የጋብቻ ሁኔታዎች አለመሟላት የሚያስከትለው ውጤት
አንቀጽ ፴፩ የዕድሜ ሁኔታ
፩. በዚህ ሕግ አንቀጽ ፯ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዕድሜአቸው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች መካከል የተፈፀመ ጋብቻ በማንኛውም ባለጉዳይ ወይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡
፪. ሕጉ የሚጠይቀው የጋብቻ ዕድሜ ከተሟላ በኋላ ጋብቻው እንዲፈርስ ጥያቄ ማቅረብም ሆነ መወሰን አይቻልም፡፡
አንቀጽ ፴፪ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና
በሥጋ ወይም በጋብቻ ዝምድና ምክንያት ጋብቻ እንዳይፈጸም የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ የተፈጸመ ጋብቻ በማንኛውም ባለጉዳይ ወይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡
አንቀጽ ፴፫ በጋብቻ ላይ ጋብቻ
፩. በጋብቻ ላይ ሌላ ጋብቻ ተፈጽሞ የተገኘ እንደሆነ በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው ተጋቢ ወይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ የኋለኛው ጋብቻ እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡
፪. ሆኖም የመጀመሪያው ተጋቢ የሞተ እንደሆነ የኋለኛው ጋብቻ እንዲፈርስ መጠየቅ አይቻልም፡፡
አንቀጽ ፴፬ በፍርድ ክልከላ ምክንያት ጋብቻን ስለማፍረስ
፩. በፍርድ የተከለከለ ሰው ፍርድ ቤት ሳይፈቅድ ጋብቻ ፈጽሞ የተገኘ እንደሆነ፣ የተከለከለው ሰው ራሱ ወይም አሳዳሪው ጋብቻው እንዲፈርስ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡
፪. የተከለከለው ሰው ጋብቻው እንዲፈርስ የሚያቀርበው ጥያቄ ክልከላው ከቀረበት ቀን ጀምሮ ስድስት ወር ካለፈ በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
፫. ጋብቻው እንዲፈርስ በአሳዳሪው የሚቀርበው ጥያቄ ጋብቻው መፈፀሙን ከአወቀበት ቀን ጀምሮ ከስድስት ወር በኋላ ወይም በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ክልከላው ከቀረ በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
አንቀጽ ፴፭ በኃይል ተግባር የተፈፀመ ጋብቻን ስለማፍረስ
፩. ማንኛውም ሰው ተገዶ ጋብቻ የፈጸመ እንደሆነ ጋብቻው እንዲፈርስ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡
፪. ስለዚህ ጉዳይ የሚቀርበው ጥያቄ የኃይል ሥራው ከቀረበት ከስድስት ወር በኋላ እና በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ጋብቻው ከተፈፀመ ከሁለት ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
አንቀጽ ፴፮ በስህተት ምክንያት የተፈጸመ ጋብቻን ስለማፍረስ
፩. ማንኛውም ሰው ከመሠረታዊ ስህተት በመነሳት ጋብቻ የፈፀመ እንደሆነ ጋብቻው እንዲፈርስ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡
፪. ስለዚህ ጉዳይ የሚቀርበው ጥያቄ መሳሳቱን ከአወቀበት ቀን ጀምሮ ከስድስት ወር በኋላ እና በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ጋብቻው ከተፈፀመ ከሁለት ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
አንቀጽ ፴፯ በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነውን ጊዜ ስላለመጠበቅ
በዚህ ሕግ አንቀጽ ፲፮ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነው ጊዜ አልተከበረም በሚል ምክንያት ብቻ ጋብቻ እንዲፈርስ ጥያቄ ሊቀርብ አይችልም፡፡
አንቀጽ ፴፰ የክብር መዝገብ ሹም ሥልጣን የሌለው ስለመሆኑ
ጋብቻው ያስፈጸመው የክብር መዝገብ ሹም በአንቀጽ ፳፪ መሠረት ሥልጣን አልነበረውም በማለት ብቻ ጋብቻው እንዲፈርስ ለመወሰን አይቻልም፡፡
አንቀጽ ፴፱ የሥነ ሥርዓት አለመጠበቅ
በዚህ ሕግ አንቀጽ ፳፭ ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፮) የተመለከቱት ሥርዓቶች አልተጠበቁም በማለት ብቻ ጋብቻ እንዲፈርስ ሊወሰን አይችልም፡፡
