ጋብቻ ለመፈጸም ማሟላት የለባቸው ሁኔታዎች


ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች

አንቀጽ ፮ ፈቃድ

 

የሚፀና ጋብቻ ተፈፀመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡

 

አንቀጽ ፯ ዕድሜ

 

፩. ወንዱም ሆነ ሴቷ አሥራ ስምንት ዓመት ሳይሞላቸው ጋበቻ መፈፀም አይችሉም፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም፤ ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ተጋቢዎቹ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንዳቸው ወላጆች ወይም አሳዳሪ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የፍትሕ ሚኒስትሩ ከመደበኛው የጋብቻ ዕድሜ ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ ፰ የሥጋ ዝምድና

 

፩. በቀጥታ የሥጋ ዘመዳሞች (በወላጆችና በተወላጆች) መካከል ጋብቻ መፈፀም ክልክል ነው፡፡

፪. ወደ ጎን በሚቆጠር የሥጋ ዝምድና፣ አንድ ወንድ ከእህቱ ወይም ከአክስቱ እንዲሁም አንዲት ሴት ከወንድሟ ወይም ከአጎቷ ጋር ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡

 

አንቀጽ ፱ የጋብቻ ዝምድና

 

፩. በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ጋብቻ መፈጸም ክልክል ነው፡፡

፪. ወደ ጎን በሚቆጠር የጋብቻ ዝምድና፣ ባል ከሚስቱ እህት ወይም ሚስት ከባሏ ወንድም ጋር ጋብቻ መፈፀም ክልክል ነው፡፡

 

አንቀጽ ፲ በሕግ ያልተረጋገጠ ልጅነት

 

የአንድ ሰው ተወላጅነት በሕግ መሠረት ያልተረጋገጠ ቢሆንም እንኳን በማኅበረሰቡ ዘንድ በተወላጅነት የሚታወቅ ከሆነ በዚህ ሕግ በአንቀጽ ፰ እና ፱ እንደተመለከተው ጋብቻን ለማስከልከል በቂ ነው፡፡

 

አንቀጽ ፲፩ በጋብቻ ላይ ጋብቻ

 

ማንኛውም ሰው አስቀድሞ በጋብቻ የተሳሰረ ከሆነ፣ ይኸው ጋብቻው ፀንቶ ባለበት ጊዜ ሌላ ጋብቻ መፈፀም አይችልም፡፡

 

አንቀጽ ፲፪ ጋብቻን በእንደራሴ መፈጸም የማይቻል ስለመሆኑ

 

፩. ጋብቻ ሲፈፀም ሁለቱም ተጋቢዎች ጋብቻውን በሚፈፀምበት ጊዜ በግንባር ተገኝተው ፈቃዳቸውን መስጠት አለባቸው፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም፣ ከባድ ምክንያት መኖሩን እና በእንደራሴ አማካይነት ጋብቻውን ለመፈፀም የሚፈልገው ተጋቢ ፈቃዱን በማያሻማ ሁኔታ የገለፀ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትሩ ሲያረጋግጥ ጋብቻው በእንደራሴ ሊፈፀም ይችላል፡፡

 

አንቀጽ ፲፫ መሠረታዊ ስህተት

 

፩. በስህተት በተገኘ ፈቃድ ምክንያት የተፈፀመ ጋብቻ አይፀናም፡፡

፪. በስህተት ምክንያት ፈቃድ ተጓደለ የሚባለው ስህተቱ መሠረታዊ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡

፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተገለፀው አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መሠረታዊ ስህተት እንዳለ ይቆጠራል፤

 

ሀ) በሚያገባው ሰው ማንነት ላይ በመሳሳቱ ምክንያት አገባዋለሁ ብሎ ያላሰበውን ሰው ያገባ ሲሆን፤

ለ) የሚያገባው ሰው ሊድን የማይችል ከባድ በሽታ ወይም ለተወላጆች ሊተላለፍ የሚችል ነዋሪ በሽታ ያለበት መሆኑን ሳያውቅ ያገባው ሲሆን፤

ሐ) ሌላው ተጋቢ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም የማይችል መሆኑን ባለማወቁ ምክንያት ያገባው ሲሆን፤

መ) ሌላው ተጋቢ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የግብረሥጋ ግንኙነት የመፈጸም ልማድ ያለው መሆኑን ባለማወቅ ምክንያት ያገባው ሲሆን፡፡

 

አንቀጽ ፲፬ በኃይል ሥራ የተገኘ ፈቃድ

 

፩. በኃይል ሥራ በተገኘ ፈቃድ ምክንያት የተፈፀመ ጋብቻ አይፀናም፡፡

፪. ፈቃድ በኃይል የተገኘ ነው የሚባለው፣ ፈቃዱን የሰጠው ተጋቢ ራሱን ወይም ከወላጆቹ ወይም ከተወላጆቹ አንዱን ወይም ሌላ ለእርሱ የቅርብ ዘመድ የሆነን ሰው ሊፈፀምበት ከተቃረበ ከባድ አደጋ ለማዳን ሲል ፈቃዱን የሰጠ ሲሆን ነው፡፡

 

አንቀጽ ፲፭ በፍርድ ስለተከለከለው ሰው ጋብቻ

 

፩. በፍርድ የተከለከለ ማንኛውም ሰው፣ ፍርድ ቤት ካልፈቀደለት በስተቀር ጋብቻ መፈፀም አይችልም፡፡

፪. ስለዚህ ጉዳይ ለፍርድ ቤት የሚቀርበውን ጥያቄ የተከለከለው ሰው ራሱ ወይም አሳዳሪው ሊያቀርበው ይችላል፡፡

 

አንቀጽ ፲፮ በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነ ጊዜ

 

፩. አንዲት ሴት አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ካላለፈ በስተቀር እንደገና ከሌላ ሰው ጋር ጋብቻ መፈጸም አትችልም፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም፣ ሴቲቱ አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሳይሞላ

 

ሀ) የወለደች እንደሆነ፣ ወይም

ለ) ጋብቻ የምትፈጽመው ከቀድሞ ባሏ ጋር የሆነ እንደሆነ፣ ወይም

ሐ) እርጉዝ አለመሆኗ በሕክምና የተረጋገጠ እንደሆነ፣ ወይም

መ) በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነውን ጊዜ እንዳትጠብቅ ፍርድ ቤት የወሰነ እንደሆነ በብቸኝነት ለመኖር ስለተወሰነው ጊዜ የተደነገገው ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

One thought on “ጋብቻ ለመፈጸም ማሟላት የለባቸው ሁኔታዎች”

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.