ጋብቻ በንብረት በኩል ስለሚኖረው ውጤት
አንቀጽ ፶፯ የባልና ሚስት የግል ሀብት (፩) ያለግብይት የተገኙ ንብረቶች
ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በየግላቸው ያገኙዋቸው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ሆነው ይቀራሉ፡፡
አንቀጽ ፶፰ (፪) በግብይት የተገኙ ንብረቶች
፩. ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በሆነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሸጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ሀብቱ ይሆናል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው ድንጋጌ ተፈፃሚ የሚሆነው በግብይት የተገኘው ንብረት የግል ይባልልኝ ብሎ አንደኛው ወገን ጥያቄ ሲያቀርብ እና ፍርድ ቤት ሲያፀድቀው ብቻ ነው፡፡
አንቀጽ ፶፱ የግል ሀብትን ስለማስተዳደር (፩) መሠረቱ
፩. እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን ራሱ ለማስተዳደርና ገቢውንም ለመቀበል ይችላል፡፡
፪. እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን ራሱ ሊያዝበት ነፃነት አለው፡፡
አንቀጽ ፷ (፪) የግል ሀብት አስተዳደርን በጋብቻ ውል ስለመወሰን
፩. ባልና ሚስት አንደኛው የሌላውን ተጋቢ የግል ሀብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት እና እንደአስፈላጊነቱ እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) በተመለከተው አኳኋን ንብረት የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው ተጋቢ በሌላኛው ተጋቢ ሲጠየቅ ስለንብረቱ አስተዳደር ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
አንቀጽ ፷፩ (፫) ስለውክልና ሥልጣን
ከተጋቢዎች አንዱ የግል ሀብቱን በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት ለሌላኛው ተጋቢ ውክልና መስጠት ይችላል፡፡
አንቀጽ ፷፪ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት
፩. ባልና ሚስት ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶቻቸው ይሆናሉ፡፡
፪. በዚህ ሕግ በአንቀጽ ፶፰ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት ነው ካልተባለ በስተቀር፣ ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ በግብይት የሚያገኙት ንብረት ሁሉ የጋራ ሀብታቸው ይሆናል፡፡
፫. በስጦታው ውል ወይም በኑዛዜው ቃል በሌላ አኳኋን ካልተመለከተ በስተቀር፣ በስጦታ ወይም በኑዛዜ ለተጋቢዎቹ የተሰጧቸው ንብረቶች ሁሉ የጋራ ሀብቶቻቸው ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ ፷፫ የሕግ ግምት
፩. አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ መሆኑን ካላስረዳ በስተቀር ማንኛውም ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
፪. የግል ንብረት መሆኑን ሦስተኛ ወገኖች የሚያውቁት ወይም ሊያውቁት የሚገባ ካልሆነ በስተቀር፣ ባልና ሚስቱ ወይም ከሁለቱ አንዱ ይኸው ንብረት የግል ነው በማለት በሦስተኛ ወገን ላይ መቃወሚያ አድርገው ሊያቀርቡት አይችሉም፡፡
አንቀጽ ፷፬ ስለባልና ሚስት ገቢ (፩) መደበኛ የገቢ አስተዳደር
፩. ባልና ሚስት እያንዳንዳቸው ገቢያቸውን በየራሳቸው ይቀበላሉ፡፡
፪. ባልና ሚስት በየግላቸው የሚያገኙትን ገቢ የግል ወይም የጋራ የባንክ ሂሳብ በመክፈት ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡
፫. ከባልና ከሚስት አንደኛው ሲጠይቅ፣ ሌላኛው ተጋቢ ያገኘውን የገቢ መጠን የማስታወቅ ግዴታ አለበት፡፡
አንቀጽ ፷፭ (፪) ልዩ ሁኔታ
፩. ከባልና ከሚስት አንዱ፣ ገቢውን ሌላኛው ተጋቢ እንዲቀበልለት ሥልጣን ለመስጠት ሙሉ ነፃነት አለው፡፡
፪. ከባልና ከሚስት በአንደኛው ጠያቂነት የአንደኛውን ገቢ ሌላኛው ተጋቢ እንዲቀበልና ለመቀበሉም ደረሰኝ እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ሊወስን ይችላል፡፡
፫. በሌላ ሕግ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር፣ ከባልና ከሚስት የአንደኛው ገቢ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲከበር በፍርድ ቤት ሊታዘዝ ይችላል፡፡
አንቀጽ ፷፮ የጋራ ሀብትን ስለማስተዳደር
፩. ከባልና ከሚስት አንዱ፣ የጋራ ሀብታቸውን በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድር ግልጽ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ባልና ሚስቱ የጋራ ሀብታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡
፪. ከባልና ከሚስት አንዱ ችሎታ የለውም ተብሎ ሲወሰን ወይም ንብረት የማስተዳደር መብቱን ሲገፈፍ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያት የጋራ ሀብታቸውን ለማስተዳደር የማይችል ሆኖ ሲገኝ ሌላኛው ተጋቢ የጋራ ሀብቱን የማስተዳደሩን ተግባር ያከናውናል፡፡
አንቀጽ ፷፯ የማስታወቅ ግዴታ
ከተጋቢዎች አንዱ ብቻ የጋራ ሀብታቸውን በሚያስተዳድርበት ጊዜ የሀብቱን አስተዳደር በተመለከተ ለሌላኛው ተጋቢ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
አንቀጽ ፷፰ (፩) የተጋቢዎች ስምምነት አስፈላጊ ስለመሆኑ
በሌላ ሕግ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር፣ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የተጋቢዎቹ ስምምነት አስፈላጊ ነው፤
ሀ) የጋራ የሆነውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ለማከራየት በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ በዚሁ ንብረት ላይ ሌሎች ሰዎች መብት እንዲያገኙ ለማድረግ፤
ለ) ዋጋቸው ከብር ፭፻ (አምስት መቶ) በላይ የሆኑ የሚንቀሳቀሱ የጋራ ንብረቶችን ወይም የገንዘብ ሰነዶችን፣ ለመሸጥ፣ ለመለወጥ በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ለማስተላለፍ፤
ሐ) ከብር ፻ (አንድ መቶ) በላይ ዋጋ ያለውን የጋራ ንብረት ወይም ገንዘብ ለሌላ ሰው በስጦታ ለማስተላለፍ፤
መ) ከብር ፭፻ (አምስት መቶ) በላይ ለመበደር ወይም ለማበደር ወይም ለሌላ ሰው ዋስ ለመሆን፡፡
አንቀጽ ፷ (፪) የስምምነት አለመኖር ስለሚያስከትለው ውጤት
፩. አንደኛው ተጋቢ ከዚህ በላይ የተመለከተውን ድንጋጌ ባለማክበር የውል ግዴታ ገብቶ የተገኘ እንደሆነ፣ ሌላኛው ተጋቢ ለፍርድ ቤት በሚያቀርበው ጥያቄ ግዴታው ሊፈርስ ይችላል፡፡
፪. ግዴታው እንዲፈርስ የሚቀርበው ጥያቄ ጠያቂው ወገን ግዴታው መገባቱን ከአወቀበት ቀን ጀምሮ ከስድስት ወር በኋላ ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ግዴታው ከተገባ ከሁለት ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
አንቀጽ ፸ የባልና ሚስት ዕዳ
፩. ከባል ወይም ከሚስት በግል የሚጠየቅ ዕዳ፣ ከባለዕዳው ተጋቢ የግል ሀብት፣ የግል ሀብቱ ዕዳውን ለመሸፈን በቂ በማይሆንበት ጊዜ ከጋራ ሀብታቸው ይከፈላል፡፡
፪. ዕዳው የመጣው ለትዳራቸው ጥቅም ከሆነ ከጋራ ሀብታቸው የጋራ ሀብታቸው፣ ዕዳውን ለመሸፈን በቂ በማይሆንበት ጊዜ ከባል ወይም ከሚስት የግል ሀብት ይከፈላል፡፡
አንቀጽ ፸፩ ለትዳር ጥቅም እንደተደረገ የሚቆጠር ዕዳ
የሚከተሉት ዕዳዎች ለትዳር ጥቅም እንደተደረጉ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
ሀ) ለባልና ለሚስት እንዲሁም ለልጆቻቸው የዕለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማሟላት የተገቡ ዕዳዎች፤
ለ) ባል ወይም ሚስት ቀለብ ለመስጠት ያለባቸውን ግዴታ ለመወጣት የተደረጉ ወጪዎች፤
ሐ) ከባልና ከሚስት በአንደኛው ወይም በዕዳ ጠያቂው አለመልካችነት ለትዳር ጥቅም ስለመሆኑ ፍርድ ቤት የተቀበለው ሌላ ዕዳ፡፡
አንቀጽ ፸፪ የትዳር ወጪዎችን ስለመሸፈን
ተጋቢዎች የትዳራቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸውና ችሎታቸው አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡
አንቀጽ ፸፫ በተጋቢዎች መካከል ስለሚደረጉ ውሎች
ባልና ሚስቱ ተጋብተው በሚኖሩበት ጊዜ በመካከላቸው የሚያደርጓቸው ውሎች፣ ፍርድ ቤት ካላፀደቃቸው በስተቀር ውጤት አይኖራቸውም፡፡
