የጋብቻ ምዝገባ


ስለጋብቻ ምዝገባ

 

አንቀጽ ፳፰ ጋብቻን ስለማስመዝገብ

 

፩. ጋብቻው የተፈፀመው በማንኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት ቢሆንም፣ አግባብ ባለው የክብር መዝገብ ሹም መመዝገብ አለበት፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ምዝገባውን ያከናወነ የክብር መዝገብ ሹም ለተጋቢዎቹ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

፫. ማንኛውም ጋብቻ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ ውጤት ይኖረዋል፡፡

 

አንቀጽ ፳፱ የጋብቻ መዝገብ ስለማደራጀት

 

፩. በዚህ ሕግ አንቀጽ ፳፰ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ተጋቢዎች ጋብቻውን ያላስመዘገቡ ቢሆንም እንኳን፣ የክብር መዝገብ ሹሙ ጋብቻ መፈፀሙን ያወቀ እንደሆነ የጋብቻ መዝገብ በሥልጣኑ ያደራጃል፡፡

፪. ይህ በሚሆንበት ጊዜ የክብር መዝገብ ሹሙ ተጋቢዎቹና እንደ ነገሩ ሁኔታ ምስክሮች ቀርበው በጋብቻው መዝገብ ላይ እንዲፈርሙ ያደርጋል፡፡

 

አንቀጽ ፴ የጋብቻ መዝገብ ይዘት

 

የጋብቻ መዝገብ የሚያመለክተው፣

 

ሀ) የተጋቢዎችን ሙሉ ስም፣ የተወለዱበትን ቀንና ቦታ፣ የመኖሪያ አድራሻቸውን፣

ለ) የምስክሮችን ሙሉ ስም፣ የተወለዱበትን ቀንና ቦታ፣ የመኖሪያ አድራሻቸውን፣

ሐ) ጋብቻው የተፈፀመበትን ሥርዓት፣ ቀንና ቦታ እንዲሁም የተመዘገበበትን ቀን ይሆናል፡፡