል (የሰው ምስክር) ወይም የጽሑፍ ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ማስረጃው በ3ኛ ወገን እጅ የሚገኝ ከሆነ ባለጉዳዩ እንዲቀርቡለት በጠየቀ ጊዜ ክርክሩን የሚሰማው አካል እንዲቀርቡ ማድረግ አለበት።
መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ መብት
ባለጉዳዩ የተቃራኒ ወገን ክስና ማስረጃ በአግባብ ሊደርሰውና ሊመለከተው እንደሚችል ከዚህ በፊት ተገልጿል። የዚህ ዓላማ በአንድ በኩል ባለጉዳዩ የራሱን መከራከሪያና ማስረጃ በማቅረብ ክሱን በቀጥታ እንዲከላከል ሲሆን በሌላ በኩል የተቆጠረበትን ማስረጃ ማስተባበል እንዲያስችለው ጭምር ነው።
በፍርድ ቤት በሚካሄድ መደበኛ ክርክር መስቀለኛ ጥያቄ የምስክሮችን ተዓማኒነት ለማሳጣትና በአጠቃላይ እውነትን ለማውጣት ውጤታማ መሳሪያ ነው። ተከሳሹ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድሉ ተነፍጐት የተሰጠ የምስክርነት ቃል ህጋዊ ብቃቱም አጠያያቂ ነው። ያም ሆኖ ግን የአስተዳደር ክርክር በዓይነቱና በይዘቱ የፍርድ ቤት ክርክር መልክ ከያዘ ውጤታማ አስተዳደርን ወደ ኋላ መጎተቱ አይቀርም። ስለሆነም የመስቀለኛ ጥያቄ መቅረት ባለጉዳዩ ውጤታማ መከላከያ እንዳያቀርብ የሚያግደው ካልሆነ በስተቀር ውሳኔ ሰጭው አካል በመብቱ ላይ ገደብ ሊያደርግ ይችላል።g ይሁን እንጂ ምስክርነቱ በቃለ መሀላ ስር የተሰጠ ከሆነ መስቀለኛ ጥያቄ መከልከል አይገባም። በዚህ ረገድ የ1967ቱ ረቂቅ አዋጅ መስቀለኛ ጥያቄ የማቅርብ መብት ለባለጉዳዩ የሚፈቅድ ግልጽ ድንጋጌ የለውም። በተቃራኒው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ (1993) በአንቀጽ 6 (3)(ሐ) ላይ ይህን መብት በግልፅ አካቷል።
የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁ. 1183/2012 በደፈናው ‘ማስረጃ ስለመመርመር’ ቢናገርም በግልጽ ባለጉዳዩ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠቅ መብት ያለው ስለመሆኑ አያመለክትም። ባለጉዳዩ ለተቋሙ የቀረቡ ማስረጃዎችን የመስማትና የመመርመር መብት የአንቀጽ 37/1/ ሐ አነጋገር መብቱ ከጽሑፍ ማስረጃ ጋር ብቻ የተቆራኘ የሚመስል ይዘት አለው። በተጨማሪ ‘ለተቋሙ የቀረቡ’ የሚለው አገላለጽ አደናጋሪ ነው።
በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ መብት ከሞላ ጎደል በሁሉም ህጎችቻን ላይ አልተካተተም። ልዩ ሁኔታ የሚገኘው በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ 847/2006 ላይ ነው። በአንቀጽ 39/2/ እንደተመለከተው የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበት ሰው የከሳሽን ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል። የመንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን ክስ በሚሰማበት ወቅት እንዲሁ ግራ ቀኙ መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ ተፈቅዶላቸዋል። በፌደራል መንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓት ደንብ ቁ. 77/1994 አንቀጽ 17/5/ እንደሰፈረው የከሳሽ ምስክሮችን ተከሳሹ፤ የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮችን የመንግስት መስሪያ ቤቱ ተወካይ፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የጠራቸውን ተጨማሪ ምስክሮች ደግሞ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ።
በጠበቃ ተወክሎ የመከራከር መብት
የባለጋራን ክስና ማስረጃ ለማስተባበል የህግ ባለሙያ እገዛ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። በተለይ ውስብስብ በሆኑ የአስተዳደር ክርክሮች ተካፋይ የሆነ ወገን ካለባለሙያ እገዛ ራሱን በውጤታማ መንገድ ለመከላከል ያለው ዕድል አነስተኛ ነው። ሆኖም በጠበቃ መወከል መሰረታዊ የመሰማት መብት አካል ተደርጐ አይቆጠርም። በመብቱ ላይ የሚጣለው ገደብ የራሱ አሳማኝ ምክንያቶች አሉት።
የአስተዳደራዊ ዳኝነት ክርክር ጥብቅ የሆነ የመደበኛ ፍ/ቤቶች ዓይነት የስነ-ስርዓት አካሄድ ሳይከተል በፍጥነት ጉዳዩን ለመቋጨት ያለመ ነው። የጠበቃ መኖር ክርክሩ የባሰ እንዲወሳሰብና ከተገቢው ጊዜ በላይ እንዲንዛዛ በማድረግ የክርክሩን ኢ-መደበኛ ባህርይ ያጠፋዋል። በአጠቃላይ አነጋገር በጠበቃ ውክልና ከሚታገዝ ይልቅ ባለጉዳዩ ራሱ የሚከራከርበት አስተዳደራዊ ክርክር በአጭር ጊዜ እልባት ያገኛል። ያም ሆኖ ግን ክርክር የሚካሄድበት ጉዳይ በባሉጉዳዩ መብትና ጥቅም ላይ ሊኖረው ከሚችለው አሉታዊ ውጤት አንጻር ማለትም የክርክሩን ክብደትና ውስብስነት መሰረት አድርጐ እንደየሁኔታው በጠበቃ የመወከል ጥያቄን ማስተናገድ ያስፈልጋል።
ምክንያታዊ ውሳኔ
ዜጐች በሰውነታቸውና በንብረታቸው ላይ እርምጃ ሲወሰድ ከመንግስት ምክንያት ይሻሉ። አንዳችም ምክንያት የሌለው ውሳኔ የአስተዳደር በደል መገለጫ ነው። ኢ-ፍትሐዊነት በሁለት መልኩ ይገለጻል፤ የመጀመሪያው ምክንያት ሳይጠቀስ በደፈናው ውሳኔ ሲሰጥ፣ ሁለተኛው ደግሞ ውሳኔው በራሱ ፍርደገምድል፣ ሚዛናዊነት የጐደለውና በአሳማኝ ምክንያት ያልተደገፈ ሲሆን።
ለውሳኔ ምክንያት መስጠት በአስተዳደር ህግ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እያያዘና እያደገ የመጣ መሰረተ ሀሳብ ነው። ያም ሆኖ ከአሜሪካው የአስተዳደር ስነስርዓት በስተቀር በእንግሊዝ ሆነ በህንድ ምክንያት እንዲሰጥ የሚያስገድድ በሁሉም የአስተዳደር አካላት ተፈጻሚ የሆነ ጠቅላላ ደንብ የለም። ሆኖም አልፎ አልፎ ማቋቋሚያው አዋጅ ለአስተዳደራዊ ውሳኔ ምክንያት እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል።
አስተዳደራዊ ውሳኔ ሊኖረው የሚገባውን ይዘትና ቅርጽ በተመለከተ በ1967 ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 13 እንዲሁም በፌደራሉ ረቂቅ አዋጅ (1993 ዓ.ም.) አንቀጽ 32 ላይ ቅድመ ሁኔታዎቹ ተዘርዝረዋል። በዚሁ መሰረት አስተዳደራዊ ውሳኔ በጽሑፍ መሰጠት ያለበት ሲሆን ውሳኔውም የክርክሩን ፍሬ ነገር፣ የማስረጃዎች ፍሬ ጉዳይና ምንጭ፣ የነገሩን ጭብጥ አወሳሰን እንዲሁም በውሳኔው መሰረት ተመስርቶ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። ምንም እንኳን በረቂቆቹ ላይ ‘ምክንያት’ የሚለው ቃል በግልጽ ባይጠቀስም የውሳኔ ምክንያትን የሚያያቋቁሙ ሁኔታዎች የተካተቱ እንደመሆኑ ምክንያት መስጠት እንደአስገዳጅ ሁኔታ ተቀምጧል ማለት እንችላለን።
ከረቂቆቹ ጋር ሲነጻጸር የአስተዳደር ስነ- ስርዓት አዋጁ የአስተዳደር ውሳኔ መያዝ ያለበትን ፍሬነግሮች የዘረዘረ ሲሆን ለውሳኔ በቂ ምክንያት መስጠትም እንደ አንድ መሰረታዊ የውሳኔ አሰጣጥ መርህ አካቶታል። በመሆኑም የአስተዳደር ውሳኔ ሲሰጥ አብሮት በቂ ምክንያት ሊሰጥ ይገባል።h የአስተዳደር ውሳኔ ይዘት በተመለከተ በጽሑፍ ሆነ የሚከተሉትን መያዝ ይኖርበታል።
1-የውሳኔ ቀንና ቁጥር ፤
2-የተቋሙን ስም ፤
3-በክርክሩ ተካፋይ የሆኑ ወገኖችን አድራሻ፤
4-አከራካሪ ፍሬ ነገር፤
5-የማስረጃዎች ትንተና፤
6-የፍሬ ነገር እና የሕግ ትንታኔ፤
7-ውሳኔ
በአንዳንድ አዋጆች ላይ ውሳኔን በምክንያት ማስደገፍ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ነው። ለአብነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁ. 980/2008 አንቀጽ 6/2/ የንግድ ምዝገባ ማመልከቻ ውድቅ ከተደረገ መዝጋቢው አካል ምክንያቱን ገልጾ ለአመልካቹ ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት።
ከቀረጥ ዋጋ አወሳሰን ጋር በተያያዘ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ተጨማሪ መግለጫ ወይም ሰነድ ከዲክላራሲዮን አቅራቢው ከተቀበለ በኋላ ስለግብይት ዋጋው ትክክለኛነት ያለውን ጥርጣሬ ማስወገድ ካልቻለ ወይም ዲክላራሲዮን አቅራቢው ምላሽ ካልሰጠ በጉምሩክ አዋጅ ቁ. 859/2006 አንቀጽ 90 መሰረት ዋጋውን መወሰን እንዳልተቻለ ይቆጠራል። በዚሁ መሰረት የቀረበው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ ተቀባይነት ያላገኘበት ምክንያት በጽሑፍ ለአስመጭው ወይም ለወኪሉ ይገለጽለታል።i
በነዳጅ አቅርቦት ስራ ለመሰማራት የተጠየቀ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተቀባይነት ካላገኘ ምክንያቱ ለአመልካቹ ይገለጽለታል።j
የስደተኝነት ዕውቅና እንዲሰጥ የሚቀርብ አቤቱታ ተቀባይነት ቢያገኝም ባያገኝም ውሳኔው ለአቅራቢው በጽሑፍ መገለጽ አለበት።k
የኢ-አድሎአዊነት መርህ
ከአድልኦ የፀዳ ፍርድ (The rule against bias) የሚለው መርህ በኮመን ሎው አገራት በስፋት የዳበረ መሰረተ ሀሳብ ሲሆን በአጭሩ ሲገለጽ አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ መሆን የለበትም እንደማለት ነው። ኢ-አድሎአዊነት አብዛኛውን ጊዜ ራሱን የቻለ የተፈጥሮ ፍትህ መርህ ተደርጐ ቢጠቀስም በተግባር ሲታይ ግን በመሰማት መብት ውስጥ የሚጠቃለል የፍትሐዊ ስነ-ስርዓት አንድ አካል ነው። አንድ ሰው በአስተዳደር ጉባዔ (Administrative Tribunal) ፊት ቀርቦ የመሰማት እድል ሊሰጠው ይገባል ሲባል በውስጠ ታዋቂነት ፍ/ቤቱ ከአድልኦ የፀዳ እንደሆነ ግምት በመውሰድ ነው።
ፍርደ ገምድል ያልሆነ፤ ያልተዛባ ውሳኔ መኖር ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ የሚያንፀባርቅ እንደመሆኑ ተፈፃሚነቱም /በተለይ በኮመን ሎው አገራት/ እጅግ ጥብቅ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የታወቁት የእንግሊዝ ዳኛ ሎርድ ሄዋርት እንዲህ ብለው ነበር።
ፍትህ መሰራቱ ብቻ በቂ አይደለም። ፍትህ ሲሰራ ጭምር በማያጠራጥርና ግልጽ በሆነ አኳኋን መታየት መቻል አለበት።
የዳኛው ልጅ ‘ቀማኛ’ ተብሎ በአባቱ ፊት ችሎት ሲቀርብ በእርግጥም በህጉ መሰረት ጥፋተኛ ላይሆን ይችላል። ጥፋተኛ ካልሆነ መለቀቁ ፍትህ ነው። ግን ለማንም አይመስልም። ፍትህ ሲሰራ አይታይምና። ዋናው ቁም ነገር ዝምድና፤ የገንዘብ ጥቅም ወይም ሌላ ምክንያት በዳኛው ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተጽእኖ አለማድረጉ አይደለም። እነዚህ ሁኔታዎች እስካሉ ድረስ ዳኛው ምንም ያህል ንፁህና ጻድቅ ሰው ቢሆን እንኳን በችሎት ላይ ተቀምጦ ሲያስችል አመኔታ ያጣል። የኢ-አድሎአዊነት መርህ ዋና አላማ ውሳኔ ሰጭው አካል የተዛባ ፍርድ እንዳይሰጥ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ራሱም ሳያውቀው እንኳን በንፁህ ህሊናው ላይ ተፅእኖ ሊያደርሱ ከሚችሉ ሁኔታዎች ነጻ ሆኖ ዳኝነት እንዲሰጥ ለማስቻል ነው።
ይህ የኢ-አድሎአዊነት መርህ በተለይ በመደበኛ ፍ/ቤት፣ በአስተዳደር ጉባኤ እና ዳኝነታዊ ውሳኔ በሚሰጡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ጥብቅ ተፈጻሚነት አለው። ውሳኔ ሰጪው አካል በያዘው ጉዳይ በህሊናው ላይ ተፅእኖ ሊያመጣ የሚችል ሁኔታ መኖሩን በተረዳ ጊዜ ራሱን ከውሳኔ ሰጪነት ማግለል አለበት። ይህ ባልሆነበት ጊዜ በቂ ጥርጣሬ ያደረበት ወገን አቤቱታ አቅርቦ ዳኛው እንዲቀየርለት ማመልከት ይችላል። ሁኔታው መኖሩ የታወቀው ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ከሆነ የዛ ውሳኔ እጣ ፈንታ ዋጋ አልባ መሆን ነው።
አድሎአዊ ውሳኔ ተሰጥቷል የሚባለው የውሳኔ ሰጭው ህሊና የተዛባ እንደሆነ ነው፡ ለመሆኑ የሕሊና መዛባት ምን ማለት ነው?
በጥሬ ትርጉሙ ሲታይ ማንኛውም ነገር በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ውሳኔ ሰጭው በነጻ ህሊናው ተመርቶ ሊሰጥ ይችል ከነበረው ውሳኔ በተቃራኒ የተለየ ውሳኔ ላይ ያደረሰ ከሆነ ህሊናው ተዛብቷል ብለን መናገር እንችላለን። ህሊና ከተዛባ የክርክሩ ውጤት (ማለትም ውሳኔው) ጉዳዩ ከመመርመሩ በፊት ድምዳሜ ተደርሶበታል። ዳኛው ከከሳሽ ወይም ተከሳሽ ጉቦ ከተቀበለ ፍርዱ ለማን እንደሚሰጥ አስቀድሞ ታውቋል። በዚህ መልኩ የሚሰጥ ፍርድ በተዛባ ህሊና የተሰጠ አድሎአዊ ፍርድ ነው።
የተዛባ ህሊና ከምንጩ አንፃር በተለያየ መንገድ ይገለጻል። በዋነኛነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
ዝምድና
ዝምድና ሲባል የስጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም በግል ግንኙነት፣ በሙያ ትስስር እንዲሁም በጓደኝነትና በትውውቅ ላይ የተመሰረተና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተፅእኖ ሊያመጣ የሚችል ዝምድና ወይም ጥላቻ ሁሉ ያጠቃልላል።
ውሳኔ ሲጪው ከአንደኛው ተከራካሪ ወገን ጋር ዝምድና ወይም ጥላቻ ያለው ከሆነ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ በሆነ መልኩ አድሎአዊ ወይም የተዛባ ፍርድ የመስጠት እድሉ ከፍተኛ ነው። የፌደራሉ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ (1993 ዓ.ም.) በአንቀጽ 29/2/ ላይ የዝምድናን ጽንሰ ሀሳብ በጣም አጥብቦታል። ድንጋጌው የግል ጥላቻ እንዳለበት የሚገምት ውሳኔ ሰጪ ራሱን በክርክሩ ሂደት ከመሳተፍ እንዲያገል ግዴታ ይጥልበታል። ከግል ጥላቻ ባልተናነሰ ትውውቅ፣ ቅርበት፣ ጓደኝነት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ይህ መሰረታዊ ቁም ነገር በረቂቅ አዋጁ ላይ ተረስቷል።
ከዚህ በተቃራኒ የ1967ቱ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ከዝምድና የሚመነጭ የተዛባ አመለካከት ከቀጥተኛ የግል ጥቅም እንዲሁም ከስጋ ወይም ከጋብቻ የሚመነጭ ዝምድና በሙሉ እንደሚያጠቃልል በግልፅ ያመለክታል። የአስተዳደር ስነ-ስር ዓት አዋጅ ቁ. 1183/2012 ከ 1967 ቱ ረቂቅ ጋር ተቀራራቢ ይዘት አለው። ውሳኔው ሰጭው ከጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ጥቅም ካለው ወይም ባለጉዳዩ የስጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ወይም በቅርብ የሚታወቅ ወዳጁ ሲሆን ወይም የእነዚህ ሰዎች የጥቅም ግጭት ያለበት ጉዳይ ከሆነ ራሱን ማግለል እንዳለበት አንቀጽ 38/1/ በፊደል ሀ እና ለ በውሳኔ ሰጭው ላይ ግዴታ ይጥላል።
በአስተዳደር ህግ ውስጥ ‘ዝምድና’ የሚለው ቃል ከስጋ ወይም ጋብቻ ዝምድና የዘለለ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርስ የሚችል ማንኛውንም አሉታዊና አዎንታዊ ግንኙነት ያቅፋል። ነገሩን ለማብራራት ያህል በአይ.ፒ. ማሴይ ‘የአስተዳደር ህግ’ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ጉዳይ እንደ መላምታዊ ምሳሌ አገራዊ መልክ በማስያዝ ማየቱ ጠቃሚ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ማዕድን የመፈለግና የማውጣት ስራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ከተሰጠው ፍቃድ ውጪ ህገ ወጥ ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ በመከሰሱ ፈቃዱ የማይሰረዝበት አጥጋቢ ምክንያት ካለ መከላከያውን ይዞ እንዲቀርብ በማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር መጥሪያ ተላከለት። ሆኖም የዚህ ድርጅት ባለቤት በአንድ ወቅት ሚኒስትሩ ለምርጫ በተወዳደሩበት ወቅት የተቃዋሚ ፖርቲ አባል ሆኖ ሚኒስትሩ እንዳይመረጡ በመጣር ከፍተኛ ተቃውሞና ቅስቀሳ አድርጓል። በሌላ ጊዜም የሚኒስትሩን ስም በማጥፋት ወንጀል ተከሶ በመጨረሻ ነጻ ወጥቷል። እንግዲህ ሚኒስትሩ የንግድ ፍቃዱን ቢሰርዝ ውሳኔው በግል ግንኙነት /ጥላቻ/ ላይ የተመሰረተና የተዛባ ነው ማለት ይቻላል?
ከህንድና ከሌሎች አገሮች ልምድ ለመረዳት እንደሚቻለው የግል ግንኙነትን ጨምሮ በሌሎች ሁኔታዎች ውሳኔ የተዛባ ነው ለማለት ተገቢ የሆነ ጥርጣሬ መኖር አለበት። የመጀሪያው መለኪያ ውጫዊ መልክ ወይም ገጽታ መሰረት ያደርጋል። ይህም ማለት የግል ግንኙነቱ ደረጃ በአንድ አስተዋይ ሰው እይታ አድሎአዊነትነት የሚፈጥር አይነት ከመሰለና ይህም ተገቢ የሆነ ጥርጣሬን የሚያሳድር ከሆነ ውሳኔው የተዛባ ስለመሆኑ መደምደም ይቻላል። ሁለተኛውና ‘ቅርብ የሆነ አጋጣሚ’ የሚባለው መለኪያ ደግሞ ትኩረት የሚያደርገው አድልኦ የሚፈጠር መሆኑ አይደለም። ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱን ጉዳይ በነጠላ በማየት ግንኙነቱ ውሳኔው ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ያለውን አጋጣሚ (ደረጃ) ይመረምራል።
ስለሆነም በውሳኔ ሰጪውና በባለጉዳዩ መካከል የስጋ ወይም ጋብቻ ዝምድና ቢኖርም እንኳን ሁለቱ ካላቸው ቅርርብ ወይም ርቀት እንዲሁም ትክክለኛ የግንኙነት ደረጃ አንጻር የተጽእኖው ደረጃ ኢሚንት የሚባል አይነት ከሆነ ውሳኔው አልተዛባም። በተቃራኒው የዝምድናው ደረጃ ሩቅ ቢሆንም እንኳን ውሳኔ ሰጪውና ባለጉዳዩ በማህበራዊ ግንኙነታቸው የጠበቀና ቅርብ ትስስር ያላቸው (ለምሳሌ ለብዙ ጊዜያት አብረው በአንድ ቦታ የኖሩና ሌላም መሰል ትስስር ያላቸው) ከሆኑ አድሎአዊ ውሳኔ የመስጠት አጋጣሚው በጣም የሰፋ መሆኑን ስለሚያሳይ የውሳኔው የመዛባት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።
ተገቢ የሆነ ጥርጣሬ ወይም ቅርብ የሆነ አጋጣሚ እንደ የተዛባ ውሳኔ /አድልዎ/ መለኪያነት እርስ በርስ በጣም የተለያዩ ቢመስሉም በተግባር ሲታዩ ዞሮ ዞሮ መድረሻቸው አንድ ነው። መሰረታዊው ጥያቄ ውሳኔ ሰጪው ህሊናው ተዛብቷል? የሚል አይደለም። የአንድን ሰው የህሊና ሁኔታ ማረጋገጥ ይከብዳል። መታየት ያለበት ውሳኔው የተዛባ ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ወይም ቅርብ ነው ብሎ ለማመን የሚቻልበት ተገቢ ጥርጣሬ ማሳደሩ ነው።
ተገቢ ጥርጣሬ ማንኛውም ተራ ስሜትና ሀሜት የሚጨምር ሳይሆን በአስተዋይ ሰው እይታ በቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ያሉትን አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች በመመርመር ተገቢ ወይም ሚዛናዊ ሊባል የሚችል የጥርጣሬ ሁኔታ መፈጠሩና ይህም በ3ኛ ወገን ላይ የሚያሳድረው ምክንያታዊ ስሜት ነው።
የገንዘብ ጥቅም
ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ጥቅም እንደ አድሎዎ መገለጫነቱ ሲታይ ሊገኝ የሚችለው የገንዘብ መጠን አነስተኛ ቢሆንም እንኳን ውሳኔውን ለመሻር አሳማኝ ምክንያት ነው። ሰዎች ከገንዘብ ጥቅማቸው በተጻራሪ ውሳኔ እንደማይሰጡ ከሰው ልጅ ባህርይና ከተፈጥሮ እውቀት መገንዘብ አያዳግትም። ጉቦ መቀበል ግልጽና ዓይን ያወጣ የገንዘብ ጥቅም መገለጫ እንደመሆኑ ከተከራካሪ ወገኖች ከአንዱ የገንዘብ ስጦታ የተቀበለ የአስተዳደር መ/ቤት ሹመኛ ወይም ሰራተኛ እንዲሁም የአስተዳደር ጉባዔ ዳኛ የሚሰጠው ውሳኔ ወዲያውኑ ሊሻር ይገባዋል። ሆኖም የገንዘብ ጥቅም የሚገለጽባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ የአስተዳደር ጉባዔ ዳኛ ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ሆኖ በቀረበው ድርጅት ውስጥ የአክሲዮን ባለቤት ከሆነ ተገቢ በሆነ ጥርጣሬ ብሎም ቅርብ በሆነ አጋጣሚ መለኪያ የሚሰጠው ውሳኔ የተዛባ ነው ብሎ መደምደም ተገቢ ይሆናል።
በፌደራሉ ረቂቅ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ (1993 ዓ.ም.) መሰረት የአስተዳደር ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው ሰው በጉዳዩ የመጨረሻ ውጤት ላይ የገንዘብ ጥቅም እንዳለው ከተረዳ ወዲያውኑ ራሱን ከውሳኔ ሰጪነት እንዲያገል ይጠበቅበታል። ይህ ካልተፈፀመ በክርክሩ ተካፋይ የሆነው ወገን አቤቱታ አቅርቦ ከችሎት እንዲነሳለት መጠየቅ ይችላል።l
ተደራራቢ (ቅይጥ) ሚና
በአንድ ጉዳይ ላይ በአጣሪነት፣ በመርማሪነት፣ በከሳሽነትና መሰል ኃላፊነቶች የተሳተፈ የመንግስት ባለስልጣን እንደገና ተመልሶ በተመሳሳይ ጉዳይ በውሳኔ ሰጭነት ስልጣኑ ከተሳተፈ የውሳኔውን አድሎአዊነት ያንፀባርቃል። አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው ተሿሚ ወይም ሠራተኛ ከውሳኔ በፊት አጣሪ፣ መርማሪ፣ ወይም በሌላ ሙያ ተሳታፊ በሆነበት ጉዳይ ተመልሶ በውሳኔ ሰጪነት ስልጣን የሚሳተፍ ከሆነ የተዛባ አድሎአዊ ውሳኔ የመስጠት እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። አንድ ሰው ራሱን የሚቃረን ውሳኔ የማይሰጥ መሆኑ ከሰው ልጅ ባህርይ የምንረዳው እውቀት ነው።
በአንድ ጉዳይ በተደራራቢ ሚና መሳተፍ በአስተዳደር ሂደቱ በውስጡ ያለ መገለጫ ቢሆንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ቁጥጥር ካልተደረገበት የፍትሀዊነትንና የርትዐዊነትን ጽንሰ ሀሳብ ድራሹን ያጠፋዋል። የአንድን ድርጅት የንግድ እንቅስቃሴ ህጋዊነት ለማጣራት በመርማሪነት ሚና የተሳተፈ የመንግስት ሰራተኛ የድርጅቱን የንግድ ፈቃድ ለመሰረዝ በተካሄደው የአስተዳደር ክርክር ላይ በውሳኔ ሰጪነት ሚና በድጋሚ የሚሳተፍ ከሆነ ተደራራቢ ሚናው አድሎአዊ ለሆነ ውሳኔ መንስዔ መሆኑ አይቀርም። በተመሳሳይ መንገድ አንድ ሰራተኛ በተከሰሰበት የዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ የመ/ቤቱ ኃላፊ የዲሲፕሊን ኮሚቴው አባል ሆኖ ከተሳተፈ በኃላፊነት ስልጣኑ የሚወስደው የዲሲፕሊን እርምጃ ከአድልኦ ያልፀዳ ነው።
ተደራራቢ ሚናን በተመለከተ ሁለቱም ረቂቅ አዋጆች ቁንጽል ድንጋጌ ቢኖራቸውም ከፍሬያማነታቸው ይልቅ ድክመታቸው ጐልቶ ይታያል። የፌደራሉ ረቂቅ አንቀጽ 29 /6/ እንዲህ ይነበባል።
በማናቸውም የአስተዳደር ተቋም ውስጥ በወንጀል ምርመራ ወይም ክስ በመመስረት ተግባር ተሰማርቶ የሚገኝ የመንግስት አስተዳደር ሰራተኛ በማናቸውም ሁኔታ በያዘው ጉዳይ ወይም ከዚሁ ጋር በፍሬ ነገር በተዛመደ ጉዳይ ላይ በሚሰጥ አስተዳደራዊ ውሳኔ በምስክርነት፣ የህግ ምክር በመስጠት መሳተፍ ወይም መምከር አይችልም።
የዚህ አንቀጽ ዋና ግድፈት የሚነጻጸሩት ተደራራቢ ሚናዎች አጣሪነት፣ መርማሪነት፣ ከሳሽነት ወዘተ… ከውሳኔ ሰጪነት ስልጣን ጋር ሳይሆን ከምስክርነት እና የህግ ምክር ሰጪነት ሚና ጋር መሆኑ ነው። የተደራራቢ ሚና ጽንሰ ሀሳብ ዋና አላማው ጉዳዩን ያጣራው ወይም የመረመረው ባለስልጣን ተመልሶ ውሳኔ ሰጪ ከሆነ ውሳኔው አድሎአዊ ሊሆን ስለሚችል ይህንኑ በመከላከል በአስተዳደር ክርክር ውስጥ ፍትህ ወይም ርትዕ ማስፈን ነው። ረቂቁ ይህን አላማ ለማሳካት ተጨባጭ ችግሩ ላይ ከማነጣጠር ይልቅ ለአስተዳደር ፍትህ አግባብነቱ ብዙም ፋይዳ በሌለው የወንጀል መርማሪነትና ከሳሽነት ሚናን ምስክር ከመሆንና የህግ እርዳታ ከመስጠት ሚና ጋር እንዳይደራረብ ገደብ ያስቀምጣል።
በ1967ቱ ረቂቅ አዋጅ መሰረት የመርማሪነት (ይህም በወንጀል መርማሪነት ሳይሆን በአስተዳደራዊ ሂደት ላይ ያሉ ሚናዎችን ያጠቃልላል።) እና የዐቃቤ ህግነት ሚና የነበረው ባለስልጣን ወይም ሰራተኛ በአስተዳደር ክርክሩ ላይ በዋናነት በውሳኔ ሰጪነት እንዳይሳተፍ ይከላከላል። ይሁን እንጂ በምስክርነት ወይም በአማካሪነት ከመሳተፍ እንደማይከለከል በልዩ ሁኔታነት በግልጽ ያስቀምጣል።
በንፅፅር ሲታይ አዋጅ ቁ. 1183/2012 የተሻለ ይዘት ያለው ቢሆንም ሁሉንም መሰረታዊ የተዛባ አመለካከት ምንጮች አልዳሰሰም። በአንቀጽ 38/1/ በፊደል ሐ እና መ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።
በመታየት ላይ ላለው ጉዳይ እንደ ባለሙያ፣ ወኪል ወይም የግል ጠበቃ ሆኖ ተሳትፎ ከሆነ፤
በመታየት ላይ ያለው ጉዳይ ሰራተኛው በስር ውሳኔ አይቶት በይግባኝ የቀረበለት ከሆነ
ከሁለቱ ውጭ በመመርማሪነት የተሳተፈ ሰው በውሳኔ ሰጭነት እንዳይሳተፍ በግልጽ የሚከለክል ድንጋጌ የለም።
 
ልዩ ሁኔታዎችና የተፈጻሚነት ወሰን
በፍርድ ቤቶች የዳበሩ መሰረታዊ መርሆዎች እንዲሁም አስገዳጅነት ያላቸው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ህጎች በሁሉም አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ወጥ ተፈጻሚነት የላቸውም። የእያንዳንዱ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከግለሰቦች መብትና አንጻር ሲመዘን ከቀላል እስከ ከባድ የሚያስከትለው ውጤት እና ተፅዕኖ ይለያያል። የውሳኔውም ዓይነት እንዲሁ ወጥ መልክ የለውም። የመንግስት ሠራተኛን ከስራ ማባረር፣ አስተዳደራዊ ቅጣት መጣል፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታ ማፈናቀል፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት (ካርታ) መሰረዝ፣ የብቃት ማረጋገጫ፣ የሙያ ፈቃድ፣ የንግድ ፈቃድ፣ የስራ ፈቃድ መሰረዝና ማገድ፣ የሊዝ ውል ማቋረጥ፣ በአንድ የስራ ዘርፍ የተሰጠ ዕውቅና (ለምሳሌ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) መሰረዝ እና ሌሎች መሰል ውሳኔዎች ህገ መንግስታዊ ጥበቃ ያገኙ መብቶችን የመጣስ ከፍተኛ አዝማሚያ ስላላቸው ፍትሐዊ ስርዓት ተከትለው መወሰድ ይኖርባቸዋል። አስተዳራዊ ቅሬታ እና ይግባኝ የሚስተናገድበት መንገድ እንዲሁ ፍትሐዊ ስነ ስርዓት እና አንጻራዊ ገለልተኘነት ካላንፀባረቀ የይስሙላ ሆኖ ነው የሚቀረው።
ስለሆነም በእነዚህ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ስር የሚወድቁና ሌሎች ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ለመሰማት መብት እና ኢ-አድሎአዊነት መርሆዎች ተገዢ ሊሆኑ ይገባል። እንደዛም ሆኖ ግትር ተፈጻሚነት ሊኖራቸው አይገባም። አስተዳደራዊ አመቺነትን ያላማከለ የሰነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ውጤታማነትን ያኮላሻል። ለምሳሌ በከፊል አስተዳደራዊ ክርክሮች በጠበቃ የመወከል መብት በአስተዳደሩ ላይ ከሚያመጣው ጫና አንጻር እንዲቀር ቢደረግ የመሰማት መብትን አያጣብብም።
ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች አንድ የአስተዳደር መ/ቤት በየዕለቱ ይቅርና በየወሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት አይደሉም። በቁጥር በእጅጉ በልጠው የሚገኙት ውሳኔዎች ግዙፋዊ የመብት መጓደል አያስከትሉም። ሆኖም በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የግለሰቦችን መብትና ጥቅም የሚነኩ ከሆነ በዘፈቀደ መወሰድ የለባቸውም። ይብዛም ይነስም በተነካው መብት ልክ ፍትሐዊነት በገሀድ እንዲታይ ይጠበቃል።
እስካሁን የቀረበው ዳሰሳ አንድ መሰረታዊ ጥልቅ መልዕክት ያስጨብጠናል። ይኸውም፤ ሁሉንም የአስተዳደራር ውሳኔዎች ለአንድ ወጥ ስነ ስርዓት ተገዢ ማድረግ ሊሞከር ቀርቶ አይታሰብም። ፍርድ ቤት ብቻ ነው አንድ ወጥ ስነ-ስርዓት የሚከተለው። ያላደገ ሆነ የዳበረ የአስተዳደር ህግ ያላቸው አገራት በማንኛውም አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አንድ ወጥ ስነ ስርዓት የላቸውም። አንድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከቀላል እስከ ጥብቅ የትኛውን ስነ ስርዓት መከተል እንዳለበት ለመወሰን ለህግ አውጪው አስቸጋሪ ስራ ነው። ውስብስብ የሆነው የአስተዳደር ስራ ባህርይ በዚህ ረገድ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል። ያም ሆኖ ግን ፈተናው በወጉ ካልተመለሰ ፍትሐዊነትና ውጤታማ አስተዳደር ሚዛናቸውን ይስታሉ።
እንደ ፒተር ዎል አገላለጽ በአስተደደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተፈጻሚ የሚሆኑት አነስተኛ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች እንደ ጉዳዩ ዓይነትና ውስብስብነት፣ የማስረጃዎችና የሚረጋገጡት ፍሬ ነገሮች ዓይነት፣ የውሳኔ ሰጭው ማንነትና የሚያከናውነው የአስተዳደር ተግባር ባህርይ እንዲሁም ውሳኔው በግለሰቦች ላይ ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት አንጻር ደረጃቸው ይለያያል።
[W]hat constitutes a minimum compliance with due process in the way of administrative hearing…will vary to a considerable extent with the nature of the substantive right, the character and complexity of the issues, the kinds of evidence and factual material, the particular body or official, and the administrative functions involved in the hearing.m
የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ፍትሐዊነት እንዲሰፍን ከዚያም አልፎ በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር እንዲያብብና እንዲጎለብት የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ በሀሳብ ሆነ በተግባር ደረጃ ተፈትኖ የተረጋገጠ ቢሆንም አፈጻጸሙ በጥንቃቄ ወሰን ካልተበጀለት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። የአስተዳደር ስነ ስርዓት ፍርድ ቤቶች እንደሚከተሉት የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ጥብቅ እና መደበኛ በሆነ ቁጥር አስተዳደራዊው ሂደት እጅና እግሩ ይታሰራል። በዚህ የተነሳ ዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ያጣሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደግሞ የዜጎችን ብሶት ‘ከፍትሕ ጥማት’ ወደ ‘አገልግሎት ረሀብ’ ቢቀይረው እንጂ ፍሬ አያስገኝም።
እ.ኤ.አ በ1946 በወጣው የአሜሪካው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ (Administrative Procedure Act) የአስተዳደር ዳኝነት መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሚል ለሁለት ተከፍሏል። መደበኛው የአስተዳደር ዳኝነት ከክስ መስማት እስከ ውሳኔው ይዘት ድረስ በዝርዝር አስገዳጅ ደንቦች የሚገዛ ሲሆን ኢ-መደበኛው ግን በቀላልና ልል ስርዓት ይመራል። አስተዳደራዊ አመቺነትን ያማከለው ይህ አካሄድ በአንድ በኩል በዘፈቀደ በሚወሰድ እርምጃ ፍትሕ እንዳይጓደል በሌላ በኩል ደግሞ በጥብቅ ስነ ስርዓት ሳቢያ ውጤታማ አስተዳደር እንዳይሰናከል ህጉ የተከተለው አስታራቂ መስመር ነው።
በመደበኛው የአስተዳደር ዳኝነት ከክስ መሰማት (hearing) ጀምሮ አጠቃላይ ክርክሩ በመዝገብ (on the record) እንዲካሄድ የሚያስገድድ ሲሆን በይዘቱም ጠበቅ ያለ ስርዓት ነው። ይህ ስርዓት ተፈጻሚ የሚሆነው በልዩ ህግ በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ ብቻ ነው። የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህጉ የመደበኛውን የአስተዳደር ዳኝነት የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች በመደንገግ ተፈጻሚነቱን ግን ህግ አውጪው በዝርዝር ህግ በግልጽ በወሰናቸው ሁኔታዎች ላይ ብቻ ገድቦታል።n በዚህ መልኩ በመደበኛው የዳኝነት ሂደት የሚያልፉ የአስተዳደር ክርክሮች በቁጥር ከአምስት ፐርሰንት አይበልጥም።o የተቀሩት ኢ-መደበኛውን ስርዓት የሚከተሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር መደበኛው አስተዳደራዊ ክርክር ተፈጻሚነቱ በልዩ ሁኔታዎች ብቻ ነው።
አሜሪካኖች ከሞላ ጎደል ሁሉም አስተዳደራዊ ክርክሮች ኢመደበኛ አካሄድ እንዲከተሉ የመረጡበት ምክንያት ንድፈ ሀሳባዊ ሳይሆን ተጨባጭና ተግባራዊ ነው። የአስተዳደር መ/ቤቶች እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እየሰሙ በማከራከር ውሳኔ የሚሰጡ ከሆነ የተቋቋሙለትን ዓላማ መቼም ቢሆን አያሳኩም። መደበኛ የአስተዳደር ክርክር ከሚፈጀው ጊዜ እንዲሁም ከሚያስፈልገው የሰው ሀይልና የገንዘብ ወጪ አንጻር በሁሉም አስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ ተፈጻሚ ቢደረግ ውጤታማ አስተዳደር ይቅርና ‘አስተዳደር’ የሚባል ነገር ራሱ አይኖርም።
በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም. እና 2001 ዓ.ም. የተዘጋጁት ረቂቅ የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጆች ይህን መሰረታዊ ተጨባጭ እውነታ በቅጡ አልተረዱትም። ሁለቱም ረቂቆች አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት መደበኛው የክስ መሰማት ስርዓት እንዲከናወን በአስተዳደር መ/ቤቶች ላይ ግዴታ ያስቀምጣሉ። ይሄ የገዘፈ ችግር በረቂቆቹ የተገታ ሳይሆን ህግ ሆኖ የፀደቀው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግም የሚጋራው ችግር ነው።p ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሜሪካ በዚህ ዓይነት የክርክር ሂደት የሚያልፉ ጉዳዮች ከአምስት ፐርሰንት አይበልጡም። የተቀረው 95 ፐርሰንት ኢመደበኛ ነው። በረቂቅ ህጎቹ የተመረጠው አቅጣጫ ደግሞ ሁሉም (ማለትም 100 ፐርሰንት) አስተዳደራዊ ክርክሮች መደበኛ ስርዓት እንዲከተሉ ያስገድዳል። በዚህ ሁኔታ አስገዳጅ ህግ ሆነው በተወካዮች ም/ቤት ቢታወጁ ሊከተል የሚችለውን አስተዳደራዊ መንዛዛት ለመገመት ከወደሁ ያስቸግራል።
የመሰማት መብት እና ኢ-አድሎአዊነት መርህ ከአገራችን ህግ አንጻር
ህገ መንግስታዊ የመሰማት መብት?
የተፈጥሮ ፍትሕ በእንግሊዝና ሌሎች ኮመን ሎው አገራት በዳኞች የዳበረ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርህ ነው። ይህ መርህ በህግ በግልጽ እንደ ቅድመ ሁኔታ ባይቀመጥም ዳኞች ተፈጻሚ እንዳያደርጉት አያግዳቸውም። በአሜሪካ እንዲሁ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኘው ዱ ፕሮሰስ ኦፍ ሎው (Due Process of Law) በመባል የሚታወቀው ህገ መንግስታዊ መርህ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን የሚገዛ ልዩ ህግ ባይኖርም እንኳን ፍርድ ቤቶች እንደ አግባብነቱ ተፈጻሚ ያደርጉታል። ሆኖም በእነዚህ ሁለት አገራት ሆነ በሌሎችም ዘንድ አስተዳደር የሚመራበት ስነ ስርዓት ምንጩ በህግ አውጪው የሚወጣ ህግ ነው።
ግልጽ የህግ ድንጋጌ ካለ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት ውሳኔ በፍርድ ቤት ሊሻር ወይም ሊሰረዝ እንደሚገባው አያጠራጥርም። አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ከሌለስ? ፍርድ ቤቶቻችን እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ፍርድ ቤቶች ፍትሐዊ የውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ማዳበርና ተፈጻሚ ማድረግ አለባቸው? ካለባቸውስ አቋማቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት አለው? በአስተዳደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የመሰማት መብት እንዲሁም ኢ-አድሎአላዊነት መርህ በህግ በግልጽ ባልተደነገገበት ሁኔታ የስነ-ስርዓት ጉድለት ያለበት አስተዳደራዊ ውሳኔ ዕጣ ፋንታ መወሰን በብዙ መልኩ ከባድ ነው።
በአንድ በኩል ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የማረጋገጥ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በሌላ በኩል ህጉን ከማንበብና ከመተርጎም ባለፈ ህግ መጻፍ ህገ መንግስታዊ ሚናቸው አይፈቅድላቸውም። በዚህ መልኩ የሚፈጠረው ‘ህገ መንግስታዊ አጣብቂኝ’ ብርታትና ጥንቃቄ ካልታከለበት በቀላሉ አይፈታም። በተጨማሪም ‘መርህ’ በተጨባጭ ‘መሬት ሲወርድ’ ከልዩ ሁኔዎች ጋር ሊጣጣምና የተፈጻሚነት ወሰኑ በአግባቡ ሊሰመር ይገባል። የመሰማት መብት የግድ የሚልበት ሁኔታ ቢኖርም ከተግባራዊ ፋይዳውና ውጤታማ አስተዳደር አንጻር የሚገደብባቸው ሁኔታዎች አሉ። በተጨማሪም የተፈፃሚነቱ ወሰን የግለሰብ መብት ወይም ጥቅም በሚነካ የዳኝነታዊ ባህርይ ባለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ብቻ ነው። ይህ የሚያሳየን አስቸጋሪው ስራ የፍትሐዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን በጠቅላላው መቀበሉ ሳይሆን እንደ ጉዳዩ አይነት ልዩ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ የተፈጻሚነቱን አድማስ መለየቱ ላይ ነው።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 43511q በ2005 ዓ.ም. በሰጠው ፈር ቀዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት አስገዳጅ የህግ ድንጋጌ ባይኖርም ከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው አካል የመሰማት መብትን የማክበር ግዴታ አለበት። የችሎቱን አቋም በጥልቀት ለመረዳት በሐተታው ክፍል የሰፈረውን የሚከተለውን አስተያየት ማየቱ ተገቢ ነው።
…የመሰማት መብት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሊከበር የሚገባው መብት ነው። የመሰማት መብት ከመጀመሪያው ክርክር ጀምሮ እስከመጨረሻው የዳኝነት ሰጪ አካል መከበር ያለበት ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱና ስለ ክርክር አመራር በተደነገጉት እንደፍትሐብሔር ስነ ስርአት አይነት ሕጎች ከተደነገጉት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
የችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ዜጎች ሀሳባቸው ሳይደመጥ መብትና ጥቅማቸውን የሚጎዳ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዳይሰጥባቸው ከለላ በማጎናጸፍ ረገድ ህገ መንግስታዊ ፋይዳው ‘ታሪካዊ’ ሊሰኝ የሚችል ነው። ከዚያም አልፎ ለአገራችን የአስተዳደር ህግ ዕድገት ችሎቱ ካደረጋቸው አስተዋጽኦዎች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። በእርግጥ የውሳኔው ፋይዳ ብቻውን በቁሙ መለካት በተግባር ያስከተላቸውን ለውጦች በማጋነን ያስተቻል። የሰ/መ/ቁ. 43511 አስተዳደሩ አካሄዱን ከችሎቱ አቋም ጋር እንዲያስተካክል በዚህም የመሰማት መብትን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ አካል አድርጎ እንዲያቅፍ የፈጠረው ጫና ሆነ በተግባር ያስከተለው ተጨባጭ ለውጥ የለም። አስገዳጁን የህግ ትርጉም መቀበልና መተግበር ያለባቸው የስር ፍርድ ቤቶችም ቢሆኑ በአስተዳደራዊ ክርክሮች የመሰማት መብትን በትጋት እንዲያስከብሩ የለውጥ ምንጭ አልሆነላቸውም። ምናልባትም ውሳኔው ስለመኖሩ ራሱ ገና አልሰሙ ይሆናል። የሰበር ውሳኔዎች የተደራሽነት ችግር እንዲሁም በውሳኔዎቹ ላይ ጠንካራ ምሁራዊ የሀሳብ ልውውጥ ባህል አለመዳበር በርካታ አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች በቅጾች መጽሐፍ ውስጥ ተቀብረው እንዲረሱ ያደርጋቸዋል።
የሰ/መ/ቁ. 43511 ከህገ መንግስታዊ ፋይዳው ባሻገር ክርክሩ የተጓዘበት መስመር ትኩረት ይስባል። የክርክሩ መነሻ አመልካቾች ከአዋጅ ውጪ የተወረሰ ቤት እንዲመለስላቸው ለኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን ኤጀንሲውም ተጠሪ ምላሽ እንዲሰጡበት ካደረገ በኋላ ማስረጃና ክርክሩን ሰምቶ ቤቱ እንዲመለስላቸው ወስኗል። በውሳኔው ባለመስማማት ተጠሪ ለኤጀንሲው ቦርድ ይግባኝ በማቅረባቸው ቦርዱ የኤጀንሲውን ውሳኔ ሽሮታል። ከመሻሩ በፊት ግን አመልካቾችን ጠርቶ ክርክራቸውን አልሰማም።
በመቀጠል አመልካቾች የመሰማት መብታቸው አለመጠበቁን በመግለጽ በቀጥታ የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም አጣሪ ችሎቱ የቦርዱን ውሳኔ የማረም ስልጣን እንዳልተሰጠው በመግለጽ ሳይቀበለው ቀርቷል። አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እንደሚያስነሳ በመጠቆም ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አመለከቱ። እዛም ተቀባይነት አጡ። አሁንም ሰሚ ፍለጋ ‘አቤት!’ ማለታቸውን ባለማቆም ጉዳያቸውን እንዲያይላቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ አቀረቡ። በመጨረሻ ጥያቄያቸው ፍሬ አግኝቶ የአጣሪ ችሎቱ ውሳኔ ተሻረ።
አመልካቾች ተስፋ ባለመቁረጥ እስከ ፌዴሬሽን ም/ቤት ድረስ ዘልቀው ድል መጎናጸፋቸው በራሱ የተለየ ስሜት ቢያጭርም በተለየ መልኩ ትኩረት የሚስበው ግን የክርክሩ ሂደት ሳይሆን የም/ቤቱ ውሳኔ ይዘት ነው። የሰበር ችሎት የዳኝነት ስልጣንን በማስፋት አዲስ ህገ መንግስታዊ መልክ ያላበሰው ይኸው ውሳኔ የሰበር ችሎት የቦርዱን መሰረታዊ የህግ ስህተት የማረም ስልጣን እንዳለው አረጋግጧል። የም/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ መነሻ ያደረገው የኤጀንሲው ቦርድ ዳኝነታዊ ስልጣን ነው። ስለሆነም ቦርዱ የዳኝነት መሰል አካል (quasi judicial body) በመሆኑና ይህ አካል የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ስልጣኑ ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው።
የስልጣን ጥያቄው እልባት ካገኘ በኋላ መዝገቡ ከፌዴሬሽን ም/ቤት ወደ ሰበር ችሎት ሲመለስ የቦርዱ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መሰረታዊ ጭብጥ ሆኖ ተነስቷል። ጭብጡን ለመፍታት ችሎቱ የቦርዱን የማቋቋያ አዋጅr የተመለከተ ቢሆንም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ቦርዱ የተከራካሪዎችን የመሰማት መብት እንዲጠብቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ አላገኘም።
በአስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ የመሰማት መብት የሚጠብቅ ህግ በሌለበት ሁኔታ ውሳኔው ሰጭው አካል በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት መብቱን እንዲያከብር ግዴታ መጫን ለችሎቱ ፈታኝ ስራ እንደሆነ አያጠያይቅም። ምክንያቱም ከህግ የመነጨ ግዴታ በሌለበት ቦርዱ የመሰማት መብት መርሆዎችን እንዲከተል ማስገደድ በውጤቱ የችሎቱን ተግባር ከህግ መተርጎም ወደ ‘ህግ መጻፍ’ ያሸጋግረዋል። ስለሆነም ችሎቱ በስልጣን ክፍፍል መርህ የተሰመረውን ድንበር ሳይሻገር በራሱ የዳኝነት ስልጣን ዛቢያ ውስጥ ሆኖ ውሳኔውን በአሳማኝ ምክንያት ማስደገፍ አለበት። ከዚህ አንጻር ለአቋሙ መሰረት ያደረገውን ምክንያት ማየቱ ጠቃሚ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ ዋናው የሀተታ ክፍል እንደሚከተለው ይነበባል።
ቦርዱ ከፊል ውሳኔ ሰጪ አካል እንደመሆኑ መጠን የሚሰጠው ውሳኔ የሕጉን ስርዓት ተከትሎ ሊሰጥ ይገባል። ከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው አካል በሕጉ ተለይቶ የተቀመጠለት የክርክር አመራርና አሰጣጥ ስርዓት እስከሌለ ድረስ በኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት የተጠበቁትን ፍትህ የማግኘት፣ የመሰማትና በእኩል ሚዛን የመታየት መብት ሊያከብር ይገባል። በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሊጠበቁ ከሚገባቸው ሕገ መንግስታዊ መብቶች አንዱ ደግሞ ክርክር የማቅረብና ማሰረጃ የማሰማት መብት ነው። ይህ የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት የግድ ከሚላቸው የስነ ስርዓት አካሄዶች አንዱ ነው። ክርክሩን በአግባቡ እንዲያቀርብ እድል ያላገኘ ሰው በኢ.ፌ.ዲ.ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀፅ 37 የተከበረለት ፍትህ የማግኘት መብቱ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
ህጉን በፍሬ ነገሩ ላይ ተፈጻሚ በማድረግ አሳሪ ውሳኔ የሚያስተላልፍ አካል ተግባሩ ዳኞች በችሎት ተቀምጠው ከሚያከናውኑት የዳኝነት ተግባር አይለይም። ስለሆነም የዳኞችን ዓይነት የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት መከተል ባይኖርበትም ቢያንስ ቢያንስ አንደኛውን ወገን ብቻ ሰምቶ መወሰን የለበትም። ችሎቱ ይህን መሰረታዊ የአስተዳደር ህግ መርህ በአግባቡ ተረድቶታል። ‘ታሪካዊ’ መባሉም ለዚህ ነው። ምክንያቱም ይሄን የመሰለ ይቅርና የሚቀራረብ ውሳኔ ከችሎቱ መንጭቶ አያውቅም።
ቀደም ብለው የተሰጡ ተመሳሳይ ውሳኔዎች ባይኖሩም ከአንድ ዓመት በኋላ በታየ መዝገብ የመሰማት መብት ህገ መንግስታዊ ዕወቅና አግኝቷል። በሰ/መ/ቁ. 92546s በዲሲፕሊን ጉዳይ የተከሰሰ ዓቃቤ ህግ በዓቃቤ ህግ አስተዳደር ዋና ጉባዔ ውሳኔ መከላከል ሳያስፈልገው ከክሱ ነጻ ከተደረገ በኋላ በድሮው አጠራር የፍትሕ ሚኒስትር (በአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ) ዴኤታ ፊርማ መከላከያውን ሳያሰማ በመሰናበቱ የሚኒስትሩን እርምጃ በመቃወም በቀጥታ ለሰበር ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቷል። ችሎቱ በውሳኔው ሚኒስትሩ ከህግ የመነጨ ከፊል የዳኝነት ሰልጣን እንዳለው በመጠቆም የማሰናበት እርምጃው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ጥበቃና ዋስትና የተሰጠውን የእኩልነትና ፍትሕ የማግኘት መብት እንደሚጻረር በመጠቆም ሽሮታል።
በህግ የተቀመጠ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት
በአገራችን ወጥ የአስተዳደር ህግ ባይኖርም የአስተዳደር መ/ቤቶች በግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ እርምጃ የሚወስዱት ሁልጊዜ በዘፈቀደ አይደለም። ይብዛም ይነስም በተለያዩ ዝርዝር ህጎች ላይ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ተደንግገዋል። ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ከክስ መሰማት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ድረስ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚከተሉት ስነ ስርዓት በዚህም ፍትሐዊነት የሚገለጽበት መንገድ ደረጃው ይለያያል። በአንዳንዶቹ ጠበቅ ያለና መደበኛነት የሚታይበት ሲሆን በሌሎቹ ደግሞ ቀላል እና ‘ልል’ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።
ከሞላ ጎደል ሁሉንም የመሰማት መብት እና የኢአድሎአዊነት መርሆዎች ያሟላ በዓይነቱ በአሜሪካው የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ላይ ‘መደበኛ’ ተብሎ የተገለጸውን የአስተዳደር ዳኝነት የሚመስል የክርክር ስርዓት የሚገኘው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006 ላይ ነው። ስርዓቱ የተዘረጋው ህግን በመተላለፍ ጥፋት በሚፈጽም ኦዲተር ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ነው። ከክስ አመሰራረት እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ የክርክሩ አመራር ስርዓት በአዋጁ ከአንቀጽ 38-43 ባሉት ድንጋጌዎች የሚመራ ሲሆን ሂደቱ አጠር ተደርጎ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል።
አዋጁ የኢ-አድሎአዊነት መርህን ለማረጋገጥ የሚና መደበላለቅን አስቀርቷል። የመርማሪነት፣ ከሳሽነት እና ውሳኔ ሰጭነት ሚናዎች በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሰራተኛ/ተሿሚ ተለይተው ተከፋፍለዋል። በዚሁ መሰረት ‘መርማሪ ሹም’ የሚባል የቦርዱ ተቀጣሪ ሠራተኛ ወይም ከቦርዱ ጋር የቅጥር ግንኙነት ያልመሰረተ ብቃት ያለው ባለሞያ የምርመራ ተግባር ያከናውናል። መርማሪ ሹሙ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያምንበት ክስ እንዲመሰረት ለቦርዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ የውሳኔ ሀሳብ ከማቅረብ ውጪ በራሱ ክስ አያቀርብም። በአዋጁ የከሳሽነት ሚና የተሰጠው ለስራ አስፈፃሚው ነው። ስራ አስፈፃሚው ክስ ለመመስረት ከወሰነ በምርመራ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩ ከመካከላቸው አንዱ የህግ ባለሞያ የሆነ ሶስት የቦርዱን ሰራተኞች በክስ ሰሚነት ይሰይማል። እነዚህ ክስ ሰሚዎች (hearing examiners) ክርክሩን ሰምተው የመጨረሻ ውሳኔ የማስተላፍ ስልጣን አላቸው።
የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበት ሰው ስለቀረበበት ክስ ይዘት የማወቅ እና በራሱ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ቀርቦ ማስረጃውን የማቅረብ፣ ምስክሮቹን በመጥራት ቀጥተኛ ጥያቄ መጠየቅና እና ለከሳሽ ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብቱ በአዋጁ አንቀጽ 39/2/ ተጠብቆለታል። በግራ ቀኙ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች በተጨማሪ ክስ ሰሚዎች ለጉዳዩ አወሳሰን ጠቃሚ ማስረጃ ይዞ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በመጥሪያ በመጥራት በቃለ መሀላ የማረጋገጫ ቃሉን መቀበልና አግባብነት ያላቸውን ሰነዶችና ማስረጃዎች እንዲያቀርብ የማስገደድ ሰፊ ዳኝነታዊ ስልጣን ተጎናጽፈዋል። ክስ ሰሚዎች በክርክሩ ሂደት የቀረቡትን ማስረጃዎችና ክርክሩን ከመረመሩ በኋላ ክስ የቀረበበት ተከሳሽ አዋጁንና በአዋጁ መሰረት የወጣን ደንብና መመሪያ መተላለፍ አለመተላፉን ይወስናሉ። የህግ መተላለፍ ከተፈጸመ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ እስከ ፈቃድ መሰረዝ ብሎም እስከ ብር 25,000 (ሃያ አምስት ሺ ብር) የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ሌሎች በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ማስተላለፍ ይችላሉ።
ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በሚወስዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች ላይ ተፈጻሚ ይደረጋል። በሲቪል አቪዬሽን አዋጅ ቁ. 616/2001 አንቀጽ 80/1/ ላይ እንደተደነገገው ባለስልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሊወስደው ስላሰበው እርምጃ ለሚመለከተው ሰው ማሳወቅና እርምጃው ሊወሰድ አይገባም የሚልበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ዕድል መስጠት አለበት። ማስታወቂያው ጥፋት መፈጸሙን የሚገልጽ ክስ ሳይሆን በምርመራ ግኝት ባለስልጣኑ ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ ድምዳሜውን ለማስተባበል የሚደረግ ጥሪ ነው። ስለሆነም በምርመራ ሂደት ባለስልጣኑ የሚሰማቸውን ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ ዕድል አይኖርም። ሆኖም ቀጣይ የአዋጁ አንቀጽ 80/4/ ድንጋጌ በጠበቃ ወይም ባለጉዳዩ በራሱ ክርክር የማሰማት መብትን የሚፈቅድ እንደመሆኑ ማስረጃ የማቅረብና ምስክር ማሰማት የስነ ስርዓቱ አካል አድርጎ መቁጠር ይቻላል። በተጨማሪም የባለስልጣኑ ሠራተኛ የግል ጥቅሙን በሚነካ ጉዳይ በምርመራ ሂደት እንዳይሳተፍ ገደብ የሚጥለው የአዋጁ አንቀጽ 80/3/ በከፊልም ቢሆን ከአድልኦ የፀዳ ውሳኔ እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ህግን በማስከበር ስልጣናቸው በቀጥታ ከሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎችና ከሚወስዷቸው እርምጃዎች በተጨማሪ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴ ዳኝነታዊ ተግባራት ሲያከናውኑ ጠበቅ ያለ ስርዓት ይከተላሉ። በኢትዮጵያ የውሀ ሀብት አስተዳደር አዋጅ ቁ. 197/1992 የማዕከል ውሀ ሀብት አስተዳደርን አስመልክቶ የቁጥጥር ተግባራት እንዲያከናውን ስልጣን የተሰጠው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የውሀ ግልጋሎት ፈቃድ የተሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ከፈቃዱ ጋር የተያያዙ መብትና ግዴታዎችን አስመልክቶ በመካከላቸው የሚነሱ ክርክሮችን እንዲሁም በባለ ፈቃድ እና በሌላ ሶስተኛ ወገኖች መካከል የሚፈጠሩ ማናቸውንም ክርክሮች ሰምቶ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል። አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በውክልና በሰጠው የህግ አውጭነት ስልጣን መሰረት ክርክሮቹ የሚመሩበት ስርዓት በደንብ ቁ. 115/1997t ተደንግጓል።
በተቆጣጣሪው ባለስልጣን ዘንድ በሚካሄደው የክርክር አመራር ስርዓት ላይ መደበኛው የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ ተፈጻሚነት አለው። በደንቡ ላይ ተለይተው የተቀመጡት ጥቂት የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎችም ቢሆኑ ጠበቅ ያሉ ናቸው። በዚህ የተነሳ በተቆጣጣሪው አካል የሚካሄደው ክርክር በይዘቱ ፍርድ ቤቶች ከሚከተሉት የሙግት ስርዓት ጋር ይቀራረባል።
ክርክሩ የሚጀመረው አቤት ባዩ በሚያቀርበው ማመልከቻ ነው። ማመልከቻው የክርክሩን ፍሬ ሀሳብ (በእንግሊዝኛው ቅጂ memorandum summarizing the dispute) እና ማስረጃ እንዲሁም የአቤት ባዩን ቅሬታ እና እንዲሰጥለት የሚፈልገውን ውሳኔ አካቶ መያዝ ይኖርበታል። ስለሆነም በይዘቱ ከመደበኛው የክስ አቤቱታ ብዙም አይለይም። ተቆጣጣሪው አካል ማመልከቻውን እንደተቀበለ ክርክሩ የሚሰማበትን ቦታና ጊዜ የሚገልጽ መጥሪያና የማመልከቻ ቅጂ ለተከሳሹ እንዲደርሰው ያደርጋል። በቀጠሮ ቀን ባለጉዳዮች በቀጠሮ ሰዓትና ቦታ ተገኝተው ጉዳያቸውን ያስረዳሉ። ማስረጃም ያቀርባሉ። በሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡ ማስረጃዎች በተቆጣጣሪው አካል ይመዘገባሉ። ተከሰሹ መጥሪያ ደርሶት ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት ይሰማል። ተቆጣጣሪው ጉዳዩን ሰምቶ የሚሰጠውን ውሳኔ ባለጉዳዮች እንዲያውቁት ማድርግ ያለበት ሲሆን በተጨማሪም የውሳኔውን መዝገብ ግልባጭ የመስጠት ግዴታ አለበት። በደንቡ ላይ ለውሳኔ ምክንያት መስጠት እንደ ቅድመ ሁኔታ አልተቀመጠም። ይሁን እንጂ ተቆጣጣሪው እንደ አግባብነቱ የፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህጉን ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ ያለበት እንደመሆኑ ምክንያት የጎደለው ውሳኔ በፍርድ ቤት መሻሩ አይቀርለትም።
ከላይ ያየነው ዓይነት ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጋር የሚቀራረብ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት አፈጻጸሙ በውስን አስተዳደራዊ ክርክሮች ላይ ብቻ ነው። በጣም በርካታ መ/ቤቶች ለስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የሚገዙት በጣም በስሱ ነው። አብዛኛው ቀዳሚ ውሳኔ /initial decision/ በአስተዳደራዊ የሙግት ሂደት ስር አያልፍም። ውሳኔ አሰጣጡ በባህርዩ መርማሪ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል አያሳትፍም። ህግ መጣሱ የሚረጋገጠው መ/ቤቱ በሚቀርብለት ጥቆማ ወይም በራሱ አነሳሽነት በሚያካሂደው ምርመራና ማጣራት አማካይነት ነው። በዚህ መልኩ ጥፋት መፈጸሙ አስቀድሞ አቋም ይያዝበታል። ሆኖም መ/ቤቱ የደረሰበት ድምዳሜ አስገዳጅነት ወዳለው የመጨረሻ ውሳኔ ከመሸጋገሩ በፊት የሚመለከተው አካል አስተያየት ወይም ምላሽ እንዲሰጥበት ይደረጋል። መልስ ሰጭው የቀረበበትን ማስረጃ የማስተባበል አሊያም ተቃራኒ ማስረጃ የማቅረብ በህግ የተጠበቀ መብት የለውም።
ልል እና ኢ-መደበኛ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ከሚደነግጉ ህጎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመድን ሰጪ ድርጅት ያካሄደው ምርመራ የመጨረሻ ሪፖርት ከመዘጋጀቱ በፊት ለተመርማሪው መድን ሰጪ ድርጅት እንዲደርሰው ተደርጎ በሪፖርቱ ላይ አስተያየቱን እንዲያቀርብ ዕድል ይሰጠዋል።u
/ንግድና ኢንዱስትሪ/ ሚኒስቴሩ ወይም የእርሱ ተወካይ የአንድ ባለዕቃ ማከማቻ ቤት የግብርና ምርት ውጤቶች ተቆጣጣሪ፣ መዳቢ፣ ደረጃ ሰጪ፣ መዛኝ ወይም ናሙና አውጭ የሥራ ፈቃድ ለዘለቄታው እንዲሰረዝ ከመወሰኑ በፊት አጥፍቷል የተባለው ጥፋት በጽሑፍ እንዲገለጽለትና በቂ ጊዜ ተሰጥቶት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥበት ወይም መቃወሚያ እንዲያቀርብበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል።v
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በማንኛውም ድርጅት ላይ የትኛውንም ዓይነት አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ድርጅቱ መከራከሪያዎቹንና ማስረጃዎቹን የማቅረብና የመሰማት መብት አለው።w
የጉምሩክ ኮሚሽን ማንኛውም ዕቃ ወይም ማጓጓዣ በዚህ አንቀጽ መሠረት ውርስ ሆኖ ለመንግሥት ገቢ ከመደረጉ በፊት የዕቃው ወይም የማጓጓዣው ባለቤት በአዋጁ አንቀጽ 143(3) ወይም (4) መሠረት የመያዝ እርምጃውን አንዲያውቀው ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ተቃውሞውን እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት አለበት፡፡x
በተጨማሪም ኮሚሽኑ በኤሌክትሮኒክስ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት የመጠቀም መብትን ከማገዱ ወይም ምዝገባውን ከመሠረዙ በፊት እርምጃው የሚወሰድበትን ምክንያት ለተጠቃሚው በጽሑፍ በማሳወቅ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ አስተያየቱን እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት አለበት፡፡y
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አንድን ፈቃድ ከማገዱ ወይም ከመሠረዙ በፊት እርምጃውን የሚወስድበትን ምክንያት ለባለፈቃዱ በጽሑፍ በመግለጽ ባለፈቃዱ ጽሁ በደረሰው በሰባት ቀናት ውስጥ የበኩሉን አስተያየት በጽሑፍ እንዲሰጥ ያደርጋል፡z
የመሰማት መብት በህግ ቢፈቀድም በጥቅል አነጋገር በሚገለጽበት ጊዜ የመብቱን ወሰን አፈጻጸም አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የክፍያ መፈጸሚያ ተቋምን ወይም የግብይት ፈጻሚዎችን ወይም የማህበራቸውን ዕውቅና ከማገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት መጀመሪያ የተቋሙ ኃላፊዎች በማስታወቂያ እንዲያውቁት ማድረግና ለባለጉዳዩ የመሰማት ዕድል መስጠት ይኖርበታል፡a የድንጋጌው አነጋገር የጠቅላላነት ባህርይ ቢታይበትም የመሰማት መብት መሰረታዊ የአስተዳደር ፍትሕ ጥያቄ እንደመሆኑ ዕውቅና ከመታገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት ቅድመ ክስ ማስታወቂያ፣ ማስረጃ የማቅረብ መብትና ተቃራኒ ማስረጃ የማስተባበል መብት ተሟልተው ሊገኙ ይገባል።
በአንዳንድ ህጎች ላይ ደግሞ የመሰማት መብት ውሳኔውን በማሳወቅ ላይ ብቻ ይገደባል። በእርግጥ ውሳኔው አግባብ እንዳልሆነ በቃል ሆነ በጽሑፍ ማስተባበል ካልተቻለ የመሰማት መብት መነፈጉን እንጂ በከፊል መገደቡን አይደለም የሚያሳየው። የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴሩ የዕፅዋት አዳቃዮችን መብት ለመሰረዝ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ለመሰረዝ የበቃበትን ምክንያት በመግለጽ ለባለመብቱ የጽሑፍ ማስታወቂያ መስጠትና መብቱ የተሰረዘ መሆኑን ለሕዝብ ማስታወቅ አለበት።b ማስታወቂያው የመሰረዝ ውሳኔውን ከማሳወቅ የዘለለ ውጤት የለውም። ባለመብቱ የእርምጃውን ህጋዊነት ለመቃወም የሚችልበት ቀዳዳ የለም።
አንዳንድ ጊዜ የመሰማት መብት የሚፈቀደው ከውሳኔ በኋላ ይሆናል። የዘር አስመጪ፣ ላኪ፣ የዘር አምራች፣ አዘጋጅ፣ ጅምላ ሻጭ፣ አከፋፋይ ወይም ቸርቻሪ በዘር አዋጅ ቁ. 782/2005 አንቀጽ 21/1/ እና /2/ መሰረት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ወይም በክልል ባለስልጣን ከመታገዱ ወይም ከመሰረዙ በፊት በድንጋጌው ላይ የተጠቀሱት በቂ ምክንያቶች እውነት ስላለመሆናቸው ለማስረዳትና ተቃራኒ ማስረጃ ለማቅረብ ዕድል አልተሰጠውም። ሆኖም ከውሳኔው በኋላ ውሳኔውን ለሰጠው አካል አስተዳደራዊ ቅሬታ የማቅረብ መብቱ በአንቀጽ 25/1/ ተጠብቆለታል። አመልካቹ በተሰጠው ምላሽ ካልረካ ቅሬታውን ለሚመለከታው የፍትሕ አካል ሊያቀርብ እንደሚችል በድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ 2 ተመልክቷል።
የመሰማት መብት በዝምታ የታለፈባቸው ድንጋጌዎች
ምክንያቱ ባይታወቅም በዜጎች መብት ላይ ቀጥተኛ እና አሉታዊ ውጤት የሚያስከትሉ አንዳንድ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ሳይዘረጋላቸው በዝምታ ታልፈዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ ፈቃድ የተሰጠው ኩባንያ አሰራሩ ለአደጋ ያልተጋለጠ፣ አስተማማኝና ጤናማ መሆኑን ለማረጋገጥ የኩባንያውን ዳይሬክተር፣ ዳይሬክተሮች ወይም ዋና ስራ አስፈፃሚ ከስራ ማገድ ወይም ማሰናበት ይችላል።c ባንኩ በምን ዓይነት ሁኔታዎችና በቂ ምክንያቶች እርምጃውን እንደሚወስድ ስልጣን በሰጠው አዋጅ ቁ. 807/2005 ላይ አልተመለከተም። በተጨማሪም እርምጃው የሚወሰድባቸው የኩባንያው ኃላፊዎች የተከሰሱበትን ጉዳይ ባንኩ ፊት ቀርበው ለማስረዳትና ማስተባበያ ማስረጃ ለማቅረብ በአጠቃላይ የመሰማት መብታቸው በአዋጁ አልተጠበቀም።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በማስታወቂያ አዋጅ ቁ. 759/2004 አንቀጽ 31/3/ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር የውጭ ማስታወቂያን ሳይጨምር የአዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ የተሰራጨን ማንኛውንም ማስታወቂያ ይመረምራል፣ ያግዳል፣ የአፀፋ ማስታወቂያ እንዲወጣ ያዛል። ነገር ግን እርምጃውን ከመውሰዱ በፊት የማስታወቂያውን ባለቤት የመስማት ግዴታ አልተጣለበትም። በእርግጥ ለእርምጃው ምክንያት የሆኑት አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ህሊናዊ ፍርድ የሚጠይቁ እንደመሆኑ ማስረጃ-ነክ ክርክሮች አይኖሩም። ሆኖም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተቃራኒውን ወገን መስማት የተዛባ አመለካከትን በማጥራት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ባለስልጣኑ የማስታወቂያ ባለቤቶችን እይታ በጥልቀት ይረዳል። ለምሳሌ በአዋጁ ክልከላ ከተደረገባቸው ህግን ወይም መልካም ስነ ምግባር እንደሚጻረሩ የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎች መካከል በአንቀጽ 7/6/ እና /8/ የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፡
የህብረተሰቡን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትና ደህንነት ለጉዳት የሚያጋልጥ ድርጊት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ማስታወቂያ
ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ የጽሑፍ መልዕክት፣ ምስል፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ ፊልም ወይም መሰል አቀራረብን የያዘ ማስታወቂያ
የአንድን ማስታወቂያ ይዘት በተጠቀሱት የተከለከሉ ተግባራት ስር ለመፈረጅ ጥንቃቄ የተሞላበት ህሊናዊ ፍርድ ይጠይቃል። በእንዲህ ዓይነቱ የውሳኔ አሰጣጥ ውጫዊ ሁኔታዎች ለምሳሌ የውሳኔ ሰጭው ግላዊ፣ ባህላዊና ስነልቡናዊ አቋም ይብዛም ይነስም ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ስለሆነም ከአድልኦ የፀዳና ያልተዛባ ውሳኔ ለመስጠት የተቃራኒው ወገን አመለካከትና እይታ ማዳመጥ ወደጎን ሊተው አይገባም።
የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ በአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ
የአሜሪካው የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ አስተዳደራዊ ክርክር /adjudication/ መደበኛ ወይም ኢመደበኛ በሚል የተከፈለ ሲሆን መደበኛው ስርዓት በጣም ውስን በሆነ ጉዳዮች ላይ የተገደበና ተፈጻሚነቱም ህግ አውጭው ባመለከታቸው ሁኔታዎች ላይ ብቻ ነው።d በጀርመን እንዲሁ አስተዳደራዊ ክርክሮች መደበኛ እና ኢ-መደበኛ በሚል የሚከፈሉ ሲሆን መደበኛው ተፈጻሚ የሚሆነው ህግ አውጭው በግልጽ ካመለከተ ብቻ ነው።e በየትም አገር ቢሆን በቁጥር ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ኢ-መደበኛውን ስርዓት ይከተላል። በአሜሪካ 90 ፐርሰንት የሚሆኑት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙት በኢ-መደበኛ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ነው። በእንግሊዝ በዳኞች የዳበረው የመሰማት መብትንና የኢ-አድሎአዊነት መርህ አካቶ የያዘው የተፈጥሮ ህግ መሰረታዊ መርህ በሁሉም ውሳኔ ሰጭ አካላት ላይ ወጥ ተፈጻሚነት የለውም። በህግ ያልተቀመጠ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታ ባለመሆኑም ዳኞች እንደየሁኔታው እያጠበቡና እያሰፉ በትርጉም በአስተዳደር ውስጥ ኢመደበኛነት እንዲሰፍን አድርገዋል። ወጥነት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ መገለጫ ባህርይ ስላለመሆኑና መደበኛው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የኢ-መደበኛው ልዩ ሁኔታ እንደሆነ እንዲሁም ህግ አውጭው የአስተዳደር ውሳኔዎችን እንደ ዓይነታቸው፤ ውስብስብነታቸው፤ በመብት እና ጥቅም ላይ የሚያስከትሉት ክብደት እና ሌሎች ተገቢ መመዘኛዎችን በመለየት ከልል እስከ ጥብቅ የትኛውን ስነ-ስር ዓት መከተል እንዳለባቸው ሊወስን እንደሚገባ በዚህ መጽሐፍ (ክፍል 5.3 ልዩ ሁኔታዎችና የተፈጻሚነት ወሰን) በስፋት የተብራራ በመሆኑ መድገሙ አስፈላጊ አይሆንም። እዚህ ላይ የሚዳሰሰው አዲስ የወጣው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ የኢ-መደበኛነትን ፅንሰ-ሀሳብ በምን መልኩ እንዲሁም እስከምን ደረጃ የህጉ አካል እንዳደረገው ይሆናል።
የአገራችን የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ ለሁሉም ተቋማት በሁሉም ሁኔታዎች ተፈጻሚ የሚሆን ወጥ እና መደበኛ ስርዓት ዘርግቷል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የአስተዳደር ተቋማት ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ጫና መደረብ ነው።
ለመሆኑ መደበኛ ሲባል ምን ለማለት ነው? አንባቢ ግልጽ መረዳት ይኖረው ዘንድ በሚከተሉት ህጎች ላይ ያሉትን መደበኛ የሚባሉ የክርክር ሂደቶች ቀንጨብ አድርገን እናያለን።
የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁጥር 847/2006 ከአንቀጽ 38 እስከ 42
የፌደራል መንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 77/1994
የዓቃብያነ ህግ የዲሲፕሊን ክስ አቀራረብ፣ ማጣራትና ውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት በተመለከተ የፌደራል የዓቃብያነ ህግ መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ 443/2011 ከአንቀጽ 91 እስከ 94 ድረስ የተዘረጋው ስርዓት
መደበኛው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚካሄደው ሙግት አምሳያ ነው። ጉዳዩን ሰምቶ አከራክሮ ፍርድ መስጠት ለፍርድ ቤቶች መደበኛ ስራቸው ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ የክርክር ሂደት በዝርዝር በተጻፈ የስነ-ስርዓት ድንጋጌዎች ይመራል። ድንጋጌዎቹ ልዩነት ሳይደረግ በሁሉም ተከራካሪዎች ላይ ተፈጻሚነት አላቸው።
ሆኖም ለአንድ የአስተዳደር ተቋም ማከራከር ተጉዳኝ እንጂ ዋና ተግባሩ አይደለም። ተቋሙ የተቋቋመበት የራሱ የሆነ ዓላማና ተግባር አለው። ተልዕኮው ይህን ዓላማ በብቃት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማሳካት ነው። ተቋሙ በህግ የተሰጠውን ተግባር ሲያከናውን በግለሰቦች መብትና ጥቅም ላይ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል የሚችል አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል። እንደ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሁሉ የተቋሙ ውሳኔ በማስረጃ የተደገፈ እና ህጉን መሰረት ያደረገ እና ፍትሐዊ ሊሆን ይገባል። ይህ በተግባር የሚረጋገጠው እርምጃ የሚወሰድበት ግለሰብ ወይም ድርጅት ጥፋተኛ እንዳልሆነና ተጠያቂነት እንደሌለበት በማስረጃ አስደግፎ ማስረዳት ሲችል ነው። በአግባቡ ማስረዳት ይችል ዘንድ ፍሬነገሩና ህጉ የሚጣራበት ይብዛም ይነስም የተወሰነ የክርክር ስርዓት መወሰን ያስፈልጋል። ስርዓቱ መደበኛ ከሆነ ፍርድ ቤት የሚከተለውን ስነ-ስርዓት ይመስላል። ይመስላል እንጂ ግን ግልባጭ አይደለም። የአስተዳደር ተቋም በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ መደበኛውን የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት የሚከተል ከሆነ ሙሉ ጊዜና ሀብቱን የሚያጠፋው የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካት ሳይሆን በማከራከከር ብቻ ይሆናል። ከዚህ አንጻር መደበኛ በሚባል የአስተዳደር ክርክር ላይ ተፈጻሚነት የሚሆኑት የስነ-ስርዓት ቅደመ ሁኔታዎች ውስንና በይዘታቸውም ጠቅላላነት የሚስተዋልባቸው ናቸው።
በተቃራኒው ሂደቱ ኢ-መደበኛ ከሆነ በጣም ልል ከመሆኑ የተነሳ የክርክር ስርዓት ብሎ ለመጥራት እንኳን ይከብዳል። በዛ ላይ በይዘቱ እና በአፈጻጸሙ ከተቋም ተቋም ከውሳኔ ውሳኔ ሊለያይ ይችላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያክል የግብርና ሚኒስቴር የሰጠውን የዕፅዋት አዳቃይ መብት ለመሠረዝ ሲወስን፦
•ሀ) ለባለመብቱ መብቱ ሊሰረዝ እንደሆነ በጽሑፍ ያሳውቃል፤
•ለ) ባለመብቱ ተቃውሞ ካለው የጽሑፍ ማስታወቂያ እንደደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ በጽሑፍ ያሳውቃል፤ እና
•ሐ) ተቃውሞ ቀርቦ ከሆነ ክርክሩን ሰምቶ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል
ይህንን እላይ ካየናቸው መደበኛ የክርክር ስርዓት ጋር ስናስተያየው ሚናቸው የተለያየ መርማሪና ከሳሽ እንዲሁም ጥፋትን የሚያስታውቅ የክስ አቤቱታ የለም። ባለመብቱ መብቱ ሊሰረዝ እንደሆነ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የራሱን ማጣራት አድርጎ ህጉን አመሳክሮ አስቀድሞ ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ለዚህም ነው የመከላከያ መልሱን ሳይሆን ማስረጃውን እንዲያቀርብ የተጠየቀው። ሚኒስቴሩ ውሳኔ የሚሰጠው ክርክሩን ሰምቶ ቢሆንም ተከራካሪ ወገኖች (ከሳሽና ተከሳሽ) የሉም። ስለሆነም ክርክሩን ሰምቶ ሲባል ባለመብቱ የሚያቀርበውን ተቃውሞ ሰምቶ ለማለት ነው። በሚኒስቴሩ ፊት ማስረጃ ከማቅረብና ተቃውሞ ከማሰማት የዘለለ የክርክር ስርዓት የለም።
በመደበኛው የፍርድ ቤት ክርክር ከክስ መሰማት በፊት የተለያዩ ጉዳዮችን የሚወስኑ በርካታ የስነ ስርዓት ድንጋጌዎች አሉ። በፍርድ ቤት ክርክር ተፈጻሚ የሚሆኑት የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች በባህርያቸው የማያወላዱ ግትር እንደመሆናቸው ለአስተዳደር ክርክር አይመቹም። በአንድ አገር ውስጥ የሚወጣ የአስተዳደር ህግ ውጤታማ አስተዳደርን ሳያሰናክል የዜጎችን መሰረታዊ የመሰማት መብት የሚያስጠብቅ ተለማጭ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት ይኖርበታል። ከዚህ አንጻር አዋጁ ሁለት ጉልህ ግድፈቶች ይታዩበታል። በአንድ በኩል የመሰማት መብትን ከክስ መሰማት ጋር አምታቶታል። በዚህ የተነሳ መሰረታዊ የሚባሉትን የመሰማት መብት ድንጋጌዎችን አልያዘም። በሌላ በኩል ተፈጻሚ የሚሆነውን ስርዓት እንደ ጉዳዮች ዓይነት /ማለትም እንደ አስተዳደራዊ ውሳኔው ዓይነት/ መደበኛ እና ኢመደበኛ ስነ ስርዓት መዘርጋት ቢኖርበትም አንድ ወጥ ቅድመ ሁኔታ በመደንገግ ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ ወቅጧቸዋል። ይህ ደግሞ በቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ እና ውጤታማ አስተዳደር ላይ የሚያስከትለው ግዙፍ ተደራራቢ ችግር በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።
በአዋጁ የሚታዩ የውሳኔ አሰጣጥ አጀማመር ብዥታዎች
በመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ /initial decision/ ሆነ በቅሬታ ስርዓት /review decision/ የአስተዳደራዊ ክርክር የሚጀመረው ከማስታወቂያ ነው። በመጀመሪያው ውሳኔ ሰጭው ባለስልጣን ለባለጉዳዩ /ለተከሳሹ/ የክስ ማስታወቂያ ይሰጠዋል። በሁለተኛው ደግሞ የባለጉዳዩ የቅሬታ አቤቱታ ለውሳኔ ሰጭው አካል ይደርሰዋል። የክስ ሆነ የቅሬታ አቤቱታ ለሚመለከተው ወገን እንዲደርስ ግልጽ የሆነ የማስታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት ሊኖር ይገባል። በዚህ መጽሀፍ በክፍል 5.3 እንደተመለከተው ማስታወቂያ ተከራካሪው እንዲቀርብ የሚሰጥ መጥሪያ ነው። በይዘቱ ባለጉዳዩ የቀረበበትን ክስ በሚገባ ተረድቶ መልሱን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ የሚያስችለው ሊሆን ይገባል።
የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጁ ከክስ መሰማት በፊት ያሉ ወሳኝ ሂደቶችን በዝምታ አልፏቸዋል። ሙሉ ትኩረቱን ያደረገው ባለጉዳዩ የአስተዳደር ጉዳይ በሚሰማበት ጊዜ በክርክ ሂደት ሁሉ ተገኝቶ ስለሚከናወነው የአስተዳደር ክርክር ብቻ ነው። በዚህ የተነሳ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓቱን ጎዶሎ አድርጎታል።
የቅድመ ክስ ማስታወቂያ ስርዓትን አስፈላጊነት በተመለከተ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአንድ ውሳኔ ላይ እንዳለው
The right to a hearing embraces not only the right to present evidence, but also a reasonable opportunity to know the claims of the opposing party and to meet them. The right to submit argument implies that opportunity; otherwise the right may be but a barren one.f
የፌደራል መንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 77/1994 በአንቀጽ 11 ላይ ክስን ስለማሳወቅ ከአዋጁ በጣም በተሻለ የሚከተሉትን ድንጋጌዎች ይዟል።
1. የዲስፕሊን ኮሚቴ ክስ የቀረበበት ሠራተኛ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ የክሱን ጽሁፍና ማስረጃዎች ቅጅ አያይዞ የክስ ማስታወቂያ ይልክለታል።
2. የክስ ማስታወቂያው ክሱ የሚሰማበትን ቦታ፣ ቀንና ሠዓት የሚገልጽ ሆኖ ክሱ ከሚሰማበት ቀን ቢያንስ ከ 10 ቀናት በፊት ለተከሣሹ መድረስ አለበት።
3. ሠራተኛው ሊገኝ ባለመቻሉ ወይም ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የክስ ማስታወቂያውን ለመስጠት ያልተቻለ አንደሆነ በመሥሪያ ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ ለ15 ቀናት እንዲቆይ ይደረጋል።
የአዋጁ ችግር የክስ ማስታወቂያን የሚደነግግ ነጠላ ድንጋጌ አለመያዙ ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ከክስ መሰማት በፊት በዝርዝር መካተት የነበረባቸው የአስተዳደር ክርክር መሰረታዊ ድንጋጌዎች በሙሉ ተረስተዋል። የውሳኔ አሰጣጥ አጀማመር በተመለከተ አዋጁ ብዥታ ይነበብበታል። የውሳኔ አሰጣጥ አጀማመር በተመለከተ የሚስተዋለው መሰረታዊ ችግር መንስዔም ይኸው ነው።

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.