የስልጣን ባህርይ እና መገለጫው።


የስልጣን ባህርይ እና መገለጫው


በአስተዳደር ህግ ውስጥ ስልጣን (power) የሚለው ጽንስ ሀሳብ ከአንድ አስተዳደራዊ ድርጊት በስተጀርባ ህጋዊ ብቃት መኖሩን ያመለክታል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ወይም የመንግስት ባለስልጣናት የአንድን ግለሰብ ወይም ድርጅት መብትና ጥቅም የሚነካ ድርጊት ሲፈፅሙ ይህን የሚፈቅድላቸው ከህግ የመነጨ ስልጣን ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ስልጣን ሁሉ ገደብ አለው፡፡ ይህ የአስተዳደር ህግ መነሻ ነው፡፡ የስልጣን ልኩና ገደቡ ካልተሰመረ የመንግስት አስተዳደር በህጋዊነት ማዕቀፍ ውስጥ አይከናወንም፡፡

ስልጣን የፍፁምነት ባህርይ የለውም፡፡ ፍፁም ስልጣን ዘውዳዊ (ንጉሳዊ) ስልጣን ብቻ ነው፡፡ ስልጣን ፍፁም ከሆነ የአስተዳደር ህግ ሆነ ህግ በጠቅላላው አያስፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የስልጣን ገደብ የአስተዳደር ህግ መነሻና መሰረቱ ነው የተባለው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር የስልጣን መገልገል በተለያዩ መለኪያዎች፤ ቅድመ ሁኔታዎች እና ስነ ስርዓቶች ገደብ ይበጅለታል፡፡ በስልጣን ላይ የሚደረግ ገደብ በተለያየ መልኩ ይገለጻል፡፡

ለአብነት በሚከተሉት ህጎች ላይ ስልጣን የተሰጠበትንና የተገደበበትን መንገድ እንመልከት፤

የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍል ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃው የተሰጠው ሰው የዚሁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብት እንደሆነ እንደሚያስቆጥረው በፍ/ህ/ቁ. 1195/1/ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ይህ የሕሊና ግምት በ1196 ላይ የተዘረዘሩት የሚከተሉት ምክንያቶች መኖራቸው ማስረዳት ከተቻለ ፈራሽ ይሆናል፡፡

(ሀ) የባለርስትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው ከደንብ ውጭ በሆነ አሠራር ወይም ይህን ለመስጠት ሥልጣን በሌለው የአስተዳደር ክፍል የሆነ እንደሆነ

(ለ) የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው በማይረጋ ጽሑፍ መሠረት የሆነ እንደሆነ ወይም ለከሳሹ መቃወሚያ ሊሆን በማይችል ጽሑፍ መሠረት የሆነ እንደሆነ

(ሐ) ከሳሹ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት ያገኘው፤ የገዛው የእርስት የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ መሆኑን ማስረዳት የቻለ እንደሆነ

በፌደራል መንግስት የፋይናንስ አስተዳደር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁ. 879/2009 አንቀጽ 2/20/ በድሮው አዋጅ ቁ. 648/2001 ላይ ተጨማሪ ሆኖ በገባው አንቀጽ 73 መሰረት በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው በአዋጆቹና አዋጆቹን ተከትለው በወጡት ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት እንደሁኔታው ዕቅድ ወይም የሂሣብ ሪፖርት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴሩ ወይም ለውጭ ኦዲተር ያላቀረበ ወይም መቅረቡን ያላረጋገጠ ወይም በውጭ ኦዲት ወይም በውስጥ ኦዲት ሪፖርት በተመለከተው መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ ያልወሰደ ወይም እርምጃ መወሰዱን ያላረጋገጠ እንደሆነ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ከብር 5 ሺ እስከ ብር 10 ሺ በሚደርስ ቅጣት ይቀጣል፡፡

የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በአዋጅ ቁ. 923/2008 አንቀጽ 42/2/ ስር የተመለከተውን ጥፋትa መፈጸሙ ሲረጋገጥ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚከተሉትን ፈቃድ የማገድ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የመውሰድ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ሀ) ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለሦስት ወር፣

ለ) ድርጊቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለስድስት ወር፣

ሐ) ድርጊቱ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለአሥራ ሁለት ወር፣

ከላይ በምሳሌነት የቀረቡት ድንጋጌዎች በአጠቃላይ ይዘታቸው ስልጣን ሰጭ ቢሆኑም በዝርዝር ሲፈተሹ የስልጣኑን ገደብ ጭምር ያሰምራሉ፡፡ በፍ/ህ/ቁ. 1196 (ተ.ቁ. 1) የተዘረዘሩት ሶስት ሁኔታዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመሰረዝ ስልጣን በተሰጠው አካል ላይ የተቀመጡ ገደቦች ናቸው፡፡ ስረዛው ህጋዊነት እንዲኖረው በሁኔታዎቹ ስር ያሉ የፍሬ ነገር እና የህግ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የምሰክር ወረቀቱ ከደንብ ውጭ በሆነ አሠራር ተሰጥቷል በሚል ለመሰረዝ መጀመሪያ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የወጣ ደንብ መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ በመቀጠል በምስክር ወረቀቱ አሰጣጥ ላይ ደንቡን በሚቃረን መልኩ የተፈጸመው ተግባር ምን እንደሆነ ተለይቶ መታወቅና በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ከደንብ ውጭ የሆነው አሰራር ምስክር ወረቀቱን ለማሰረዝ የሚያበቃና መሰረታዊ ካልሆነ የመሰረዝ እርምጃው የሚወሰድበት አሳማኝ ህጋዊነት ምክንያት የለም፡፡ ለምሳሌ የቴምብር ቀረጥ ሳይከፈል ከተረሳ ክፍያው ሊፈጸም ይገባል እንጂ በዚህ እንጭፍጫፊ ምክንያት ብቻ የስረዛ እርምጃ ሊወሰድ አይገባም፡፡

በተራ ቁ. 2 ላይ እንዲሁ እያንዳንዱ ሐረግ የስልጣን ገደብን ይወስናል፡፡ በመጀመሪያ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሾመው ወይም የተመደበ ሰው ሪፖርት የማቅረብ፣ እንዲቀርብ የማስደረግና በሪፖርቱ መሰረት ማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ስልጣንና ተግባሩ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ከዚያም አልፎ ግዴታውን ስላለመወጣቱ በፍሬ ነገር ረገድ በበቂ ማስረጃ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ፍሬ ነገሮቹም ግዴታውን ስላለመወጣቱ አሳማኝ ድምዳሜ ላይ የሚያደርሱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ግልጽ ከሆነው ገደብ በተጨማሪ በቅጣት አወሳሰኑ ላይ ህግ አውጭው በተዘዋዋሪ ማዕቀብ አድርጓል፡፡ የቅጣ መጠኑ ከ5 ሺ እስከ 10 ሺ ብር ድረስ እንደመሆኑ የጥፋቱ ደረጃ እና ቅጣቱ ሚዛናዊ በሚባል መልኩ የተመጣጣኝነትን መለኪያ ማሟላት ይኖርበታል፡፡

በተራ ቁ. 3 ላይ ጥፋት ተብሎ በህጉ የተዘረዘረው ድርጊት በማስረጃ ሊደገፍና ቅጣቱ ሲወሰን ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከድንጋጌው ይዘት ከሚመዘዙት ገደቦች በተጨማሪ በአዋጁ ሌሎች ድንጋጌዎች ላይ ውሳኔ ሰጭው ስልጣኑን ሲገለገል ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ተዘርግቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 26 በተቀመጠው ስርዓት መሰረት መብቴ ተጥሷል የሚል ሰራተኛ አቤቱታውን አዘጋጅቶ ሲያቀርብ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የአቤቱታውን ቅጂና ደጋፊ ሰነዶች በማያያዝ አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ መልሱን በጽሁፍ እንዲያቀርብ የመጥሪያ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ የመጥሪያ አሰጣጥ ስርዓቱ በአዋጁ ላይ ባይጠቀስም ድንጋጌው የተከሳሹን የመሰማት መብት የማስጠበቅ ዓላማ ያለው እንደመሆኑ መጥሪያው በአግባቡ ሊደርሰው ይገባል፡፡ መጥሪያ ሳይላክና ተከሳሹ ደርሶት መልሱን ሳያቀርብ ሚኒስቴሩ ወይም ባለስልጣኑ በራሱ አነሳሽነት ቅሬታ የቀረበበትን ድርጊት አጣርቶ የሚወስደው እርምጃ ህገ ወጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ተከሳሹ ሳይሰማ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በአዋጁ ስልጣን አልተሰጠውም፡፡

Leave a Reply

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.