
⚖️⚖️⚖️ሞባይል ድንጋጤ📞📞📞
በፍርድ ቤት መቆም በብዙ ሰዎች ላይ ያልተመለመደ ድንጋጤን ይፈጥራል፡፡ አንዳንዱ ሲናገር አፉ ይተሳሰራል፡፡ ሌላው የሚናገረው ይጠፋበታል፡፡ በተለይ ሞባይሉን ሳያጠፋ የገባ ባለጉዳይ በችሎት መሐል ሞባይሉ ሲያንቃጭልበት ያ የሚያውቀውን ቀፎ እንኳን በወጉ ለመዝጋት ይደነጋገራል፡፡ በአንድ ወቅት በችሎት ፊት እንደቆመ ድንገት ሞባይሉ ያንቃጨለበት ባለጉዳይ ሞባይሉን ሊዘጋው ቢለው ቢለው ከተፈጠረበት ድንጋጤ የተነሳ እምቢ ይለዋል፡፡ ድንጋጤው ሌላ ድንጋጤ ሲወልድ መታገሉን ተወና ሞባይሉን በመስኮት አሽቀንጥሮ በመጣል ከድንጋጤውና ከዳኛው ግልምጫ ሊያመልጥ ችሏል፡፡
፥፥፥፥፥፥፥፥ገገማ፤ ጠማማ፦፦፦፦፦
የተከሳሽ ጠበቃ የመከላከያ መልሱን ለማሻሻል አቤቱታ ቢያቀርብም በስነ ስርዓት ህጉ መሰረት የክስ አቤቱታ እንጂ የመከላከያ መልስ ማሻሻል አይፈቀድም በሚል ምክንያት ውድቅ ተደረገበት፡፡ ጠበቃው በዳኛው አላዋቂነት በግኗል፡፡
ዳኛው ትዕዛዙን አንብበው እንደጨረሱ ጠበቃው “ጌታዬ!” አለና ዲስኩሩን ጀመረ፡፡ “ጌታዬ እኔ እርስዎን ገገማ እና ጠማማ ብዬ ብጠራዎት ምን ያደርጋሉ?”
ዳኛው በተራቸው በገኑ፡፡ “ምን አልክ አንተ? ሞክረኛ! በችሎት መድፈር የእጅህን አቀምስህና ፈቃድህ እንዲሰረዝ አደርጋለው፡፡” “ቃል ሳይወጣኝ እንደዛ ኖት ብዬ ባስብስ?” ጠበቃው መልሶ ጠየቀ፡፡ “እንደዛ ከሆነ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ የፈለግከውን የማሰብ መብትና ነጻነት አለህ፡፡” ዳኛው ተረጋግተው አረጋጉት፡፡
“እንግዲያውስ ጌታዬ! እርስዎ ገገማ እና ጠማማ ኖት ብዬ እንዳሰብኩኝ በመዝገቡ ላይ ይመዝገብልኝ!”
፥፥፦፦፦የተከበረችዋ ፍርድ ቤቷ፦፥፦፦
በየትም አገር ቢሆን ፍርድ ቤት ይከበራል፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ክብር ጉዳይ ለብዙ ሰዎች ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ በተለይ በኛ ሀገር አብዛኛው ሰው የፍርድ ቤት ክብርን የሚያያይዘው ከፍርሀት ጋር ነው፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤት በወጉና በስርዓቱ ዳኝነቱን እንዲያከናውን ሊከበር እንጂ ሊፈራ አይገባውም፡፡ ይኸው የፍርድ ቤት ክብር ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ ከሚገለጽበቸው መንገዶች አንዱ በክርክር ወቅት ፍርድ ቤት የሚጠራበት የአክብሮት ስያሜ ነው፡፡
በብዙ አገራት my lord! Your honor! እያሉ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ በአገራችንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጌታዬ! እያሉ ሙግት መጀመር እንዲሁ የተለመደ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣም ተቀባይነት ያገኘው አጠራር “ክቡር ፍርድ ቤት” ወይም “የተከበረው ፍርድ ቤት” የሚል ነው፡፡
አንዳንድ ባለጉዳዮች “ክቡር ዳኛ” ማለት ቢያዘወትሩም ይህ አጠራር ግን ለክቡር ዳኞቻችን ብዙም አይመቻቸውም፡፡ አንዳንድ ምንም ዕውቀቱ የሌለው ወይም ግብረ-ገብነት ያልገባው ባለጉዳይ ደግሞ “አንተ” ወይም “አንቺ” የሚልበት አጋጣሚ ቢኖርም ይህ አጠራር ግን ለዳኞች ፈጣን ተግሳፅ ይዳርጋል፡፡
በአንድ ወቅት ስለ ፍርድ ቤቱ አጠራር ግራ የተጋባ የሐረርጌ ሰው ከአንድ ሴት ዳኛ ፊት ይቀርባል፡፡ ዳኛዋ በዕድሜ ወጣት ሲሆኑ አለሳበሳቸውም ለእርስዎ አይመችም፡፡ ታዲያ “ክቡር ፍርድ ቤት” የሚለው አገላለፅ ለተባዕታይ ፆታ መስሎት “የተከበረችዋ ፍርድ ቤቷ” በማለት ክርክሩን ጀምሯል፡፡
ሠ እና ብ፣
ዐቃቤ ህግ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ባላቸው ሁለት ግለሰቦች ላይ ክስ አቅርቦ ሁለቱም ተከሳሾች ከቀጠሮው ቀን በፊት በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስ ታጅበው ችሎት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን ክስ ከመነበቡ በፊት ክሱ የደረሳቸው መሆኑን ይጠይቃቸዋል፡፡ ሁለቱም በአዎንታ መልስ ይሰጣሉ፡፡ በመቀጠል ዳኛው ማንነታቸውን ለማረጋገጥ በክሱ ላይ የተቀመጠውን የአንደኛ ተከሳሽ ስም መጥራት ጀመሩ፡፡
“ሠሩክ? ሠሩክ አንተ ነህ?”
1ኛ ተከሳሽ—“ሠሩክ አይደለሁም፡፡ ስሜ ብሩክ ነው፡፡” በዚህ ጊዜ ዳኛው ወደ ዐቃቤ ህግ ዞረው ምንም ሳይናገሩ መልስ ፍለጋ በሚመስል አመለካከት ማየት ጀመሩ፡፡ ክሱን ቀድሞ ባለማንበቡ ትንሽ የሐፍረት ስሜት የተሰማው ዐቃቤ ህግ ነገሩን በማቅለል “አዎ የተከበረው ፍርድ ቤት እነዚህ ፀሐፊዎች የፈጠሩት ስህተት ነው፡፡ በዛ ላይ ትንሽ የስራ ጫና አለብኝ፡፡” ዳኛው ግን ስህተቱን እንደቀላል አላዩትም፡፡ “ክሱን ከማቅረባችሁ በፊት አታነቡትም እንዴ?”
ዐቃቤ ህግ “ያው አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ስህተት ይፈጠራል፡፡” ዳኛውም “ተከሳሹ እኮ ብሩክ ነው፡፡ እናንተ ክሱ ላይ ሠሩክ ብላችሁ ነው የፃፋችሁት፡፡ ተከሳሹ እሱ ስለመሆኑ እንዴት ይታወቃል? ስለዚህ ክሱ መሻሻል አለበት፡፡” በማለት ዐቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል አዘዙ፡፡ ይሄኔ ነው አስቂኝ የችሎት ምልልስ የተጀመረው፡፡
ዐቃቤ ህግ—“ክቡር ፍርድ ቤት ብ ይጨምርልኝ፡፡ ነገሩ ቀላል ነው፡፡”
ዳኛ—“ቀላል አይደለም፡፡ በስነስርዓት ህጉ መሠረት ክሱ መሻሻል አለበት”
ዐቃቤ ህግ—“ኧረ የተከበረው ፍርድ ቤት ብ ን ይጨምራት”
ዳኛ—“ክሱ መሻሻል አለበት”
ዐቃቤ ህግ—“ለ ብ ተብሎ ብ ብትጨመርልኝ ምናለበት?”
ዳኛ—“ክሳችሁን መጀመሪያውኑ አስተካክላችሁ ማቅረብ ነበረባችሁ”
ዐቃቤ ህግ—“ገብቶኛል ብ ነች እኮ!”
ዳኛ—“አይ አይሆንም ክሱ መሻሻል አለበት”
ዐቃቤ ህግ—“ወይ ጣጣ ለ ብ?”
፥፥፥፥፥፥፥ ዳር ዳሩን፣ ፦፦፦፦፦፦፦
በአንድ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መዝገብ የግል ተበዳይ የዐቃቤ ህግ ምስክር ሆና ቃሏን እየሰጠች ነው፡፡ ዐቃቤ ህግ ዋና ጥያቄ ሲጨርስ ተከሳሽ መስቀለኛ ጥያቄ እንዲጠይቅ ዕድል ተሰጠው፡፡
ተከሳሽ——“ቆይ ግን አንቺ “ዳር ዳሩን ንካ ወደ ውስጥ ግን እንዳትገባ” አላልሽኝም?”
ምስክሯ እየተቅለሰለሰች “እንደዛማ ብዬሃለው!”
በዚህ ጊዜ ተከሳሹ ወደ ዳኛው ዞር አለና ክሱን የረታ ያክል ፊቱ ላይ ድል እየተነበበት “የተከበረው ፍርድ ቤት ልብ ይበልልኝ! ችሎቱም ያውቀዋል፡፡ እዛ ደርሶ ማን ይመለሳል?”
፦፦፦ከአክስትህ ጋር ዝምድና አለህ?፦፦፡፡
በፍርድ ቤት በሚደረግ ክርክር አንዳንድ አስቂኝ ጥያቄዎችና መልሶች ለፍርድ ቤቱ እንግዳ ከሆኑ ምስክሮችና ተከራካሪ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በህግ ሙያ ከተካኑት ጠበቃዎችና ዳኞች አፍ ጭምር አምልጠው ይወጣሉ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ምስክር ዳኛው ፊት ቀርቦ ቃለ መሓላ ከፈጸመ በኋላ ለተለመዱት የመግቢያ መደበኛ ጥያቄዎች መልስ መስጥት ይጀምራል፡ ዳኛው ስም፤ ዕድሜ፤ አድራሻና ስራ ካጣሩ በኋላ
“ተከሳሽን ታውቃታለህ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
ምስክሩም “አዎ አውቃታለው አክስቴ ነች” በማለት መለሰ፡፡
በመቀጠል ዳኛው ቀጥሎ መቅረብ ያለበትን የተለመደ ጥያቄ ከተከሳሹ ምላሽ አንጻር ሳያስተካክሉ “ከተከሳሽ ጋር ጠብ ወይም ዝምድና አለህ?” በማለት ጥያቄውን እንደወረደ አቅርበውለታል፡፡
መሪ ጥያቄ፣
በወንጀል ጉዳይ ተከሳሹ ቀርቦ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች እየተሰሙ ነው፡፡ ከምስክሮቹ መካከል አንደኛው የወንጀሉን ድርጊት ተከሳሹ ራሱ እንደፈጸመውና ይህንንም በዓይኑ እንዳየ በመግለጽ ቃሉን ይሰጣል፡፡
ዋና ጥያቄ ካለቀ በኋላ ዳኛው ተከሳሹን “የመስቀለኛ ጥያቄ አለህ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
ተከሳሹም “አዎ” ካለ በኋላ ምስክሩን “ድርጊቱን ስፈጽም አይተኸኛል” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ምስክር— “አዎ አይቼሃለው”
ተከሳሽ– “እሺ በወቅቱ ምን ለብሼ ነበር?”
ምስክር— “ከላይ ጃኬት ከስር ጨርቅ ሱሪ!”
ተከሳሽ— “ምን ዓይነት ጃኬት?”
ምስክር— “ምን ሌላ ጃኬት አለህና ነው ያው ያችኑ ቀዳዳ ቡኒ ጃኬት ነዋ!”