የጋብቻ ውጤት
አንቀጽ ፵ ሁሉም የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው ስለመሆኑ
፩. በማናቸውም ዓይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት መሠረት የተፈፀመ ጋብቻ ተመሳሳይ ሕጋዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡
፪. በዚህ ረገድ ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ወይም በሃይማኖት ወይም በባህል በታዘዙት ሥርዓቶች መሠረት የተፈፀመም ቢሆን ልዩነት አይደረግበትም፡፡
አንቀጽ ፵፩ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም
የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት በዕውነት መፈፀሙ ወይም ተፈጽሟል ተብሎ መገመቱ፣ ጋብቻው ለሚያስከትለው ውጤት አስፈላጊ አይደለም፡፡
አንቀጽ ፵፪ (፩) የጋብቻ ውል
፩. ተጋቢዎቹ ጋብቻቸው ንብረታቸውን በተመለከተ ስለሚያስከትለው ውጤት ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸው በሚፈፀምበት ዕለት በውል መወሰን ይችላሉ፡፡
፪. እንዲሁም ግላዊ ግንኙነታቸውን በሚመለከት የሚኖሯቸውን መብቶችና ግዴታዎች በዚህ ውል መወሰን ይችላሉ፡፡
፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) እና (፪) መሠረት ተጋቢዎቹ የሚያደርጓቸው ውሎች አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎችን የሚቃረኑ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
አንቀጽ ፵፫ (፪) የተጋቢዎቹ ችሎታ ማጣት
፩. በፍርድ የተከለከለ ሰው የሚያደርገውን የጋብቻ ውል እርሱ ራሱ ካልፈፀመውና ፍርድ ቤት ካላፀደቀው በስተቀር ውጤት አይኖረውም፡፡
፪. በሕግ የተከለከለ ሰው፣ የጋብቻ ውል መዋዋልን በተመለከተ ችሎታ እንዳለው ይቆጠራል፡፡
አንቀጽ ፵፬ (፫) የውሉ ፎርም
የጋብቻ ውል በጽሑፍ ካልተደረገና አራት ምስክሮች፣ ሁለት በባል ወገን፣ ሁለት በሚስት ወገን፣ የፈረሙበት ካልሆነ በስተቀር ውጤት አይኖረውም፡፡
አንቀጽ ፵፭ (፬) የውሉ ሰነድ ስለሚቀመጥበት ቦታ
፩. የጋብቻ ውሉ አንድ ቅጅ በፍርድ ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ዘንድ ይቀመጣል፡፡
፪. ተጋቢዎች ወይም ከተጋቢዎች አንዱ ለማየት በፈለጉ ጊዜ እንዲሁም በፍርድ ቤት ወይም ከተጋቢዎቹ በአንዱ የተፈቀደላቸው ሰዎች የውሉን ሰነድ ለማየት ይችላሉ፡፡
አንቀጽ ፵፮ (፭) ውል ለመዋዋል ስላለው የነፃነት ወሰን
፩. ተጋቢዎች በጋብቻቸው ውል ውስጥ በሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ላይ ግዴታን የሚያስከትሉ ስምምነቶችን ማድረግ አይችሉም፡፡
፪. እንዲሁም ተጋቢዎቹ ባሕልን ወይም ሃይማኖትን ወይም የአንድን አገር ሕግ በጥቅሉ በመጥቀስ ብቻ ተስማምተናል በማለት የሚያደርጉት የጋብቻ ውል ውጤት አይኖረውም፡፡
አንቀጽ ፵፯ (፮) የጋብቻ ውልን ስለማሻሻል
፩. የጋብቻ ውል እንዲሻሻል የቤተሰቡ ጥቅም የሚጠይቅ ሲሆንና ተጋቢዎቹ ሲስማሙ ውሉን በማሻሻል ፍርድ ቤት እንዲፀድቅላቸው መጠየቅ ይችላሉ፡፡
፪. ፍርድ ቤት በተጋቢዎቹ ተሻሽሎ የቀረበው የጋብቻ ውል የቤተሰቡን ጥቅም የማይጎዳ መሆኑን ሲያረጋግጥ የተሻሻለውን ውል ተቀብሎ ያፀድቃል፡፡
፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) በተመለከተው ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ውሉን ያፀደቀው እንደሆነ፣ የተሻሻለው ውል በፍርድ ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ዘንድ ይቀመጣል፡፡
አንቀጽ ፵፰ (፯) የሕግ ተፈፃሚነት
የጋብቻ ውል በሌለ ጊዜ ወይም የጋብቻ ውል ቢኖርም በሕግ ሳይፀና የቀረ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
